የሀገሬ መልከ ብዙ በዓላት  ዙሪያ ገብ የበዓላት ወግ፤

እኛ ብቻ ሳንሆን በርካታ የዓለም ሀገራት እንደ ባህላቸው፣ እንደ ታሪክና ወጋቸው በየዓመቱ እየዘመሩ የሚቀበሏቸው፣ እያደመቁ የሚያከብሯቸው፣ እየደገሱ የሚደሰቱባቸውና ክብረ በዓላቱ ሲጠናቀቁም “የዓመት ሰው ይበለን!” እየተባባሉ ተመራርቀው የሚሸኛኙባቸው በርካታ በዓላት እንዳሏቸው ይታወቃል።

በዓላቱ በአብዛኛው በይዘታቸው ከተፈጥሮ ክስተት ጋር የተያያዙ፣ ከመንፈሳዊ ይዘቶች ጋር የተጣመሩ፣ የድንገቴ ባህል ሆነው የጸደቁ፣ በፖለቲካ ይሁንታ የተመረጡ፣ ከነጻነት ቀን ጋር የተቆራኙ ወዘተ. ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ። ባህር ማዶ በመሻገር የባዕዳኑን የበዓላት ይዘትና የጥንት አመጣጥ ታሪካቸውን በፈርጅ በፈርጁ ለመዘርዘር የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ስላይደለ የምናልፈው በደምሳሳውና እውነታውን በማስታወስ ብቻ ይሆናል። ይዘርዘሩ ቢባልስ የማንን ሀገር ጠቅሰን የማንን ልንተው እንችላለን? “የማይዘልቅ ቤት፤ በበዓል ስፌት” እንዳይሆንብን በመስጋት በራሳችን ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮሩን መርጠናል።

የእኛን መልከ ብዙ ባህልና በዓላት የምናሞግሰውና ልዩ ክብር እየሰጠን የምንዘክራቸው “ለራስ ሲቆርሱ…” የሚለው ሀገራዊ ብሂል ተጽእኖ ስለሚያሳድርብን ብቻ አይደለም። በርግጥም በዓላቶቻችን በአግባቡ ቢጠኑና፣ ከየትና እንዴት እንደመጡ ታሪካቸው በጥልቀት ቢፈተሽና ሥረ-መሠረታቸው ቢመረመር ከሙገሳም ያለፈ ክብር ሊያሰጣቸው እንደሚችል መግለጹ ከግነት የሚያስቆጥር አይሆንም።

ይህ ጸሐፊ በባህል ጉዳይ ላይ ጥናት እንዳደረገ አንድ ዜጋ፣ ከፍ ሲልም በሀገር ውስጥና በውጭ ምሁራን የተጠኑ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ዋቢ በማቆምና ዩኔስኮም ጭምር አክብሮ የዓለም ቅርስ ያደረጋቸውን ብሔራዊ በዓላቶቻችንን በማስታወስ ብቻ “ለእኛዎቹ መንፈሳዊ ሀብቶቻችን” አፍ ሞልተን ተገቢውን ክብርና አክብሮት እየሰጠን አጉልተን ብናዳንቅ ሊያሳፍረንም ሆነ ሊያሸማቅቀን አይገባም ባይ ነን።

በግርድፍ ዳሰሳ ስለ በዓላት ምንነትና ይዘት ስንናገር አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ሳናስታውስ ማለፉ ተገቢ አይሆንም። ሀገራዊና ሕዝባዊ በዓላት መልካቸውም ሆነ ዓይነታቸው የትየለሌ ይሉት ብጤ ነው። ከመሠረታዊው የኅብረተሰብ አስኳል ከቤተሰብ እንኳን ብንነሳ እያንዳንዱ በደም ዝምድና የተሳሰረ የግለሰቦች ስብስብ ቤተሰብ የእኔ የሚላቸውና ከዓመት ዓመት የሚያከብራቸውና የሚዘክራቸው የራሱ በዓላት ይኖሩታል። ለምሳሌ፡- የቤተሰቡ አባላት የልደት ቀናት፣ የጋብቻ በዓላት፣ አልፎም ተርፎ የሙት ዓመት በዓላትም ሳይቀሩ በበርካታ ቤተሰቦች ዘንድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው “በፈኩ ሻማዎችና በደማቅ ድግሶች” እየታጀቡ ይከበራሉ። በበዓላቱ መከበርም የቤተሰቡ አባላት ደስታና ፍስሃ ደመቅ ብሎ ሊፈካ ይችላል።

ከቤተሰብ ከፍ ሲልም በአንድ አካባቢ ወይንም የተለየ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ማሕበረሰቦች (Com­munities) “የእኔ/የእኛ ብቻ” የሚሏቸው በርካታ ዓመታዊ ክብረ በዓላትን ያከብራሉ። እነዚህ በዓላት አንድም ሃይማኖታዊ አለያም ታሪካዊ ወይንም ፖለቲካዊ ይዘቶች ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በአንዳንድ ሀገራትም የመመሰጋገኛ፣ የመሞጋገሻና በአንድ ጉዳይ ከዓመቱ ቀናት አንድ ዕለት ተመድቦላቸው የሚከበሩና የሚታዋሱ በዓላትም በብዛት መኖራቸው አይዘነጋም።

ከማሕበረሰብ ከፍ ሲልም በሀገር (Societal) ደረጃ በብሔራዊ በዓልነት በየሀገሩ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ/መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ በዓላት ቁጥራቸውም ሆነ ዓይነታቸው እጅግ ብዙ የሚሰኙ ናቸው። በሀገራችን አውድም ካሌንደር ዝግ አድርጎ የሚከበሩት ብሔራዊ በዓላቶቻችን እንኳን በቁጥር 13 ያህል ይደርሳሉ። በሃይማኖታዊ ቀኖና ዶግማ ውሳኔና በአንድ አካባቢ በሚኖሩ ሕዝቦች ይሁንታ የተቸራቸው እጅግ በርካታ በዓላትን እናስታውስ ብንል የዓይነታቸውን ብዛትና የአከባበራቸውን ባህል ዘርዝሮ ለመጨረስ መሞከር የዚህን ውሱን አምድ ፈተና ላይ መጣል ይሆናል።

ብሔራዊ ተሰኝተው በየካሌንደራችን ላይ በጉልህ ተጽፈው ከምናገኛቸው ሀገራዊ አውደ ዓመቶች መካከል ጳጉሚትን አክለን በ13 ከመደብናቸው ወራት መካከል ሁለቱን እንጥቀስ እንኳን ብንል መስከረምና ሚያዝያ ወራት ብቻ በርከት ያሉ በዓላቶቻችንን በመሸከም ቀዳሚዎች እንደሆኑ ማስተዋል ይቻላል። በ2016 ዓ.ም የመስከረም ወር ብቻ መንግሥታዊ ተቋማት ተዘግተው፣ ሠራተኞች ከመደበኛ ሥራቸው አርፈው በብሔራዊ ደረጃ የምናከብራቸው በዓላት አሥራ ሦስት ሲሆኑ፤ በመስከረም ወር ሦስት፣ በሚያዝያ ወር አምስት ያህል ብሔራዊ በዓላት ይኖሩናል።

በተለይ በመስከረም ወራት የምናከብራቸው በዓላት ከአዲስ ዓመት ጋር ስለሚቆራኙ እንኳን ሰው የሚባለው ሰብዓዊ ፍጡር ቀርቶ ተፈጥሮ ራሷ ራሷን በአበቦች ስለምትሸልም ወሩ ልዩ ውበት እንደሚጎናጸፍ ለማንም ተመልካች ግልጽ ነው። በመስከረም ወር የሚከበሩት በዓላት የሚደምቁት በፈንጠዝያና በመገባበዝ ብቻ ሳይሆን በብሩህ ተስፋ ጭምር ለምልመው ነው። ይህንን እውነታ ለማረጋገጥ የሀገሬን ገበሬ እንጉርጉሮ ማዳመጡ ብቻ ዋቢ ሆኖ ሊቆጠር ይችላል።

“በመስከረም ደረሰልኝ ገብሴ፣

በጥቅምት እላለሁ ጥቂት፣

በኅዳር እላለሁ ዳር ዳር፣

በትሣሥ እጅንፉ ድረስ።”

ይህንን የገበሬውን እንጉርጉሮ እንተንትነው ብንል እጅግ ጠጣር የሆኑ የፍልስፍና ሃሳቦችን ልንመዝ እንችላለን። የመስከረም ነፋስ የገበሬውን አዝመራ ከወዲያ ወዲህ እያዘናፈለ ሰብሉን በደስታ “ሲያስፈነጥዝ” አራሹ ወገኔ ምን ስሜት ሊሰማው እንደሚችል ለመገመት አርሱን መሆን ግድ ይሏል። “ደረሰልን ገብሴ” የሚወክለው ጠቅላላውን የአዝመራ ዓይነት መሆኑንም ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።

“በጥቅምት እላለሁ ጥቂት”፡- ገበሬው፣ ቤተሰቦቹና ሠፈርተኛው ካሸተው አዝመራ ላይ በጥሬውም በእንኩቶውም እየቀማመሱ ፈጣሪያቸውን ሲያወድሱና ተፈጥሮን ሲባርኩ ማስተዋል በተመልካችና አድማጩ ዘንድ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል በቄያቸው ተገኝቶ ምስክር መሆን ይቻላል።

“በኅዳር እላለሁ ዳር ዳር” የሚለው አገላለጽም የራሱ የሆነ ትልቅ ምሥጢር አለው። አዝመራው ለጎተራ ሊበቃ የተቃረበበት ወቅት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መቼም ከገበሬውም ጓዳ ቢሆን አልፎ አልፎ ማእዱ መጉደሉ ስለማይቀር ከአጨዳ በፊት በኅዳር ወር ከደረሰው አዝመራ ላይ የገበሬው ሚስት “ጊዜያዊ ችግርን ለመቋቋም” ከማሳው ላይ ያዘረዘረውን በረከት እየሸመጠጠችና እየቆንጠረች በእፍኟም ሆኖ በወፍጮ የቤተሰቧን የዕለት ምግብ ማዘጋጀት የተለመደ ክስተት ነው። ስለዚህም ነው በኅዳር ወር “ዳር ዳር” ተብሎ የተገለጸው።

የታኅሣሥ ወር አዝመራው እየተበራየ ወደ ጎተራ የሚገባበት “የድል ወር” ነው። ከእነ ብሂሉም “የክረምትን ውሃ ጥምና የትሣሥን ርሃብ ለእናትም ቢሆን አይገባትም” የሚባለው ስለዚሁ ነው። በክረምት የሰማይ ጠል ቀን ከሌት ስለሚዥጎደጎድ “ውሃ ጠማኝ” ብሎ የሚያማርር ሰው ጅልም ድኩምም ነው። በታኅሣሥም እንዲሁ አዝመራው በየደጃፉ ወይ ተከምሮ ወይ እየተወቃ አለያም ወደ ጎተራ እየተጓጓዘ ስለሚሆን ርሃብ የጠናበት ሰው ወደ አንዱ ደግ ገበሬ ቤት ጎራ ብሎ “ጉርሻ” ቢጠይቅ ማንም ፊት የሚነሳው የለም። “እስከ ጅንፉ” የተባለውም “እስኪጠገብ” የሚለውን አገላለጽ ይወክላል። “ጅንፉ” በዱላ ጫፍ ላይ የሚገኝ “ድቡልቡል” የተፈጥሮ አካል ወይንም የብረት ተቀጥላ ነው። “ጥጋብ እስከ አንገት” እንዲሉ።

በጥርና በየካቲት የሚውሉ አውዳመቶች በነፃነትና በተዝናኖት የደመቁ ናቸው። በተለይም በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ገበሬው አዝመራውን ወደ ጎተራው ከቶ ስለሚያጠናቅቅና ማሳውም ቢሆን ለጥቂት ወራት ከመተራስ ስለሚያርፍ እንስሳት ያለ ከልካይ በፈለጉበት ቦታ እየዋሉ የሚቦርቁበት፤ የእረኝነት የሥራ መደብ የተሰጣቸው ልጆችም አርነት ወጥተው እረፍታቸውን የሚያጣጥሙበት ጊዜ ነው። ጥርና የካቲት ሌላው መለያቸው በርከት ያሉ ጎጆ ወጪዎች ጉልቻቸውን የሚጎልቱባቸው ወራት መሆናቸው ነው። ስለምን ቢሉ እህሉ ስለሚረክስ፣ ወዳጅ ዘመድም ከግብርናው የሚያርፍባቸው ወራት መሆናቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍል “መንፈሳዊ ድባብ” ጠንከር ብሎ የሚጫናቸውና የበልግ ወራት በመባል የሚታወቁት የመጋቢትና የሚያዝያ ወራትም በራሳቸው ዐውድ የሚነገርላቸው በርካታ ማስታወሻዎች አላቸው። ግንቦትና ሰኔም እንዲሁ የክረምቱ መቃረቢያ ወራት ስለሆኑ አርሶ አደሩ ወገናችን ለቀጣዩ የመከር ጊዜው ራሱን የሚያዘጋጅበት ወቅት ስለሆነ እያንዳንዱን ቀን የሚጠቀምበት በስስትና እንዳይባክኑበት እየተጠነቀቀ ጭምር ነው።

ሀገራዊ አውዳዓመቶቻችን የረቀቀና የመጠቀ ምሥጢር አላቸው የምንለው “በከንቱ ውዳሴ” ራሳችንን ለመደለል ብቻ ሳይሆን በርግጥም እውነት ስለሆነ ነው። ስለ በዓላቱና ወራቱ ደግ ደጉን በመተረክና በማንቆለጳጰስ ብቻ በቡራኬ ቃል ይህንን ጽሑፍ አንደመድምም። የክርስትናና የእስልምና እምነቶች በአንድ ቀን ተጣምረው መስቀልና መውሊድን በጋራ ያከበርንበትን የትናንቱን ዕለት መለስ ብለን ስናስታውስ የሚቆጩንና የሚያስተክዙን ብዙ ሀገራዊ ችግሮች በዙሪያችን መኖራቸውን ባናስታውስ መልካም አይሆኑም።

ከዘጠና ከመቶ በላይ የሀገሪቱ ምእመናን የሚከተሏቸው እነዚህ የሚሊዮኖች የጋራ እምነቶች በተከበሩበት ዕለት ኢትዮጵያችን የዋለችው ፊቷ ፈክቶና ደስታ አርብቦባት አልነበረም። እንዲያውም ፊቷ ገርጥቶና ተክዛ ነበር ብንልም ያስኬደናል። የወትሮው የ“እንኳን አደረሰህ/ሽ!” ልባዊ የደስታ መግለጫ “ወግ ስለሆነ” ቀርቷል ለማለት ባያስደፍርም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢ ባለው ግጭትና ነውጥ ምክንያት በዓላቶቻችን ምልዑ ነበሩ ብንል ፈጣሪ፣ ህሊናችንም ሆነ በችግር ላይ ያሉት ወገኖቻችን ይታዘቡን ይመስለናል።

ኢትዮጵያ እንደዚህ ወቅት ፊቷ ገርጥቶና መከራዋ በዝቶ አውዳመቶቿን በትካዜ ያሳለፈችባቸው ዓመታት አልነበሩም ብሎ መደምደም ባይቻልም የዚህ ወቅት ችግሯ ግን በእጅጉ የገዘፈ ይመስላል። በየቦታው ባሉ ግጭቶች ምክንያት ሞት ነግሦ ፍጥረትን እያረገፈ መሆኑን ስናስተውል “ምን ነካን! አዚም ያደረገብንስ ማነው?” እያል ለመጠየቅ መገደዳችን አይቀርም።

“እንኳን አደረሰህ/ሽ!” እየተባበልን በዓላቶቻችንን በፈካ ፊት፣ ለቸርነት በተዘረጉ እጆች ከማክበርና ከመከባበር ይልቅ “ይዋጣላን!” እያሉ በመፎከር አሸናፊ ለመሆን ራስን እልኸኛ ማድረግ ለግላችን እፍረት በዓለም ማሕበረሰብም ዘንድ ትዝብትን “ከማዝመር” የዘለለ ምንም ፋይዳ ሊኖረው አይችልም።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን መስከረም 19/2016

Recommended For You