
ለመስክ ሥራ ከአዲስ አበባ ውጭ ቆይቼ ስመለስ የሚያጋጠመኝ ችግር ነው። የመስክ ጉዞ የመጓተት ጣጣ ስለሚበዛበት አዲስ አበባ ስንገባ ይመሻል። የአዲስ አበባ መንገድ ደግሞ የተዘጋጋ ስለሆነ ቤት ለመድረስ የበለጠ ይመሻል። ከቤቴ አካባቢ ስደርስ ሱቅ የሚባል ነገር፣ ምግብ ቤት የሚባል ነገር አይኖርም። አብዛኞቹ ይዘጋሉ። መድኃኒት ቤቶች ሳይቀር በጊዜ ይዘጋሉ። ይሄ ነገር በተለይም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ቀጥሎም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በነበረው ስጋት ልማድ ሆኖ ቀረ።
ገና ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እንኳን ሳይሆን አገልግሎት ሰጪ ቤቶች ሁሉ ተዘግተው ሳይ፤ እንዴት አንዲት ዓለም አቀፍ ከተማ በፈለጉ ሰዓት የፈለጉት ነገር የማይገኝባት ትሆናለች? እያልኩ አስባለሁ። በሌሊት ሊሠሩ የሚችሉት ጭፈራ ቤቶች ብቻ ናቸው። ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ ምናልባትም ግሮሰሪዎች ናቸው። ለሁሉም ሰው አገልግሎት የሚሰጡት ግን ዝግ ናቸው።
ከሁለት ዓመታት በፊት ይመስለኛል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች ሥራ በፈረቃ ሊሆን ነው የሚሉ ዜናዎች ተሰምተው ነበር። ከሳምንታት በፊት ደግሞ ከምሽት አራት ሰዓት በፊት ንግድ ቤቶች እንዳይዘጉ የሚከለክል አዋጅ እንደወጣ ሰምተናል። የፈረቃው ጉዳይ ግን ምን ላይ እንደደረሰ ሳይታወቅ አጀንዳው ተረስቷል። ፈረቃም ሆነ እስከ ምሽት አራት ሰዓት መሥራት ለአዲስ አበባ መዘግየት ነበረበት ወይ?
ለፈረቃ ሥራው በወቅቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም አንደኛው ግን ‹‹አዲስ አበባ ተኝታለች›› ከሚል የመጣ ነው። አዲስ አበባን ያህል ትልቅ ዓለም አቀፍ ከተማ ተኝታለች፤ ከሚሠራበት ሰዓት ይልቅ የማይሠራበት ሰዓት እየበለጠ ነው። ውድ የሆነው ጊዜ እና የሰው ኃይል እየባከነ ነው። የመውጫና መግቢያ ሰዓት አንድ ዓይነት በመሆኑ መንገዶችም እየተጨናነቁ ነው።
የመንግሥት ሠራተኞች ሥራ በፈረቃ መሆን የግል ንግድ ቤቶች ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ጥቅሙ እነርሱም አምሽተው እንዲሠሩ ያደርጋል፤ መንግሥት ባያስገድዳቸው እንኳን ቢዝነስ ያስገድዳቸዋል። ለምሳሌ፤ የሥራ ፈረቃው እስከ ምሽት አራት ወይም አምስት ሰዓት ይቆያል እንበል። በዚያን ሰዓት መደበኛ እንቅስቃሴ አለ ማለት የግል ንግድ ቤቶች ተጨማሪ ሠራተኛ ቀጥረውም ቢሆን በፈረቃ ይሠራሉ ማለት ነው። መንግሥት አስገድዷቸው ሳይሆን ለቢዝነስ ሲሉ ማለት ነው፤ ምክንያቱም በዚያን ሰዓት የሚንቀሳቀሰው ሕዝብ አገልግሎት ይፈልጋል። ማታ በጊዜ የሚዘጉት ተገልጋይ ስለሌለ ነው። አብዛኛው ሰው ከምሽት 2፡00 በፊት ተጠቃሎ ስለሚገባ ነው። ከዚያ በኋላ የሚያመሸው ደግሞ መጠጥ እንጂ ሌሎች ነገሮች ላይ እምብዛም ስለሆነ ነው። መደበኛ እንቅስቃሴ ካለ ግን መደበኛ አገልግሎቶች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም፣ የግል ንግድ ቤቶችም ክፍት ሆኑ ማለት፤ አዲስ አበባ እውነተኛ ዓለም አቀፍ ከተማ ሆነች ማለት ነው። የከተማ ደንቡ እንደዚያ ነው፤ በከተማ ቀኑ እና ሌሊቱ እምብዛም ልዩነት የለውም፤ ሁሌም እንቅስቃሴ ነው። ስለዚህ የሥራ ፈረቃው ለሠራተኞች ጥቅም ብቻ ሳይሆን ከተማዊ ገጽታንም ያሳምራል ማለት ነው።
በፈረቃ ሥራው ላይ በወቅቱ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ነበር። በማህበራዊ ገጾች ሲወሩ ከሰማኋቸው ስጋቶች አንዱ የደህንነት ሥጋት ነው። በተለይም በምሽት ሰዓት ዝርፊያ የተለመደ ሆኗል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለኅ ይወት አስጊ የመሆን ደረጃ ላይ የደረሱ እገታዎችና ድብደባዎች እያጋጠሙ ነው። 10 ሺህ ብር ለማያወጣ ስልክ ብለው የሰው አካል የሚያበላሹ ወንበዴዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡
ዳሩ ግን እነዚህ ወንጀሎች በምሽት የበዙበት ምክንያት ጨለማ ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ በምሽት እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ስለሆነ ነው። እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ናቸው ማለት አንድ ግለሰብ ብቻውን ቢንቀሳቀስ አስፈሪ ነው ማለት ነው። በዚያን ሰዓት የእንቅስቃሴ ነፃነት ያላቸው ሌቦች ናቸው። እንቅስቃሴው መደበኛ ቢሆን ግን ልክ እንደ ቀኑ ይሆናል ማለት ነው። መንገዱ ሁሉ ሰው ከሆነ ያን ያህል አይደፋፈሩም። ምሽቱን የሚፈልጉት ለጨለማው ብቻ ሳይሆን ለፀጥታውም ጭምር ነው፡፡
ይህ ማለት ግን ጨለማው አያግዛቸውም ማለት አይደለም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህን ነገር ሲያስብ መሠረተ ልማቶችንም አብሮ ማሰብ አለበት። ዋና ዋናዎቹ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በኮሪዶር ልማት የተዋቡ እና ያማሩ ቢሆንም አሁንም፤ አስፈሪ የሆኑ አካባቢዎች ስላሉ በተለይ በቂ አምፖል የሌለባቸው መታጠፊያና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ስጋት ናቸው። የተቆፋፈሩ መንገዶች መስተካከል አለባቸው። የፀጥታ አካላት በበቂ ሁኔታ ሊመደቡ ይገባል። ምክንያቱም ምንም ቢሆን የሰው ቁጥር እንደ ቀኑ አይበዛም፤ ምሽት ሲሆን መቀነሱ የግድ ነውና ዘራፊ መብዛቱ አይቀርም።
የፀጥታ ኃይል ተጠናክሮ፣ የጨለማ ቦታዎች ሁሉ መብራት ከኖራቸውና መደበኛ እንቅስቃሴዎች ከተለመዱ ዝርፊያ እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው። ምንም እንኳን ዘራፊ በቀንም የሚያጋጥም ቢሆንም የምሽት ሲሆን ግን የተባባሰ ነው። ስርቆትን ሥራዬ ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ተስፋ ሲቆርጡ ሌላ አማራጭ ይፈልጋሉ። ስለዚህ የፈረቃ ሥራ ቢኖር በተገቢው መንገድ ከተሠራበት የሌባ ቁጥርን ይቀንሳል እንጂ አይጨምርም።
እኛ ኢትዮጵያውያን ጊዜ እንደምናባክን ዓለም አውቆብናል። ቢያንስ ግን የሀገሪቱ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ እንኳን ጊዜ ዋጋ ይኑረው። በአዲስ አበባ ተጀምሮ ውጤቱ ሲታይ ሌሎች ከተሞችም ይሠሩበታል ማለት ነው። ያኔ በመንግሥት አቅጣጫ ሳይሆን አሠራሩ በራሱ ልማድ ይሆናል፤ ንግድ ቤቶች ምናልባትም 24 ሰዓት የሚሠሩ ይሆናሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን ከምሽት በኋላ ምንም ነገር የሚሠራ አይመስለንም፤ አሁን የታሰበው የፈረቃ ሥራ ይህን የገነገነ ልማድ መለወጥ ያስችላል።
የፈረቃ ሥራው ሌላኛው ጠቀሜታው ሠራተኞች የራሳቸውን ሥራ እንዲሠሩ ነው ተብሎ ነበር። የጠዋት ተረኛ የሆነ ከሰዓት የራሱን ሥራ ይሠራል፤ የከሰዓት የሚሆነውም እስከሚገባ ድረስ የራሱን ሥራ ይሠራል። ይህ ደግሞ ፈጠራንና ትጋትን ያለማምዳል ማለት ነው። እዚህ ግባ ለማይባል ሥራ ከጠዋት እስከ ማታ የቢሮ ወንበር ላይ መዋል ብክነት ነው። ያ ሰው የግል ሥራውን ቢሠራ ለግሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገሩም ይጠቅማል። ዜጎች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ሲችሉ ነው አንዲት ሀገር ተጠቀመች የሚባለው። ብዙ ሠራተኛ ከጠዋት እስከ ማታ ቢሮ ውስጥ አጉሮ ማዋል እንዲያውም የሀገርና የመንግሥት ሸክም እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
እርግጥ ነው ፈረቃ ተደረገ ማለት ሁሉም ሰዎች ሥራ ፈጥረው ይሠራሉ ማለት አይደለም፤ የግማሽ ቀን የቅጥር ሥራ ያገኛሉ ማለትም አይደለም፤ እሱ እንደ ግለሰቦች ጥረት ይወሰናል። ዳሩ ግን ዕድሉን መፍጠርና አሠራሩን ማለማመድ ጥሩ ጅማሮ ነው።
ከምንም በላይ ግን ከተማዋን የዓለም አቀፍ ከተማ ቅርጽ ያስይዛል። ምሽትን ተገን አድርጎ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ይቀንሳል። የሥራ ባህልን ያዳብራል። አገልግሎትን ያፋጥናል። አዲስ አበባ ጊዜ ላይ ተኝታለችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይሄን ነገር ቢያስብበት! ነዋሪዎችም ባህል እናድርገው!
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም