የበጎ ፈቃድና በጎ ምግባር አዝመራዎች

በሀገራችን መረዳዳት እና መደጋገፍ የቆየ እሴት መሆኑ ይታወቃል። ቀድሞውንም የነበረ ጠንካራ ማኅበራዊ መሠረት ያለው ከመሆኑም ባሻገር ባህላዊ እሴት መሆኑን የሚያመላከቱ በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። በርካታ ዜጎች በእነዚህ ምሳሌዎች ለብሰዋል፤ ጎርሰዋል፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ቀና ተደርጓል፤ አመት በዓል ሲደርስ ቤታቸው አመት በዓል አመት በዓል እንዲሸት ሆኗል፣ ወዘተ.፡፡

በሀገራችን አሁንም በርካታ የመንግሥትንና የማኅበረሰቡን ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች ይገኛሉ። በተቋም ደረጃ ሊሠሩ የሚያዳግቱ ኅብረትን፣ በጎ ፍቃደኝነትን የሚጠይቁ አያሌ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ዜጎች በመታደግና ማኅበራዊ ኃላፊነቶች በመወጣት በኩል በአንዳንድ ተቋማት የሚከናወኑ ተግባሮች እንዳሉ ሆነው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ኅብረተሰቡን እያስተባበረ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየሠራ ይገኛል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ዜጎችን ለመታደግ በተነሳሽነት እያከናወናቸው ያሉ የመደጋገፍ ምግባሮች ጎልተው እየታዩ ነው፡፡ በመንግሥት አነሳሽነት እየተከናወኑ ያሉ የመደጋገፍ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በማኅበረሰቡ ብሎም በሀገር ደረጃ እየጎለበተ እንዲመጣ እያደረገም ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በበዓላት ወቅት አቅሙ የፈቀደ ሰው እጁ ያጠረበትና ድጋፍ የሚሻ ወገኑን «አለሁ ባይነትን» ማሳየቱ፣ ማዕድ ማጋራቱ እየጎለበተ መጥቷል፤ መኖሪያ ቤታቸው ለፈረሰባቸው መኖሪያ ቤት መጠገን እየተለመደና ባህል እየሆነ ይገኛል፡፡ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር፣ በትራፊክ ማስተናበር እየተሠሩ ያሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እየሰፉና እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡

ወይዘሮ መስከረም አብርሃ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የቤት እድሳት እድል ተጠቃሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የቀድሞ መኖሪያ ቤታቸው ለኑሮ ምቹ አልነበረም። ፈሳሽ ውሃ የሚያልፍበት ቱቦ የነበረበት እንዲሁም በቆርቆሮ የተሠራ ለቅዝቃዜ የሚያጋልጥ ነበር። በዚህ ቤት ውስጥ ከአምስት ልጆቻቸው ጋር ለመኖር ተገደው እንደነበር ወይዘሮ መስከረም ያስታውሳሉ።

«አሁን በተሻለ ቤት ውስጥና የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን» የሚሉት ወይዘሮ መስከረም፤ አቅመደካሞችን በመለየት ለቤት እድሳት ተጠቃሚ መደረጉም በማስመልከት የከተማ አስተዳደሩ፣ የወረዳ እና የብሎክ አመራሮች ጨምሮ ሁሉም ድጋፍ ያደረጉ ተቋማት እና ባለሀብቶችን አመስግነዋል። አቅመ ደካማ የሆነን ሰው መንገድ ከማሻገር ጀምሮ መደጋገፍ ያለው ለሌለው ማሰቡ ደስታን የሚሰጥ በመሆኑ እርሳቸውም በተመሳሳይ አቅም በፈቀደ ሁሉ ለተቸገሩት መልካምነትን በማድረግ ውስጥ የሚገኘውን ደስታ ለመጋራት እንደሚያስቡም ተናግረዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳው አንድ በጎ ፈቃድ ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ አመለ አለባቸው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በ90 ቀናቱ በተደረገ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሠሩ ሥራዎች በገንዘብ ቢተመኑ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርስ ነው። በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ የማይችሉ 179 ሰዎች ከሆቴሎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተከናወኗል። 116 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ ተደርጓል። 377 ሰዎችም በከተማ ግብርና ተጠቃሚ ተደርገዋል። 30 ሜትር ኪዩብ ቆሻሻ ተነስቷል። ማዕድ በማጋራትም በመጀመሪያ ዙር 636፣ በሁለተኛ ዙር 695 ሰዎች የተጠቀሙ መሆኑን ተናግረው እንዲሁም ለመስቀል በዓል 118 ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስተባባሪዋ ይገልፃሉ።

«ስድስት አባወራዎች የቤት እድሳት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል» የሚሉት አስተባባሪዋ፤ በአንደኛ ዙር ከሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በሁለተኛ ዙርም ከአንድ ነጥብ 69 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሥራ መሠራቱን ይናገራሉ።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ብርሃኑ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በበዓሉ ዋዜማና ከበዓሉ ማግስትም ከተማዋን ፅዱና ወብ በማድረግ በተለይ በመስከረም ወር የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ዜጎች በነፃነት እንዲያከብሩ የመሥራት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዓሉ ያለው ለሌለው እያካፈለ በመተሳሰብ፣ በአበሮነት እና በመደጋገፍ ማክበር ይገባል የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጇ፤ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ከተማዋን የሚያቆሽሹ ጉዳዮች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በበዓሉ ማግስትም በቀጣይነት ማጽዳት እንደሚገባ በዚህም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በወጣቱ መሰጠት እንደሚኖርበት ገልፀዋል።

የመስቀል፣ የእሬቻ በዓልን ጨምሮ በርካታ በዓላት መከበሪያ እና የቱሪዝም ወቅት በመሆኑ ከተማዋ እንደከዚህ በፊቱ በቆሻሻ እንዳትታወቅ ሁሉም አካባቢውን አጽድቶ ከተማዋ ጽዱና ወብ ለቱሪስት እንድትሆን ለማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ እየተሠራ መሆኑንም። ከከተማ ውበት እና ፅዳት ጋር ተያይዞም ከተማዋን ከማስዋብ ጀምሮ ከብሎክ እስከ ክፍለከተማ ያለው ሁሉም አካባቢውን ለማስዋብ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክፍለ ከተማው በበጎ ሥራዎች ጋር ተያይዞ ክረምቱን በሙሉ ቤት የፈረሰባቸውና ቤት የሌላቸውን የማገዝ ሥራዎች መሠራቱን ገልፀዋል። ባለፉት ስድስቱ የጳጉሜ ቀናት ብቻ ከ35 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች ማዕድ የማጋራት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል። በክፍለ ከተማ በሚደረጉ የጽዳት ንቅናቄዎችም በየወረዳው ስድስቱን የጳጉሜ ቀናት የፅዳት ንቅናቄ ወቅት ኅብረተሰቡ ወጥቶ አካባቢውን የሚያጸዳበት ከተማዋን የሚያጸዳበት የቆሸሹ የውሃ ማስተላለፊያ ቦዮችን የሚያጸዱበት ሁኔታዎች ነበሩ፤ በቀጣይነትም ይሠራል ብለዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመከላከል ነው። በዚህም በበጎ ፈቃደኝነት ትራፊክ ፖሊስን በማገዘ እግረኛ መንገድ እንዲያቋረጡ የሚያግዙ አስተናባሪዎች ይሳተፋሉ።

ወጣት ሰላማዊት ነዒም በበጎ ፈቃደኝነት ትራፊክ በማስተናበር ትሠራለች። የዝግጅት ክፍላችን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለገሐር አካባቢ ስታስተናብር አግኝቷታል። በጎ ፈቃደኛ ለ8 ወራት መሥራቷን ትናገራለች። ሰዎች ብዙ ጊዜ በሃሳብ ላይ ሆነው መንገድ ሲያቋርጡ ለአደጋ ስለሚጋለጡ ሕይወት ለመታደግ በፈቃደኝነት እየሠራች ትገኛለች። ኅብረተሰቡ መንገድ ሲያቋርጥ መጠንቀቅ እንደሚገባው በማስገንዘብ በፈቃደኝነት ለሚደረገው ትራፊኩን የማስተባበር ሥራም እገዛ እንዲያደርጉና በታዛዥነት በእግረኛ ማቋረጫ ብቻ እንዲሻገሩ ትመክራለች።

«እግረኞች ለተሽከርካሪ አደጋ እንዳይጋለጡ እና አካል ጉዳተኛ እንዳይሆኑ በምሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጣም ደስተኛ ነኝ» የምትለው ወጣቷ ባለፉት ስምንት ወራት ጠዋት 12 ተኩል እስከ አራት ሰዓት፤ ከሰዓት ከዘጠኝ ተኩል እስከ 12 ሰዓት ተኩል ኅብረተሰቡን እያገለገለች እንደሆነ ትናግራለች። ኅብረተሰቡ በተለይ በበዓላት ቀናት እና የአደባባይ በዓላት በሚከበርበት ወቅት እራሱን እና ቤተሰቡን ከተሽከርካሪ አደጋ እንዲጠብቅ አሳሰባለች።

የመደጋገፍና በጎ ምግባርን እንደ ባህል የማስረፅ የቆዩ እሴቶችን ተቋማዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በመንግሥት ስር ተቋቁመው በተደራጀ መልኩ በጎ ምግባር ሥራን ከሚሠሩት ተቋሞች ውስጥ የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አንዱ ነው። በተለይ በመዲናዋ በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እና ፕሮግራሞች በማስተባበር ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አቶ አብርሃም ታደሰ እንደሚገልፁት፤ በ2015 በጀት ዓመት በ14 ፕሮግራሞች እና 18 መርሃ ግብሮች መጀመሩን ያስረዳሉ። ከስድስት ሺህ 415 በላይ ቤቶች ታድሰው ለኅብረተሰቡ የተላለፉ ሲሆን፤ በማዕድ ማጋራትም ከ800 ሺሀ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። በልዩ ፍላጎቶች ላይም ትምህርትና ሥልጠናዎች በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በቀይ መስቀል ደም ልገሳ፣ የመንገድ ትራፊከ ደህንነት፣ የአካባቢ ሰላም፣ የኪነጥበብ እና ስፖርታዊ እንቀስቃሴዎችና የወሰን የለሽ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጭምር ተሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ የወሰን የለሽ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሲዳማ ክልል በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋ፣ እና በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ልምድን የማካፈል እና የበጎ ሥራዎች በጋራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በአጠቃላይ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ሥራ ላይ የዋለበት እና ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሆኑበት መሆኑን አንስተዋል። ትግበራዎቹም ማኅበረሰቡ ከተጋገዘ እና ከተረዳዳ የማይሻገረው ችግር እንደሌለ ማሳያ መሆኑን ያስረዳሉ።

«የክረምቱ ወር በጎ ፈቃድ አገልግሎት ግንቦት ወር የተጀመረ ሲሆን ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የተጀመረ ነው» የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት እንደታሰበ ይገልፃሉ። መርሀ ግብሩም እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ መሆኑንም ይናገራሉ። በክረምቱ በአጠቃላይ ከተጀመሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ በላይ የቤቶች እድሳት አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም የተጠናቀቁ አንድ ሺህ 686 ቤቶች መተላለፋቸውን ተናግረዋል። ቀሪዎቹም በቀጣይ ጊዜ እየተጠናቀቁ ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉም አመላከተዋል።

አቶ አብርሃም እንደሚናገሩት፤ በተለይ የቤት እድሳት መርሃ ግብሩ ሰፊ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑ ስድስት ሺህ 415 ቤቶች ተገንብተው ከተሰጡት መካከል ከአንድ ሺህ 30 በላይ የሚሆኑት ቤቶች በሕንፃ ደረጃ ተሠርተው የተሰጡ መሆናቸውን ይናገራሉ። እነዚህም ቤቶች በዝቅተኛ ደረጃ ውስጥ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ ለሀገር ባለውለታዎች ሆነው ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሸ የሚያደርግ ነው። ግንባታውን ለማከናወን የከተማዋ ባለሀብቶች ሚና ከፍ ያለ መሆኑ በመግለፅም በተመሳሳይ እቅዱን እውን ለማድረግ ወጣት በጎ ፈቃደኞች ተቋማት ሰፊ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

«በኑሮ ውድነት ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ በተሠራ ሥራም በ2015 በጀት ዓመት ከ800 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል» የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ በክረምቱ እና በበዓሉም ከ300 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። የበጎ ሥራ ትግበራው በዝቅተኛ ኑሮ የሚገኙ ነዋሪዎችን ከማገዙ በተጨማሪ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍሉን በማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በመፍጠር፣ ማኅበራዊ ችግርን በመፍታት፣ በተዘዋዋሪም የተረጋጋ ፖለቲካ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሆነም አስረድተዋል።

አቶ አብርሃም በጎ ፈቃደኝነት እርዳታ ሳይሆን ከልብ ወገንን መደገፍና ቸር መሆንን እንደሚጠይቅ ገልፀው፤ ወገንን የማገዝ፣ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ። አሁን በጎ የሚደረግላቸው ሰዎች ነገ ለሌሎች የሚደርሱ በመሆኑም ተዘዋዋሪ እና ተሻጋሪ ውጤት ያለው መሆኑንም ይገልፃሉ። አያይዘውም አንድ ሰው ታሞ መንገድ ላይ ቢወድቅ ድጋፍ የሚያገኘው ገንዘብ ስላለው ወይም ሀብት ስላለው ሳይሆን በተገቢው ቦታና ጊዜ የሚደግፈው ሰው ሲገኝ መሆኑን አንስተው፤ የማኅበረሰቡ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ይገልፃሉ። እንዲሁም በጎነት ከፍተኛ የኅሊና እርካታ የሚገኝበት እንደማኅበረሰብ ደግሞ ለሌሎች ደስታን እየፈጠሩ ለራስ የኅሊና ሰላም ለመገብየት ትልቅ አቅም በመሆኑ ሊሰፋ እና ሊያድግ የሚገባ መሆኑን አመላክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You