ሞያን መሠረት ያደረገ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን የሚደግፍ አዋጅ ለማጽደቅ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– ሞያን መሠረት ያደረገ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን የሚደግፍ አዋጅ ለማጽደቅ እየተሠራ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዴስክ የሥልጠናና ስርጸት ባለሞያ አቶ እንደገና ፍቃዱ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሞያተኞች ባላቸው ሞያ መሠረት አገልግሎቱን መስጠት እንዲችሉ የሚደግፍ አዋጅ ለማጽደቅ እየተሠራ ነው፡፡

እንደ አቶ እንደገና ገለጻ፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በሀብትና በሰው ኃይል በማቀናጀት በፖሊሲ መምራት ያስፈልጋል፤ አገልግሎት ሰጪዎች ከሞያቸው ጋር በተጣጣመ መልኩ አገልግሎቱን አለመስጠት በውጤታማነቱ ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እንዳላቸው የጠቀሱት ባለሞያው፤ በኢትዮጵያም አሁን እየተከናወነ ካለው በተሻለ መልኩ ውጤታማ ማድረግ እንዲቻል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ ትኩረት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ ሞያን መሠረት ያደረገ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነው፡፡ በሞያቸው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት ለሚፈልጉ በጎ አድራጊዎች ድረ ገጽ በመጠቀም ያላቸውን ሞያና አድራሻ በድረ ገጹ ላይ እንዲሞሉ በማድረግ እንደሚሠራ አቶ እንደገና ገልጸው፤ ለዚህም የአዋጁ መጽደቅ እየተጠበቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለው የሕክምና ባለሞያ እጥረት ምክንያት በቀላል ሕክምና ሊድኑ የሚችሉ ዜጎች ሕይወታቸውን እያጡ በመሆኑ ይህንንም ለመቀነስ ሞያን መሠረት ያደረገ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

አገልግሎት ሰጪዎች በሞያቸው ዘርፍ በመሥራት ሞያቸውን የሚያዳብሩበትና ተቀባዩም ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን አሁን ካለበት የተሻለ ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በጎ ፍቃደኞች አገልግሎቱን በሚሰጡበት ወቅት አደጋ ቢያጋጥማቸው ሊደገፉ የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ እራሳቸውንና ማኅበረሰቡን እንዲጠቅሙ እያደረገ ሲሆን ይህም በወጣቱና በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ቅርበት ለመጨመር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ትልቅ ትኩረት በመስጠቱ ሁሉም ተቋማት እየተሳተፉበት እንደሚገኝ አንስተው፤ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለሦስት ሳምንታት በሁሉም አካባቢዎች ተካሂዶ የተለያየ ቋንቋና ባህል ባላቸው ወጣቶች መካከል ማኅበራዊ መስተጋብርን ማጠናከር መቻሉን አውስተዋል፡፡

አቶ እንደገና እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ከሰኔ 16/2015 ዓ.ም ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደቤተሰቦቻቸው የሚመጡ ወጣቶችን ማዕከል በማድረግ ወሰን ተሻጋሪና ለሦስት ወራት የሚቆይ የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመባል በሁለት ዓይነት መልኩ እየተከናወነ ሲሆን ይህም እስከ መስከረም 30/2016 ዓ.ም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በዚህም ከ20 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ 51 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማትረፍ እንደታቀደ አስታውሰው፤ እስካሁን ባለው አፈጻጸም አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ በመሆኑ በቀሩት ጊዜያት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የተሻለ አፈጻጸም እንደሚመዘገብ አቶ እንደገና ተናግረዋል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You