
አዲስ አበባ፡– በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ገቢ ያላቸውን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የቱሪዝም ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያ አቶ አሸናፊ ደስታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በመስከረም ወር በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የአደባባይ በዓላት ለቱሪዝም ገቢው ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በኢትዮጵያ የተለያየ ሃይማኖትና ባህል የሚንጸባርቅባቸው በርካታ የአደባባይ በዓላት እንደሚከበሩ አንስተው፤ በአደባባይ በዓላቱ የኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ባህልና ትውፊት በስፋት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎችን መሳብ ይቻላል ብለዋል።
በኮቪድ ወረርሽኝና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ወደኢትዮጵያ ይመጡ የነበሩ ቱሪስቶች ቁጥር ባለፉት ዓመታት የመቀነስ አዝማሚያ መታየቱን ጠቁመው፤ አሁን ላይ የሚከናወኑ የአደባባይ በዓላትን ይበልጥ በማስተዋወቅ ቱሪዝሙን ማነቃቃት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ አሸናፊ ገለጻ፣ በመስከረም ወር በኢትዮጵያ የሚከበሩትን የመስቀል ደመራ፣ ኢሬቻ፣ ያሆዴ፣ መሰላ፣ ማሽቃሮ፣ ጊፋታ ጋሪወሮ፣ ሄቦ፣ ዮ መስቀላ፣ ጋዜና ሌሎች የአደባባይ በዓላት ላይ በርካታ ቱሪስቶችን መሳብ ይቻላል።
የቱሪስቶችን ፍሰት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታን ማጎልበት የሚቻልበትን ዕድል ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል።
በዓላቱ ከቱሪዝም ዕድገት በተጨማሪ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጎልበት አንድነትን ለማጠናከር እንደሚረዱ ተናግረዋል።
የአደባባይ በዓላቱ በሚከበሩበት አካባቢዎች የበዓሉ ተሳታፊዎች የሚደምቁባቸውን አልባሳት፣ ጌጣጌጥ እና የአካባቢውን ባህላዊ ምግቦች አዘጋጅቶ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላትን ወቅቱን ጠብቆ ከማክበር ባለፈ በቅርስነት ለመጠበቅ፣ ለሌሎች ሀገራት ለማስተዋወቅና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
አቶ አሸናፊ እንዳመላከቱት፤ በአደባባይ በዓላት ላይ የሚታዩት ጭፈራዎችና ዘፈኖች ለኪነጥበብ ዘርፉ ዕድገትና ባህልን ለማስተዋወቅ ይረዳሉ።
ሌላኛው የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ቃለአብ በላቸው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአደባባይ በዓላት የማኅበረሰብ ባህላዊ መገለጫዎች ናቸው።
በዓላቱን የቱሪዝም ገቢ ምንጭነት በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ግንታችንን ማስፋት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያን የአደባባይ በዓላት በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ድረ-ገጾች በቀጥታ ማስተላለፍ የሚቻልበትን ዕድል በመፍጠር የተለያዩ ቱሪስቶችን መሳብ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
አደባባይ በዓላት ሲከበሩ የኢትዮጵያን ሃይማኖት፣ ባህልና ትውፊት በሚያሳይ መልኩ መሆን አለበት ያሉት አቶ ቃለአብ፤ አንዱ ብሔር የሌላውን ባህል፣ ዕምነት፣ አስተሳሰብና ማንነት በማክበር በጋራ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የአደባባይ በዓላት አከባበር ለመጎብኘት ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶችን በአግባቡ ተቀብሎ በማስተናገድ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ማድረግና የቱሪዝም የገቢውን ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም