
አዲስ አበባ፡- በመቐለ ከተማ ያለውን የውሃ እጥረት ለመፍታት የረጅምና የአጭር ጊዜ መፍትሔዎች ተበጅተው እየተሠራ መሆኑን የመቐለ ከተማ የውሃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ገለፀ።
የመቐለ ከተማ የውሃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አሸናፊ ዘአብርሃ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በመቐለ ከተማ ለሚኖረው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ሰፊ የውሃ አቅርቦት ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ለከተማዋ ሕዝብ የውሃ ፍላጎት በቀን 120 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በመቅረብ ላይ ያለው 30 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ይሰጣሉ ተብለው የተያዙ ፕሮጀክቶች በሁለት የተከፈሉ መሆኑን አብራርተው፤ የረጅምና የአጭር ጊዜ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጠው እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአጭር ጊዜ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የተቀመጠው በጣም ለተቸገሩ ሰዎች በቦቴ ውሃ ማዳረስ መሆኑን ተናግረዋል። በመቐሌ አካባቢ የሚገኘው ‹‹የገረብ ሰገን›› ግድብ በሙሉ አቅም እንዲሠራ ከበጎ አድራጊዎች ጋር በመነጋገር የመለዋወጫ ዕቃ እንዲሟሉ በማድረግ በፍጥነት አገልግሎት ማስጀመርም ከተያዙ የአጭር ጊዜ የመፍትሔ ሥራዎች መካከል ሌላው ነው ብለዋል።
የውሃ ችግሩን ለማቃለል ትላልቅ ድርጅቶች የራሳቸው የውሃ ጉድጓድ እንዲያዘጋጁ እየተነጋገርን ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
ከፌዴራልና ከክልሎች ጋር በመግባባት ተጀምሮ የቆየው ‹‹የገረብ ግባ›› ፕሮጀክት ዳግም እንዲጀመርና ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁኔታዎች ማመቻቸት፤ እንዲሁም ለቀጣይ ከከተማዪቱ መስፋትና ዕድገት ጋር ተያይዞ የውሃ አቅርቦት ከተከዜ የሚገኝበት መንገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በዘላቂ እንዲፈታ ማድረግ ከተያዙ የረጅም ጊዜ መፍትሔዎች ውስጥ መሆናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል።
የውሃ እጥረት እንዲከሰት ምክንያቶች ከሆኑት መካከል በዋናነት የምርት ችግር እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር አሸናፊ፤ የመብራት መቆራረጥ ራሱን የቻለ ዘርፉ ላይ ችግር እየፈጠረ ያለ እንደሆነና የከተማው ውሃ የሚያመርቱ አነስተኛ የውሃ ጉድጓዶች በመበላሸታቸው፤ አስፈላጊ የመለዋወጫ ዕቃዎች ባለመገኘቱ፤ ቢገኝም ተቋሙ ለመግዛት አቅም በማጣቱ ነው ለተጨማሪ ችግሮች እየተዳረገ መሆኑን አመላክተዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ተከስቶ የነበረው ጦርነትም ትላልቅ የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎችና ተመሳሳይ ዕቃዎች እንዲበላሹ ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል።
ኃላፊው፤ ችግሩ በጣም ሰፊ ስለሆነ በዋናነት ማኅበረሰቡ የውሃ አገልግሎት የሚሰጡ ዕቃዎች እንደ ራሱ በመመልከት እንዲንከባከባቸው መክረዋል። የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት አሁንም በተመሳሳይ እገዛቸው ያስፈልገናል ብለዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም