ከዓድዋ ድል ማግስት ኢትዮጵያ የግዛት ማስፋፋት ልታስብ ትችላለች በሚል የብዙ ቅኝ ገዥ ሀገራትን ትኩረት ስባ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በሰሜንና በደቡብ ምስራቅ ጣሊያን፣ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ እንዲሁም በምስራቅ ፈረንሳይ እንደከበባ ያለ አካሄድ ቃጥቷቸው ነበር፡፡
የድንበር የውል ስምምነቶችን ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት መሞከር ጣሊያን ለረጅም ጊዜ የሰራችው ኢትዮጵያን የመያዣና ለበቀል የሚሆን ጊዜ የማመቻቸት ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነው ጣሊያን በቅኝ በያዘቻት የያን ጊዜዋ የጣሊያን ሶማሌላንድና በኢትዮጵያ መንግሥት በ1900 ዓ.ም የተደረገው ስምምነት ነው፡፡
ጣሊያን በዓድዋ የገጠማትን ሽንፈት ቁስል በድል ለመሻር ሀገሪቱን ለመምራት ወደ ስልጣን የመጡት ሁሉ እያሰቡና እየተመኙ ዓመታት ቢያልፉም በ1922 ወደ ስልጣን የመጣው ሞሶሎኒ ተንኮል በመፈለግ እረፍት እንዳልነበረው ይጠቀሳል፡፡በሐረር የኦጋዴን አውራጃ የወልወል ወረራም በዚሁ ስሜት የተወለደ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል።
በኅዳር ወር 1927 ዓ.ም ለወልወል ግጭት በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገ የድንበር ስምምነት ስምምነቱን ለማስተግበር ወደ ስፍራው የሄዱ ኮሚሽነሮች ቦታው ላይ ሲደርሱ የጣሊያን ወታደሮች ቀድመው የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በማግኘታቸው ለቀናት በፍጥጫ ከቆዩ በኋላ ወደ ጦርነት አምርተዋል፡፡
ወልወል የኢትዮጵያ ይዞታ ብትሆንም በመንግሥቱ የጥበቃ መዳከም ተጠቅማ የሰፈረችው ጣሊያን በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ ማሳደሯን ቀጥላ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የተፈጠረው መካረርም ወደ ጦር መማዘዝ እንዲያድግና የዓድዋን የሽንፈት ካባ አውልቃ ኢትዮጵያን ድል ነስታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያጣችውን ክብር ለመመለስ አጋጣሚውን እንደ መንደርደሪያም ተጠቅማበታለች።
ከሮም የተላከው የጣሊያን ጦር መስከረም 22 ቀን 1928 የመረብን ወንዝ ተሻግሮ በዓድዋ፣ በአዲግራት ጦርነት ከፍቶ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን አርበኞችና መሪዎችም ዓለም የጣሊያንን ወራሪነት እንዲያይና በከበባ ትጥቁን እንዲሁም ስንቁን ለማስጨረስ በማሰብ ጦሩ ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥመው ወደ መሀል ሀገር እንዲገባ ፈቀዱ፡፡
በ9 ክፍለ ጦሮች ተዘጋጅቶ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የጣሊያን ጦር ቤታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ እርሻቸውን ሁሉ ትተው ጫካ በገቡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች እረፍት እያጣም ቢሆን ለአምስት ዓመታት ቆይታ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያን የመንፈስና የአካል ጉዳት አቅም ሊያሳጣቸው ቢሞክርም ጠላትን እምቢ በማለት ዓድዋ ላይ ድል ያደረጉ አባቶችን ታሪክ በመድገም ከአምስት ዓመታት ትግል በኋላ ሀገራቸውን ከፋሽስት ነጻ አውጥተዋል፡፡
በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችንን በወረራ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለሀገር ክብር ሲሉ በተለያየ አውደ ውጊያዎች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ሀገር በጠላት በተወረረ ወቅት ሕዝቡ ቀፎው እንደተነካ ንብ ከየአቅጣጫው በመትመም ጠላትን ድባቅ ለመምታት ዘምቷል፡፡ በወቅቱ የነበረው ትውልድ ይህን የአርበኝነት ባህል ከአባቶቹ የዓድዋ ድል የተቀበለውና የወረሰው ነው፡፡ እስከ 1928ቱ የጠላት ወረራ ወቅት ድረስ ጎልቶ ይንጸባረቅ የነበረው የአርበኝነት አስተሳሰብ ‹ማንም ወራሪ ኃይል ቢመጣ እኛ ኢትዮጵያውያንን ማሸነፍ አይችልም›› የሚለው ነበር፡፡ ይህ አስተሳሰብ የመነጨው ከታሪካችን ነው፡፡
ከወረራው በፊት የነበረው ታሪካችን የድል እንጂ የሽንፈት አይደለም፡፡ የጣሊያን ፋሽስት ጦር ሀገሪቷን ለአምስት ዓመት በወረረበት ወቅት በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የአርበኝነት እንቅስቃሴ መካሄዱ ወራሪው ኃይል የተረጋጋ መንግሥት እንዳይመሰረት እንቅፋት ሆነውበታል፡፡ አርበኞቹ የጠላትን እለታዊ እንቅስቃሴ በማወክ፣ ሕዝቡ ተስፋ እንዳይቆርጥና ሀገር ለጠላት እንዳትገዛ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው የፋሽስት ወረራ ከዓድዋው ዘመን የተለየ የሚያደርገው ከጠላት በኩል በጦር ኃይል፣ በፕሮፓጋንዳ፣ በሥነ ልቡና፣ በወታደራዊ ዝግጅት ጠላት ሙሉ ለሙሉ የበላይነት የነበረው መሆኑ ነው፡፡
በተቃራኒው ከኢትዮጵያ አንጻር ደግሞ የሀገሪቷ ማዕከላዊ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ በፈረሰበት፣ በዘመናዊና በበቂ የጦር መሳሪያ ያልተደራጀ ሠራዊት የነበረበት፣ ንጉሠ ነገሥቱ የተሰደዱበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ እኛ ኢትዮጵያውያንን ማንም አያሸንፈንም የሚለው ለዘመናት ስር የሰደደ አስተሳሰብና በራስ የመተማመን መንፈሳዊ ጸጋ ፈተና ውስጥ የወደቀበት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ከባድና ተስፋ አስቆራጭ ወቅት ነበር በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ለሀገር ክብር መስዋዕት ለመክፈል የአርበኝነት እንቅስቃሴ የተደረገው። የአርበኝነቱ እንቅስቃሴ ይደረግ የነበረውም ፍቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች በግል የነበራቸውን ኋላቀር ጠመንጃ፣ ሽጉጥ ፣ጦር፣ ጎራዴና ጩቤ በመያዝ ጫካ በመግባት ነበር፡፡
ጣሊያን 40 ዓመታት ያክል ስትዘጋጅ ቆይታ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ኢትዮጵያን የወረረች ቢሆንም የኢትዮጵያ አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት በድጋሚ ድል ማድረግ ተችሏል፡፡ የዚህ ድል ባለቤት ከሆኑትና ለኢትዮጵያ ሕዝብም ባለውለታ ከሆኑ ጀግኖች ውስጥ አንዱ ደጃዝማች ኡመር ሰመተር አንዱ ናቸው፡፡
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ለሀገራቸው ነጻነት ሲሉ በፍጹም ሀገራዊ ፍቅር መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን የከፈሉ አካላቸውን ያጎደሉ በርካቶች ናቸው፡፡ የቀደሙትን የእነዚህን አባቶች ውለታ አቅም በፈቀደ በምናስታውስበት በዚህ ገጽ ዛሬ ዕድል ቀናንና ታላቁን ኢትዮጵያዊ ጀግና ደጃዝማች ዑመር ሰመተረን ልንዘክር ተገናኘን….. እነሆ ሰውየው!!!
አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው ከታላቁ አንዋር መስጊድ አጠገብ “ዑመር ሰመተረ አንደኛ ደረጃ ት/ ቤት’’ የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ት/ቤት (አሁን ፈርሶ ፓርኪንግ ሆኗል) ሲያስቡ ከታሪኩ በስተጀርባ መታሰቢያ የቆመላቸው እኚህ ሰው ማን ናቸው ብለው መጠየቅዎ ወይም በሌላ ሰው መጠየቅዎ አይቀርም፡፡
የዛሬው ባለታሪካችን የተወለዱት በኦጋዴን አካባቢ ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ሲሆን ዓመቱም 1871 ዓ.ም ነው፡፡ በልጅነታቸው የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ባህላዊ ሥርዓቶችን እየተማሩ ያደጉት እኚህ ሰው የአስተዳደር ሰው ለመሆን በነበራቸው ፍላጎት የመሪነት ክህሎታቸውን ሊያሳኩ የሚችሉ የተለያዩ ጥረቶችን እየሟከሩና ከአካባቢው የጎሳ መሪዎች አሰራርና ተሞክሮን እየቀሰሙ ማደጋቸው ይነገራል፡፡ ለአካለ መጠን ሲደርሱም በአካባቢ አስተዳደር ሥራ በመሰማራት ሀገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን በቅድሚያ በባላባትነት ማዕረግ በመቀጠልም የሱልጣን ዓሊ የሱፍ እንደራሴ ሆነው በናኢባነት እንደዚሁም የኤል- ቡር ገዢ በመሆን ለ23 ዓመታት ሀገራቸውን በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል፡፡
የታሪክ ጠላታችን ፋሺስት ኢጣልያ የዓድዋ ሽንፈቱዋን ለመበቀል ሴራ መጠንሰሱዋን አሀዱ ያለችው በወልወሉ ግጭት ነበር:: የወልወል ግጭት መሠረቱ እንዲህ ነው… የእንግሊዝና የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ በኩል ባለው የግዛታቸው ወሰን በደንብ ለመከለል ስምምነት አድርገው ስለነበር ቀን ተቆርጦ ወደሥራ ሲገባ ሥራውን እንዲያከናውኑ ከእንግሊዝ ኮሎኔል ክሊፎርድ ከኢትዮጵያ ወገን ደግሞ ፊታውራሪ ተሰማ ባንቴ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት የወሰን ክልሉን ለማጥናት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ካፒቴን ሺማትሩ የተባለ የኢጣልያ ተወላጅ ቀደም ሲል ከደረሰበት የወሰን ስምምነት መቶ ኪሎ ሜትር የሚያህል አልፎ እንደጠብ አጫሪነት መተላለፊያ ከለከለ….. በዚህ ነገር ግራ የተጋቡት የኢትዮጵያ ተወካዮች በሰውየው አድራጎት ላይ ማብራሪያ ለመስማት እንኳን ባላስቻለ ፍጥነት ጦሩን አዝምቶ በአየርና በምድር ጦርነት በመክፈት ያለተዘጋጁትን የኛን ወገኖች አጠቃቸው…… በዚህ ጦርነት ፊታውራሪ ዓለማየሁን ጨምሮ ቁጥራቸው 107 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በክብር ሲወደቁ 75 ያላነሱ የፋሽስት ወታደሮች ሞቱ፡፡
የኢጣልያ ጦር በወልወል የጫረው እሳት በሰሜን ተያይዞ በነበረበት በዛ ቀውጢ ቀን ሀገር በጣልያን እንዳትወረር በዱር በገደሉ ሲጠባበቁ በነበረበት ወቅት በምሥራቁ ኢትዮጵያ ክፍል ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ጋር በመሆን ዑመር ሰመተር የትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ፡፡ በዚህም ወቅት ከአቻ ወንድሞቹ ጋር በተለያዩ የጦር አውደ ግንባሮች የተሰለፈው የሶማሌ ጦር ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥቶ የእግር እሳት ሲሆንበት በተለይም ደግሞ በዑመር ሰመተረ የሚመራው ጦር ጎርበሌ ላይ መሽጎ እየወረወረ የጠላት ጦርን መድረሻ አሳጣው በመሪው በኡመር ሰመተር ኢትዮጵያውያን በድል ጎዳና ተራመዱ……አይቀጡ ቅጣት የተቀጣው የጠላት ጦር ሊመሽበት እንደሆነ ተረዳና ከሱው ብሶ ስሞታ ለዓለም መንግሥት አሰማ…… በዚህ ስሞታው ካሳ እንዲከፈለው ብቻ አልጠየቀም ጀግናው ዑመር ሰመተር እንዲሰጠው ጭምር እንጂ……. በተለያዩ የጦር አውደ ግንባሮች ድልን መጎናጸፍ የጀመረው የዑመር ጦር ኤል ቡር ላይ ፋሺስት ቦታውን በስድስት ባታሊዮን ጦር ተከበበ…. እውነታው የገባቸው የጦር አበጋዙ ለጊዜውም ቢሆን ማፈግፈጉን መረጡ… ፋሽስት ድል ያገኘ መሰለው… ይሁንና ለ5 ወራት ያህል ጦራቸውን በማደራጀት የቆዩት ዑመር በ1930 ዓ.ም ሌሊት በጠላት ጦር ላይ ያልታሰበ አደጋ ጣሉ ያንን የተፈራ ባለ ብዙ ባታልዮን ጦር ከጥቅም ውጭ አደረጉት…. በድል እየዘመሩ ለሌላ ጥቃት ሽላቦ ላይ ሰፈሩ….. አሁንም ፋሺስት ሽላቦ ድረስ እየመጣ አላስቀምጥ አላቸው… እንደገና ገጥመው ድል አደረጉት…. በቆራሄም ጠላት አፈረ ከጠላት ምሽግ የጨበጣ ውጊያ በማካሄድ ታላቅ ጀብዱ ፈጸሙ፡፡
የጠላት ጦር ኃይሉ እየከበደ ሲመጣ በጉርለጉቤው ጦርነት ዑመር በጠላት ጥይቶች ተመቱ፡፡ ደጃዝማች ዑመር ሰውነታቸው በስድስት ጥይቶች በመቁሰሉ በጦርነት ለመሳተፍ ከማይችሉበት ደረጃ ደረሱ፡፡ በዚሁ ምክንያት ለሕክምና በቅድሚያ ሀርጌሳ ከዛም በኬንያ በኩል ተጉዘው ወደ ሎንደን ተላኩ፡፡
እስከ ጦርነቱ ማብቂያ በሎንዶን የቆዩት ዑመር ሰመተር ነጻነት ሲመለስ ባንዲራ ሲሰቀል አርበኛው ሁሉ እየፈኮረና እያቅራራ ግዳጅ ሲጥል የድል አጥቢ አርበኛውም ለጀግንነቱ ምስክር ሲገዛ ፊታውራሪ ዑመር(በኋላ ደጃዝማች) በኦጋዴን ከጦርነቱ የተረፉትን አርበኞች አክብረው የሚገባቸውን ሸለሟቸው!!!
ታላቁ ጀግናችን ዑመር ሰመተረ የተጣለባቸው የጠላት ጥይት ጤና እየነሳቸው ቁስሉም እየመረቀዘ ስላስቸገራቸው በሐረር ከተማ ሀኪሞች ባሉበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወሩ ቢታከሙም ለመዳን ግን ሳይችሉ ቀረ በተወለዱ በ61 ዓመታቸው መጋቢት 10 ቀን 1936 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ!!!
ሐረር ከተማ በሚገኘው በአብደል መካነ መቃብር መኳንንቶችን አስከትለው ክርስቲያንና እና እስላሙ በነቂስ ወጥቶ ለጀግና በሚሆን በሙሉ ወታደራዊ ክብር ተሸኙ!!!
በዚህ የቀብር ሥነ ሥርዓት አብዶ ሀይድ የተባሉ የትግል ጓዳቸው ይህንን አንጀት የሚበላ ቅኔ ተቀኙላቸው።
ተገዳይ እወልወል እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ አፍዱግ ላይ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ቆራሄ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ሀነሌ እጠረፉ ላይ፤
የመትረየሱ ሼክ የለበን መምህር፤
ሞት ጠራህ አንተንም ዑመር ስመጥር!!!
ምንጭ፡
- የኢትዮጵያ ታሪክ – ተክለ ጻድቅ መኩሪያ
- ያልተዘመረላቸው – በፍጹም ወ/ማርያም • የተለያዩ ድረ ገጾች
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2026