እንደ ሀገር ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ከሁሉ በላይ ትምህርት ከፍ ያለ ስፍራ እንዳለው ይታመናል። ከዚህም የተነሳ ሀገራት ለትምህርት ሁለንተናዊ ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ፤ በዚህም ወደፈለጉበት የዕድገት /የብልጽግና ማማ መድረስ ፤ ዛሬ ላይ የሕዝቦቻቸውን ሕይወት በተሻለ መልኩ መምራት የቻሉ ሀገራት የዚህ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።
በእኛም ሀገር፣ በዘመኑ የነበረው ትውልድ በውስጡ የነበረውን ሀገርን ከፍ ያለ የስልጣኔ/የዕድገት ማማ ላይ የማቆም ተስፋ እውን ለማድረግ ለትምህርት ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ ለመንቀሳቀስ ሞክሯል። ትምህርት ነገዎችን ብሩህ ማድረግ የሚያስችል አቅም መሆኑን በመገንዘብ፤ ራሱን በትምህርት ብቁ ለማድረግ፣ በዚህም ሀገርን እንደ ሀገር ለመታደግ ረጅም ርቀት ተጉዟል።
በተለይም ከ1920ዎቹ ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን የነጻነት ተጋድሎ ተሸንፎ መውጣቱን ተከትሎ፤ እንደ ሀገር ለዘመናዊ ትምህርት ከፍ ያለ ትኩረት ተሰጥቶት በመላው ሀገሪቱ ሰፊ እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ዙሪያ የተፈጠረው መነቃቃት ከመንግሥት ባለፈ፤ የተለያዩ ሀገራትን እና የግሉን ዘርፍ በስፋት ወደ ዘርፉ እንዲሰማሩ ከፍ ያለ መነሳሳት ፈጥሮ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።
በርግጥ በቀደመው ዘመን የነበሩ ነገሥታት ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ተስፋ ያደረጓቸውን ብሩህ ነገዎች ተጨባጭ ለማድረግ ለትምህርት ትኩረት የመስጠታቸው እውነታ፤ የነገሥታቱ የታሪክ ትርክት አንድ አካል እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህም ሆኖ ግን ሀገሪቱ ከውስጥም ከውጭም ካጋጠሟት ተግዳሮቶች አንጻር ያሰቡትና የተመኙትን ያህል ፍሬ አፍርቶ ውጤቱ ሀገርን እንደ ሀገር የዕድገት ከፍታ ላይ ሊያስቀምጣት አልቻለም።
ይህ እውነታ በዚህም ዘመን ትልቅ ሀገራዊ ተግዳሮት ሆኖ የመቃጠሉ እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ጥራትን በዘነጋ መልኩ ትምህርትን በስፋት ለዜጎች ለማዳረስ፤ ለትምህርት መሠረት ልማት ትኩረት ተሰጥቶ የተሄደበት መንገድ አሁን ላይ ሀገር ያልተገባ ዋጋ እንድትከፍል እያስገደዳት ይገኛል።
ችግሩ አሁን ባለው ትውልድ እየተስተዋሉ ላሉ ከባህሉ፣ ከሃይማኖቱ እና ከማንነቱ ያፈነገጡ ተግባራት ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝም የብዙዎች እምነት ነው። እንደ ሀገር እያጋጠሙን ካሉ የሰላም እና የመልካም አስተዳደር ፈተናዎች በስተጀርባም የችግሩ ግዝፈት ከፍ ያለ ስለመሆኑም የተለያዩ ጥናቶች በተጨባጭ እያረጋገጡት ያለ እውነታ ነው።
የትምህርት ጉዳይ እንደ ሀገር ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ትልቁ አቅም መሆኑን ፣ ከዚያም በላይ አሁን ላይ በዘርፉ እየተስተዋለ ያለው ችግር እያስከተለ ያለውም ሆነ ወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን ፈተና የተገነዘበው መንግሥት፤ በተለይም ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ችግሩ እንደ ሀገር ካለው ግዝፈት አንጻር አሁን ላይ ስለ ውጤት ለመናገር የሚያስደፍር ነገር ባይኖርም፤ ተስፋ ሰጭ ጅምሮች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ችግሩ መኖሩን ተረድቶ ለመፍትሔው እራስን በቁርጠኛነት ዝግጁ ማድረግ በዋናነት ሊነሳ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።
የትምህርት ጥራትን አደጋ ውስጥ የከተተውን የተማሪዎች የኩረጃ ባህል ለመቀየር የተጀመረው አሰራር ፤ የመምህራንን ደረጃ ለማወቅ የተሄደበት መንገድ ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተወሰደ ያለው ርምጃ፤ የትምህርት ፖሊሲዎችን ለመከለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች፤ ከሁሉም በላይ ዜጎች ስለትምህርት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየተደረጉ ያሉ ሥራዎች ተጠቃሽ ነው።
እነዚህ ሥራዎች የአንድ ጊዜ ወይም ወቅት ሥራዎች ሳይሆኑ፤ ለውጤታማነታቸው በየጊዜው እየተገመገሙ፤ በተሻለ መንገድ ተግባራዊ የሚሆኑበት ወጥነት ያለው አሠራር የሚፈልጉ ናቸው። ለስኬታማነታቸው የአንድን ተቋም /የትምህርት ሚኒስቴርን ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ዜጋ የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቁ ናቸው።
በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች የበለጸገች ሀገር ተፈጥራ ለማየት ለነበራቸው መሻት፤ ለትምህርት የነበራቸው ትልቅ ዋጋ ትርጉም ያለው ፍሬ እንዲያፈራ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ከፍ ያለ ነው። ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ አሁን ያለውን ሀገራዊ መነቃቃት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊመለከተው ይገባል!
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016