
አዲስ አበባ፡- በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ የማዕድን ወጪ ንግድ 20 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን የአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡ በዘርፉ ለ45 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
በአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከማዕድን የወጪ ንግድ 20 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡
የተቀመጠውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የታቀደው፤ በዋናነት ከሁለት ማዕድናት ገቢ እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፤ የመጀመሪያው በወርቅ ምርት ሲሆን፤ በጎንደርና በተለያዩ አካባቢዎች የወርቅ ክምችት መኖሩ በጥናት በመረጋገጡ በቀጣይ ባለሀብቶችን ለማሰማራት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ሌላኛው ሰፊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያስገኝ የሚጠበቀው የማዕድን ምርት ኦፓል ነው ያሉት አቶ ታምራት፤ ማዕድኑ በስፋት በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከማዕድን ወጪ ንግድ በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ መታቀዱን አቶ ታምራት አመላክተዋል።
በ2015 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ የማዕድን ገቢ 75 ሚሊዮን ብር መገኘቱን ያነሱት ምክትል ኃላፊው፤ በ2016 በጀት ዓመት ገቢውን ወደ 100 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ መታቀዱን አስታውቀዋል።
አቶ ታምራት እንደገለጹት፤ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት በክልሉ የሚገኙ ማዕድናት ያሉበትን ቦታ፣ የክምችት መጠናቸውንና ዓይነታቸውን የመለየት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል።
ከጥናትና የቦታ መረጣ ሥራዎች በተጓዳኝነት የማዕድን ክምችታቸው በተረጋገጡ ቦታዎች ላይ ባለሀብቶች ገብተው እንዲሠሩ ጥረት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በሚከናወኑ የማዕድን ልማትና ንግድ ሥራዎች ለ45 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙን አመላክተዋል፡፡
በተለይ ወጣቶች በማዕድን ቁፋሮና እሴትን ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ሰፊ ዕድል እንዳለ አቶ ታምራት ጠቁመዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራው ባለፈ ሕጋዊ ነጋዴዎችና የማዕድን አውጪዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመከላከል የተቋቋመውን ግብረኃይል ድጋሚ በማዋቀር ሥልጠናና አስፈላጊውን ግንዛቤ
የማስጨበጥ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
ከቁጥጥር ሥራው ባለፈ ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርና ንግድን ለመከላከል የወጣው መመሪያ 10 ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑም ተሻሽሎ ሥራ ላይ እንዲውል የሚረዳ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመቆጣጠር የሚረዳ የሕግ ማዕቀፍ ለክልል ምክር ቤቱ ቀርቧል ያሉት አቶ ታምራት፤ ከፍትህ ቢሮ አስተያየት እንደተሰጠበት አመላክተዋል።
በቀጣይም ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍና ቁጥጥርን ተግባራዊ በማድረግ የማዕድን ዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም