‹‹የቱሪዝም ሥራ በመልካም ሥም ላይ የተመሠረተ ነው››አቶ ስለሺ ግርማ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ

አዲስ ዓመት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም የሚነቃቃበት ጊዜ ነው። የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ደግሞ መዳረሻዎች ናቸው። የአደባባይ በዓል በመሆናቸው በእነዚህ በዓላት ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን የሚመጡበት ወቅት ነው። በሀገር ደረጃም ማህበረሰቡ በየአካባቢው በተለያየ ዝግጅት የሚያከብራቸው በመሆኑ የተለየ ድባብ አለው።

በበዓሉን ለመታደም ከሚመጣው ቱሪስትም የሚገኘው ገቢ በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ አስተዋጽኦ በማበርከት ዘርፉ ከፍ ያለ ሚና አለው። በየአመቱ በተለያየ መሪ ሃሳብና ዝግጅት በሚከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን ደግሞ ዘርፉን የማነቃቃት ሥራ ይሠራል። የማነቃቃቱ ሥራ የበለጠ ቱሪስቶችን ለመሳብ ያለው ፋይዳም ከፍ ያለ እንደሆነ የባለፉት እንቅስቃሴዎችና ተሞክሮዎች ያሳያሉ።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሰላምና መረጋጋት የሚፈልግ እንደሆነ ይታወቃል። ያለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም። የዓለም ሥጋት ሆኖ ያለፈው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ ሀገር ውስጥ ያጋጠመው ሰላምን የሚያደፈርሱ ክስተቶች ኢንዱስትሪውን ረብሾታል። በዚህ ውስጥም ሆኖ ግን የቱሪዝም ኢንዱስትሪው አልተስጓጎለም። ጫናዎችን ተቋቁሞ ዘርፉ ተልእኮውን እንዲወጣ የማድረጉ ሥራ እንዴት እንደቀጠለና ከዚሁ ጎን ለጎን የዓለም ቱሪዝም ቀንን አስመልክተን ከቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ መደፍረስ ችግር ጫና ተቋቁሞ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ ስለሺ፡- በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ጫና መፈጠር የጀመረው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ነው። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተካሂዶ የነበረው ጦርነት ደግሞ ችግሩን የከፋ አድርጎታል። እነዚህ ለተከታታይ ዓመታት የነበሩት ችግሮች ዘርፉ ላይ ጉዳት አስከትለዋል።

በተለይ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽ ወቅት የዓለም አቀፍ በረራዎች ባለመኖራቸው እንቅስቃሴዎች ተገትተው ነበር። ወረርሽኙ ንኪኪንም የሚከለክል ስለነበር ሰዎች ለመሰባሰብ ስጋት ውስጥ ነበሩ። በዚህ የተነሳ ሆቴል ቤቶችን ጨምሮ ለቱሪስቱ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሥራው የተስተጓጎበት ጊዜ ነበር።የጉብኝት ሥፍራዎችም ያለፉት በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ነው።

የቱሪስት ቁጥር በመቀነሱ በዘርፉ ተፈጥሮ የነበረ የሥራ ዕድል ላይ መቀነስና መቀዛቀዝ አስከትሏል።ገቢ በማስገኘትም እንዲሁ በተመሳሳይ ተጽእኖ ፈጥሯል። በተለይ ከሥራ ዕድል ጋር በተያያዘ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞችን ለመቀነስ በመገደዳቸው በርካቶች ከሥራ ውጭ ሆነዋል።

በጦርነቱ ወቅት ደግሞ አባዛኛዎቹ ኤምባሲዎች የጉዞ ክልከላዎች እንዲደረግና ሰዎችም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ በየድረ-ገጾቻቸው መልእክት በማስተላለፍ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ስለነበር የዘርፉ እንቅስቃሴ እንዲቀዛቀዝ አሉታዊ ጎን ነበረው።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ገቢ ጎብኚዎችን በመሳብ ብቻ ሳይሆን ለተለያየ ስብሰባ፣ ለኤግዚቢሽን ተሳትፎ፣ ዘመድ ጥየቃ፣ ለመዝናናትና ለጉብኝት፣ ወደ ሌላ ሀገር ለመሸጋገር ለተወሰነ ሰአት ወይም ጊዜ ቆይታ (ትራንዚት) ከሚያደርጉ ጭምር የሚገኝ ገቢ እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። ከዚህ አንጻር በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝና በፀጥታ ችግር ምክንያት ብቻ በትንሹ ከአንድ ቢሊን ዶላር ያላነሰ ገቢ አጥተናል።

በሥራ ዕድል በኩል ደግሞ በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ በዘርፉ 30 ከመቶ በላይ የሚሆን የሥራ እድል ተፈጥሮለት የነበረ ዜጋ ከሥራ ውጭ ሆኗል። ጦርነቱ አይሎ በነበረበት ወቅት ደግሞ ክፍተቱ የነበረው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ነው። በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያትም በረራዎች ባለመኖራቸው ትግራይ ክልል አክሱም፣ አማራ ክልል ላልይበላ፣ አፋር ዳሎል ኤርታሌ የቱሪስት መዳረሻዎች ሥራ አቁመው ነበር።

በወቅቱ ሙሉ ለሙሉ ዝግ የነበሩና በከፊልም የሚሰሩ ነበሩ። ምክንያቱም ክልከላውን አልፈው የሚመጡ ቱሪስቶች ነበሩ። ምንም አይነት ችግር ቢኖር ተቋቁመው መጥተው የሚያዩ ነበሩ። የማይሰረዝ ጉዞ ወይም ፕሮግራም ያላቸውም ነበሩ። ትውለደ ኢትዮጵያውያንም ዘመድ ለመጠየቅ እንዲሁም እንደሀገር ለዲያስፖራ የተደረገውን ጥሪ ተቀብለው የመጡ ነበሩ። ለመዝናናትም ቢሆን የመጡ ነበሩ።

ለመዝናናት ምቹ የሆኑ ወደ አምስት የቱሪዝም ቀጣናዎች አሉ። የታሪካዊ የመሥመር ጉዞ የምንለው አንዱ ሲሆን፣ ከአክሱም ላልይበላ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ሸዋ አልፎ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ መስመር ነው። ሁለተኛው መስመር ነው። በጅማ፣ ቦንጋ፣ አጋሮ አድርጎ ነቀምት፣ጋምቤላ ድረስ የሚሄድ ነው። ሶስተኛው የምሥራቅ ኢትዮጵያ የጉዞ መሥመር ሲሆን፣ ይህም ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ጅግጅጋ ድረስ የሚሄድ ነው። አራተኛው አዲስ አበባ ከተማና በዙሪያው ያለው ነው። አምስተኛው ደቡብ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ በአብጃታ ሻላ፣ በሐዋሳ፣ አርባምንጭ፣ ዶርዜን ይዞ የደቡብ አካባቢዎችን የሚነካካ የጉዞ መስመር ነው።

ከነዚህ የጉዞ መሥመሮች ውስጥ ሰላማዊ የጉዞ ቀጣናዎች ነበሩ። ለምሳሌ የምሥራቅ የጉዞ መሥመር በአውሮፕላንም በመጠቀም ወደ ስፍራው የሚሄዱበት እድል ነበር። በደቡብና በአዲስ አበባ ከተማም የነበረው በተመሳሳይ ምቹና ጥሩ እንቅስቃሴ ነው። የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች በተወሰነ የጉዞ መሥመር ላይ ተንቀሳቅሰዋል። ይህ እንዲሆንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን አምባሳደሮችን እነዚህ ቦታዎች ድረስ በመውሰድ ካዩ በኋላ የጉዞ ክልከላዎችን እንዲያነሱ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። በጥንቃቄ ቱሪስቶ እንዲጎበኙ ጥረት ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም ወይም እንዲነቃቃ የተሠሩት ሥራዎችን ለአብነት ቢጠቀሱ።

አቶ ስለሺ፡- ዘርፉን ለማነቃቃት ከተሠሩት ሰፊ ሥራዎች አንዱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ቶሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ነው። ለአብነትም ኮቪድ ተከስቶ በነበረ ጊዜ በዘርፉ ውስጥ ላሉ የንግድ ተቋማት በገንዘብ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በተመቻቸ በጀት ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ በአነስተኛ ብድር በመያዣ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል። ተቋማቱ ሠራተኞቻቸውን ከሥራ እንዳያስወጡ፣ የሚሰጡት አገልግሎትም እንዳይቋረጥና የቱሪዝም ንግድ እንቅስቃሴውም እንዲኖር ታስቦ የተደረገ ድጋፍ ነው።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበርም፤ አገልግሎት ወደ ማቋረጥ ደረጃ ደርሰው ለነበሩ ተከታታይ ዘርፉን ሊያነቃቃና ወደ ሥራቸው ለመመለስ የሚያስችላቸው የተግባቦትና የሙያ ክህሎት የሚያስጨብጥ ሥልጠና በጎንደርና ላልይበላ፣ በቅርቡ ደግሞ በትግራይ ክልል ሰጥቷል።

ሶስተኛ በሚኒስቴሩ የተደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ኤምባሲ አምባሳደሮች፣ በተለይም ለሀገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያላቸው ላይ ትኩረት በማድረግ የጉብኝት መርሃግብር በማዘጋጀት ወደ ተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች በመውሰድ፣ በክብረበዓላት ጊዜም እንዲታደሙ በማድረግ በቱሪስት መዳረሻዎች ያለውን የፀጥታ ሁኔታ፣ ዘርፉም የሚገኝበትን ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለዚህም የጉዞ ክልከላ እንዲያነሱና በነርሱ በኩል ሊደረግ የሚችለውን ትብብር እንዲያደርጉ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል።

ከመረጃ ጋር በተያያዘም በተለያዩ አካባቢዎች የቱሪስት መረጃ እንዲኖር የግንባታ ሥራዎችም ተከናውነዋል። ግንባታው የተከናወነው አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በአየር መንገድና በሌሎችም ነው።በተጓዳኝም መረጃ ለማግኘት የሚያስችሉ የጥሪ ማዕከላት ተቋቁመዋል። በኮቪድ ጊዜ የነበሩ የንክኪና አስፈላጊ የጥንቃቄ ተግባራት እንዲከበሩ የማድረግ ሥራም ተሰርቷል።

ጦርነቱ በቅርሶችና በተለያዩ የዘርፉ እንቅስቃሴዎች ላይ የደረሰውን ጉዳትም በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልች በጥናት ለመለየት ጥረት ተደርጓል። ጥናቱ በመሠረተ ልማት፣ በቅርሶች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ የደረሰውን ጉዳት በቁጥር ይህን ያህል ነው ብሎ ማስቀመጥ ባይቻልም ከፍተኛ እንደሆነ ግን መለየት ተችሏል። በተለይ ግን በትግራይ ክልል የደረሰው ጉዳት 70 በመቶ በሚባል ደረጃ ነው። ጥናቱን መሠረት በማድረግም ከክልሎቹ ጋር ውይይት አድርገናል። በቅርቡ የመጨረሻውን ውይይት ያደርግነው ከትግራይ ክልል ጋር ነው። በውይይቱ የዘርፉ ሥራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። በእኔ እምነት መንግሥት በሚችለው ሁሉ ጥረት አድርጓል። መሠረታዊ የሆኑ ሥራዎችም ተሠርተዋል።

በዘርፉ ላይ የሚገኙትም ተስፋ ሳይቆርጡ ተንቀሳቅሰዋል። በአሁኑ ጊዜም ትግራይ ክልል በአክሱምና ሽሬ ለማስጎብኘት እንግዶች መቀበል ተጀምሯል። በመቀሌ በኩል አፋርንም መጎብኘት ተጀምሯል።ይሄ ትልቅ መነቃቃት ነው። በአማራ ክልልም በተመሳሳይ በኮቪድና በጦርነቱ ሙሉ ለሙ በሚባል ደረጃ የዘርፉ እንቅስቃሴ ቆሞ ነበር።

በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ኮንሶና ሐረር አካባቢዎች እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። በቱሪዝም ዘርፉ ከኮንፈረንስ ጋር የተያያዘው MICE Tourism (Meeting incentives conference and exhibition) የሚባለው ኮቪድና ጦርነት ስጋቶች ባልነበሩበት ወቅት ከነበረው በላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል።

በውስን የስብሰባ ማዕከላት ውስጥ ተገድቦ የነበረው ዓለምአቀፍ ኮንፈረንሶች በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሆቴሎች ውስጥም እየተስተናገደ ይገኛል። በአንድ ሆቴል ውስጥ እስከ ሁለት ኮንፈረንሶች የሚካሄዱበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። የማይስ ቱሪዝም ተአምራዊ እድገት እያመጣ ነው ብዬ አምናለሁ።

ትልቁ ስጋት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ባለው ምቹ ሁኔታ እንዳይገደብ ነው። ለማይንስ ቱሪዝም ባህርዳር፣ሐዋሳ፣ አዳማ፣ ወደፊት ደግሞ መቀሌ በሁለተኛ አማራጭ ተይዘዋል። ትልልቅ የስብሰባ ማዕከሎች እንዲሠሩ በማድረግ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭም ማይንስ ቱሪዝም እንዲካሄድ መሥራት ይኖርብናል።

ሌላው ትኩረት ሰጥተን የሠራነው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ ነው። ባለፉት ጊዜያት ዓለማዊም መንፈሳዊም ይዘቶች ያሏቸው በርካታ ኩነቶች ነበሩ። ብዛት ያለው የሀገር ውስጥ ነዋሪ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሷል። ተማሪዎች ጉብኝት የማድረክ ተሞክሮ የዳበረበት፣ ሀገርህን እወቅ ክበባትን በማቋቋም ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ጥረት ተደርጓል።

በሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የአልባሳትና የጌጣጌጥ ግዥዎች በማካሄድ በግብይት ውስጥ የነበረውም ጥሩ የሚባል ነበር። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴው ከሌላው ዓለም ቱሪስት ለመሳብ ትልቅ ኃይል ሆኖ አገልግሎናል። በዚህ ረገድም መገናኛ ብዙሃን ዘርፉን በማነቃቃት ሚና ተጫውተዋል።በአጠቃላይ በዘርፉ ባለፈው ዓመት ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረው ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የመልሶ ማልማት ሥራ የሚፈልግ አለ? ካለ የሚሠራውንም ሥራ አብረው ይግለጹልን።

አቶ ስለሺ፡- መልሶ ማልማት በመንግሥትም በእቅድ ተይዟል። ቀደም ሲል የነበረን ሃሳብ የነበረንን አገልግሎት ማሳደግ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በጦርነቱ በቅርሶች፣አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ፣ የአየር ማረፊያዎችን ጨምሮ ጉዳት ደርሷል። ጉዳቱ በጥናት ተለይቶ ለመንግሥት ቀርቧል። መልሶ ማልማት ወይንም ማቋቋም ሥራ እንደሚያስፈልጋቸው ለውሳኔ ለመንግሥት የቀረበው ነው። የአየር ማረፊያዎችን መልሶ ማልማት የማይቀር ጉዳይ ነው።

የተጎዱ ቅርሶችን መጠገን ላይ በተመሳሳይ ሥራዎች ያስፈልጋሉ። የደሴ ሙዚየምን ከቅርስ ባላደራ ማህበር ጋር በመሆን ሙዚየሙን ወደነበረበት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው። በትግራይም በተመሳሳይ ጥገናዎች እንዲደረጉ እየተሠራ ነው። በአጠቃላይ ልማት የሚፈልጉት ላይ በአስቸኳይ እንቅስቃሴ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው።

የግሉ ዘርፍም በአቅሙ ሊሠራ የሚችለውን እንዲሠራ፣ ከቀረጥ ነጻ እድል ተሰጥቷቸው እቃዎችን ከውጭ እንዲያስመጡ፣ ከባንክ አዲስ ብድር እንዲያገኙና ቀደም ሲል የነበረባቸው ብድር እንዲራዘምላቸው በማመቻቸት በርብርብ ተሠርቷል። በዚህ ረገድም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከባንክና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል። ሙሉ ለሙሉ ውድመት ለደረሰበት መፍትሄ ላይኖረን ይችል ይሆናል እንጂ ለአብዛኞቹ በተቻለ መጠን ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን።

ቱሪስቶች በምንፈልገው ቁጥር ልክ መጥተው አገልግሎት ሰጪዎች ተከታታይ ገቢ እስካላገኙ ድረስ ከዘርፉ ይገኝ የነበረው ገቢ የሚጠበቀውን ያህል ላይሆን

 ይችላል። ይህን ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች ላይ እንደ ሀገር እየተሳተፍን ነው።

ጀርመን፣ ስፔንና በተለያዩ ላቲን አሜሪካን እንዲሁም በአፍሪካ በሚካሄዱ ትላልቅ መድረኮች ላይ መንግሥትም የግሉ ዘርፍም በጋራ በመሳተፍ ላይ እንገኛለን። ይሄ ትኩረትና እንቅስቃሴ የሀገር ገጽታንም ይገነባል። ቱሪስቶችንም ለመሳብ ያግዛል። በዚህ መልኩ ውጤት ማግኘት ከተቻለ በዘርፉ ላይ የሚገኘውን ገቢ ለማግኘትና ሠራተኞቹንም ለማስተዳደር ያስችለዋል። ተጨማሪ የማስፋፋትና በዘርፉ ኢንቨስትመንት የመሳብ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ።

የመጨረሻውና ዋናው መፍትሄ የሚሆነው ዘርፉ አሁንም ማመንጨት የሚችለውን ኢኮኖሚና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ማስጠበቅ ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ በመንግሥት ድጎማና ድጋፍ ብቻ የቱሪዝም ዘርፍ ሊነቃቃ አይችልም። የቱሪዝም ዘርፍ መንግሥት የሚመራው ግን የግሉ ዘርፍ የሚያሽከረክረው ነው። በዋናነት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ሞተር ሆኖ የሚያገለግለው የግሉ ዘርፍ ነው። ከመንግሥት የሚያስፈልጉ የተለያዩ ድጋፎች ግን እንደተጠበቀ ነው። አዳዲስ የሕግና መመሪያ ማሻሻያዎች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ሆኖ ይሠራል።

በዘርፉ ላይ ክልሎችም ኃላፊነት ወስደው መሥራት ይኖርባቸዋል። ሁሉ ነገር ፌዴራል ላይ ብቻ የሚመጣ ከሆነ በዘርፉ ላይ የሚፈለገው ለውጥ ላይመጣ ይችላል። ዋና ዋና የሚባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች በክልሎችና በከተማ አስተዳደር እጅ ናቸው። ለምሳሌ ከቅርስና ከብሄራዊ ፓርኮች ጥበቃ ጋር ተያይዘው ያሉ ሥራዎች ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት እድል አለ። ብዙ የገንዘብ ወጪ ሳያስፈልግ የሰው ሀብትን በማስተባበር ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በአካባቢው የሚገኙትን ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም ለሥልጠና፣ ለጥናትና ምርምር በመጠቀም ዘርፉን ማሳደግ ስለሚቻል መረባረቡ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ ወቅት በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደስጋትና መልካም ጎን የሚጠቀሱ ምንድን ናቸው?

አቶ ስለሺ፡- በዘርፉ እንደመልካም የምወስዳቸው መንግሥት ቱሪዝም እንዲያድግ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑ በመልካም ይወሰዳል። በተለይ ከመዳረሻ ልማት አንጻር በተለያዩ የመዳረሻ ቦታዎች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሀብት በማሰባሰብ ረገድ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታችና የሚመሰገን ነው።

ከዚህ ቀደም ቱሪዝም ላይ የአደረጃጀት ክፍተቶች ይስተዋሉ ነበር። አሁን ላይ አንድ ጠንካራ የሆነ የቱሪዝም ሚኒስቴር አለ። ስለዚህ በዚህ ጠንካራ ሚኒስቴር መሪነት ጠንካራ የሆነ አንድ ወጥ ሀገራዊ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ። ሌላው የፖሊሲ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ለምሳሌ የአዋጅ ማሻሻያ ተደርጓል። በዚህ አዋጅም የቱሪዝም ፈንድ እንድናቋቁም ተፈቅዷል። ይህ የቱሪዝም ፈንድ ከቱሪዝም አንጻር፤ በተለያዩ የዓለም ገበያዎች በመሄድ ቱሪዝሙን እንዳናስተዋውቅ ወደ ኋላ ያስቀረን የነበረው የሀብት ማነስ ነው።

አሁን ይህን ሀብት ከቱሪስት ታክስ በመሰብሰብ፣ በኢንዱስትሪው ላይ ካሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሚያገኙት ገቢ የተወሰነ አበርክቶ እንዲያደርጉ ማድረግ ስጦታዎችን መቀበል፣ በዘርፉ የሚመጡ እድሎችን ተወዳድሮ የማሸነፍ አቅም መፍጠር፣ እነዚህን ሰብስቦ ቱሪዝም ፈንድ አቋቁሞ ለምንፈልገው ቱሪዝም መዳረሻ ልማት፣ ዘርፉን ለማስተዋወቅና ለአቅም ግንባታ መጠቀም የምንችልበት ዕድል አለ።የአዋጅ ማሻሻያው፣ የተቋሙ ምሥረታ፣ና የመንግሥት ቁርጠኝነት ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ናቸው።

ሌላው የግሉ ዘርፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ከችግር ፈጥኖ መውጣት (Resilient) የተረዳ ነው። ይህ ማለት በኮቪድም ሆነ በጦርነት በማንኛውም ፈተና አልፎ የቱሪዝም ዘርፉ መኖር እንደሚችል፣ ቱሪስቶችም መምጣት እንደሚችሉ ትምህርት የወሰድንበት ነው። የዘርፉ ከችግር መውጣት ባህሪ ከምንም በላይ በሆነ ነገር ጠፍቶ የሚቀር እንዳልሆነ ነው።

እንደ ቻይና እና አፍሪካ ያሉ አዳዲስ ገበያዎች ትኩረት ያደርግንባቸው መዳረሻዎች አሉ። እነዚህ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል። የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ ማይስ ቱሪዝም፣ እነዚህ አዳዲስ ትኩረት ያደረግንባቸው፣ የአፍሪካና የኤሺያ ገበያ፣ የሀገር ውስጥ ገበያ፣ ከምርት አንጻር ደግሞ እንደ ማይስ ቱሪዝም ትልቅ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ተስፋ ሰጪ እድል መኖሩን ያሳያል።

ከስጋት አንፃር ለተነሳው፤ ትልቅ ችግር ይሆናል ብዬ የማምነው ዓለምአቀፍ ሁኔታው በምንፈለገው ልክ እንዳንቀሳቀስ ሊያደርገን ይችላል። የኢኮኖሚ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አለ። ዓለምአቀፍ ገበያው በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ሰዎች ከቦታ ቦታ ላይንቀሳቀሱ ይችላሉ።ወይም ደግሞ የሚኖራቸው የጊዜ ቆይታ ሊቀንስ ይችላል። በዚህ ምክንያት የምንፈልገውን ያህል ተጠቃሚነት ላይኖር ይችላል።

ሌላው ሰላምና ፀጥታ ከሌለ የቱሪዝም ጉዳይ አይታሰብም። ቱሪስቶች ጊዜ ገድበው አይመጡም። የቱሪዝም ባህሉ ተቀይሯል። አንድ ቱሪስት ወደ አንድ አካባቢ ከሄደ መመለስ የሚፈልገው በአጭር ጊዜ ሁለትና ሶስት ሀገሮችን ጎብኝቶ ነው። የሚጎበኘው ቀጣናውን ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ ቀጣናው ሰላም መሆን ይኖርበታል። ሱዳን ላይ ያለው ችግር በኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንደማያመጣ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል።

ነገር ግን ከውስጣዊ ችግር ባላነሰ በዙሪያው ወይም በቀጣናው ባለው ችግር የተነሳ ቱሪስቶች ሰላማዊ በረራ አይኖርምና በሰላምም ጎብኝተን አንመጣም የሚል ስጋት ያድርባቸዋል። ለሰላም ቅድሚያ ስለሚሰጡ አማራጮችን ይፈልጋሉ።

አዲስ ዘመን፡- የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ተፈጥሮአዊ የሆኑ ሀብቶችን በማስጎብኘት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይነገራል። ከእነዚህ ተጨማሪ ዘርፉ የሚፈለገው ወይም የሚጠይቀው ነገር አለ?

አቶ ስለሺ፡- የቱሪዝም ሥራ በጣም ሰፊ ነው። የቱሪስት ሀብት ገና ተለይቶ አላበቃም። አጠቃላይ በኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብትነት ሊያዙ የሚገቡትን የመለየት ሥራ ይጠበቃል። ከዚህ በፊት ከሚታወቁት በተጨማሪ አዳዲስ መልማት ያለባቸው አሉ። ብዙዎች የማያውቋቸው የዱር እንስሳት፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ባህልና ታሪክ ያሏቸው ቦታዎች አሉ። እነዚህን ሀብቶች ወይንም የቱሪዝም ፀጋዎች የመለየት ሥራ ጊዜ ይወስዳል። ከፍተኛ ወጭም ይጠይቃል። ሆኖም ግን ሥራዎች ተጀምረዋል። በዘርፉ ያለውን ሀብት ወይም የሀሴት ማፕ የማዘጋጀት ሥራ ተጀምሯል።

በሁለተኛ ደረጃ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ሥራን ማጠናከር ነው። ለአብነትም የቡና መስመር ተብሎ በተለየው አካባቢ የለማ መሠረተ ልማት የለም። በመሆኑም ወደእነዚህ አካባቢዎች መሠረተ ልማቶችን ማልማት፣ መረጃ ማዕከሎችንና ማረፊያ ቦታዎች እንዲሟሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ሶስተኛው ለዘርፉ የሚያስፈልገው መረጃ መስጠትና ዘርፉን በማስተዋወቅ የገጽታ ግንባታ ሥራ ነው።አራተኛው በጣም ወሳኝ የሚሆነው፤ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም በመገንባት የአገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ ነው። በዚህ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ሆቴሎች ይጠቀሳሉ። የአገልግሎት ጥራትን ማላቅ ወሳኝ በመሆኑ ሆቴሎቹ በሚኖራቸው ንጽህናና ሌሎችም ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ካሟሉ ከአንድ ኮከብ እስከ አምስት ኮከብ ደረጃ ያገኛሉ።

አምስተኛው ተግባርና መሠረታዊ ጉዳይ አገልግሎት የሚሰጡትን ሰዎችንም ተቋማቸውንም በእውቀት፣በክህሎት፣ በሥነምግባር፣ በአመለካከት አቅም መገንባት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዘርፉ ለኢኮኖሚ፣ለማህበራዊ ትስስር ያለውን አተዋጽኦ፣ ዘርፉ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲወዳደር ያለው ልዩነትን መሠረት አድርጎ በጥናትና ምርምር ማሳየት የሚሉ ሥራዎች ተካትተዋል።

የዘርፉን አጠቃላይ እድገት ጥናት ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል። ምን ያህል ጎብኒዎች መጡ? የት ጎበኙ? ምን ያህል ገቢ ተገኘ? ዘርፉ ለኢኮኖሚው ያበረከተው አስተዋጽኦና ችግሮች ካሉም ለይቶ እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለውን ሁሉ ለይቶ ለማወቅ ያስችላል።

ይህን ታሳቢ በማድረግ ደግሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከክልሎች፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከሲቪል ማህበረሰቡ፣ከዲፕሎማቲክ ኮሙኒቲው ጋር የቱሪዝም ዘርፉን ለመደገፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ የበለጠ ያጠናክረዋል።በቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። መረጃ መስጠት፣ ባህል፣ ቅርስና የዱር እንስሳ መጠበቅ የኛ ሥራ ነው።

የግሉን ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪው ማምጣት፣ በተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች የማህበረሰብ ኢንተርፕራይዞች ተመሥርተው የአካባቢ ሎጅ ኖሯቸው፣ በአስጎብኝነትና መሰል ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል። እንዲህ ያለው ተግባር ደግሞ የክልሎችን ትብብር ይጠይቃል።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዋና ተልእኮ ፖሊሲ፣ ስትራቴጅዎችንና የሕግ ማእቀፎችን መቅረጽ፣ እንዲሁም እነዚህ ማስተዋወቅና መተግበራቸውን ማረጋገጥ ቢሆንም ከላይ የጠቀስኳቸውን ተልእኮዎችንም ይወጣል።

አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ፓርኮችን ጨምሮ ለቱሪዝም መዳረሻ የሚሆኑ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ትኩረቱ ወደ አዳዲሶቹ እንዳይሆን ነባር ከሚባሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር ተጣጥመው እንዲሄዱ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ስለሺ፡- ነባር የቱሪስት መዳረሻ የምንላቸው ለኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መለያ (አይከን) ናቸው። ነባር ከሚባሉት፣ ላልይበላ፣ አክሱም፣ ጎንደር፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጅንካ፣ አፋር ፣ ዶርዜ፣ አዲስ አበባ ከተማ ላይም ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ የተወሰኑ ሙዝየሞችና አብያተክርስቲያናት ይጠቀሳሉ። አሁንም ወደፊትም ለኢትዮጵያ ቱሪዝም መሠረት ሆነው የሚቀጥሉ ናቸው። ያላቸው ታሪክ፣ መስህብ እንዲመሩ ያደርጋቸዋል።

አሁን ላይ የተሰሩና በመሠራት ላይ ያሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች ቀደም ሲል የተሠሩትን ነባሮች ብለን እንደምንጠራቸው ሁሉ የአሁኖቹን ደግሞ የዚህ ዘመን ቅርሶች አድርገን እንወስዳቸዋለን። እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ ለቱሪዝም ገበያ በማዋል እንጠቀምባቸዋለን።

ለምሳሌ ጎርጎራ ሐይቅ ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ መሠረተ ልማት እና ሌሎችንም ሥራዎች በማሟላትና ከመስህብነት ወደ መዳረሻ የማሳደግ ሥራ ነው። ቱሪስት መሳብ የሚቻለው እንዲህ ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ነው ። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የመስህብ ሥፍራ ያላቸው አካባቢዎች አሉ።

ለቱሪስት መስህብ የሆኑ ምንም አይነት መሠረተ ልማት የሌላቸው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አሉ።ለአብነትም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የደን ሀብት፣ ሰሜን ኢትዮጵያ አልጣሽ አካባቢ ከሱዳን ጋር የሚያገናኝ ትልቅ ብሄራዊ ፓርክን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ አንጻር አዳዲስ ልማቶች መኖራቸው ተወዳዳሪነትን ይጨምራል። እንደውም የሚያስፈልገው የጉዞ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚነትን ማሳደግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በ10 ዓመቱ መሪ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ነው።በአቅዱ መሠረት የተከናወነው ሥራ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ስለሺ፡- ከአስር ዓመት መሪ እቅድ ሶስት አመት ተጠናቅቋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከፀጥታና ከፍተኛ ገንዘብ ከሚፈልጉ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ያልተሳኩ ቢኖሩም ከመዳረሻ ልማት፣ ከአቅም ግንባታ፣የአግልግሎት ሰጪ ተቋማትን ጥራት ከማረጋገጥ፣ ከቅርስና ፓርክ ጥበቃ ሥራዎች አኳያ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከዓለም እይታ ውጭ እንዳትሆን ችግሮችን ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ጥሩ አፈጻጸም ተመዝግቧል።በቀሪው ዓመታት የበለጠ በመንቀሳቀስ እቅዱን ለማሳካት ርብርብ ይደረጋል።

አዲስ ዘመን፡- የዓለም ቱሪዝም ቀንን አስመልከቶ ስላለው ዝግጅት ቢገልጹልን

አቶ ስለሺ፡- አዲስ ዓመትን ተከትሎ የሚመጡት የመስቀልና እሬቻ በዓላት አሉ። በአጠቃላይ መስከረም ወር የቱሪዝም ወር ነው። የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይነቃቃል። ከውጭ ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰቱ የሚጨምርበት ጊዜ ነው። መልክአምድሩ ሁሉ የሚደምቅበት ጊዜ በመሆኑ መስህብነቱ ይጨምራል። ታህሳስና ጥር ደግሞ የውጭ ቱሪስቶች በስፋት ወደ ሀገራችን የሚመጡበት ወራት በመሆናቸው ዛሬ መስከረም 17 የሚከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል።

የዓለም ቱሪዝም ቀን በየዓመቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማክበር ነው የተለመደው። ዘንድሮም ዝግጅት የተደረገው በደቡብ ምእራብ ክልል ለማክበር ነው። ክልሉ ባህላዊ፣ታሪካዊና የተፈጥሮ መስህብ ሀብቶች ያሉት በመሆኑ ጥሩ በዓል እንደሚሆን ይጠበቃል። ክልሉም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ያለውን ፀጋ ያስተዋውቃል።

አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ለተሰማራውና ለማህበረሰቡ መልእክት ካለዎት።

አቶ ስለሺ፡- ቱሪዝም በአንድ ተቋም ብቻ የሚሠራ አይደለም። ሥራው ሰፊ ነው። የቱሪዝም ሥራ በመልካም ሥም ላይ የተመሠረተ ሥራ ነው። መልካም ሥም የሚመጣው ደግሞ በሚሠሩ የገጽታ ግንባታ ሥራዎችና በሚሰጡ መረጃዎች ላይ ይመሰረታል። ሁሉም ሰው ባገኘው አጋጣሚ አካባቢውን በማስተዋወቅ፣ መረጃ በመስጠት፣ በገጽታ ግንባታ ላይም በመሥራት፣ የኢትዮጵያ መገለጫ በሆኑ የእንግዳ አቀባበል እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። በዘርፉ ላይ ያለውም ሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ አምባሳደር ሆኖ ዘርፉን በማገዝ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፋለሁ።

አዲስዘመን፡- አመሰግናለሁ።

አቶ ስለሺ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You