በአዲስ አበባ 20ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

– በምርቃቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ማዕድ አጋርተዋል

አዲስ አበባ፦ በአዲስ አበባ 20ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን በማዕከሉ ለአረጋውያን ማዕድ አጋርተዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትናንት በተከናወነው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ለከተማችን ነዋሪዎች ተጨማሪ የአዲስ ዓመት ስጦታ ይሆን ዘንድ 20ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት አገልግሎት አስጀምረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም በተጠቃሚዎቹ ስም ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል።

የምገባ ማዕከሉ ከ500 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው አቅመ ደካማ ነዋሪዎች በቀን አንድ ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ የሚያቀርብ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በአጠቃላይ በከተማችን ባሉ 20 የምገባ ማዕከላት ከ35 ሺህ በላይ ወገኖቻችን አገልግሎት እያገኙ ነው ብለዋል።

«በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አስመርቀን ሥራ አስጀምረናል። ነገር ግን የፕሮጀክቶቻችን ሁሉ ሜጋ ፕሮጀክት የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ናቸው» ሲሉም ተናግረዋል።

በ2013 ዓመተ ምህረት የመጀመሪያውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ሥራ ማስጀመራቸውን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፤ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ኢትዮ ሴራሚክ ፊት ለፊት የተገነባው 20ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል መርቀን ከፍተናል ብለዋል።

የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከልን ወደ ሥራ ለማስገባት ስናቅድ ከሆቴሎች ምግብ እንዲመጣ ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያውያን ተባባሪነት በምገባ ማዕከሉ ምግብ ማዘጋጀት እንደተቻለ ገልፀው፤ ምድራችን እንዲባረክ አረጋውያንን እና የተቸገሩትን መርዳት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በማዕከሉ ምርቃት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአካባቢው አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርተዋል፡፡

20ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል የተገነባው በቶኩማ ቢዝነስ ግሩፕ ሲሆን በቋሚነት ምገባ የሚያከናውነው ደግሞ ብዟየሁ ፋውንዴሽን ነው። ማዕከሉ አምሥት መቶ አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን በቀን አንድ ጊዜ የሚመግብ ሲሆን ለአሥራ ስድስት እናቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You