በክልሉ ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል

• ከ36 ሺህ በላይ የሚሆኑት ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል

 አዲስ አበባ፡- በጋምቤላ ክልል ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ ከ36 ሺህ በላይ የሚሆኑት ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የጋምቤላ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር አገልግሎት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ሉል ጎኝ ባንጎት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ባጋጠመው ጎርፍ ዜጎች ተፈናቅለዋል ንብረት ወድሟል። በዚህም የጎርፍ መጥለቅለቅ ከደረሰባቸው ዘጠኝ ወረዳዎችና ጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ውስጥ 25 ሺህ 140 ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ 36 ሺህ 129 የሚሆኑት ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል፡፡

ተፈናቃዮቹ በትምህርት ቤቶችና በቤተ እምነት ስፍራዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ያነሱት ተወካይ ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመቅረፍ እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከልም ለተፈናቃዮቹ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አፋጣኝ ድጋፍ የሚደርስበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንደ አቶ ሉል ጎኝ ገለጻ፤ በጋምቤላ ክልል የጎርፍ አደጋ በክረምት ወቅት የሚፈጠር የተለመደ ክስተት ነው። በጋምቤላ ከተማ ስር በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ዜጎች ተፈናቅለው በተለያዩ ስፍራዎች የተጠለሉ ሲሆን ይህ መሆኑም በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ የሚያባብስ ክስተት ነው፡፡

የዜጎች መፈናቀል እና ጉዳት ላይ መውደቅ ዜጎች ሕይወታቸውን በአግባቡ እንዳይመሩ እንቅፋት በመሆን እንደ ምግብ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ያሉ ፍላጎቶችን በመጨመር ሰብአዊ ቀውስ ያስከትላል ብለዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ የዝናብ መጠን በመስተዋሉ እንደ ባሮ እና ጊሎ ያሉ ዋና ዋና ወንዞች ሞልተው በመፍሰሳቸው ምክንያት በአኙዋክ፣ ኑዌር ዞኖች እና በኢታንግ ልዩ ወረዳ የጎርፍ መጥለቅለቁ ሊያጋጥም ችሏል ነው ያሉት።

ጎርፉ በጤና ኬላ እና ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ሲሆን ለምሳሌ በኢታንግ ጤና ጣቢያ ላይ ጫና በማሳደሩ አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች እንደሆነ አቶ ሉል ጎኝ ጠቁመዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You