ለራሳችንም ሆነ ለመጪው ትውልድ ባለውለታ እንሁን!

 በዘመናት መካከል ባለ የትውልዶች መንሰላሰል እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ የሆነ ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ ኃላፊነት አለበት፤ ይህን ኃላፊነቱን በአግባቡ የመወጣቱም ሆነ ያለመወጣቱ እውነታ በራሱም ሆነ በመጪው ትውልድ እጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ሆነ አዎንታዊ ጫና ከፍያለ ነው። በዛሬው ትውልድ ሁለንተናዊ እሳቤና አኗናር ላይ የሚኖረውም ተጽእኖ ትልቅ ነው።

ዓለም አቀፍ የታሪክ መዛግብት እንደሚያመላክቱት፤ አሁን ላይ ለዜጎቻችው የተሻለች ሀገር መፍጠር የቻሉ ሀገራት ሕዝቦች ሆኑ፤ ሕዝቦቻቸው ዛሬን ማሸነፍ አቅቷቸው በብዙ መከራ፣ ስቃይ እና ጠባቂነት ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ሀገራት ሕዝቦች አሁነኛ የልዩነት ምንጫቸው በትውልዶች መካከል የተፈጠረ ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ክፍተት እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም ዛሬ ላይ በድህነትና በኋላ ቀርነት ተጠቃሽ የሆኑ ሀገራት የቀደሙ ትውልዶች በአንድም ይሁን በሌላ ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመረዳታቸው፤ ተረድተዋል የሚባሉትም ቢሆኑ ኃላፊነታቸውን ስኬታማ በሆነ መንገድ መወጣት የሚያስችል በቂ አዕም ሯዊ እና ስ ነ ልቦናዊ ዝግጁነት መፍጠር አለ መቻላቸው አሁን ላሉበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ዳርጓቸዋል።

ከትናንቶች ይልቅ ለዛሬ ትኩረት ያለመስጠት፤ ዛሬን ለነገ ብሩህ ተስፋ አድርጎ ከመውሰድ፤ ለዚህ የሚሆን ትውልዳዊ የአዕምሯዊ ውቅር ከመፍጠር ይልቅ፤ ዛሬዎችን በከንቱ ላለፉ ትናንቶች የመስዋዕት በግ አድርጎ በማቅረብ ትርጉም ማሳጣት፤ በዚህም ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ጭምር ተስፋ ቢስ ማድረግ የመጡባቸው መንገዶች መገለጫዎች ናቸው።

እነዚህ መንገዶቻቸው የሀገራቱን ሕዝቦች ሆኖ የመገኘት ተስፋም ሆነ፤ ሆኖ የመገኘት አቅም በመገዳደር አሁን ላሉበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ዳርጓቸዋል። ዛሬ ላይ ከችግሩ ለመውጣት የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ዋነኛ ፈተና በመሆን፤ ለመስዋዕት የመዘጋጀታቸውንና መስዋዕት የመክፈላቸውን ያህል ስኬታማ መሆን እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።

ለዚህ ደግሞ በሀገራችን ከ50ዎቹ ጀምሮ ሀገራዊ ለውጥ በማምጣት የመላውን ሕዝባችንን ኑሮ ለመለወጥ የተደረጉ የለውጥ ንቅናቄዎች፤ ንቅናቄዎቹ ያስከፈሉት ዋጋ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ሀገራዊ የለውጥ ተሞክሮው ራሱን የለውጥ ኃይል አድርጎ በመቁጠር በተንቀሳቀሰው ትውልድ ላይ የፈጠረው ጥላ የታሪካችን አንዱ ጥቁር ምዕራፍ ስለመሆኑም ለማንም የሚነገር አይደለም።

ትውልዱ ለለውጥ ብቻ ሳይሆን ለለውጡ ስኬታማነት የነበረው ቁርጠኝነት የቱን ያህል ሕይወትን እስከ መክፈል በደረሰ የመስዋዕት ዝግጁነት የታጀበ፤ የተከፈለውም ዋጋ ምንያህል ውድ እንደነበር፤ ለዓላማ የመሰዋት ቁርጠኝነቱ ጥሎት ያለፈውም ጠባሳም በዛሬዎቻችን ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እና ነገዎቻችን ላይ የፈጠረው ግርዶሽ ለዚህ ትውልድ እንደ አዲስ የሚነገረው አይደለም።

ይልቁንም ይህ ትውልድ በዘመናት እየተንሰላሰሉ በመጡ ችግሮች ዛሬም ዋጋ እየከፈለ የሚገኝ ከመሆኑ አኳያ፤ እውነታዎቹን ከታሪክ ትርክት ባለፈ ሊመለከታቸውና ሊያጤናቸው ይገባል። ይህም አሁን ላይ ሀገርን እንደሀገር ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ለማሻገር በሚደረገው ጥረት እንደ ትውልድ ያለበትን ኃላፊነቱን በስኬት መወጣት እንዲችል ትልቅ አቅም እንደሚሆነው ይታመናል።

የቀደመው ዘመን ሀገራዊ የለውጥ መነቃቃት መንገድ ስቶ ትውልዱን፣ ሀገርና ሕዝብን ከፍ ያለ ዋጋ እንዳስከፈለ፤ አሁን የተጀመረው ለውጥ በተመሳሳይ መልኩ፣ ሀገርና ሕዝብን ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍል ከትናንት ትውልዶች ስህተት በአግባቡ መማር፤ ቢያንስ ቢያንስ የነሱን ስህተት ባለ መድገም ከራስ ጋር መታረቅ ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ ከስሜታዊነትና ከአልተገባ እልኸኝነት መውጣት፤ እያንዳንዱን የለውጥ እንቅስቃሴ በተረጋጋ መንፈስና በሰከነ አእምሮ መመርመር፤ እንቅስቃሴው ለግለሰቦች ወይም ለቡድኖች ሊያስገኙ ከሚችሉት ተጠቃሚነት ይልቅ እንደ ሀገር ለመላው ሕዝባችን ያላቸውን ፋይዳ ማመዛዘን ተገቢ ነው።

ከጥፋት ትርክቶች፤ ከሁከትና ልዩነት ሰባኪዎች፤ ከሀሰተኛ መረጃዎችና መረጃዎቹ ከሚፈጥሩት አደጋ እራስን መጠበቅ፤ ከሁሉም በላይ ለውጥ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ፣ ከትናንት መውጣት፣ ዛሬን መኖር እና ነገን ባለ ተስፋ ማድረግ የሚያስችል ማኅበራዊ ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ከቀደሙት ትውልዶች ስህተት በመማር፤ ዛሬን በሚዋጁ፣ ነገን ብሩህ ተስፋ በሚያላብስ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ እውነታዎች አስተሳሰባችንን መግራት፣ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅብናል። ይህ ከመጣንበትና ካለንበት የግጭት አዙሪት ወጥተን ለራሳችን ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች ባለውለታ የሚያደርገን ትልቁ ኃላፊነታችን ነው!

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You