ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላምና አንድነት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ

– 1498ኛው የነብዩ መሐመድ ልደት በዓል በድምቀት ተከበረ

 አዲስ አበባ፡- ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና ሊሠራ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን ገለጹ።1498ኛው የነብዩ መሐመድ ልደት (መውሊድ) በዓል በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጅድ ተከብሯል።

በአዲስ አበባ ታላቁ አንዋር መስጂድ ትናንት በተከበረው የ1498ኛ የነብዩ መሐመድ ልደት (መውሊድ) በዓል ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ሰላም ከሌለ ሀገር አትኖርምና ለሀገራችን ሰላም ልንሠራ ይገባል ብለዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ መተዛዘንንና መቻቻልን ያስተማሩንን ነብይ ልደት ስናከብር የእሳቸውን ፈለግ ተከትለን መሆን አለበት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዘንድሮ መውሊድ በዓል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር ውሃ ሙሌት በተከናወነበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ተናግረዋል። ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና ሊሠራ እንደሚገባም ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን አሳስበዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፋት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያዊያንም ሰውን የመውደድ፣የማክበርና የማፍቀር የምንኮራበት እሴት አለን፡፡ ይህን ጠንካራ እሴት ጠንቅቀው የማያውቁ አካላት ግን ሊከፋፍሉን የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

ሊቀ ትጉሃን ታጋይ እንዳሉት፣ ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ከዛሬ 1 ሺህ 400 ዓመት በፊት ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሲልኩ ኢትዮጵያውያን ፍትሕ እና ርትዕ ያላቸው እንዲሁም ሁሉንም የሚያከብሩ መሆናቸውን በማወቃቸው ነው።

ይህ የነብዩ መልዕክት እኛ ኢትዮጵያውያን የምንኮራበት የአብሮነት እሴታችን ስለሆነ ይህንን የሚያኮራ ታሪካችንን ይዘን መከባበራችንን፣ መዋደዳችንን እና አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ በዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓላትን ስናከብር ሰላምና ፍቅር ልንሰብክባቸው ይገባል ብለዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You