ቱሪዝምን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የሀገርን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል!

 ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሠራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ናት። የተመዘገቡ እና ያልተመዘገቡ ሌሎች በርካታ ጥንታዊ ቅርሶችና የቱሪዝም መስህቦችም ባለቤት ናት።

ነገር ግን ግን ሀገሪቱ ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የበለፀገችና በርካታ የቱሪስት መስህብ ያላት ሀገር እንደመሆኗ ዘርፉ አድጓል ለማለት ጊዜው ገና ነው። ለዚህ አንዱ ማሳያ በዩኔስኮ በተመዘገቡ ቅርሶች ብዛት ከኢትዮጵያ የሚያንሱ ሆነው በጎብኚዎች ቁጥር ግን ከኢትዮጵያ የሚበልጡ የአፍሪካ ሀገራት መኖራቸው ነው።

ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም አቅምና መዳረሻዎች አንፃር እያገኘችው ያለው ጥቅም እጅግ አነስተኛ መሆኑ ግን ድብቅ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዱና ትልቁ ችግር በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ያሉ የመሠረተ ልማትና ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እጥረቶች ናቸው፡፡

ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በተፈጥሮ መሰጠትንም ጥረትንም ይጠይቃል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እመርታ እያሳየ እንደሚገኝ መካድ አይቻልም። መንግሥት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በዚህም በተፈጥሮ የሚገኝ የሰዎችን ቀልብ የሚማርኩ፣ ለምርምር የሚገፋፉ ጸጋዎችን ወንዝ፣ ሃይቅ፣ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ደን፣ እጽዋትና እንስሳት፣ ባህል፣ ወግና ቋንቋ፣ ታሪክና ታሪካዊ ቅርሶችን ለቱሪዝም ለመጠቀም አበረታች ጅምሮች እየታዩ ነው።

እነዚህ የተፈጥሮ ስጦታዎች ግን በራሳቸው ቱሪስቶችን ለመሳብና ለማሰንበት በቂ አይደሉም። ከማስተዋወቅ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ያስፈልጋሉ። የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ለትምህርትና ለጤና አገልግሎት፣ ለምርምር እንዲመጡ ማድረግ የሚያስችሉ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን ማካሄድ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ያስፈልጋሉ፡፡

በብሔራዊ ፓርኮች ያለውን የመሠረተ ልማት ደረጃ ማሻሻል፣ ፓርኮችና ሎጆችን ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኙ መጋቢ መንገዶችን ደረጃ ማሻሻል፣ እንዲሁም በፓርክና በእንስሳት መጠበቂያ የሚገኙ የዱር እንስሳት አደንን መከላከል፣ ቅርሶች የሚገኙበትን አካባቢ መጠበቅና የመሳሰሉ ሥራዎች ትኩረት ይፈልጋሉ። ከዚህ በተጓዳኝ የቱሪዝም ሚኒስቴር የተፈጥሮና ባህላዊ ቅርሶችን በመንከባከብና በማልማት፣ የባህልና የቱሪዝም ቁሳቁሶችን ለገበያ በማቅረብ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን የላቀ በማድረግ፣ የባህልና የቱሪዝም የመረጃ ሥርዓት በማሻሻል፣ እንዲሁም የልማት አጋሮችን በላቀ ደረጃ ማቀናጀት ላይ ይበልጥ ሊሠራ ግድ ይገባል።

ቅርሶችን በአግባቡ በመያዝ፣ ለትውልድ በማሳየትና፣ የገቢ ምንጭ ከማድረግ አንጻር ብዙ ሥራ ይቀራል። ለዚህ ደግሞ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስፋትና ማስተዋወቅ ላይ ያለው ክፍተት አንዱ ምክንያት ነው።

የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ የአፈጻጸም አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ግልፅ ነው። ፖሊሲና ስትራቴጂን መሠረት ባደረገ መልኩ ቱሪዝምን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ መሥራት ይገባል። መንግሥት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ለማስቻል ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በዚሁ መሠረት የቱሪዝም ዘርፉን ለማልማት የታዩ ጅምሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም እምቅ አቅም ቢኖራትም ከዘርፉ ስታገኝ የነበረው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። አሁን ይህ ሁኔታ እየተቀየረ ነው። መንግሥት ነባራዊ ሁኔታውን ለመቀየርና ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ተገቢውን ድርሻ እንዲይዝ አስቻይ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ለዘርፉ ዕድገት ምቹ መደላድል ለመፍጠር ፖሊሲዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ባለፈ ቱሪዝምን ከማኅበራዊ ዘርፍ ወደ ኢኮኖሚ ዘርፍ ማሸጋገር እየቻለ ይገኛል፡፡ በቀጣይነት ቱሪዝም ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ሰፊ የሥራ እድል መፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ግኝትንም በጉልህ ሊያሳድግ የሚችል በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ የማስተዋወቅና ጉብኝትን የማነሳሳት ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ሊሠራ ይገባል። የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የመሠረተ ልማትና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስፋፋትም እየተሠሩ የሚገኙ እንደ ገበታ ለሀገር ፤ ገበታ ለሸገር ፤ ገበታ ለትውልድ አይነት ኢኒሼቲቮችና በርካታ ፕሮጀክቶች አይነተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይታመናል፡፡ ይህ ሲሆን የቱሪዝም ዘርፉ በተለይ አሁን በሀገሪቱ ጎልቶ የወጣውን የሥራ አጥነት ችግር በመፍታትና ሀገራዊ ገቢን በማሳደግ ህዝብን ቀጥተኛ ተጠቃሚ ማድረግ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል!

አዲስ ዘመን  መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You