ትውልድን የተመረኮዘው የሀገር ግንባታ

ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ ሲሉ ይተርታሉ አበው። እንዲህ ያለው ቃል ለዚህ ጉዳይ ተገቢ አማርኛ ነው። ሀገርን ለመገንባት ትውልድን ማብቃት አቻ የሌለው ተግባር ነው። ትውልድን ብቁ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። አሁን ላይ ትናንት አብነት ይደረጋል። ዛሬንም እንደ መልካም ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል። ትውልድ እንደ ሻማ ነው። ከተንከባከቡት ቀልጦ ይበራል፤ ካልሆነ ጥቅም ሳይሰጥ ይቀልጣል። ትውልድን መገንባት ለእከሌ ተብሎ የተጣለ ግዴታ አይደለም። የሁሉም ኃላፊነት ነው።

ትውልድ ብቁ፣ ጠንካራ የሥነ ልቦና ውቅር ያለው መሆን አለበት። በሥነ-ምግባር ሊታነጽም ይገባዋል። ማኅበራዊ እሴቶችን ያዳበረ አርቆ አሳቢ ትውልድ ለማፍራት የቤት ሥራዎች አይታጡም። ግለሰቦች፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ቤተ-እምነቶች ኃላፊነት በመውሰድ ረገድ ግንባር ቀደም ናቸው።

ሀገራት መለያያ መንገድ አያጡም። ሀብት፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀት እንዲሁም ባህልና እሴት አንዱን ከሌላው ይለያሉ። እነዚሁ ሀገራት ልዩነቶችን ለማጥበብ ጎንበስ ቀና ሲሉ መመልከት የተለመደ ነገር ነው። ይህም መልካም ዕድሎችን ለመጠቀም ያስችላል። እዚህ ላይ የዳያስፖራው ያለው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጉዳዩን በሚመለከት ጠይቋል። መላሹ አቶ ደመቀ ነጋሳ ይባላሉ። በአውሮፓ ኔዘርላንድ ለብዙ ዓመት ኖረዋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው። ስለትውልድ ግንባታ የልባቸውን አውግተዋል። ኢትዮጵያውያኑ የውጭ ነዋሪዎች ትውልድን በመገንባት ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና አላቸው።

በሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ማምጣት ላይ ዳያስፖራው ስላለው አስተዋፅኦ በአቶ ደመቀ ተጠቅሷል። እውቀትን፣ ልምድን፣ ቴክኖሎጂን ለማሸጋገር ኢኮኖሚን ከመደገፍና የሀገሪቱን ዲፕሎማሲ ማሳደግ ላይም ሚናቸው ከቁጥር በላይ ነው ባይ ናቸው። ዳያስፖራው የሀገሪቱን ባህል፣ እሴት ለተቀረው የዓለም ክፍል ያስተዋውቃል። ይህን ለማድረግ ጠቃሚ የሆኑ አዲስ አሠራሮችን ወደ ሀገራቸው ማስተላለፍ ተገቢ ነው።

ሀገርን በዘላቂነት ለመገንባት ትውልድ ላይ መሥራት የማይዘነጋ ቀዳሚ ተግባር ነው። ዳያስፖራው በቴክኖሎጂ ሊያለማ ይገባዋል። በመሠረተ ልማት ላይም መሳተፍ አለበት። አቶ ደመቀ በኢንቨስትመንትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ቢሳተፉ መልካምነቱን ገልጸዋል። ለኢትዮጵያውያኑ ትውልድን መገንባት ጎን ለጎን ሌሎችም ሥራ አሏችሁ ብለዋል። ለልጆቻቸው ባህል፣ ታሪክ፣ እሴትና ቋንቋቸውን ማሳወቅ አለባቸው።

ብርሃኑ ገረመ (ዶ/ር) ቀጣይ አስተያየት ሰጪ ናቸው። አውሮፓ ነዋሪ ናቸው። የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ምን ይጠበቅብናል ለሚለው ምላሽ ሰጥተዋል። ትውልዱ ላይ ስለሚከወኑ ተግባራት አስፈላጊነት ገልጸዋል። የዳያስፖራው ተሳትፎ መጠነከር መቻል አለበት ብለዋል።

ዳያስፖራዎች በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሳታፊ ናቸው። የትምህርትና የምርምር ተቋማት ላይ ይገኛሉ። ይህም በትምህርት ላይ ሰፊ ተግባር ለማከናወን አቅም ይፈጥራል። በዚህ ብቻ መቆም አያስፈልግም። ቀጣይ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል። ያለውን ተሞክሮ ማካፈል ይገባል። ዴሞክራሲ ማጎልበት ሂደት ላይ ሚናው ጉልህ ነው። በቴክኖሎጂ ሽግግርና መልካም አስተዳደር ግንባታም ላይ ሥራው ቀላል አይባልም። በተለያዩ ዘርፎች ያለ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ይመክራሉ።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You