ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማስመዝገብ እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት በአገልግሎት እና በማምረቻ ዘርፍ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማስመዝገብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ዕቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ እናትነሽ ታመነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ በዋናነት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በመጀመሪያ ደረጃ የአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በዚህም በ2016 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ ከአገልግሎትና ከማምረቻ ዘርፍ ሰባት ቢሊዮን ብር ለማስመዝገብ ያቀደ ሲሆን ከኢንቨስትመንት ፍቃድ እና ከተለያዩ የድጋፍ አገልግሎቶች 26 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡

እንደ ወይዘሮ እናትነሽ ገለጻ፤ በዚህ ዓመት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ለ700 ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል፡፡ ተቋሙ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች አብዛኛው በቴክኖሎጂ በመደገፍ የሚሰጡ በመሆኑ በተያዘው በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ፈቃድና ፈቃድ ነክ አገልግሎቶችን ኦንላይን ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል፡፡ የኮሚሽኑን የመረጃ አያያዝ ሥርዓትም ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ በዚሁ በጀት ዓመት ለመሥራት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ባለሀብቶች የሚጠይቁትን የድጋፍ አገልግሎቶች ፈጣን እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ እና በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የመሬት እና የብድር ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሁም ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ አመራሩ በትክክል መሥሪያ ቦታው ላይ በመሄድ ችግሩን የማጣራት ሥራ እየሠራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ እናትነሽ፤ ተቋሙ እነዚህን የባለሀብቶች ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት እንዲያመች ከተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ሰነዶች አዘጋጅቶ በመፈራረም ላይ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽኑ የገቢም ሆነ የአገልግሎት ዕቅዱን ለማሳካት በዋናነት ለባለሀብቱ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፤ ባለሀብቱ ባለበት ሆኖ ስለ ኢንቨስትመንት መረጃ እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ የኦንላይን አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ እንዲሁም ለአገልግሎት ክፍያዎችን በካሽ እና ከፖስ ማሽን በተጨማሪ በቴሌብር እና በሲቢኢ ብር እንዲጠቀሙ ማድረግ የዚህ ዓመት ሁነኛ ሥራዎች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል ዳይሬክተሯ፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You