«ደመራ ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና በአንድነት የመቆም ምሳሌያችን ነው»ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

/ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደመራ/መስቀልን በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል/ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!

ደመራ፣ መደመር፣ ደመረ፣ አከማቸ ማለት ነው። ደመራ የመለወጥ ምልክትነትም ነው። ለወንጀለኞች ስቅላት ይውል የነበረ መስቀል ዋጋና ምልክቱ የተለወጠበት ነው። ደመራ ብዙ ሰዎችን ሰብስቦ በኅብረት የሚያቆም ነው። ደመራ ባነሰው ላይ መጨመር ነው። ደመራ የተበተነውን መሰብሰብ ነው። የተዘረዘረ ነገርን የሚደምርና የሚያገናኝ ነው። ጸጋዬ ገ/መድኅን በግጥሙ…

ነጋ አዲስ ዘመን ችቦ፤

ምድር ሕይወት አፈለቀች፤

የምሥራች አዝርዕቷን፤ አዲስ ቡቃያ ወለደች፤

የአደይ አበባን ለገሰች፣

ለአዲስ ዘመን አዲስ ብርሃን፤ አዲስ መስከረም

ገበየች፣

…እንዳለው የአዲስ ዘመን ችቦ በአዲስ የፈካ ዘመን የሚጀመርበት ነው። የሰዎችም አዲስ ተስፋ አዲስ ጅምር የሚታይበት ነው። የመስቀል ወፍ የምትታሰርበት፤ አዝዕርት የሚበቅልበትም ነው።

ደመራ ለበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት ነው። እንጨቶች ተሰብስበው ችቦ፤ ችቦዎች ተሰብስበው ደመራ የሚሆኑበት ነው። የችቦ እንጨቶችና ጭራሮዎች ምን ቢበዙ ወደ አንድ ካልመጡ ችቦ አይሆኑም። እንጨቶቹን የሚያስተሳስራቸው የማሠሪያ ልጥ አለ። ችቦዎቹም በጋራ ተደጋግፈው ካልቆሙ ደመራ አይሆኑም። ችቦዎቹን አንድ አድርጎ የሚያቆማቸው የመሐሉ እንጨት አለ። ይህ እንጨት ጠንካራና በዙሪያው የተሰባሰቡትን ችቦዎች መሸከም የሚችል ነው። ይህ ምሰሶ ኢትዮጵያን የሚወክልም ነው።

የችቦው ሁሉም ጭራሮዎች አንድ ዓይነት አይደሉም። ከአንድ ቦታም አይለቀሙም። ሁሉም ችቦዎችም ተመሳሳይ አይደሉም፤ ከአንድ ቤት አይመጡም። ሁሉም እንጨቶች በየራሳቸው ይቆማሉ፤ ግን ደግሞ ብርታትና ጥንካሬ፣ አቅምና ጉልበት እንዲኖራቸው ችቦ ሆነው ይደመራሉ። እንጨቶቹን እንደሚያስተስሥስረው ልጥ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስሩ ልዩ ልዩ ማንነቶች አሉ። ደመራ በመሰባሰብ የሀገራችንን ከፍታ እውን ለማድረግ የምንሰባሰብበት ተምሳሌታችን ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ችቦ እንጨቶች ብዙ ባህሎች፣ እምነቶች፣ ሀብቶች፣ ዕሴቶች፣ አመለካከቶች፣ ታሪኮች አሏት። ሁላችንም የግድ አንድ ዓይነት ማሰብ አይጠበቅብንም፤ የግድ ከአንድ ባህል፣ ከአንድ ቋንቋና ከአንድ ማንነት መገኘት አይኖርብንም። እነዚህን ሁሉ ጸጋዎች ከደመርናቸው፣ መጀመሪያ እንደ ችቦው አካባቢያዊ አቅም ይሆኑናል። ቀጥሎ ደግሞ እንደ ደመራው አስተሳስረን በአንድ ዓምድ ላይ ካቆምናቸው ትልቅ ሀገር እንገነባለን። ይህ ችቦዎቹን አንድ አድርጎ የሚያቆመው የመሐል እንጨት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የምንፈጥርበት የፌዴራል ሥርዓት ነው። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ነው። ኢትዮጵያዊነታችን ነው። በዚህ የኢትዮጵያዊነትና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ደመራ፣ ግርማዋ የሚያስፈራ፣ የበለጸገች፣ ጠንካራ፣ ታላቅ የጋራ ሀገር መገንባት እንችላለን። የዚህ ሁሉ ቀመሩ ግን- እንደ ደመራው፣ መደመር ነው።

ችቦውን በየግልና በየአካባቢያችን ልንሠራው እንችላለን። ደመራውን ግን በጋራ ካልሆነ አንደምረውም። የመጣንበት መንገድ ለየቅል ሊሆን ይችላል። እምነታችን፣ ምርጫችንና ምኞታችንም የየብቻችን ችቦ ሊሆን ይችላል። ሀገራችን ግን የጋራችን ደመራ ናት። ያለሁላችን አትኖርም። ምን ብንጓጓ ደመራውን ቸኩለን ለብቻችን አንለኩሰውም። የግድ ሌላውን እንጠብቃለን። እንደ ሀገር እንጂ እንደ ንዑስ አካባቢ፣ ወይም እንደ ሠፈር እኔና የኔ ብቻ ማለት አንችልም። ደመራው ለሁላችን በሚሆን ሥርዓት የሚመራ የሁላችንም ሀገር መስታወት ነው።

ደመራው በኔ ችቦ በኩል ቀድሞ ይለኮስልኝ አንልም። ደመራው ሲለኮስም ‹የኔ ችቦ ትቀጣጠል› ይሆን ብለን አንሠጋም። ከየትም ይጀመር ከየት፣ ሙቀትና ብርሃኑ ለሁሉም እንጨቶችና ችቦዎች በሂደት ይዳረሳል። የኢትዮጵያ ሠናይ እሳት የሆነው የኢትዮጵያ ዕድገት፣ የትም መንደድ ቢጀምር፣ በጊዜ ሂደት ለሁላችን ይደርሳል። አንዱ እንጨት ለሌላው፣ አንዱ ችቦ ለሌላው ብርሃን እንዲሆን በማጋራቱ ከእርሱ የሚጎድልበት ነገር የለም። ነገር ግን የሚጨምረው አቅም አለ። ሁሉም እየተለኮሱ በሄዱ ቁጥር፣ የብርሃኑ አቅም እየጨመረ ይሄዳል።

እኛም ለሌላው ወገናችን ባካፈልን ቁጥር የሚጎድልብን ነገር የለም። የኢትዮጵያ አቅም ግን እየጨመረ፣ እየጠነከረ ይሄዳል። ትኩረታችን የገዛናት ወይም ሠርተን ያመጣናት ችቧችን ሳትሆን ትልቁ ደመራ ነው። የበዓሉ አመስጥሮ ያለውም ከዚሁ ነው።

ችቦውን ልንገዛውና ልንሸጠው እንችላለን። ደመራው ግን ልክ እንደ ኢትዮጵያ ነው። አይሸጥም አይለወጥም። ሁሉም በግል ይዤው ልሂድ አይልም። እዚያው በጋራ ደምረን፣ በጋራ ልቦናችን ይዘነው የምንሄደው – የወል እውነታችን ነው። የእኛነታችን ካስማችንም ጭምር ነው።

ደመራ እውነተኛው መስቀል የተገኘበት ጠቋሚ ኮምፓስ ነው። ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና በአንድነት የመቆም ምሳሌያችን ነው። ደመራ አቅጣጫ ነው። እውነተኛው መስቀል የተለየበት። ኢትዮጵያም ልጆቿ የሚቆሙበትና የሚሄዱበት እውነተኛ አቅጣጫ ለተስፋዋ ብርሃን፣ ለጥንካሬዋም ፈለግ ይሆናታል። ልክ መስቀሉን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ሆኖ ጊዜ እንደወሰደው ብልጽግናን መሻትም እንዲሁ ብዙ ድካምና ጥረት ይፈልጋል። መስቀሉን ማግኘት የብዙዎችን መተባበርና ምክር እንደመፈለጉ በሀገራችን ብልጽግናን ማረጋገጥም በዚሁ ልክ መተባበርና አብሮነትን መፈለጉ ከልቦናችን ይቀመጥ።

የዘንድሮውን የደመራ በዓል እነዚህን ታላላቅ እሳቤዎች እያሰላሰልን እንደምናከብረው ተስፋ አደርጋለሁ።

መልካም የደመራና የመስቀል በዓል ለሁላችን ይሁን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መስከረም 16፣ 2016 ዓ.ም

አዲስ ዘመን  መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You