በኢትዮጵያ ህገ ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪን በቁጥጥር ስር ለማዋል ለ3 ሰዓት የበረረ አውሮፕላን ተመልሶ እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ ግለሰቧ በቁጥጥር ስር መዋሏን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀው፥ ከትላንት በስቲያ እኩለ ለሊት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ያለመፈተሽ መብቱን ተጠቅሞ ወደ ቻይና ለምትጓዝ ግለሰብ ከፍተኛ መጠን ያለው የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶችን የፍተሻ መስመሩን አሳልፎ ለማቀበል ይሞክራል።
ይሁንና ይህን የተመለከቱ የአየር መንገዱ የፍተሻ ሰራተኞች እና የጉምሩክ ሰራተኞች ወደ ቻይና ለምታቀናው ግለስብ አሳልፎ ሊያቀብል የነበረውን ሻንጣ በመቀበል ይፈትሻሉ።
የአየር መንገዱ የፍተሻ እና የጉምሩክ ሰራተኞቹ በጋራ ሻንጣውን ሲፈትሹም በውስጡ 6 ሺ 170 ፓውንድ፤ 33 ሺ 115 ዩሮ እና 1 ሚሊዮን 264 ሺ 975 የኢትዮጵያ ብር በማግኝታቸው ሰራተኛውን በቁጥጥር ስር ያውሉታል።
የአየር መንገዱ ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ቢውልም፤ የገንዘቡን ኖቶቹን ተቀብላ ወደ ቻይና የምትወስደው ግለሰብ ግን ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተነሳው አውሮፕላን ወደ ቻይና በትኬት ቁጥሯ መሰረት ጉዞዋን ትጀምራለች።
በዚህም መሰረት ግለሰቧን በቁጥጥር ስር ለማዋል የጫናትን አውሮፕላን ከ3 ሰዓት በረራ በኋላ ዳግም ተመልሶ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ በማድረግ ግለሰቧ በቁጥጥር ስር ውላለች።