ሊትየም ወደ ማምረት እየተሸጋገረ ያለው ኩባንያ

ኢትዮጵያ በማዕድን ሃብት ዕምቅ አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሀገሪቱ ከዚህ እምቅ አቅም እየተጠቀመች ያለችው በተወሰኑት ማዕድናት ለእዚያውም በተወሰነ መጠን መሆኑ ይታወቃል፡፡

ለአብነትም ሀገሪቱ ከወርቅ ማዕድኗ ስትጠቀም የቆየች ብትሆንም አሁንም አብዛኛው አመራረቷ ከባህላዊ መንገድ ያልወጣ ነው፡፡ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት ቢኖራትም ተጠቃሚ መሆን የጀመረችው በቅርቡ ነው፤ እሱም ቢሆን ከጥራት፣ ከገበያና በስፋት ከማልማት አኳያ ብዙ ሥራዎችን ይጠይቃል፡፡ ሌሎች የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ግብአት ማዕድናት በስፋት ያላት ቢሆንም በማልማት በኩል ገና ብዙ ይቀራል፡፡

በሌላ በኩልም የማዕድን ሃብቱን ፈልጎ ማግኘት፣ የተገኘውም ማዕድን በምን ያህል ክምችት እንዳለ በማወቅና በማልማት በኩል ገና ብዙ የሚቀሩ የቤት ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ ለዚህም ዋናው ማነቆ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖሩ አንዱ ሲሆን፤ ማዕድንን ለማልማት አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ አለመኖራቸውና ዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ የማዕድኑ ዘርፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየለሙ ያሉት አብዛኞቹ ማዕድናት በመሬት የላይኛው ክፍል የሚገኙና በቀላሉ ሊለሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ በመሬት ውስጥ ያሉ ገና ያልተደረሰባቸው በርካታ ማዕድናት አሉ። እነዚህን ማዕድናት ፈልጎ ለማግኘትና አልምቶ ለመጠቀም ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አልተሠራበትም፡፡

ሀገሪቱ ገና ያልነካቻቸው የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ማዕድናት ባለቤት መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሌሎች በቅጡ ያለሙ ማዕድናት እንዳሏትም ይታወቃል።

ሀገሪቱ እምቅ የማዕድን ሀብቶቿን በሚገባ በማልማት ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ለማዋል በአስር አመቱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅዷ አካታ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይህን ተከትሎም በከርሰ ምድር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ማዕድናትን አውጥቶ መጠቀም የሚያስችሉ ዕድሎች እየተፈጠሩ ናቸው፤ ባለሃብቶችም በስፋት ወደ ዘርፉ እየገቡ ይገኛሉ፡፡

በወርቅ ልማት ዘርፍ ያለውን ብንመለከት በባህላዊ መንገድ ብቻ ሲመረት የኖረውን የወርቅ ማዕድን በኩባንያዎች በስፋት ማምረት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ኩባንያዎቹ ግንባታቸውን ጨርሰው ወደ ማምረት ሲሸጋገሩ በባህላዊ መንገድ ሲመረት የቆየውን ምርት አምስት እጥፍ ማምረት እንደሚያስችሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሰሞኑን ደግሞ የሊቲየም ማዕድንን የሚያለማ ኩባንያ ማሽነሪዎችን ወደ ሀገሪቱ ማስገባት መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡ ይህ በዓይነቱ ለየት ያለና የሊቲየም ምርትን ለማምረት ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ኩባንያ ቀንጢቻ ማይኒንግ ይባላል። ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማኅበር፤ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጉጂ ዞን ሰባቦሩ ወረዳ ቀንጢቻ አካባቢ የሚገኝ በማዕድን ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ ነው፡፡ የሊትየም ማዕድንን ለማልማት የተቋቋመው ኩባንያው፣ በውጭ ባለሃብቱ ሚስተር ብሩስ ቲኒ እና በኢትዮጵያዊው ባለሃብት ሼህ ዓሊ ሁሴን ከፍተኛ የሼር ድርሻ የተቋቋመ ነው፡፡

ኩባንያው ለመኪና ባትሪ ምርት ዋነኛ ግብዓት የሆነውን ሊትየም የተባለ ማዕድን ማምረት የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሊትየምን ፕሮሰስ በማድረግ እሴት ጨምሮ ማምረት የሚያስችለውን የመጀመሪያ ዙር ማሽን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የሊትየም ምርትን እያመረተ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ከሰሞኑ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባቸውን ዘመናዊ ማሽኖች ባስጎበኘበት ወቅት ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የአፍሪካ ማይኒንግና ኢንጂነሪንግ ተወካይ እና የቀንጢቻ ማይኒንግ ከፍተኛ የሼር ባለድርሻ ሼህ ዓሊ ሁሴን እንዳሉት፤ የሊትየም ማዕድንን አልምቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ኩባንያው ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው የሊቲየም ምርትን አግኝቶ በማልማት ቀዳሚ መሆኑን የጠቀሱት ሼህ ዓሊ ሁሴን፤ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ ማሽን ማስገባቱን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ማሽኑ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከአውስትራሊያና ከካናዳ በተውጣጡ ኢንጅነሮች የተሠራ ዘመናዊ ማሽን ነው፡፡ ማሽኑ በሰዓት 20 ቶን የሚደርስ የሊቲየም ምርትን ፕሮሰስ የማድረግ አቅምም አለው፤ ለልማቱ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ማሽኖች በቀጣይም ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ፡፡

ማሽኑ የሊትየም ምርትን ፕሮሰስ በማድረግ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ይህን ዘመናዊ ማሽን በመጠቀም የሚመረተው ሊትየም ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የሚያሳድግና ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንደሚፈጥር ሼህ አሊ አስታውቀዋል፤ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል ብለዋል፡፡

ሼህ ዓሊ እንዳሉት፤ በዋናነት ለመኪና ባትሪ አገልግሎት የሚውለው ይህ ሊትየም የተሰኘው ማዕድን፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በእጅጉ ይፈለጋል፡፡ በርካታ ሀገራትም የማዕድን ሃብቱን ተጠቅመው ማደግ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም በተፈጥሮ የታደለቻቸውንና ተዝቀው የማያልቁ የተፈጥሮ ሃብቶች ያላት ሀገር እንደመሆኗ እነዚህን ሃብቶች በመለየት አውጥቶ መጠቀምና ማልማት ይገባል፤ ለዚህም ቀንጢቻ ማይኒንግ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የሊትየም ማዕድን ፈልጎ ወደ ልማቱ የገባ ብቸኛ ኩባንያ መሆን ችሏል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ከሚጠይቀው ወጪ በበለጠ ለሀገሪቷ ይዞ የሚመጣው በረከት ትልቅ በመሆኑ ኩባንያው ለፕሮጀክቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያን ለማሳደግ ከተፈለገ በከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኙ የማዕድን ሃብቶችን እንደ ነዳጅና ማዕድናት ያሉትን ማልማት የግድ ነው ያሉት ሼህ ዓሊ፣ ለዚህም መንግሥትን ጨምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ግንዛቤው ኖሮት ተባባሪ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ፕሮጀክቱ ማዕድኑን በማልማት ከሚፈጥረው የሥራ ዕድልና ከሚያመጣው የውጭ ምንዛሪ ባለፈ ለመላው ኢትዮጵያዊ ሃብት መሆኑንም አስታውቀዋል፤ ሀገሪቷን ወደ ላቀ የዕድገት ጉዞ የሚወስዳትና ካደጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ትልቅ አቅም ያለው እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ዕምቅ አቅም ያላት ቢሆንም ፈልገን ያገኘነውና ለማልማት የሞከርነው እጅግ በጣም ጥቂቱን ነው›› ያሉት ሼህ ዓሊ፤ ማዕድናቱን ፈልጎ የማግኘቱ ሥራ ቀዳሚና እንደሆነና ገና ብዙ መሥራትን እንደሚጠይቅም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት እየለሙና በሕገወጥ መንገድ እየወጡ ያሉ ማዕድናት ከመሬት የላይኛው ክፍል በቀላሉ የሚገኙት እንጂ በከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኙ ማዕድናት አለመሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሀገር ውስጥ ያሉ ማዕድናት ገና ያልተነኩና ያልተመረቱ ስለመሆናቸው አስታውቀዋል፡፡

ዘመናዊ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ማዕድኑን ፈልጎ ለማውጣትና ለማልማት መሰል ተቋማት ወሳኝ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት፣ ከልማቱ በተጨማሪ መሰል ኩባንያዎች በሕገወጥ መንገድ የሚወጡ ማዕድናትን ለመከላከል አቅም እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹በቀጣይም ቀንጢቻ የማዕድን ፋብሪካ ከሚያመርተው ማዕድን በተጨማሪ በተለያየ መንገድ ማዕድን ከሚያወጡ አካላት ጋር በጋራ ይሠራል›› ያሉት ሼህ ዓሊ፤ ማንኛውንም ማዕድን በጥሬው ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ ሲላክ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝም ነው የተናገሩት። ኩባንያው በቀጣይም የተለያዩ ማሽነሪዎችን በማስመጣት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ቀንጢቻን የመሳሰሉ ኩባንያዎች ሲበራከቱ ሀገሪቱ በዋናነት በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክሎጂ ሽግግር ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችልም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ የሚወጣውን ማዕድን መከላከልና መቆጣጠር እንደምትችልም ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከማዕድን በተጨማሪ የነዳጅ ሀብት ያላት ሀገር እንደመሆኗ በነዳጅ ሀብት ልማትም እንዲሁ ጠንክሮ መሥራትን ይጠይቃል›› ያሉት ሼህ ዓሊ፤ ኩባንያው በቀጣይም በነዳጅ ሃብት ልማት ላይ የመሰማራት ዕቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል። በዚህም ሀገሪቷንና ሕዝቧን ከድህነት ማውጣት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም ማኅበረሰቡ በተለይም በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኘው የጉጂ ማኅበረሰብ አሁን የገቡትን ማሽነሪዎች እንደ ግል ሃብቱ ተመልክቶ ሊጠብቃቸው፣ ሊንከባከባቸውና ሥራውን ሊያግዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ዘርፉ የሚያመነጨው ሃብትም ኦሮሚያን ጨምሮ ለመላው ኢትዮጵያ ፋና ወጊ ነው ብለዋል፡፡

ሊትየም ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ለማዕድን ዘርፉ ትልቅ ተስፋ መሆኑን የጠቀሱት የአፍሪካ ማይኒንግና ኢነርጂ ምክትል ሥራ አስኪያጅና በቀንጢቻ ማይኒንግ ሼር ያላቸው አቶ ሳሚ ሚሊዮን፣ ኩባንያው ሊትየምን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ይናገራሉ፤ አሁን ምርቱን ማምረት የሚያስችለውን ዘመናዊ ማሽን ማምጣት እንደቻለም ተናግረዋል፡፡ ቀንጢቻ ማይኒንግ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላትን ዕምቅ አቅም አውጥታ መጠቀም እንድትችል ትልቅ አቅም መሆን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

ዓለም የመኪና ባትሪን እየተጠቀመ ባለበት በዚህ ወቅት ለመኪና ባትሪ አገልግሎት የሚውል ንጥረ ነገርን ማግኘት ተስፋ ሰጪና የሚበረታታ መሆኑን አቶ ሳሚ ተናግረዋል፡፡ ሊትየም በተገኘበት አካባቢ ከዚህ ቀደም ታንታለም ይመረት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሳሚ፤ ኩባንያው ሊቲየምን ፈልጎ ወደ አካባቢው እንደሄደም አስታውቀዋል። በዚህም ሊቲየምን ማግኘት እንደቻለና ወደ ውጤት እየቀረበ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ኩባንያው በቀጣይ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥም ማሽኑን በመትከል የሙከራ ምርት ያመርታል፡፡ ኩባንያው ማሽኑን ከማስገባት ባለፈ ቴክኖሎጂውን ማሸጋገር ችሏል፤ ይህም እንደ ሀገር ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመቅረፍ ረገድ ዓይነተኛ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ በዘርፉ ትልቅ የአቅም ግንባታ መፍጠር ተችሏል፡፡

ኩባንያው ማሽኖችን ባስገባበት ወቅት የተገኙት የቀንጢቻ ማይኒንግ ኩባንያ ጀኔራል ማናጀርና ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ብሩስ ቲኒ በበኩላቸው፤ ቀንጢቻ ማዕድን ፋብሪካ ሊትየምን ለማምረት የሚያስችሉትን ዘመናዊ ማሽነሪዎች ማስገባት እንደጀመረና በቅርቡም ወደ ምርት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ይህም ለሀገሪቷ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ የሚኖረው ከመሆኑም በላይ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያዊ የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው የማዕድን ሀብቱን ከማልማት ጎን ለጎን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ የጤና ተቋማትና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እያሟላ መሆኑንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት ትልቅ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ በማዕድን ዘርፍ ብዙ መሥራትና መጠቀም ይኖርባታል ብለዋል፡፡ ወቅቱ የሊትየም ምርት በዓለም ላይ ተፈላጊነቱ በእጅጉ እየጨመረ ያለበት መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ብሩስ፤ ኢትዮጵያም በቀጣይ በሊትየም ምርት ከፍተኛ ገቢ የምታገኝበትና የውጭ ባለሀብቶችን ትኩረት መሳብ የምትችልበት ጊዜ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቀንጢቻ ማይኒንግ በአውስትራሊያ እና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተቋቋመ በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የተመሠረተ ኩባንያ ሲሆን፤ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ1000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ዘርፉ በተለይም በውጭ ምንዛሪ ግኝት ለሀገሪቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያ ከርሰ ምድር የተገኘው የሊትየም ማዕድን በሙሉ አቅም መመረት ሲጀምርና ለዓለም ገበያ ሲቀርብ ኢትዮጵያ በዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደምትችልም ነው መረጃዎች ያመለከቱት፡፡

የቀንጢቻ ማይኒንግ ኩባንያ ባለበት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጉጂ ዞን ሰባ ቦሩ ወረዳ ቀንጢቻ አካባቢ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ የታንታለም ማዕድን ክምችት በሩሲያ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች የተገኘ ስለመሆኑና በማዕድን ክምችቱም ከታንታለም ውጪ የዩራኒየምና ሊቲየም ማዕድናት እንደሚገኙ ስለመረጋገጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You