በዓላት ለአብሮነትና ለጠንካራ መስተጋብር

በኢትዮጵያ በርከት ያሉ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ይከበራሉ፡፡ ዘንድሮም በመስከረም ወር የመውሊድ፣ የደመራ፣ የመስቀል እና ኢሬቻ በዓላት በልዩ ድባብ ይከበራሉ፡፡ በተለይ በደቡብ የሀገራችን ክፍል የሚከበሩ የዘመን መለወጫዎች በጉጉት የሚጠበቁ በዓላት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ለበዓላት ከፍ ያለ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ የበዓላቱ ድምቀት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ወዳጅ፣ የዘመድ አዝማድና ጎረቤት አብሮ የሚከበርበት ነው፡፡ መጠያየቁና እንኳን አደረሳችሁ መባባሉ ታዲያ በአንድ ቤተ እምነት ስር ባሉ ብቻ ሳይሆን የተለያየ እምነት ተከታይ በሆኑ ሰዎች መካከል ጭምር የሚከናወን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዓላት በሕዝቦች መስተጋብር መጠናከር እና አብሮነት መጎልበት የማይተካ ሚና እንዳለው የሚያመላክት ነው ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡

ይህን ጠንካራ መስተጋብር እና አብሮነት እንዴት ለሀገር ሰላም መስፈንና አብሮነት መጠናከር እንጠቀመው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በበዓላት አከባበር ወቅት የሚስተዋሉ መልካም እሴቶች ኅብረተሰቡን ከማስተሳሰር አንጻር ያለው እንድምታ እንዴት ይገለጻል? በቀጣይነትስ በምን መልኩ እንጠቀምባቸው በሚለው ላይ የዘርፉን ምሁራን አነጋግሯል፡፡

የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የሃይማኖት፣ የባህልና የሌሎችም ጉዳዮች ብዝሃነት ያለባት ሀገር ናት፡፡ ይህን ብዝሃነት በትክክል ከተጠቀምንበት ለሀገራችን ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ እምቅ ሀብት ነው፡፡

ብዝሃነት ያለበት ሀገር ውስጥ ተቻችሎ፣ ተከባብሮ መኖርና ሁሉንም የራስ አድርጎ መውሰድ እንደሚጠይቅ የሚጠቅሱት ዶክተር ኃይለኢየሱስ፤ ማኅበረሰቡ ብዝሃነት ስጋት ሳይሆን ሀብት መሆኑን በመገንዘቡ ለዘመናት የሌሎችን በዓላት እንደ ራሱ ተቀብሎ በዓላትን በጋራ እያከበረ ዘልቋል፡፡ ይህም አንዱን ማኅበረሰብ ከሌላው ጋር ያለው ቁርኝት ጠንካራ እንዲሆን ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስብስብና መጠላለፍ የበዛበት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የገነባው መልካም እሴት ግን አብሮነታችን እንዳይበጠስና መስተጋብራችን እንዲጠናከር አድርጓል፡፡ ይህን ጠንካራ ትስስር በመፍጠር በኩል ደግሞ በዓላት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

በመሆኑም ይህ መልካም እሴት ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍና የሕዝቦች አንድነት እንዲጠናከር መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች በዋናነት ከፖለቲካው የሚመነጩ መሆናቸውን የሚጠቅሱት ዶክተር ኃይለኢየሱስ፤ ለማኅበረሰቡ የሚያስቡ መስለው በሕዝቦች መካከል መቃቃር የሚፈጥሩ አካላት በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ የኢትዮጵያውያን ዕጣፈንታ ተከባብሮና ተግባብቶ መኖር ስለሆነ ማኅበረሰቡ የሚከሰቱ ችግሮችን በዝምታ ከማየት ወጥቶ አብሮነቱ ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላትን መቃወም ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህሩ አቶ አንዷለም አሰፋ በበኩላቸው፤ በዓላት የመሰባሰብ፣ የአንድነትና የተጣሉ የሚታረቁበት ነው፡፡ ይህም በማኅበረሰቡ መካከል የመከባበር፣ የመተባበርና የመቻቻል እሴት እንዲጎለብት አድርጓል፡፡

በበዓላት ወቅት የሚስተዋሉ አብሮነትና የመተባበር መንፈስን የየዕለት ተግባራችን ማድረግ እንደሚገባ የሚጠቁሙት ምሁሩ፤ በየአካባቢው ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የተጣላን ለማስታረቅና ለመተባበር የሚውሉ መስተጋብሮችን እንደመነሻ በመውሰድ በሀገር ደረጃ መተግበር ይጠበቅብናል ይላሉ፡፡

በተለይ በፖለቲካው መድረክ ዋና ተዋናይ የሆኑ አካላት የማኅበረሰቡ መልካም እሴቶች የሆኑትን አብሮ የመኖር፣ መፈቃርና መቻቻልን በፖለቲካው ላይ ቢተገብሩት እንደ ሀገር ያጋጠሙንን ፈተናዎች መሻገር እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡

እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ በዓላትን በመሰባሰብ ማክበራችን በማኅበረሰቡ መካከል ጠንካራ መስተጋብርና ግንኙነት እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በበዓላት ወቅት ላለመለያየት ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ተነጋግሮ የመፍታትና የመታረቅ ትልቅ ልምድ አለ፡፡ በመሆኑም ከመገፋፋትና ከመነታረክ ወጥተን በሰላም እንድንኖር ፖለቲከኞች የማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች በፖለቲካው መድረክ መጠቀም ይኖርብናል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You