የበዓሉና የሠላሙ ባለቤት ስኬት!

 በኢትዮጵያ በተያዘው መስከረም ወር በርካታ በዓላት ተከብረዋል፤ በኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ አዲስ አመት በዓል አሀዱ ያለው የመስከረም ወር፣ ሰሞኑን ደግሞ በመስቀል ደመራ፣ በመውሊድ፣ እንዲሁም በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባከበሯቸው በዓላት አምሮ ደምቋል፡፡

በዓላቱ የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የመተባበር፣ ወዘተ የቆዩ እሴቶች ጎልተው የሚወጡባቸው እንደመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ እንቅስቃሴ የታየባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በዓላት ሚሊዮኖች አደባባይ ወጥተው ያከበሯቸው ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ፣ የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ ከተለያየ አካባቢ ተሰባስቦ ያከበራቸው ናቸው፡፡

እነዚሀ በዓላት የተነፋፈቀ ቤተሰብ የሚገናኝባቸው በመሆናቸውም አያሌዎች በዓላቸውን ለማክበር ቤተሰቦቻቸው ወዳሉበት ሀገር ቤት ተመዋል፡፡ ቤተሰብም እነዚህን የናፈቁትን ልጆቹን፣ ዘመዶቹን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ ሲያስተናግድ ሰንብቷል።

እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓላት በድምቀት መከበራቸውን የመገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ስርጭትና በተለያዩ መንገዶች ያስተላለፏቸው ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ በዓላቱ በእርግጥም ደማቅ በሆነ መንገድ ስለመከበራቸው የመስቀል ደመራ፣ የመውሊድ እንዲሁም የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የአዲስ አመት በዓላት አከባበርን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎችም ያረጋግጣሉ፡፡

መንግሥት እነዚህ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ አስቀድሞ ብዙ ሠርቷል፡፡ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አድርጓል፤ በዓላቱ እምነቶቹ በሚፈቅዱት ሥርዓት በድምቀት እንዲከበሩ ከሁለቱም ሃይማኖት አባቶችና ከሠላም ወዳዱ ሕዝብ ጋርም ለመሥራት በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር ተመሳሳይ ዝግጅት በማድረግ ሠርተዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱም በዓላቱ በሠላም እንዲከበሩ ምዕመናኑን በማስተባበር ጭምር በራሳቸው የተለያዩ ዝግጅቶችን አድርገው ነው በዓላቱን ወደ ማክበር የተሸጋገሩት፡፡

መንግሥት በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ለማድረግ ዋና አቅም አድርጎ የወሰደው ሕዝቡን ነው፡፡ የሠላሙ ባለቤት ሕዝቡ ነው የሚል ጽኑ አቋም ያለው በመሆኑም ነው ይህን ያደረገው፡፡ በሀገሪቱ ሠላም ለማስፈን በተደረጉ ጥረቶችና በተገኙ ውጤቶች የሕዝቡ ሚና ምንጊዜም ይጠቀሳል፡፡

በእነዚህ በዓላት አከባበር ወቅትም የሆነው ይኸው ነው፡፡ በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብረዋል፡፡ ለእዚህ ደግሞ በሕዝቡ፣ በሃይማኖት ተቋማቱ፣ በየደረጃው ባለው የመንግሥት አደረጃጀትና በፀጥታ ኃይሉ የተደረገው የተቀናጀ ርብርብ በዓላቱ በሠላምና በድምቀት እንዲከበሩ አስችሏል፡፡ በእዚህ ላይ በተለይ የሕዝቡ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሰሞኑን ከመስቀል ደመራና መውሊድ በተጨማሪ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የብሔሮች ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት ተከብረዋል፤ በዓላቱም ከፍተኛ መጠን ያለው ሕዝብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ያከበራቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በዓላት አዳዲስ የአስተዳደር ክልሎች መፈጠራቸውን ተከትሎ የተከበሩ በመሆናቸው ካለፉት አመታት ከፍ ባለ ድምቀት የተከበሩበት ሁኔታም ታይቷል፡፡ እነዚህ በዓላት ሁሉ ናቸው በሠላም የተከበሩት፡፡

እነዚህ ሁሉ በዓላት የበዓሉ ባለቤቶች በሚፈልጉት መልኩ በድምቀትና በሠላም መከበራቸው ሕዝቡና የፀጥታ አካሉ በዓላቱ በድምቀትና በሠላም እንዲከበሩ ያደረጉት ጥረት ስኬታማነት ማሳያ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ የበዓላቱ ብዛትና መደራረብ እንዲሁም ሁሉም በሠላም መከበራቸው፣ ሠላምን በማስጠበቅ በኩል እየተፈጠረ ያለው አቅም ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱንም ያመለክታል፡፡

በዓላቱ በባህሪያቸው የውጭ ዜጎችን ጭምር የሚያሳትፉ እንደመሆናቸው በሠላም መከበራቸው ለእነዚህ የውጭ ዜጎችና ለመላው ዓለምም ሀገሪቱ ሠላምን በማስጠበቅ በኩል አሁንም በጥንካሬ ላይ ጥንካሬ መደረቧን የሚያሳይና ትልቅ መልዕክት የሚተላለፍበት ነው፡፡

በዓላቱ ተደራርበው የነበረበት ሁኔታ ሠላም የማስከበር ሥራውን በእጅጉ ፈታኝና ውስብሰብ ሊያደርገው የሚችል ቢሆንም፣ ሕዝቡን በማስተባበር በተከናወነው ተግባር በዓላቱን በሠላም በማከበር በኩል አኩሪ ተግባር መፈጸም ተችሏል፡፡ ይህ ሥራ ሠላም እና ደህንነትን ከማስጠበቅ አኳያ አቅም የተገነባበት ሊባልም የሚችል ነው፡፡

ይህ አቅም፣ እነዚህ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ ያስቻለው የተቀናጀ ርብርብ በቀጣይ ሳምንት በድምቀት በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ወቅትም ሊደገም ይገባዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ ብዙ ሚሊዮኖች በተገኙበት እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ በበዓሉ ላይ ከመላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከመላ ዓለም ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች ጭምር ይሳተፋሉ፡፡ ስለሆነም በዓሉ በሠላምና በፍቅር እንዲከበር አሁን የተፈጠረውን አቅም በሚገባ መጠቀም ይገባል፡፡ የበዓሉም የሠላሙም ባለቤት ሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝቡን ይዞ በዓሉ በሠላም እንዲከበር ማድረግም ቀላል ነው፡፡ ከሰሞኑ የታየውም ሁኔታም የሚመሰክረው ይሄንኑ ነው! አዲስ ዘመን  መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You