
አዲስ አበባ:- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚከበሩት ዓመታዊ በዓላት መካከል የሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ «ጋሪ ዎሮ» በዓል በአሶሳ ከተማ ተከበረ።
በዓሉ በየዓመቱ መስከረም ወር አጋማሽ ላይ የሚከበር ሲሆን በዓሉን ለመታደም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ይሰባሰባሉ። በዓሉ ትናንት በአሶሳ መከበር የጀመረው በብሔረሰቡ ታላላቅ አባቶች ባደረጉት የምርቃ ሥነ-ሥርዓት ነው።
የብሔረሰቡ የሀገር ሽማግሌ አቶ ለማ አልጋ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ በዓሉ የብሔረሰቡ አባላት ወደ አዲስ ዓመት በመሸጋገራቸው ለፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው።
የበዓሉ አከባበር በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት የሚጀመር ሲሆን በእዚህም አዲስ የለማ ሰብል በረከት እንዲኖረው ከመመኘት በተጨማሪ ዓመቱ እንደሀገር ሰላምና ደህንነት የሰፈነበት እንዲሆን ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
በእዚህም የሀገር ሽማግሌዎቹ ለአዲሱ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ፤ ዘመኑ የሰላምና የፍቅር ይሁንላችሁ እያሉ ይመርቃሉ ብለዋል። በበዓሉ መክፈቻ ላይ ከምርቃት ጎንለጎን ደመራ የመለኮስ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
አቶ ለማ እንዳሉት በዓሉ ከመከበሩ አስቀድሞ በሽናሻ ብሔረሰቡ ባህል መሠረት የተጣሉ እንዲታረቁ እና ፍቅር እንዲያወርዱ ይደረጋል። በእዚህም በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የጋሪ ዎሮ በዓል የእርቅና የአንድነት በዓል በመባልም እንደሚታወቅ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ለማ ገለጻ፤ የሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ «ጋሪ ዎሮ» በዓል ሲከበር የተቸገሩ ሰዎችን ከመርዳት በተጨማሪ በዓሉን በአብሮነት ማሳለፍ የባህሉ እሴቶች ናቸው።
በበዓሉ የብሔረሰቡን ባህላዊ እሴቶች በመጠበቅና በማጎልበት ለትውልድ ማስተላለፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የብሔረሰቡ ምሁራን እና ተወላጆች ያካተተ የፓናል ውይይት እንደሚደረግም ታውቋል።
የጋሪ ዎሮ የዘመን መለወጫ በዓል በአሶሳ ከተማ ሲከበር ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ሲሆን የሽናሻ ብሔረሰብ አባላት በስፋት በሚገኙበት ገጠራማ አካባቢም ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም