ፍትሕ የናፈቁት – የሀገር ባለውለታ

የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 በተለምዶ ልደታ ኮንዶሚኒየም ተብሎ ወደሚጠራው ሰፈር ይወሰደናል፡፡ በጉዳይነትም ለልማት ከተነሱ ቤቶች የካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ውዝግብን ይዳስሳል፡፡

የነገሩ መነሻ፣ «በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የቤት ቁጥር 177 የተመዘገበ ቤቴ በ2002 ዓ.ም ለልማት የፈረሰ ቢሆንም፤ መንግሥት ለልማት ተነሺዎች መክፈል የሚገባውን የካሳ ክፍያ ሊከፍለኝ አልቻለም፡፡ በተፈጠረብኝ በመልካም አስተዳደር ችግር በጡረታ ዘመኔ ለከፋ ችግር ተዳርጌያለሁ፡፡ እየደረሰብኝ ያለውን በደል መንግሥትም፣ ሕዝብም ይወቅልኝ፤” ሲሉ ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ዝግጅት ክፍል አባሪ መረጃዎችን ጭምር በመያዝ በደል የፈጠረባቸውን ምሬት መግለጻቸው ነው፡፡

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ዝግጅት ክፍልም ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛን አቤቱታ መነሻ በማድረግ፣ እንዲሁም ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች በመመርምር በማደራጀት የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅቷል፡፡

ከአቤቱታ አቅራቢው አንደበት

የዛሬው ጡረተኛ ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ፣ ከውስጥ እና ከውጭ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ከተነሱ እና ከሚነሱ ጠላቶች ለመከላከል ከሀገሬ በፊት እኔ ብለው በ1951 ዓ.ም የውትድርና ሙያን ተቀላቀሉ፡፡ ሀገራቸውን በወታደርነት እያገለገሉ እያለም፣ በኮንጎ (ዛየር ግጭት ተቀሰቀሰ)፡፡ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም የተባበሩት መንግሥታት ለኢትዮጵያ ጥሪ አደረጉ፡፡ በጥሪው መሠረት ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ የሰላም አስከባሪ አባል ሆነው በ1954 ዓ.ም ወደ ሀገረ ኮንጎ አመሩ፡፡ በ1955 ዓ.ም በኮንጎ የነበረውን ግዳጃቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡

ከተመለሱ በኋላ ከደመወዛቸው ቆጥበው በቀድሞ አጠራር ‹‹ተክለሃይማኖት አውራጃ ከፍተኛ አራት ቀበሌ 49››፤ በአሁኑ አጠራር ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ወይም በተለምዶ ልደታ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ለመኖሪያ ቤት የሚሆን ቦታ ገዝተው ቤትም ሰሩ፡፡ በቤቱም ለስምንት ዓመታት ተቀመጡ፡፡ እየኖሩ እያለ በኤርትራ የተደራጁ ቡድኖች በፈጠሩት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት ለግዳጅ ወደ ኤርትራ አቀኑ፡፡

ኢትዮጵያ በኤርትራ የተነሳውን ግጭት ሳትቋጭ በምስራቅ በኩል በሶማሊያ ተወረረች፡፡ ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛም ከኤርትራ ተነስተው ሶማሊያ ጥቃት ወደ ከፈተችበት ምስራቅ ኢትዮጵያ አመሩ፡፡ ኢትዮጵያም ከሶማሊያ የተቃጣውን ወረራን መክታ መለሰች፡፡

ከድል መልስ የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ በደብረ ብርሃን ከተማ አካባቢ በሚገኝ የወታደር ማሰልጠኛ ወታደር የማሰልጠን ግዳጅ ተሰጣቸው፡፡ ወታደር እያሰለጠኑ ባሉበት ወቅት ሻቢያ የከፈተው ውጊያ አድማሱን እያሰፋ መጣ፡፡ በዚህም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኤርትራ ለግዳጅ ተላኩ፡፡ በኤርትራም ለስምንት ዓመታት ከስምንት ወር ቆዩ፡፡

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ በተመለሱ ጊዜ ግን ከደመዛቸው ቆጥበው የገዙትን ቤት የቀበሌ 49 ጽሕፈት ቤት ለግለሰቦች አከራይቶት አገኙት፡፡ ይህን ተከትሎ ጉዳዩን ለመንግሥት አቤት አሉ፡፡ መንግሥትም ቤቱ የራሳቸው ስለመሆኑ አምስት ምስክር እንዲያመጡ አዘዘ፡፡ አምስት ምስክር በማምጣት ቤቱ የእርሳቸው ስለመሆኑ በፍርድ ሸንጎ አስመሰከሩ፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ሸንጎ ታይቶ ቤቱ የእርሳቸው ስለመሆኑ ፍርድ ሸንጎ ሕጋዊ ማህተም እና ፊርማ እንዲሁም ቁጥር ያለበትን ሰነድ ለከፍተኛ አራት በማቅረብ ቤታቸው እንዲመለስላቸው ጠየቁ። ይሁን እንጂ የከፍተኛ አራት አስተዳደር ከከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ደብዳቤ ካላመጣህ በፍርድ ሸንጎ ውሳኔ ብቻ ቤቱን መመልስ አንችልም ሲሉ ይነግሯቸዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ስለጉዳዩ በማመልከቻ አሳወቁ፡፡ ሚኒስቴሩም ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቶ ቤቱ የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ መሆኑን አረጋግጦ የባለቤትነት ደብተር ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ ደብተር በተጨማሪ ቤቱን በአስቸኳይ እንድታስረክቡት የሚል ደብዳቤ ለከፍተኛ አራት ከነማ ነዋሪዎች ማህበር ጽሕፈት ቤት መጻፉን ይናገራሉ፡፡

በመቀጠል ‹‹ቤቴን አስረክቡኝ›› ሲሉ በከፍተኛ አራት የቀበሌ 49 ክልል አስተዳደሩን ጠየቁ። የቀበሌውም ምላሽ ግን ‹‹በቤቱ ሰዎች አሉ፤ ሰዎቹ ቤት ሰርተው ሲወጡ በዚያ ጊዜ ጠይቀን›› የሚል ሆነ፡፡ ‹‹እኔ በኪራይ ቤት ተቀምጬ እንዴት እንዲህ ይደረጋል?” ሲሉ ቀበሌውን መጠየቃቸውን ያስረዳሉ፡፡

የቀበሌ 49 አስተዳደር የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ጉዳዩን ለከፍተኛ አራት አሳወቁ፡፡ ከፍተኛ አራት ለመሸንገል በሚመስል መልኩ በአካባቢው የሚገኝ የቀበሌ ቤት አፈላልግና ስታገኝ ቤቱን እንሰጥሃለን ሲል አዘዘ፡፡ በዚህም የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ እኔ የምኖረው እንጦጦ አውራጃ ከፍተኛ 13፤ እንዴት ተክለሃይማኖት አውራጃ የሚገኝን ባዶ ቤት ላውቅ እችላለሁ? ከፍተኛ አራት ይህን ማለቱ ትክክል አይደለም! ሲሉ የከፍተኛ አራትን የውሳኔ ሃሳብ መቃወማቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ከፍተኛ አራት ጉዳዩን በመመልከት ቀጠሮ ሰጥቶ አሰናበታቸው፡፡ በተቀጠሩበት ቀን ቢመለሱም ጉዳያቸው ሊፈታ አለመቻሉን ይገልጻሉ፡፡

በዚህም ጉዳያቸውን ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ወሰዱት፡፡ ማዘጋጃም ውዝግብ የተነሳበት ቤት የአንተ ስለመሆኑ ምን ማስረጃ አለህ? የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ፶ አለቃ አሰፋም የቤት ባለቤትነት ደብተር አለኝ በማለት የቤት ባለቤትነት ማረጋጋጫ ደብተራቸውን አሳዩ፡፡ የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ሕጋዊ መሆኑን ያረጋገጠው የማዘጋጃ ቤትም 10 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቤቱን አስረክባችሁ ምላሻችሁን እንድታሳውቁኝ የሚል ደብዳቤ ለከፍተኛ አራት ፃፈ፡፡

ይህን ተከትሎ ከፍተኛ አራትም ቤቱን የያዙትን ሰዎች አስለቅቀን እስከምናስረክብ የ፶ አለቃ አሰፋ ባለበት ቤት ኪራይ እንዳይከፍሉ የሚል ደብዳቤ ጃንሜዳ አካባቢ ለሚገኝ እንጦጦ አውራጃ ከፍተኛ 13 ጻፈ፡፡ በዚህም ጃንሜዳ አካባቢ በሚኖሩበት የቀበሌ ቤት በነፃ ተቀመጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለሚኖሩበት ቤት ኪራይ ባይከፍሉም ልደታ ለሚገኘው እና ለሰሩት ቤት ግን ግብር የሚገብሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡

ልደታ ለሚገኘው ቤት ግብር ከመክፈል ጎን ለጎን፣ ቤታቸው እንዲመለስላቸው ለበርካታ ጊዜያት እየተመላለሱ ከፍተኛ አራትን ቢጠይቁም መልስ የሰጣቸው አካል አልተገኘም፡፡ በዚህ ሂደት ላይ እያለ በ2002 ዓ.ም ሳይኖሩበት ግብር ሲከፍሉበት የነበረው ቤት ለልማት በሚል ፈረሰ፡፡ ከፈረሳው በኋላ ለልማት በሚል ከቦታቸው ለሚነሱ ሰዎች የሚደረግላቸው የመብት ማስከበር ሥራ ለእርሳቸውም እንዲሰጣቸው የልደታ ክፍለ ከተማን ጠየቁ፡፡ ክፍለ ከተማውም የእናንተ ቤት የተካካሰ ነው፡፡ ትንሽ ጊዜ ቆዩ እና ካሳ ይከፈላችኋል ተብለው የካሳ ክፍያቸውን እየተጠባበቁ እያለ በ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ መጣ፡፡

በለውጡም ችግራቸው እንዲፈታላቸው በማሰብ ያልደረስኩበት ቦታ የለም የሚሉት ፶ አለቃ አሰፋ፤ ጉዳዩ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ከንቲባ ቢሮ ሄደው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ከንቲባ ቢሮ ደግሞ ጉዳዩን የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ይፈታዋል ብሎ እንደጠቆማቸው፤ መሬት አስተዳደር ደግሞ ተግባረ ዕድ አካባቢ ለሚገኝ የካሳ ጉዳዮች ሰሚ ጉባዔ እንደላካቸው፤ የካሳ ጉዳዮች ሰሚ ጉባዔ ደግሞ የልደታ ክፍለ ከተማ ስለጉዳዩ ካልመራልህ አልቀበልህም ማለቱን ይገልጻሉ፡፡

፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ፣ የተቋማቱን የፋይል አያያዝ ችግርን አስመልክቶ ግርምት በተላበሰ ስሜት ስለ ጉዳዩ ሲያስረዱ፤ ‹‹የሚገርመው ነገር፣ ክፍለ ከተማ በሄድኩ ወቅት በደርግ ዘመነ መንግሥት ከከተማ ልማት ያመጣኋትና ቤቱን አስረክቡት የምትለው ደብዳቤ ብቻ በእኔ ማህደር ተገኘች፤” በማለት ነበር። ይህን ተከትሎ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ማህደራቸው እንደሚገኝ ከክፍለ ከተማ ተጠቁመው ወረዳ 09 መላካቸውን ይናገራሉ፡፡ ወረዳ 09 ሲሄዱ ፋይላቸውን ለማየት የአንድ ወር ቀጠሮ እንደሰጣቸው እና ከወር በኋላም ወደ ወረዳው ሲመለሱ “በእኛ የሚፈፀም ነገር የለም፡፡ ብትፈልግ ክሰስ” የሚል መልስ እንደሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡

ይህን ተከትሎ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስደውት እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ከማሳረፍ ይልቅ፣ “ይህ ጉዳይ የሚመለከተው የልደታ መሬት ልማትና አስተዳደር እንጂ እኛን አይደለም” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው የሚናገሩት ፶ አለቃ አሰፋ፤ በዚህም እስከ ዛሬ ድረስ ጥያቄያቸው ምላሽ አለማግኘቱን ይናገራሉ፡፡

 በዚህ መልኩ ፍትሕ አጥተው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የሚናገሩት ፶ አለቃ አሰፋ፤ “አሁን ላይ አቅም አጣሁ፤ ፍትህም አጣሁ፤ በሰው ሀገር ደምቼ እና ቆስዬ ባገኘሁት ገንዘብ የሰራሁትን ቤት ተነጠቅሁ፡፡ ሲሆን ለሀገሬ የደከምኩኝ ለሀገሬ የለፋሁ ሰው ልደገፍ ይገባኝ ነበር፡፡ ካልሆነ ደግሞ በደሜ እና በላቤ የሰራሁትን ቤት መቀማት አልነበረብኝም፡፡ እውነት ኢትዮጵያ ለእኔ ውለታዬን እንዲህ ነበር መክፈል የሚገባት?” ሲሉ ሃሳባቸውን በጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ምንም እንኳን በማካካሻነት በወሰዱት ቤት ዛሬም ኪራይ የማይከፍሉ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የሚገኙበት ቤት ለልማት ከፈረሰው ቤት በጥራትም ሆነ በስፋት ሊወዳደር እንደማይችል የሚገልጹ ፶ አለቃ አሰፋ፤ እርሳቸው የሰሩት ቤት 150 ካሬ ላይ ያረፈ ሁለት መኝታ ቤት፣ መጸዳጃ እና ማብሰያ ቤት ያለው እንደነበር ነበር ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በማካካሻነት የተሰጣቸው ግን ለመኖር አስቸጋሪ የሆነ እና ለአዛውንት ምቹ ባለመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ለፈረሰው ቤት ተገቢውን ካሳ ማግኘት እችል ዘንድ በመተባበር የበኩላችሁን ተወጡ›› ሲሉ አዛውንቱ ፶ አለቃ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች

ሰነድ አንድ፡- ሰኔ 19 ቀን 1972 ዓ.ም የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ለ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ በቁጥር 4/23240 በተመዘገበ ሰነድ ላይ የከተማ ቤት ባለቤትነት ማረጋጋጫ ደብተር መሰጠታቸውን ያትታል፡፡

ሰነድ ሁለት፡- አዲስ አበባ አጠቃላይ ነዋሪዎች ማህበር ምክር ቤት በቀን 29/9/1977 ዓ.ም በቁጥር ከ4/ቀ49 /የፍመቁ /299/1 ለከፍተኛ አራት ከነማ ጽሕፈት ቤት የተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡ ደብዳቤውም፣ በከፍተኛ አራት ቀበሌ 49 የቤት ቁጥር 177 ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ስለመሆኑ በፍርድ ሸንጎ አስመስክረዋል፡፡ ስለሆነም ከቤቱ ጋር ተያይዞ ለሚጠየቁት የመብት ጥያቄ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግላቸው ሲል ይገልፃል፡፡

ሰነድ ሦስት፡- የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በቀን 07/10/1977 ዓ.ም፤ በቁጥር ከቤ/ከ4/ቀ49/2490/77 ለከፍተኛ አራት ከነማ ነዋሪዎች ማህበር ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ እንደጠቆመው የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ በከፍተኛ አራት ቀበሌ 49 የቤት ቁጥር 177 ተመዝግቦ በሚገኘው ቤት ላይ የባለቤትነት ማስረጃ ከፍርድ ሸንጎ ቢያስመሰክሩም የከፍተኛ አራት ከነማ ነዋሪዎች ማህበር ጽሕፈት ቤት ከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ደብዳቤ ካላመጣህ የባለቤትነት ጥያቄውን አንቀበልም ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከፍርድ ሸንጎ የተመሰከረበት ማስረጃ በከፍተኛ አራት ከነማ ነዋሪዎች ማህበር ጽሕፈት ቤት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ውሳኔ በመስጠት ለከፍተኛ አራት ከነማ ነዋሪዎች ማህበር ጽሕፈት ቤት ማሳወቅ ይችል ዘንድ የከፍተኛ አራት ከነማ ነዋሪዎች ማህበር ጽሕፈት ቤት ማስረጃውን እንዲልክልን እናሳስባለን የሚል ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ ከፍተኛ አራትም በአዲስ አበባ አጠቃላይ ከተማ ነዋሪዎች ማህበር ምክር ቤት ሥም በቁጥር ከ4/16852/77 በቀን 25/10/1977 ዓ.ም ለከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በላከው ሰነድ እንዳረጋገጠው ውዝግብ የተነሳበት ቤት የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ስለመሆኑን አረጋግጧል፡፡

ሰነድ አራት፡- በቀን 27/5/1981 ዓ.ም የከፍተኛ አራት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ላይ የተገኘ ማስረጃ እንደሚመላከተው፡- አንደኛ ቤቱ በቅጽ 004/014 ተሞልቶ በማህደራቸው ውስጥ አልተገኘም፡፡ በተጨማሪም በቤቱ አበል አልበሉበትም፡፡ ሁለተኛ ቤቱን ከአዋጅ በፊትም ሆነ በኋላ በመኖሪያ ቤት እንጂ በድርጅትነት አልተያዘም በተጨማሪም ከአዋጁ በኋላ ሌላ ቤት አልሸጡም። ሦስተኛ ቤቱ የግላቸው ስለመሆኑ በ15/9/1977 ዓ.ም በቀበሌው ፍርድ ሸንጎ በሶስት የሕግ ምስክሮች የተረጋጋጠ ሰነድ በፋይላቸው ውስጥ ይገኛል። አራተኛ በቤቱ አበል አያገኙም፤ ቤቶችንም አላስረከቡም የሚል ነው፡፡ ይህ ቃለ ጉባዔ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የተላከ ነው፡፡

ሰነድ አምስት፡- የአዲስ አበባ አጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎች ማህበር ምክር ቤት በቀን 2/8/1981 በቁጥር ከ4/985/81 ለከፍተኛ አራት ለቀበሌ 49 ከነማ ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ እንዳመላከተው በቀበሌ 49 በቤት ቁጥር 177 ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ስለሆነ ቤቱ ለ፶ አለቃ አሰፋ እንዲለቀቅላቸው እናስታውቃለን የሚል ነው፡፡

ሰነድ ስድስት፡- የተክለሃይማኖት አውራጃ አስተዳደር በቁጥር ከ/269/49/82 በቀን 25/1/1982 ዓ.ም ለቀበሌ 49 ከነማ ጽሕፈት ቤት በፃፈው ደብዳቤ እንዳመለከተው በቀበሌ የሚገኘው የቤት ቁጥር 177 የሆነ ቤት ባለንብረት የሆኑት ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ቤታቸው በተከራይ የተያዘ በመሆኑ እንዲለቀቅላቸው በከፍተኛ አራት ከነማና ከአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ የተላለፈላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

የአመልካቹን ቤት መለቀቅ አስመልክቶ የአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ጽሕፈት ቤት ግንቦት 24 ቀን 1981 በቁጥር አም12/4/27 በተጻፈ ደብዳቤ፤ አመልካች በከፍተኛ 13 ቀበሌ 05 ውስጥ ተከራይተው የሚኖሩበት የቤት ቁጥር 907 የሆነ ቤትና ሊለቀቅላቸው የሚገባው በከፍተኛ አራት ቀበሌ 49 የሚገኘው ቤት ኪራይ እኩል ስለሆነ በአመልካች ቤት ያሉ ተከራዮች ወደ ከፍተኛ 13 ቀበሌ 05 የቤት ቁጥር ተዛውረው የ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ቤት እንዲለቀቅ መመሪያ የተሰጠ ከመሆኑም በላይ በመመሪያው መሠረት፤ እንዲፈፀም የከፍተኛ አራት ከነማ ጽሕፈት ቤት ግንቦት 28 ቀን 1981 ዓ.ም በቁጥር ከ4/1259/81 በተጻፈ ደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ሆኖም የቀበሌው ጽሕፈት ቤት እንደ ትዕዛዙ መፈጸም ሲገባው ትዕዛዙን ካለመፈጸሙም በላይ የገጠመውን ችግር እንኳን አልገለፀም። በዚህ ምክንያት አመልካቹ ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ስለዚህ ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ጽሕፈት ቤት በቁጥር አም 1214/27 እና ከከፍተኛ አራት ከነማ በቁጥር ከ4/1259/81 በተጻፉ ደብዳቤዎች መሠረት ተፈጽሞ ውጤቱ ከጥቅምት 10 ቀን 1982 በፊት እንዲገለጽልን በጥብቅ እናሳስባለን የሚል ነው፡፡ በዚህ ሰነድ የተመለከተው ቤቱ ለ፶ አለቃ አሰፋ እንዲመልስ ነበር፡፡

ሰነድ ሰባት፡- የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ዲዛይን እና ግንባታ አስተዳደር ልማት ጽሕፈት ቤት በቀን 06/06/2004 ዓ.ም በቁጥር ል/ክ/ከ/ወ/8/ዲ/ግ/ል/ጽ0567/04 ለየካ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 04 ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት በተፃፈ ደብዳቤ እንደተጠቀሰው፤ ውዝግብ የተነሳበት ቤት በቀበሌው በልማት እንደፈረሰ እና ይህ ቤት በወቅቱ መንግሥት የማያስተዳድረው መሆኑን የገለጸበት ደብዳቤ ነው፡፡

የልደታ ክፍለ ከተማ ምላሽ

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡን የልደታ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ሥራዎች ዘርፍ አቶ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ሲሆኑ፤ ጉዳዩን በዝርዝር ለማየትም ሆነ ለመወሰን ሕጎች፣ አዋጆችና፣ መመሪያዎች ምን እንደሚሉ መገንዘብ ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ። እኔ የምሠራበት ዘርፍ መብት ከተፈጠረ በኋላ የሚያስተናገድ እንጂ መብት ያልተፈጠረለት አካል ለሚያቀርበው ቅሬታ ምላሽ የምንሰጥበት አግባብ የለም ብለዋል፡፡

ይሁንና ግን እንደ ዜጋ አንድ ግለሰብ ሲበደል ወይንም ፍትህ ሲዛባ አንመለከትም ማለት አይደለም የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ፶ አለቃ አሰፋ አዱኛ ሕጋዊ አካሄድን ጠብቀው የሚመጡበት አግባብ ከተፈጠረ በአስተዳደራዊም ሆነ በሌላ ሕጋዊ አካሄድ እልባት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የልደታ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ነጂባ አብደላ፣ የዝግጅት ክፍላችን በምርመራ ባገኛቸው ሰነዶች ላይ ባለሙያዎች ማብራሪያ ይሰጣሉ ቢሉም፤ ከተቋማቸው ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ ሊሰጡን የሚችሉ ባለሙያዎችን ማግኘት አልተቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ባለሙያዎቹ እንደ ምክንያት የሚያነሱት፣ ጉዳዩ ባለሙያዎች ተመልክተው የሚፈቱት ወይንም ማብራሪያ የሚሰጡበት ሳይሆን፤ ከጉዳዩ ውስብስብነት አኳያ አስተዳደራዊ መልክ ያለው ነው፡፡

አያይዘውም ጉዳዩ የባለሙያዎችን ሳይሆን የበላይ ኃላፊዎችን ማብራሪያ የሚጠይቅ እንደሆነም በመግለጽ፤ ጉዳዩ ሕጋዊ አግባብን ጠብቆ የሚመጣ ከሆነ፣ እንዲሁም የበላይ ኃላፊዎች ይሁንታ እና ትዕዛዝ ከታከለበት ፶ አለቃ አሰፋን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውንም ባለሙያዎቹ አረጋግጠዋል።

የዝግጅት ክፍሉ ግኝት

አንደኛ፣ በአሁኑ ወቅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል፣ ከልደታ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ያገኘው የሲአይ ኤስ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ቤቱ በቁጥር 177 የቀበሌ ቤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ የሲአይ ኤስ ሰነድም የ፶ አለቃ አሰፋ በግል ቤትነት ማረጋገጫ ይዘው ግብር ሲከፍሉበት ከቆዩባቸው ሰነዶች ጋር የሚጣረስ ብቻ ሳይሆን፤ በአንድ ቤት ላይ ሁለት ዓይነት አሰራር የተከተለ መሆኑን አረጋግጧል። ይሄም የመረጃዎችን አሻሚነትና የአሰራር ችግር መኖሩን ለመገንዘብ አስችሏል፡፡

ሁለተኛ፣ የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ለ፶ አለቃ አሰፋ ከሰጣቸው የከተማ ቤት ማረጋገጫ ሰነድ ጋር የተቃረነ ነው፡፡

ሦስተኛ፣ የዝግጅት ክፍላችን በምርመራ ካገኛቸው ሰነዶች መካከል፤ በዚሁ ቤት ከ፶ አለቃ አሰፋ በተጨማሪ በ2001 ዓ.ም በአንድ ሌላ ግለሰብ ስም የቤት ግብር ሲከፈል እንደነበር፤ ግለሰቡም በቦታው ምትክ በቂርቆስ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይት ባለ ሁለት መኝታ ቤት መውሰዳቸውን የሚያረጋገጥ ሰነድ ይገኝበታል፡፡

የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት

ውድ አንባቢያን በጉዳዩ ዙሪያ ከተገኙ ሰነዶችና ማስረጃዎች፣ እንዲሁም ከመረጃ ሰጪ ተቋማት መረጃን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን አኳያ ጉዳዩ ሰፋ ያለ ምርመራ የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝበናል። በመሆኑም የምርመራውን ውጤት በሚቀጥሉት ዝግጅቶቻችን የምናሳውቅ ይሆናል።

በተያያዘም፣ የዝግጅት ክፍላችን፣ መረጃ ለማግኘት ከተቸገረባቸው ተቋማትና ኃላፊዎች መካከል የልደታ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ነጂባ አብደላ ለሚነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ የተሟሉ መረጃዎችን ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡

ሙሉቀን ታደገ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You