የመስከረም ኪሶች

እንደ መታደል ሆኖ፣ መስከረም መታወቂያው ብዙ ነው። በአዲስ ዓመት መግቢያነት ይታወቃል። በአብዮት መፈንዳት ይታወቃል። በትምህርት ቤቶች መክፈቻነት ይታወቃል። በተደራራቢ በዓላት አስተናጋጅነቱ ይታወቃል። መሸጋገሪያውን ማንም የሌለውን፣ ጷጉሜን በማድረጉ ይታወቃል። በይፋ አይነገርለት እንጂ፣ ዛሬ ይዘን በተነሳነው ርዕሰ ጉዳይም ይታወቃል።

ከላይ በጠቃቀስንለት አበይት ጉዳዮች የሚታወቀው መስከረም፣ በሚያስተናግዳቸው ጉዳዮች ይታወቅ እንጂ፣ በጉዳዮቹ በጀት አነቃናቂነት ግን ብዙም አይታወቅም። ማለትም፣ ሁሉም በሆዱ እንጂ በቃሉ አይለውም። በ“ሆድ ይፍጀው″ ያልፈዋል እንጂ ወደ ከንፈሩ አምጥቶ ለፍሬ ከናፍር አያበቃውም።

ሴትየዋም ቢሆኑ፣

መቼስ ማል ጎደኒ፣

ፈርሶ መስከረሚ፣

ቀጠንጠን ጎደኒ – – –

አሉ እንጂ አላፍረጠረጡትም። “አላፍረጠረጡትም” እንበል እንጂ፣ ከሁሉም ግን እሳቸው ይሻላሉ። ሌላውማ ያው ከላይ እንዳልነው በ“ሆድ ይፍጀው” እየተፈጀ ወደ ጥቅምት (አንድ አጥንት) መሸጋገርን ነው የሚመርጠው።

ለመግቢያ ያህል እህችን ያህል ከተግባባን፣ በቀጥታ ወደ ጉዳያችን እንሂድ።

መስከረም እንደ ማንኛውም ወር፣ እሱም ያው ወር ነው። የተለየ ነገር የለውም። ይሁን እንጂ የተለየ የሚያደርጉት በርካታ ማህበራዊ-ባህላዊ ጉዳዮች አሉት፣ ጷጉሜ ወርን ተንተርሶ መምጣት፣ የአደባባይ በዓላት መብዛት፣ የትምህርት ቤቶች መከፈት፣ የገበሬው ጎተራ “ለሚቀጥለው ምርት ቦታ ለመልቀቅ” ሲባል መጉደል፣ ወቅቱ ፀደይ መሆኑ ∙ ∙ ∙ ወዘተ ለየት ያደርጉታል።

እየተነጋገርን ያለነው ስለርእሳችን ነው። መስከረም ወር ስላራቆታቸው ኪሶች፤ ወይም ስላደኸያቸው ቦርሳዎች። (መስከረም ጭር ስላደረጋቸው ግሮሰሪዎች ግን አይደለም።)

ምክንያቶቻችን ምንም ይሁኑ ምን ግን አንድ ሁላችንንም የሚያስማማ ጉዳይ አለ፣ እሱም መስከረም ወር ልክ እንደ ሌሎች አቻዎቹ ፈታ፣ ለቀቅ እንል ዘንድ የሚፈቅድልን አለመሆኑ ነው። ቦርሳ ከፈት ላጥ፣ መዥረጥ እናደርግ ዘንድ ንፉግ መሆኑ ነው። ከ“ወዳጅ ዘመዶቻችን” ጋር ሁሉ ሳይቀር ከ“ሻይ ቡና” ሥነስርዓት ማስተጓጎሉ ነው። አዎ፣ መስከረም ሰው አደኸያለሁ ብሎ ራሱም እንደ ጓደኞቹ ደምቆና ፈክቶ “ቺርስ” እየተባለበት እንዳያልፍ በየዓመቱ ራሱ በራሱ ላይ ማዕቀብ ጥሎ በገደምዳሜው እየታለፈ ይገኛል።

የዘንድሮን መስከረም ከሁሉም ለየት የሚያደርገው ከእስከዛሬዎቹ መስከረሞች በተለየ ሁኔታ የኑሮ ውድነትና ጋሻ ጃግሬዎቹ የከበቡት መሆኑ ነው። አዎ፣ የዘንድሮ መስከረም በአጓጉል ሁኔታ ተከቧል። ኪሎ ጤፍ መቶን ሊዘል ጥቂት ፈሪ እየሆነ ነው እየተባለ ነው፣ የአንድ እንቁላል መግዣ የድሮ ሰንጋ ዶሮ መግዣ ከሆነ ሰንብቷል ተባለ።

የትምህርት ቤቶች ክፍያ ነገረ ስራው ሁሉ “ካልፈለክ ተወው”ን ይመስላል። ከስጋ ጋር የተለያየው ሕዝብ ቁጥር ብዛት “ሁሉም” ለመባል ምንም አልቀረውም። በዓሉን የተመለከቱ ቸበር ቻቻዎች (ልክ እንደነ ድንጋይ ኳሱ ሁሉ) ለእነ ብር ወረቀቱ እንጂ በሌላው ዘንድ “ይለፈኝ” ከተባሉ ያልተቆጠሩ አስርታት አልፈዋል ነው የሚባለው። ምኑ ቅጡ – – –

እዚህ ላይ ስለ ተራቆቱ ኪሶች ስናወራ፣ ሀዘናችንን ለራሳችን ጭምር ስናደርግ፣ እነ “እቅድ የለሾች” ን አካትተን አይደለም (ቆይ ቆይ – – – ስጋ ቀለብ ነው እንዴ?)። “አንድ በሬ ላራት” ማስገባታቸውን ከቁም ነገር ቆጥረው ጆሯችን እስኪቃጠል ሲወተውቱን ለነበሩት እንኳን ኪሳቸው ምናቸውስ ቢደርቅ ምናገባን። “አንድ በሬ ለስድስት” ስ ቢሆን የምን አትርሱኝ ሆነና ነው ለወሬ የሚበቃው?።

ድምፃዊው “ምላስና ሰምበር – – -፤ ጉራ ብቻ – – -” እንዳለው ካልሆነ በስተቀር ከብክለት፣ ብክነትና ጤና ማጣት በስተቀር የስጋ ብዛት ምን ያደርጋል? በሚቀጥለው መስከረም ላይደገም ብንስማማ መልካም ነው።

“ሰው ምን ይመስላል ቢለው፣ ዘመኑን” አለ ይባላል።

 ያለንበት ዘመን “ክፉ ዘመን” ከሚባሉት ስር የሚያርፍ ነው። እዚህ ዘርዝረን በማንጨርሳቸው ችግሮች ተከብበን ነው ያለነው። መውጫ ቀዳዳ እንዳጣችው የበዓሉ ግርማ “ዝምብ” (“ደራሲው”ን አስታውስ) ዝም ብለን ጥዝዝዝዝ- – – – እንዳልን አለን። ታዲያ በዚህ ጥዝዝዝዝዝዝዝዝ —— እያልን ባለንበት ሰዓት “አንድ በሬ ለአራት” ጨዋታ ውስጥ እየገባን በማግስቱ ሀሳብ ትካዜ ውስጥ ገብተን ሰውንም ሀሳብ ትካዜ ውስጥ የምንዘፍቀው ለምንድን ነው? ጥያቄው ይሄ ነው። ይህ በ2017 መስከረም ባይደገም በጣም ጥሩ ነው።

እንደ አካባቢ ችግር ላይ ነን። እንደ አገር ችግር ላይ ነን። እንደ አሕጉርም ችግር ላይ ነን። እንደ ዓለም አካልም ችግር ላይ ነን። የቱ ጋ ሰላም ሆኖ የቱ ጋ እንኳን ችግር እንዳለ መለየት ያቃተን ጊዜ ላይ ነው ያለነው። እነ “ብር ወረቀቱ”ን ሳይጨምር፣ እያደረግን ያለነው ስራ ግን ለሰሚ ግራ ነው።

ከላይ የገለፅናቸው ብልህ እናት “ፈርሶ መስከረሚ – – -”እንዳሉት በመስከረም

ነገሮችን በዘዴ፣ ቀጠንጠን አድርጎ ማለፍ እየተቻለ “አንድ በሬ ላራት” ተማን አንሼ ጨዋታ ውስጥ እየገቡ መደናበር ለማንም እንደማይበጀው ሁሉ ለማንም አይጠቅምም። ባበደ የገበያ ሁኔታ ውስጥ ጭራሹን ያብድ ዘንድ፣ ስርዓት ያጣ ዘንድ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ያለፈ ምንም አይነት የኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊም ሆነ አውዳመታዊ ፋይዳ የለውም።

ገበያን እሚያሳብደው ሰው እንደ ሆነው ሁሉ፣ ገበያን የሚያረጋጋውም ሰው ነው። እንደው ለደንቡ “ገበያ መር” ሲባል ይሰማ እንጂ ገበያው የሚመራው ተወደደም ተጠላ በሰው ነው። ይህ ደግሞ በተራዛሚውም ቢሆን ለዛሬ፣ ለጠላው ቀጠንጠን ማለት ተጠያቂዎቹ እኛው ነን። ለኪሳችን መሳሳት ተወቃሾቹ ማንም ሳይሆን ለ“አንድ በሬ ላራት”ግብይት ቦርሳችን ውስጥ እየገቡ ሲመዥርጡ የነበሩት ጣቶቻችን እንጂ ቦርሳዎቻችን አይደሉም።

እናጠቃለው፣ መስከረም እንደ ማናቸውም ወራት ወር ይሁን እንጂ፣ ልክ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የራሱ ልዩ ባህርያት አሉት። ባጭሩ፣ ወጪ ይበዛዋል። ወጪ ደግሞ ኪስ ያሳሳል። ኪስ ሲሳሳ ደግሞ ወኔ ሁሉ ሳይቀር ይቀዛቀዛል። በመሆኑም፣ በራስ የመተማመን፣ ለአደጋ ፈጥኖ የመድረስ ነገር ሁሉ አደጋ ላይ ይወድቃል ማለት ነው። ስለዚህ የዘንድሮውና የእስከ ዘንድሮው ያለው ሁሉ አልፏል። ለ2017 ዓ∙ም እንዳይደገም፤ ኪሳችንም ዳግም እንዳይሳሳ ከወዲሁ ቃል እንግባ። በእቅድና በራስ ሕሊና መመራትን መርሀችን እናድርግ!!!

መልካም አዲስ ዓመት!!!

 ግርማ መንግሥቴ

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You