‹‹የጋራ ባህላዊ ዕሴት ለጠንካራ አገራዊ አንድነት ›› በሚል መሪ ቃል ዛሬ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው አውደ ርዕይ በኪነጥበብና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበዋል። ውይይት ተደርጎባቸዋል።
አውደ ርዕዩን የከፈቱት የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ተፈረ መላኩ ባደረጉት ንግግር፤ መንግስታት እንደ ወንዝ ሲመጡና ሲሄዱ ኖረዋል ፡፡የዚህች ሀገር ህዝብ ግን ከድህነቱና ከዕርዛቱ ጋር ትላንትም ዛሬም አለ፤ በመሆኑም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ለሀገራቸው ሰላምና ዕድገት በየሙያቸው የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በአውደ ርዕይው የጥዋቱ መርሀ ግብር ላይ “የጋራ ባህላዊ እሴት ለጠንካራ አገራዊ አንድነት” እና “ኪነ-ጥበብ ለአገራዊ አንድነት ያለው ሚና” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ እና በሰርፀ ፍሬ ሰብሃት አንኳር ንግግር ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል፡፡
“ኪነ ጥበባት ለትውልድ ቀረፃ የነበራቸውና ሊኖራቸው የሚገባ ሚና” በሚል ንፅፅራዊ ጥናት በደራሲ አበረ አዳሙ የቀረበ ሲሆን፤ በጥናቱ ላይ ውይይት ተከሄዶበታል፡፡
በአቶ ገብረሃና ዘለቀ የቀረበውና “ትንቢተ ሀዲስ አለማየሁ በፍቅር እስከመቃብር” የሚል ርዕስ የተሰጠው አህፅሮተ ጥናት፤ በፍቅር እስከ መቃብር የረዥም ልብወለድ መፅሀፍ ላይ የተገለፁ ህልሞች፣ ምሳሌዎች መልካምድርን፣ እንስሳትን፣ ሰው ሰራሽ ሁነቶችንና የልደት የሞት ገጠመኞችን የተረጎመ ነው፡፡
“ዓርአያ ደምሳሽነትና ልማድ አፍራሽነት በድህረ 83 የአማርኛ ልቦለዶች ውስጥ (የቡርቃ ዝምታ እና ሚክሎስ የመቻል ሚዛን እንደማሳያ)” በሚለው ልቦለዶች ላይ ባተኮረውና በአቶ አካል ንጉሴ የቀረበው ጥናት፤ ስነፅሁፍን በማህበረ ፖለቲካዊ አውድ ውስጥ የመተንተንን አቅጣጫን እንደ መስከንተሪያ (ማሳያ) በመውሰድ አርአያ ደምሳሽነትና ልምድ አፍራሽነት በድህረ 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ ልብወለዶች ውስጥ ምን መልክ እንዳለው ፈትሿል። መርምሯል።
በዚሁ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መድረክ ላይ የተለያዩ አርቲስቶች፣ የዩኒቨርስቲው መምራን፣ የአስተዳዳር ሰራተኞች፣ የአከባቢው ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የተገኙ ሲሆን፤ አውደ ርዕይው እስከ ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ .ም ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በሀይማኖት ከበደ