
– 202 ሺህ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል
አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር በተከሰተው ድርቅ 452 ሺህ ዜጎች መጎዳታቸውንና 202 ሺህ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ በተከሰተው ድርቅ 452 ሺህ ዜጎች ተጎድተዋል፡፡ በተለይ 202 ሺህ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
እንደ አቶ ሰላምይሁን ገለጻ፤ በዞኑ በሚገኙ ጃናሞራ፣ ጠለምት፣ የበየዳ ወረዳዎችን ጨምሮ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጠለምትና የተወሰኑ የደባርቅ አካባቢዎች በድርቅ ተጎድተዋል፡፡
ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ሳቢያ በዞኑ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ለድርቅ ተጋልጠዋል ያሉት አቶ ሰላምይሁን፤ በድርቁ ሳቢያ 19 ሺህ አምስት መቶ ሄክታር ሰብል ጉዳት እንደደረሰበት አመላክተዋል፡፡ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች በተከሰተው የዝናብ እጥረት 103 ሺህ እንስሳት ለድርቅ አደጋ መጋለጣቸውን ጠቁመው፤ 53 ሺህ የሚደርሱ እንስሳት በድርቁ ሳቢያ መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጠለምትና ጃናሞራ ወረዳዎች በድርቁ ምክንያት ከአራት ሺህ በላይ ዜጎች ከአካባቢያቸው ለቀው ወደ ወረዳ ማዕከላት መምጣታቸውን በመግለጽ፤ ዞኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ድጋፍ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡
የድርቅ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ክልሉ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ኩንታል በላይ የምግብ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት አቶ ሰላምይሁን፤ ድጋፉን የችግሩ ተጋላጭ ለሆኑ 14 ሺህ ዜጎች ማድረስ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በድርቁ አካባቢዎች ላይ ተላላፊ በሽታዎች በተለይም የኮሌራ በሽታ መከሰታቸውን አስታውቀው፤ የዞንና የክልሉ ጤና ቢሮዎች ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ ለሚገኙ ዜጎች አስቸኳይ የዕለት ምግብ፣ መድኃኒቶች፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ውሃና የእንስሳት መኖ ድጋፍ አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዞኑ የተለያዩ ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሀብት የማፈላለግ ሥራ ጀምሯል ያሉት ኃላፊው፤ የችግሩ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየከፋ በመሄዱ የሚመለከታቸው አካላት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በድርቁ ሳቢያ ዜጎች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ በመሆኑ ሁሉም አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ በመግለጽ መንግሥት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ አጋር አካላት የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያቀርቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም