በጣሳ ችርቻሮ ተጀምሮ ለዓለም ገበያ የበቃው የቡና ንግድ

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር እንደመሆኗ ቡና ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፤ ሀገሪቱ በ2014 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር፣ በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ አንድ ነጥብ 33 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷ ሲታሰብ ቡና ለሀገሪቱ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ሀገሪቱ ጥራት ያለው ቡና በብዛት ለዓለም ገበያ በመላክ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራች ትገኛለች።

ቡና ለዜጎችም የገቢ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። ከቡና ልማት ጀምሮ በግብይት ሰንሰለት ሂደት ውስጥ ብዙ ሚሊዮኖች ዜጎች ሲሳተፉ የሚታየውም በዚሁ ምክንያት ነው።

በተለይም የቡና አምራች የአገሪቱ አካባቢዎች አርሶ አደሮች የኑሮ ዋስትና ቡና ነው። አርሶ አደሮቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቡናው ዘርፍ በልማቱም በግብይቱም በስፋት በመሳተፍ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ስኬታም እየሆኑ ይገኛሉ።

የዕለቱ የስኬት አምድ እንግዳችንም በቡና ንግድና ልማት ተሰማርተው በርካታ ዜጎች መካከል ስኬታማ መሆን የቻሉ ናቸው። አቶ ንጉሴ ገመዳ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት በሲዳማ ዞን በንሳ ወረዳ ቡራ ቀበሌ ነው። እንግዳችን ከአርሶ አደርና አርብቶ አደር ቤተሰብ የተገኙ ናቸው። ይህ በመሆኑም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአርሶ አደር ልጅ ቤተሰባቸውን በእርሻ ሥራ እንዲሁም ከብቶች በማገድ እያገዙ አድገዋል። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ተወልደው ባደጉበት በዚሁ ቀዬ ነው የተከታተሉት።

ከትምህርታቸው ጎን ለጎን አቅማቸው በፈቀደ መጠን ቤተሰባቸውን በሥራ ሲያግዙ ያደጉት አቶ ንጉሴ ገመዳ፤ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው የቡና ንግድ ቀልባቸውን ይገዛዋል። ለዚህም ምክንያቱ አካባቢያቸው ቡና አምራች መሆኑ ነው፤ አቶ ንጉሴ በርካቶች በቡናው ዘርፍ ተሰማርተው ሲሰሩ ይመለከታሉ። ‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም›› የሚለውን አባባል ወደ ጎን በመተው በአካባቢያቸው ያስተዋሉትን የቡና ንግድ ለመቀላቀል ትምህርታቸውን አቋረጡ።

ቤተሰቦቻቸው በእርሻ ሥራና በከብት እርባታ ብርቱዎችና ሞዴል አርሶ አደር ሆነው የተሸለሙ መሆናቸውን ይገልጻሉ። እሳቸው ግን ቀልባቸው በቡና ንግድ ተሳበ። የቡና ሥራ የልጅነት ህልማቸው በመሆኑ ከቤተሰብ ውጭ ሆነው በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ቡና ንግዱ ገቡ። የቡና ንግድን የጀመሩት በአካባቢያቸው የሚመረተውን ቡና በፈረስ እየጫኑ አጎራባች በሆኑ የኦሮሚያ ወረዳዎች በመውሰድ በችርቻሮ ይሸጡ ጀመር።

‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ›› እንዲሉ አበው የትዳር አጋራቸው በቡና ንግዳቸው ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው አቶ ንጉሴ ያስታውሳሉ። በባህላዊ መስፈሪያ /ጣሳ/ ቡናውን መሸጥ የባለቤታቸው ድርሻ ነበር። በአንድ ፈረስ ጭነት የተጀመረው የቡና ንግድ በሁለትና በሶስት ፈረስ እየተጫነ ተጠናክሮ ቀጠለ። በዘርፉ ውጤታማ መሆን ትልቁ ህልማቸው የሆነው አቶ ንጉሴ፣ ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ጥረት ማድረጉን በከፍተኛ ሁኔታ ተያያዙት።

ቡና ራሳቸውን ከማስተዳደር ባሻገር ህይወታቸውን መለወጥ ያስቻላቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ንጉሴ፣ አዋጭነቱን ተረድተው በዘርፉ ብዙ መሥራት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። በ2005 ዓ.ም የደረቅ ቡና ንግድ ፈቃድ በማውጣት ወደ ቡና ንግድ ሥራ የገቡት አቶ ንጉሴ፤ የቡና ንግድ ጥረታቸው የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ የጀመረው በፈረስ ከመነገድ በጭነት መኪና በስፋት እየተዘዋወሩ መነገድ ውስጥ በገቡ ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ።

የቡና ዋጋ አንዳንዴ የሚገጥመው ፈተና እንዲሁም ለቡና ልማት የተፈጠረው መደላድል ደግሞ ሌሎች አቅሞች ይሆኑላቸውና አቶ ንጉሴ በቡና ልማቱም ተሰማሩ። ይህ ሁኔታ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስቻላቸው፤ ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘትን ቀዳሚ ግባቸው አድርገው እንዲንቀሳቀሱም ሌላ አቅም ፈጠረላቸው።

ኢትዮጵያ ከየትኛውም የዓለም አገር ለቡና ተስማሚ መሬትና የአየር ንብረት እንዳላት የሚገልጹት አቶ ንጉሴ፣ ሀገሪቱ በቡና ልማት ስመጥር አገር ብትሆንም በዛ ልክ ግን አልተሠራም ይላሉ። በተለይም አልምቶ ከመጠቀም አንጻር ውስንነቶች እንዳሉ ያመለክታሉ። ይህን ውስንነት ሊቀረፍ የሚችለው ደግሞ የቡና አምራች ገበሬዎች ሲበረታቱና ድጋፍ ሲያገኙ እንደሆነ የገለጹት አቶ ንጉሴ፤ እርሳቸውም አንድም በዚሁ ቁጭት ወደ ቡና ልማቱ መግባታቸውን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ የቡና መገኛና ከፍተኛ ቡና አምራች መሆኗን ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ በቡና ልማትና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ።

ከ2005 እስከ 2011 ዓ.ም የቡና ዋጋ ወርዶ አንደነበር ያስታወሱት አቶ ንጉሴ፤ ያ ወቅት ንግዱ ፈታኝና አድካሚ እንደነበር ይገልጻሉ። ፈተናውን ለመሻገርም ቡናን በጥራት ማዘጋጀት ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑን ይረዳሉ። በአስር ሺ ብር መነሻ ካፒታል የቡና ንግድ ሥራን የጀመሩት አቶ ንጉሴ፤ ከባንክ ባገኙት አንድ ሚሊዮን ብር ብድር የቡና ልማት ሥራቸውን ‹‹ከራሞ ቡና ላኪ ድርጅት›› በሚል መጠሪያ አቋቁመው ወደ ልማቱ ገብተዋል። በሲዳማ ክልል ስድስት የተለያዩ ቦታዎች ቡናን እያለሙ ያሉት አቶ ንጉሴ፤ አስር ከሚደርሱ ቡና አቅራቢዎች ጋር ትስስር ፈጥረው በጋራ እየሠሩ ሲሆን፤ በ2014 ዓ.ም ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ከሶስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማምጣት ችለዋል።

በወቅቱም ብዙ ከማምረት ይልቅ ጥራት ያለው መጠነኛ ቡና ለማምረት አቅደው ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ ሠርተዋል። ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በቡና ልማት የተሠማሩት አቶ ንጉሴ፤ ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት ጥራት ያለው ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ ተሰማርቷል። በመሆኑም በ2014 ዓ.ም በተደረገው የቡና ጥራት ውድድር (cap of excellence) ተሸላሚ መሆን ችሏል። በወቅቱም አንድ ኪሎ ቡና በብር 14 ሚሊየን 452 መሸጥ ችለዋል። በዚህም ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እውቅናም አግኝተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 12ኛ ጊዜ ውድድር በተካሄደበትና ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት ውድድርም እንዲሁ ቡናቸው በነጥብና በሽያጭ መጠን አንደኛ ሆኖ መመዝገቡን አቶ ንጉሴ ይጠቅሳሉ፤ ይህም እንደ አገር በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ እንዳስቻላቸው ይገልጻሉ። ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ በቡናው ዘርፍ ያላትን እምቅ ሃብት ተጠቅማ በተለይም የባለ ልዩ ጣዕም ቡናን ለዓለም ገበያ በማስተዋወቅ የገበያ አድማሷን ለማስፋት በር እንደከፈተላት ይጠቅሳሉ። በጥራት የሚመረት ቡና በገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነት እንዲጨምር ማድረግ እንደቻለም ይገልጻሉ።

የቡና ንግድን በጣሳ ከመቸርቸር ተነስተው በፈረስና በመኪና ከቦታ ቦታ ወስደው ያካሄዱት አቶ ንጉሴ፤ ዛሬ በልማቱም ጭምር ተሳትፈው ጥራቱ የተጠበቀ ቡና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ናቸው። በባለቤታቸውና በልጃቸው ስም የተለያዩ የቡና እርሻ እርሻዎች፣ መፈልፈያዎችም አሏቸው። በተለይ ለጥራት በሰጡት ትልቅ ትኩረት ቡናቸው በተለያዩ የገበያ መዳረሻዎች ተፈላጊነቱ እየጨመረ ስለመምጣቱም አጫውተውናል።

ቡናቸው በተለያዩ የዓለም አገራት ተደራሽ መሆን ችሏል፤ ቡናው አሜሪካን ጨምሮ ጃፓን፣ ለንደን፣ ስዊድን፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አገራትም እየደረሰ መሆኑን አቶ ንጉሴ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ ቡናው በጥራት እየታወቀ መምጣቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ይገኛል፤ ለዚህም ትንሽ ቡና ልከው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያስቻላቸው ልዩ ቡና መላክ መቻላቸው ነው። ጥራት ያለው ቡና በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለአገር ከሚያስገኙ የቡና ልማት ገበሬዎች መካከል አቶ ንጉሴ አንደኛው መሆን መቻላቸውን ይናገራሉ።

በዘርፉ ብዙ መሥራትና መለወጥ እንደሚቻል የሚያምኑት አቶ ንጉሴ፤ ጠንክረው መሥራት በመቻላቸው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መለወጥ መቻላቸውን ይጠቅሳሉ። ከቤተሰባቸው ባለፈም ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ አካባቢዎች ባቋቋሟቸው የቡና ልማት ሥራዎች ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዚያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ለሌሎች አርሶ አደሮችም የእርሳቸውን ተሞክሮ በመውሰድ ቡናን ማልማት ቢችሉ በቀላሉ መለወጥ እንደሚችሉ ይመክራሉ።

መንግሥትም ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ፣ በዘርፉ ትርጉም ያለው ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። በተለይም መንግሥት የ‹‹ካፕኦፍ ኤክሰለንስ›› ውድድርን ማምጣቱ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉና ጥራት ያለው ቡና ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በትንሹ የቡና ንግድ ጀምረው በቡና ልማት የተሰማሩት አቶ ንጉሴ፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ይናገራሉ። በሥራ ዘመናቸው ካገኙት ገንዘብ ጥቂት የማይባለውን ለማህበራዊ አገልግሎት እንደሚያውሉ ይገልጻሉ፤ የሲዳማ ክልል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ 10 ሚሊየን ብር በመመደብ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት በአጭር ጊዜ ገንብተውና ሙሉ ቁሳቁሱን አሟልተው ለማስረከብ በገቡት ቃል መሰረት በቅርቡ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል። በእዚህም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ይታይ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እገዛ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ። በተለይም የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መንግሥት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት። በተጨማሪም ለሁለት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ቁሳቁስ ገዝተው አበርክተዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ለሚያቀርባቸው ማንኛቸውም ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ የጠቀሱት አቶ ንጉሴ፤ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ማድረጋቸውን እንዲሁም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የቤት ክራይ መክፈል ላልቻሉ አቅመ ደካሞች ኪራይ በመክፈል ህይወታቸውን መታደግ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

‹‹ራእይና ተስፋ ሰንቆ መሥራት ካሰቡት ያደርሳል›› የሚል ጽኑ እምነት ያላቸው አቶ ንጉሴ፤ በቀጣይ በሀዋሳ ከተማ የሲዳማ ክልልንና የከተማዋን ገጽታ የሚገልጽ፤ በአዲስ አበባ ከተማም እንዲሁ የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑ ግዙፍ ህንጻዎችን በመገንባት የኢትዮጵያን ቡና የበለጠ የሚያስተዋውቁ ድርጅቶችን ለመክፈት አቅደው እየሰሩ ናቸው። ለዕቅዳቸው ስኬትም መንግሥት ትልቅ ድርሻ እንዳለው በመግለጽ፤ የመስሪያ ቦታና ሌሎች ለሥራ ምቹ የሆኑ ከባቢዎችን መፍጠር ከመንግሥት እንደሚጠበቅ ነው ያመለከቱት።

ይህን ማድረግ ሲቻል በአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና ማሳደግ በእዚህ ሁሉ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል አስታውቀዋል። እንደ አገር ልማትን ወደኋላ የሚያስቀሩ ግጭቶችን በመፍታት ሰላምን ማስፈን ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን  መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You