የመስቀል ደመራ በዓል ታሪክና አከባበር

 እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሰን አደረሳችሁ! አሜን። እንዲሁም ለያሆዴ፣ መሰላ፣ ማሽቃሮ፣ ጊፋታ፣ ጋሪዎሮ፣ ሄቦ፣ ዮ መስቀላ እና ጋዜ መስቀላ የዘመን መለወጫ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ !

ግራ ቢገባኝና ቢቸግረኝ ዛሬ ደግሞ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ በዓሎቻችን በሕይወታችን አልታይ አልገለጥ ያሉት መንፈሳዊ ትዕምርቶችንና አንድምታቸውን በውል ስላልጨበጥን ይሆን በሚል ስለመስቀል በዓል መንፈሳዊ አንድምታና አከባበር ይቺን መጣጥፍ ይዤ መጣሁ። ከ2000 ዓመታት በፊት በመስቀሉ ድል የተነሳው ጥል ፣ ልዩነት ፣ ዘረኝነት ፣ ወዘተረፈ እንዴት እንደ እባብ አፈር ልሶ ተነስቶ ሀገራችንን እንዴት በዚህ ደረጃ ሊንጣት ቻለ? የህልውናዋ ስጋት ሊሆን ቻለ? በነገራችን ላይ እንደ ክርስትና መንፈሳዊ በዓላት ኢሬቻንም ሆነ ረመዳንን ፣ አረፋንም ሆነ ጨምበለላን ፣ ወዘተረፈ ከማክበር ወጥተን በተግባር በሕይወታችችን እስካልኖርናቸው ድረስ እንዴት ከአዙሪቱ ልንወጣ እንችላለን? የሶስቱ አብርሃማዊ እምነቶች መገኛ ነን እያልን ከመታበይ ባለፍ ከቀውስ ቀለበት ሰብረን መውጣት ካልቻልን ምን ዋጋ አለው? መንግሥትም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወስዶ ልዩነትን መዋቅራዊና ተቋማዊ ያደረጉ አሠራሮችንና አደረጃጀቶችን በማሻሻል ሕዝብን ካላገዘ ከዚህ አዙሪት እንዴት መውጣት ይቻላል? ይሄን ለማድረግ ደግሞ የግድ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን መጠበቅ አያሻም ። ጊዜ የለንማ ። ወደ መስቀል በዓል አከባበር ስንመለስ ፤

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከወደቀበት መርገም ያድነው ዘንድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በ33 ዓመቱ በራሱ ፈቃድ በመስቀል ላይ ተሰቀለ።በመገረፉ ቁስል እኛ ተፈወስን (1ጴጥ 2፥24):: በስቅለቱም ዲያብሎስን ድል ነሥቶ በወህኒ /በሲዖል/ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው (1ጴጥ 3፥18-19):: የሰው ልጅ በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ፍጹም ነጻ ወጣ።ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ ሕዝብና አሕዛብን በአንድ አካል ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ (ኤፌ 2፥16)።ከፍተኛ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ብቻ ይሰቀሉበት የነበረው መስቀል ከጌታ ስቅለት በኋላ የመዳን ምልክት ሆነ፡፡

ዳሩ ግን ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን በማድረጉ የታወኩ አይሁድ መስቀሉን ከሰዎች እይታ ለመሠወር ወሰኑ።ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት።መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል የቆሻሻ መጣያና ማከማቻም አደረጉት።ምንም እንኳን አይሁድ ለጊዜው መስቀሉን ከዓይን ለመሰወር ቢችሉም ከክርስቲያኖች ልቡና ግን ሊያወጡት አልቻሉም።የመስቀሉ ብርሃን በልቡናቸው የሚያበራ ክርስቲያኖች እየበዙ መጡ።መስቀሉንም መፈለግ ጀመሩ፡፡

ንግሥት እሌኒ ልጇን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ክርስትና ሃይማኖትና ስለ ክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር።ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት አዋጅ አወጀ።ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነች።ንግሥት እሌኒም የተፈጠረውን አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችንን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡

ንግሥት እሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነፅ ለእግዚአብሔር ተሳለች።ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ.ም ተጠመቀ።ቅድስት እሌኒም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች እንደደረሰችም ስለ ክብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች።ቦታውን የሚያስረዳት ግን አላገኘችም።አይሁድ የተቀበረበትን ቦታ ለማሳየት ባይፈልጉም በኋላ ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመላከታት ዳሩ ግን ኪራኮስ ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከነበሩት ከሦስቱ ተራሮች ውስጥ መስቀሉ የሚገኝበት የትኛው እንደሆነ ለይቶ ማወቅ አልቻለም፡፡

ንግሥት እሌኒ ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት በእግዚአብሔር መልአክ ርዳታ ደመራ አስደምራ ብዙ እጣንም በመጨመርና በማቃጠል ጸሎት ተያዘ።የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት።ቅዱስ ያሬድም ጢሱ ሰገደ ብሎታል።ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች።ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡

የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡: መስቀሎቹን ወስደው በሞተ ሰው በተራ ቢያስቀምጡ ጌታችን የተሰቀለበትና በዕለተ ዐርብ ተሰቅሎ የዋለበትና በደሙ መፍሰስ የተቀደሰው መሰቀል የሞተውን ሰው በማስነሣት በሠራው ተአምር ሌሎቹ ሁለቱ ታምራት ባለማድረጋቸው የጌታን መስቀል ለይቶ ማወቅ ተችሏል። እሌኒና ክርስቲያኖች ሁሉ ለመስቀሉ ሰገዱለት።በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ጊዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ።ንግሥት እሌኒ ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ ከሠራችለት ጊዜ ጀምሮ በመስከረም 17 ቀን አሁን በኢትዮጵያ እንደሚከበረው በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀል ይከበር ነበር።

ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጣ?

የጌታ መስቀል ለብዙ ዓመታት በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት መስቀሉን ለመውሰድ ጠብ ፈጠሩ።በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣ የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት።ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ለአራት ከፍለው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት።የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በግብፅ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት የግብፅ ክርስቲያኖች በአማሌቃውያን ከሚደርስባቸው ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ በማድረጋቸው የግብፅ ፓትርያርክ የከበሩ ስጦታዎችን ላኩላቸው።ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ወርቅ ሳይሆን ጌታ የተሰቀለበትን መስቀሉን እንደሆነ ገለጹላቸው።በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች።ይህ ግማደ መስቀል በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ኢትዮጵያን እየባረከ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስቀልን ከሐዋርያት በተማረችው መሠረት የወርና የዓመት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች።መስከረም 16 ቀን ደመራ ደምራ ጸሎትና ምሥጋና ታቀርባለች። ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት መሬት በእሌኒ አማካኝነት መገኘቱን ስታስብ በአሁኑ ዘመን ከብዙ ሰዎች ልቡና የተሠወረው መስቀል እንዲገለጥላቸው ትጸልያለች።በመስቀል የሚገኘውን በረከት እየተቀበለች በመስቀል የሚመሰለውን መከራ ሁሉ ትታገሣለች።መስቀል በካህናት በምእመናንና በምእመናት ልቡና ተስሏል።በአንገታቸውና ልብሳቸውም መስቀል አለ።ሥራ ሲጀመርና ምግብ ሲቀርብ በመስቀል አምሳያ ይማተባል።መስቀል ለሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ነው።“እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ 16፡24) እንዳለ ጌታችን ቤተ ክርስቲያናችን ዕለት ዕለት መስቀሉን ትሸከማለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የምትደምረው ደመራ ሀገራዊ አንደምታም አለው።የመስቀል ደመራ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና ተሰጥቶት ዓለም አቀፋዊ ቅርስ ተብሎ ተመዝግቧል::

ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓጼ ዳዊት ስናር በሚባል በረሃ ላይአረፉ ።ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው።ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ እንደነገሠ ወደ ስናር ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተመቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማችው ‘’አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል‘’ ወዳጄ ዘርዐ ያዕቆብ ሆይ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚል ሕልም አዩ፡፡

ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር ስማቸው ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ፣ ከሮም የመጣው ከለሜዳው፣ ሐሙት የጠጣበት ሰፍነግ /ጽዋ/፣ ዮሐንስ የሳለው ኩርዓተ ርዕሱ ስዕል እንዲሁም የተለያዩ የቅዱሳን አጽም፣ ከግብጽ ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር፣ የዮርዳኖስ ውሃ ይገኛል።ንጉሡም መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ በመፈለግ ከብዙ ቦታ አስቀምጠውት ነበር።ለምሳሌ በሸዋ በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም፣ በመናገሻ ማርያም፣ በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር።ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታ ባለማግኘታቸው በራዕይ እየደጋገመ አንብር መስቅል የበዲበ መስቅል መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር።ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብም ለሰባት ቀን ሱባዔ ገቡ፡፡

በዚያም የተገለጸላቸው መስቀለኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምደ ብርሃን ይመጣል አላቸው።እርሳቸውም ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ የብርሃን ዓምድ ከፊታቸው መጥቶ ቆመ።በዚያ መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል አምባ መርቶ መስከረም21 ቀን 1440 ዓ.ም አደረሳቸው።በእውነትም ይህች ግሸን የተባለችው አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረጻት የተዋበች መስቀለኛ ቦታ ሆና ስላገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው።በዚያም አምባ ታላቅ ቤተመቅደስ ሰርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳቱን በየመዓረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጡዋቸው።ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡

በሀገራችን በኢትዮጵያ የመስቀል በዓል የሚከበረው አበቦች በሚፈኩበት የጥቢ ወራት መግቢያ በመሆኑ ጸሎቱም (መስቀል አብርሃ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርኣየ) ሲሆን ሕዝባዊ ዜማውም (ኢዮሀ አበባዬ ፤ መስከረም ጠባዬ) በማለት የመስቀልን ክብር ሳይለቅ ነው፡፡

በተያያዘም በወሎ ክፍለ ሀገር በአንባሰል አውራጃ ውስጥ በዛሬው ደቡብ ወሎ ግሸን ማርያም የምትባል ደብር ትገኛለች።ግሸን አምባ ከአዲስ አበባ 480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቅድስት ሥፍራ ናት። ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ በደላንታ በየጁ መካከልና በበሽሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙርያውን በገድል የተከበበች አምባ ናት።በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ፣ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው።ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሃን አቋርጦ ተለያየን ወንዝና በሽሎን በመሻገር የተጠማዘዘ አስፈሪ ገደሉን ማለፍ ግድ ይላል።ግሸን የመጀመርያ ስሟ ደብረ እግዚአብሔር በመባል ይጠራ ነበር፡፡

ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተመቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራ ነበር።ከዚያም በዓጼ ድግናዥን ዘመነ መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብረ ነጐድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ደብረ እግዚአብሔር ተብላለች።ከዚያም በ14ኛው መቶ ከፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ደብረ ነጐድጓድ የሚለው ደብረ ከርቤ በማለት ተቀይሮአል።በጊሸን ደብረ ከርቤ አምባ በሁሉም ማዕዘን አብያተ ክርስቲያናት የታነፁ ሲሆን ከመስቀሉ ራስጌ የእመቤታችን፣ ከመስቀሉ ግርጌ የቅዱስ ሚካኤል ከቀኝ ክንፉ ላይ ቅዱስ ገብርኤል ከግራ ክንፉ ደግሞ ቅዱስ ዑራኤል ሲሆኑ መካከሉ ላይ መስቀሉ የተቀበረበት የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You