ባህላዊ ወረቶቻችንን ለአብሮነትና ለአንድነት፤

ዶ/ር ጆሴፍ ጎብልስ የናዚው አዶልፍ ሒትለር የአስገድዶ የማሳመንና የማጥመቅ ወይም ኢንዶክትሬሽን አልያም የፕሮፓጋንዳ ቀኝ እጅ ሲሆን ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል ይል ነበር። እኛ ግን አይደለም ውሸትን ደጋግሞ በመንገር እውነት ማድረግ እውነቶቻችንንም እውነት ማድረግ ተስኖናል። የታቀፍናቸው ቱባ በባህላዊ ወረቶቻችን በሦስቱ አብርሃማዊ እምነቶች ማለትም በክርስትና፣ በይሁዲና በእስልምና በትውልድ ቅብብሎሽ የታሹ፣ የተፈተኑና የተረጋገጡ እውነቶች ቢሆኑም እውነት ማድረግ፣ መኖር፣ በሕይወታችን መግለጥ ተስኖን በሀገራችን ልዩነት፣ መጠራጠር፣ መፈራረጅና መከፋፈል ሠልጥኗል። ለባህላዊ ወረቶቻችንን ዋጋ ያልሰጠነው፣ ትኩረት የነፈግነው፣ ኬሬዳሽ የሆነው ደጋግመን በማንሳት ከፍ ሲልም ሀገርንም ሕዝብንም ሌት ተቀን በመነዝነዝ ቀዳሚ አጀንዳ ማድረግ ባለመቻላችን ነው።

እነዚህ ወረቶቻችንን የመነጋገሪያ «አንገብጋቢ ጉዳይ» ወይም “Issue Salience” ብናደርጋቸው ኑሮ ዛሬ ሀገራችን የምትገኝባቸውን ቋጠሮች ሁሉ በፈታቱልን። እነዚህን የእርቅ ፣ የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የይቅርባይነትና የሰላም ወረቶች በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል እንዲሉ። ለሀገራዊ ምክክር ከእነዚህ ወረቶቻችን ቀምረን አማካኝ መላ ይዘን መምጣት እየቻልን ለቅልውጥ ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ ባልዘለቅን። በዚህ ጋዜጣ ላይ ደጋግሜ እንደ ዝሀ ዘጊ የምመላለስበት የባህላዊ ወረቶቻችን ወይም ማኅበራዊ ወረቶቻችን ካልቸራል/ሶሻል ካፒታልስ ጉዳይ ምን አልባት አንድ ቀን ለአቅመ አጀንዳ ይበቃል በሚል ተላላነት ነውና ። ባህላዊ ወረቶቻችን በብዛት በመላው ሀገራችን በብዛት በሚገለጡበት በዚህ ወር እንደገና ይዤው ተመልሻለሁ።

ወርሃ መስከረም በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓሎች የሚከወንበት ባለደማቅ ቀለማትና ህብራዊ ወር ነው። ተፈጥሮም ኢትዮጵያውያንም የሚያጌጡበት ሽቅርቅር ወር ነው። ባህላዊ ወረቶቻችን Cultural Capitals በርከት ብለው የሚገኙበት ባለጸጋ ወር ነው። ሆኖም በሌሎች ወራትም እንደ መስከረም ሁሉ ከፍ ያሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ወረቶች ቢኖሩም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እየገለጥናቸው፣ እየኖርናቸው፣ እየተረጎምናቸው እየወጣን እየገባንባቸው ስላልሆነ እና ላለፉት 50 አመታት ልዩነት፣ ጥላቻ፣ ጎሰኝነትና የፈጠራ ትርክት ተቋማዊና መዋቀራዊ ሆነው ስለተለፈፉ፤ እዚህም እዚያም ቀውስ ፣ ነውር ለማመን የሚቸግሩ ጭካኔዎችን ፣ ግፎችን ፣ መከፋፈል ፣ መጠራጠር እያስተናገድን ነው ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጥልቅ በሆነው ምርመራውና ጥናቱ የደረሰበትን ግኝት ይፋ ተደርጐ የሚዘገንኑ፣ ለመስማት የሚሰቀጥጡ፣ ኢሰብአዊ አረመኔያዊ ግፎችን ስንታዘብ የሦስቱ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች ማለትም ክርስትና፣ አይሁድና እስልምና በአንድነት በሚገኙበት ሀገር እንዴት ሊፈጸም ቻለ? ዋቄ ፈና የሚከተል ሕዝብ ባለበት እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ ባህላዊ ወረቶቻችን በአግባቡ አልምተን ስላልተጠቀምንባቸው ነው።

ለመሆኑ ባህል፣ ባህላዊ ንብረትስ ምንድን ነው የሚለውን ለመግባቢያ ያህል እንመለከት። ባህል ሁሉንም የሚያስማማ የሚያግባባ ወጥ የሆነ ትርጉም ብያኔ ባይኖረውም የአንድ ማኅብረሰብ ወይም ሕዝብ እምነት፣ ልማድ ፣ ወግ በኪነ ጥበብ እና በሥነ ጥበብ ተዳውሮ፣ ተሸምኖ፣ ተንሰላስሎ የመገኘት፣ የመገለጥ ዥጉርጉር ኅብራዊ ቀለም ነው። በደስታ፣ በኀዘን፣ በሥራ፣ በሃይማኖት፣ በትምህርት፣ ወዘተ የሕይወት ገጾች ይገለጻል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባህልን፦ የኅብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ ፣ ወግ፣ ልማድ ፣ እምነት፣ …። በማለት ሲተረጉመው። የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በበኩሉ ባህል፦ ልማድ፣ ደንብ ሲል ይፈታዋል።

ባህላዊ ወረት (cultural capital) የሚለው ሐረግ ፔሬ ቦርዴው በተባለ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የተነሳ የሥነ ኅብረተሰብ ተመራማሪ እንደተፈጠረ የተለያዩ የዘርፉ ድርሳናት ያትታሉ። ባህላዊ ወረት በማኅበረሰብ ውስጥ ያለን ተቀባይነት ቦታ ከፍ ለማድረግ እውቀትን፣ ፀባይና ክህሎትን የማሳደግ የማካበት ሂደት ነው። ባህላዊ ንብረት ወይም ወረት በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ ከፍ ሲልም በሕዝብ በሀገር ይሰላል። የበለፀገ ባህላዊ ንብረት ያካበተ ግለሰብ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገው ሁሉ ያደገ የለማ ባህላዊ ንብረት ያለው ማኅበረሰብ ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ ያለ ተቀባይነት ይኖረዋል።

ባህል ማለትም የኅብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ፣ ወግ፣ ልማድ፣ እምነት ፣ ወዘተ . በሂደት በእውቀትና በክህሎት እየበለፀገ፣ እየዳበረ ሲሄድ ለሀገር ሰላም ፣ አንድነት ከፍ ሲልም እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተቃራኒው ባህል በእውቀት፣ በክህሎት ካልበለፀገ አይደለም ለሀገር ሰላምና ዕድገት መዋል ይቅርና የማኅበረሰቡን እሴቶች ጠብቆ ማቆየት ካለማስቻሉ ባሻገር የዕለት ተዕለት ችግሮችን እንኳ መፍታት የሚሳነው ይሆናል። ባህላዊ ንብረት እንደ ኢኮኖሚያዊ ንብረት ማለትም ገንዘብ በአግባቡ ኢንቨስት ተደርጎ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ እርቅን፣ መነጋገርን ፣ መቀባበልን፣ መከባበርን ፣ መተባበርን፣ አንድነትን ፣ ወዘተ . እውን ማድረግ ካልቻል እንደባከነ እንደከሰረ ሊቆጠር ይችላል።

ሀገርን ሕዝብን ከግጭት፣ ከቀውስ፣ ከመፈናቀል፣ ከመጠራጠር፣ ከጥላቻ ፣ ከበቀል ፣ ወዘተ . መታደግ አልቻለማ። እስኪ ለአንድ አፍታ ባህሎቻችንን እምነቶቻችንን ወይም ባህላዊ ንብረቶቻችንን ከዚህ አኳይ እንመዝናቸው። ባክነዋል ወይስ በአግባቡ ሥራ ላይ ውለዋል!? አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ ቁመና አንጻር ባክነዋል ቢባል የሚያስኬድ ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ባህላዊ ንብረቶቻችንን እንደ ጦር ዕቃ ለብሶ እንደ ጥሩር ደፍቶ መውጣት መግባት፣ መመላለስ ለምን ተሳነን ? መልሱ ቀላል ነው። ላይ ላዩን እንከውናቸዋለን እንጂ አንኖራቸውም። በቃል እናነበንባቸዋለን እንጂ በልባችን አላተምናቸውም። በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንሯሯጣለን እንጂ በሥርዓተ ትምህርታችን አካተን ትውልድን ለማነጽ አላዋልናቸውም። ለብሔራዊ መግባባት፣ እርቅ፣ አንድነትና ሰላም ካላቸው ፋይዳ ይልቅ ስለሚስቡት ጎብኝና ቱሪስት እንጨነቃለን። ወደ ተራ ሸቀጥ እናወርዳቸዋለን። ይህ የተንሸዋረር እይታ ሊስተካከል ይገባል።

ባልንጀራህን፣ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ የሚሉ አብርሃማዊ እምነቶችን ማለትም ክርስትናን፣ እስልምናንና አይሁድን እየተከተልን እንዴት በጥል ግድግዳ ተለያየን!? በአንድ አምላክ በዋቄ ፈና እያመን ኢሬቻን በየአመቱ እያከበርን እየከወን ይቅር መባባል ለምን ተሳነን? መልሱን ለማግኘት ምስጢሩን ለማወቅ ሞራ ማስገለጥ ወይም ኮከብ ማስቆጠር አያሻም። መልሱ ቀላል ነው። እሱም ባህላዊ ንብረቶቻችንን በካዝና ቆልፈን አስቀመጥን እንጂ ሥራ ላይ ስላላዋልናቸው (ኢንቨስት) ስላላደረግናቸው ነው። ትልቁን የመደመር ፍልስፍናም ሆነ ሀገራዊ ሠላምና አንድነት እውን ለማድረግ የተቆለፈባቸውን ባህላዊ ንብረቶች ከካዝና አውጥቶ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ በፍጥነት ማፍሰስ ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል።

በኢኮኖሚክስ አስተምህሮ ባህል ከተፈጥሮ፣ ከሰውና ከአካላዊ ፣ ቁስ አካላዊ (physical) ቀጥሎ 4ኛው ንብረት ሆኖ መጠናት፣ መተንተን ከጀመረ ከራርሟል። በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሀገር እድገትና ለዘላቂ ሠላም አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሠላም በሌለበት ኢኮኖሚያዊ እድገትም ሆነ ብልፅግና ሊታሰብ አይችልምና። የመደመር ሦስቱን አላባውያን መሰብሰብ፣ ማከማቸትና ማካበትን እውን ማድረግ አይታሰብም።

ለሀገር ግንባታ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ወሳኝ ሚና ከሚጫወተው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ሥርዓት በተጨማሪ ለዘመናት እንደ ሕዝብ ፣ እንደ ሀገር አጋምዶ ያቆየን ባህላዊ ንብረታችን ነው። ሁነቱን፣ ክዋኔውን፣ መንፈሱን ጠብቆ ተንከባክቦና አልምቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ፣ ማስቀጠል፣ ማክበርና ማስተዋወቅ ትልቅ ኃላፊነትም አደራም ነው። ሆኖም የመጨረሻ ግብ ሆኖ ግን ሊወሰድ አይገባም። ቱባነቱን እንደጠበቀ ማደግ ዘመንና ትውልድ መዋጀት ይጠበቅበታል። አዎ ! የትውልዱንና የዘመኑን ህፀፅ የሚያርም ለምፅ የሚያነጻ ፣ የሚዋጅና የሚቤዥ መሆን አለበት።

ዘረኝነትን፣ ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ደባን፣ መከፋፈልን፣ ወዘተ መቤዥ፣ መዋጀት አለበት። ባህላዊ ንብረታችንን ይበልጥ በማጎልበት፣ በማልማትና በማስፋት ለመጻኢ ዕድላችን፣ ለነገ ተስፋችን፣ ለእርቅ፣ ለሠላም፣ ለአንድነት፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና፣ ለመደመር ወዘተ. ልናውለው ይገባል። ስኬቶቻችንን የምናወድስበት፣ ፈተናዎቻችንን የምንሻገርበት ነገአችንን የምንተልምበት ጭምር አድርጎ ስለመጠቀም አበክረን ማሰብ ያስፈልጋል።

የፍቅር፣ የእርቅ ፣ የሠላም ፣ የአብሮነት ፣ የማካፈል፣ የመተባበር፣ የመተጋገዝ፣ የመረዳዳት፣ የምስጋና፣ ወዘተ ባህሎች፣ ልማዶች ፣ እምነቶች ፣ ሃይማኖቶች ከፍ ሲልም ድምር ባህላዊ ንብረቶች ባለቤት እንዲሁም የጥንታዊት ሀገር ባለቤት ሆነን አንድነትን በመከፋፈል ከሰዋን፣ ፍቅር ከጎደለን፣ እርቅ ከገፋን፣ ሠላም ከራቀን፣ አብሮነትን በቀዬአዊት ከተካን፣ ማካፈልን በስስት ከቀየርን፣ መተባበርን በመለያየት ከለወጥን፣ ምስጋናን በእርግማን ከተካን፣ ወዘተ ምኑን ሙሉኡ ሆነው? ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ያለፍንባቸው ሀገራዊ ውጣ ውረዶች፣ አሳፋሪ ድርጊቶች እውነት የእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ፀጋዎች ባለቤት ስለመሆናችን የሚመሰክሩ ናቸው? እስኪ ሌሎችን አቆይተን ካለፉት 19 ቀናት ወዲህ እንዲሁም ወደፊት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከበሩ መንፈሳዊና ባህላዊ ሁነቶች የተሸከሙትን ግዙፍ መልዕክቶችና አንድምታዎች አለፍ አለፍ ብለን እየተመለከትን ሂሳብ እናወራርድ።

ፍቼ ጨምበለላ፣ ቡሔ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ፣ ሶለል አይነ ዋሬ ፣ እንቁጣጣሽ ፣ መስቀል ፣ መስቀላዮ፣ አጋመ፣ ጊፋታ፣ ኢ ሬቻን ፣ ጋሮ ፣ ቺሜሪ፣ ወዘተ . በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ የሀገራችን ማኅበረሰቦች የሚከበሩ ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ክዋኔዎች ናቸው። ሁሉም ማለት ይቻላል ተስፋን ፣ ፍቅርን ፣ ነፃነትን ፣ አብሮነትን፣ ምስጋናን ፣ እርቅን ፣ ይቅርታን ፣ ወዘተ. የሚያውጁ፣ የሚለፍፉ ናቸው። ግን በነቂስ ወጥተን ለዘመናት በየአመቱ በአደባባይ የምናከብራቸው የምንዘክራቸውን ያህል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አንኖራቸውም። አንለማመዳቸውም።

ከገጠሙን ቀውሶች፣ ፈተናዎች መውጣት ማገገምና ማንሰራራት የቻልነው በቀሩን ሽርፍራፊ እንጥፍጣፊ በባህላዊ ንብረቶቻችን ነው። በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት ቀን ከሌት እንደተሰበከው ልዩነት ፣ ጥላቻና ዘርኝነት ቢሆን ኑሮ እርስ በእርስ ተበላልተናል። ተጨራርሰናል። ለዚህ ነው መዳኛችን፣ ማገገሚያችንና ማንሰራሪያችን የሆነውን ባህላዊ ንብረት ወደሙላቱ መመለስ ለነገ የሚባል ጉዳይ የማይሆነው። ባህላዊ ንብረታችን ለበጎ ዓላማ ሲውል ሀገርን ከጥፋት ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ በጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል።

ቁጣ አብራጁ ይህ የጋሞ አባቶች ልመና (ጋሞ ወጋ) እየጠፋ፣ ትኩረት እየተነፈገው ያለው ባህላዊ ንብረታችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ ሀገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው። የጋሞ አባቶች የ2011 ዓ.ም ልዩ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆናቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለ አንዳንች ልዩነት ዳር እስከዳር አድናቆትን ተቀባይነትን ያተረፈው በዚህ እሳቤ ነው።

ሠላምን ፣ ፍቅርን ፣ ይቅርታን ለማነፅ ፣ ለመገንባት ከምንሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ በየአካባቢው እንደ ጋሞ ወጋ ዓይነት የሽምግልና፣ የእርቅ ባህላዊ ካፒታሎቻችንን ላይም መሥራት ይጠበቅብናል። ከዚህ መሳ ለመሳ የአክራሪነት አዝማሚያ፣ እኩይ አስተሳሰብ እንዲገታ ብሎም ተሸንፎ ከሰላምና ከእርቅ መንገድ ገለል፣ ዘወር እንዲል ድልብ የሆኑ ባህላዊ ንብረቶቻችን ጥንስስ፣ ወረት የማይተካ ሚና አላቸው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህላዊ ንብረቶች ባለፀጋ ስለሆኑ የየራሳቸውን መዋጮ ማበርከትና ወደ ሥራ መግባት ይጠበቅባቸዋል።

በየአካባቢያችን፣ በየቀዬአችን የምናንፀው፣ የምናቀነቅነው ከባቢያዊ ብሔርተኝነት ወደ አክራሪነት፣ ፅንፈኝነት የሚያንደረድር ወደገደል አፋፍ የሚገፋ ስለሆነ እነዚህን ባህላዊ ወረቶች በመጠቀም መግታት ያስፈልጋል። የዜጎች ማንነት እሴት እንደተከበረ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚያደርሰንን ቀና መንገድ በቅንነት መቀላቀል ፣ መያያዝ ይገባል። ይህ ሀገራዊ ብሔርተኝነትም ከገደቡ ፣ ከውሃ ልኩ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ። አይደለም ዘውጌአዊ፣ ወንዜአዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በአግባቡ ካልተያዘ ፤ የጎረቤቱን የሚጎመጅ ፣ የሚመኝ፣ የሚመቀኝ ሆኖ የመውጣት አደጋ ስላለው በብልሀት ፣ በማስተዋል ሊቀነቀን ይገባል ።

ሻሎም !!! አሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You