የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ንግሥት እሌኒ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል:: ንግሥቲቷ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂርቆስ በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ:: የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት ጠይቃ፣ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች:: መስቀሉም ከወራት ቁፋሮ በኋላ ወጥቷል:: ከዚያን ወቅት ጀምሮ መስከረም 16 ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓትና መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል::
በንግሥት እሌኒ አማካይነት ከተቀበረበት የወጣው መስቀል ክፋይ በሰሜን ኢትዮጵያ በግሸን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ ሲሆን፣ በዓሉን ለማክበር ወደ አካባቢው የሚሄዱ በርካቶች ናቸው::
የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው እንደየማኅበረሰቡ ባህልና ወግም ይከበራል:: ከሌሎች ዓውደ ዓመቶች የመስቀል በዓል በተለየ ድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች የብዙ ጎብኚዎችን ትኩረትም ይስባል:: በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት የሰፈረውም ለዚሁ ነው::
ከእነዚህ በዓሉን በትልቅ ጉጉት ከሚጠብቁት እንዲሁም ለየት ባለ ባህላዊ አከባበር ከሚያከብሩት የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ደግሞ የጉራጌ የተለየ ነው:: መስቀል ሲነሳ የጉራጌ ብሔረሰብ ለበዓሉ የሚሰጠው ልዩ ቦታ ተያይዞ ሊወሳ ግድ ነው:: የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ስለ በዓሉ አከባበር ባዘጋጀው ጽሑፍ እንደገለጸው ‹‹የመስቀል በዓል የጉራጌ ብሔረሰብ የበዓላት ሁሉ አውራ ሆኖ ለዘመናት ሲያከብረው የነበረና የሚቀጥልም በዓል ነው››::
መስቀል በጉራጌ አንድ ቀን ክብረ በዓል ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ከደመራና መስቀል ቀናት በፊትና በኋላም በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች የሚከበረው በዓሉን ለየት ያለ ድባብ ይሰጠዋል::
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር የገጠመው ወይም የገጠማት ከሀገር ውጭ የሆነ ወይም በጠና የታመመ ካልሆነ በቀር የጉራጌ ተወላጅ ሆኖ በመስቀል ሀገር ቤት የማይገባ የለም:: ሁሉም ተወላጆች ወደቀዬአቸው በመሄድ በአንድነት የሚያከብሩት በዓልም ነው:: በዚህም ዓመት ሙሉ ያጠራቀሙትን ይዘው በመግባት በወላጆቻቸው ይመረቃሉ ይህ ምርቃት ደግሞ ሥራ ያቀናል ጉዞን ያሰምራልም ተብሎ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል::
የመስቀል በዓል አከባበር ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በተለያየ ሥነ ሥርዓቶች የሚቀጥል ሲሆን፣ ሴቶች ከበዓሉ ዝግጅት ጀምሮ በልዩ ሁኔታ የሚያከብሯቸው ዕለቶችም አሏቸው:: መስቀል በጉራጌ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ዝግጅቱም ሰፊ ነው:: የመስቀል በዓል ከተከበረበት ዕለት ጀምሮ ለሚመጣው ዓመት መስቀል መሰናዶ ይጀመራል:: ከትውልድ ቀዬአቸው ርቀው የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለመስቀል በዓል ቤተሰቦቻቸውን ለመቀላቀል ውሳኔ ላይ የሚደርሱትም ከወራት በፊት ነው:: ተወላጆቹ የአቅማቸውን ያህል ገንዘብ አጠራቅመው ወደ ትውልድ መንደራቸው ያቀናሉ::
ለመስቀል በዓል ዝግጅት ሲደረግ ሥራ በጾታና በዕድሜ ይከፋፈላል:: በዚህ መሠረት ልጆችና ወጣት ወንዶች ለደመራ የሚሆን እርጥብ እንጨት ከጫካ ለቅመው፣ ከደረቀ በኋላ ይፈልጣሉ:: በዕድሜ ከፍ ያሉት አባወራዎች ደግሞ ለበዓሉ የሚታረዱ ከብቶችን ሣር በመቀለብ ያደልባሉ::
በተለይም ሴቶች የቤት ምሰሶዎች የበዓል ማሳመሪያ ድምቀቶች ከመሆናቸው አንጻር በጉራጌ መስቀል በዓል ላይም ጫና ከፍ ብሎ የሚታየው በእነሱ ላይ ነው:: ሁሉም ሴቶች ማለት ይቻላል ለሚመጣው መስቀል በዓል የሚሆን ቅቤ ማጠራቀም የሚጀምሩት የመስቀል
በዓል እንደተጠናቀቀ ነው:: ይህ እንግዲህ የመጀመሪያው ዝግጅታቸው ሲሆን ቤት ማሳመሩና እቃዎችን ለበዓሉ ዝግጁ ማድረጉ የጎደሉትን ማሟላቱም የሴቶች ኃላፊነት ነው::
ሴቶች በዓሉ ሦስት ወራት ሲቀሩት መሰናዶውንም ይጧጡፉታል:: ቤት ቀለም ሲቀቡ፣ ለበዓሉ የሚሆን እንሰት ፍቆ ማዘጋጀትና ጅባ መሥራት በተለይም የቡሄ በዓል ከተከበረ በኋላ የመሰናዶውን ፍጥነት ይጨምራል::
የጉራጌ ሴቶች የመስቀል በዓል መከበር በሚጀምርበት መስከረም 12 ቀን ለምግብ ማቅረቢያ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ከግድግዳ ያወርዳሉ:: በዕለቱ የመመገቢያ ቁሳቁሶች እንዲሁም ቤት ይፀዳል:: በየቤቱ አዳዲስ ጅባዎች ይነጠፋሉ:: ቀጣዩ ቀን ወሬት ያሸና ወይም ወልቀነ ይባላል:: ሴቶች የጎመን ክትፎ የሚያዘጋጁበት ሲሆን፣ ከቆት የሚበላበት ዕለት በመባል ይታወቃል::
በጉራጌ ባህል መስከረም 14 ደንጌሳት ይባላል:: የጎመን ክትፎ በሸክላ ጣባ ለመላው ቤተሰብ የሚቀርብበት ዕለት ነው:: በዕለቱ የሚወጣውን ወጪ በሙሉ የሚሸፍኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው:: ሴቶች ዓመቱን በሙሉ ለመስቀል ባጠራቀሙት ገንዘብ ሙሉ ዝግጅቱን ሸፍነው ቤተሰባቸውን ያስተናግዳሉ:: በደንጌሳት ማታ በየቤቱ ደመራ ይለኮሳል:: ሥርዓቱ የባዮፕ ኧሳት ቀን ይባላል:: ደመራው ሲቃጠል ሴቶች እልልታ ያሰማሉ:: ለበዓሉ””በሰላም በመድረሳቸውም ፈጣሪን ያመሰግናሉ::
ወከመያ ወይም ጨርቆስ አልያም በሌላ አጠራሩ የእርድማይ የሚባለው መስከረም 15 ነው:: በዕለቱ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሁለትና ከዚያ በላይ የደለበ በሬ ያርዳል:: እርዱ ተጠናቆ የከብት ሥጋ ወደ ቤት እንደገባ ጥሬ ሥጋ በቅቤ ተነክሮ ይበላል:: ቡና በቅቤም ይጠጣል ይህንንም የሚያዘጋጁት ሴቶች ናቸው::
የአካባቢው ማኅበረሰብ በኅብረት ደመራ የሚያበራበት የባንዳ ኧሳት ወይም የጉርዝ እሳት የሚባለው መስከረም 16 ቀን ይከበራል:: ዕለቱ በየአድባሩ ደመራ የሚበራበትና ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበት ነው:: ትልቁን ደመራ የማብራት ሥነ ሥርዓት ሲጠናቀቅ በየአካባቢው መጠነኛ ደመራዎች ይበራሉ:: ደመራው ሥር ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይጨፈራል::
ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቆ ወደቤት ከተገባ በኋላ ሴቶች ያዘጋጁት ክትፎ በጣባ እየተደረገ ለቤተሰቡ ይቀርባል:: በነጋታው ንቅባር (የከሰል ማይ) የተባለ ሥርዓት አለ:: ሥርዓቱ በአንድ አካባቢ ያሉ ዕድርተኞች ደመራ የተቃጠለበት ቦታ ተሰባስበው ቃል የሚገባቡበት ነው:: በዕለቱ አዳዲስ የዕድር ዳኞች ይሾሙና ካለፈው ዓመት ዳኞች ጋር የኃላፊነት ርክክብ ይካሄዳል:: አዳዲስ የዕድር አባላት ምዝገባም ይኖራል::
መስከረም 18 የፊቃቆማይ ይባላል:: ሴቶች የተለያዩ የስፌት ቁሳቁሶች ለማዘጋጀት የሚውል ስንደዶ መልቀም የሚጀምሩበት ነው:: የአካባቢውን ባህላዊ ዜማ እያሰሙ ስንደዶ ይለቅማሉ:: ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 23 ያለው የጀወጀ ወይም አማች መጠየቂያ ጊዜ ነው::
በአማች መጠየቂያ ወቅት ሴቶች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ ለአባቶቻቸው ባርኔጣና ጭራ ይገዛሉ:: ባሎቻቸው ደግሞ ሙክት ይሸምታሉ:: ወቅቱ ልጆች በወላጆቻቸው እንዲሁም ባለትዳሮች በአማቾቻቸው የሚመረቁበትም ነው::
የመስቀል በዓል አከባበርን ከሚያጎሉ ሥርዓቶች መካከል የአዳብና ባህላዊ ጭፈራ ሥነ ሥርዓት ተጠቃሽ ነው:: አዳብና ከመስከረም 16 ቀን እስከ ጥቅምት በዓል ባሉት ቀናት ይከናወናል:: በመገበያያ ቦታዎችና ሌሎችም የጋራ መሰብሰቢያ ቦታዎች አዳበና ሲጨፈር ወንዶችና ሴቶች ሎሚ፣ ብርቱካንና ሸንኮራ አገዳ በመለዋወጥ ፍቅራቸውን ይገላለጻሉ በዛውም ይተጫጫሉ::
ወይዘሮ ሙሉ ሰይፈ የጉራጌ ብሔር ተወላጅ ናት:: ወይዘሮ ሙሉ በዓመት ውስጥ ያሉ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ በዓሎች ቢደመሩ የመስቀልን ያህል ልቧን አይሞሉላትም:: መስቀል ለእሷ ልዩና ከልጅነቷ ጀምሮ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው በዓል ነው::
ዘንድሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገር ቤት መግባት ባትችልም መስቀልን ግን በቤቷ ከልጆቿና ከባለቤቷ እንዲሁም አዲስ አበባ ካሉ ቤተሰቦቿ ጋር በጥሩ ሁኔታ ለማክበር ተዘጋጅታለች::
በዓል ምን ጊዜም ቢሆን ሴቶችን ያደክማል የምትለው ወይዘሮ ሙሉ ለመስቀል ጊዜም ተመሳሳይ ድካም ይኖራል በተለይም ሀገር ቤት ስገባ ቤተሰቡም ብዙ ስለሚሆን ሴቶች ሥራ ይበዛብናል፤ ነገር ግን በዓመት አንድ ጊዜ በናፍቆት ከመምጣቱ አንጻር ደግሞ ድካሙን ልብ አንለውም ትላለች::
በዓሉ ቀደም ብሎ የሚጀመር ከመሆኑ አንጻር በተለይም ሀገር ቤት ያሉ ሴቶች ለዝግጅቱ የሚሆን ቅቤ ያጠራቅማሉ፤ ቤት ያጸዳሉ ፤የመመገቢያ ጅባዎችን ይሰራሉ፤ ቆጮ ይፍቃሉ፤ በእለቱም ይጋግራሉ ከእርድ አንስሳ ውጭ ያለው አብዛኛው ወጪም በሴቶች የሚሸፈን በመሆኑ ዓመቱን ሙሉም ገንዘብ ማጠራቀም ይጠበቅባቸዋል:: ይህ ሁሉ ኃላፊነት ቢኖርም ግን እለቱን በፍጹም ደስታ ነው የምናከብረው በማለት ትገልጻለች::
እሷም ባህሏን በተለይም በሴትነቷ ታደርጋቸው የነበሩ የመስቀል በዓል ዝግጅቶችንም አንድ በአንድ ለሴት ልጆቿ ለማውረስ ከፍ ያለ ሥራንም እንደምትሰራና ልጆቿም የእሷ ፈለግ መከተላቸውን ትናገራለች::
ሌላዋ ያነጋገርናት ወይዘሮ ትዕግሥት አካሉ እንደምትለው የመስቀል በዓል በእኛ በጉራጌዎች መገለጫችን ነው በዚህም በጣም ደስተኞች ነን:: የበዓሉ ዝግጅትም የሚደረገው ዓመቱን ሙሉ ነው:: እኛም ከተማ ያለንም ሆንን በገጠር ያሉት ይዘጋጃሉ እኔም ተዘጋጅቼያለሁ፤ ወደገጠርም እሄዳለሁ ብላለች::
በገጠር ያሉ ሴቶች እለቱን አሳምሮ ለማሳለፍ ከከተማና ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ እንግዶችን በጥሩ ሁኔታ አስደስቶ ለማዋል ብዙ አድካሚ ዝግጅቶችን ያደርጋሉ:: ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእርድ ውጪ ያለው ወጪ የሚሸፈነው በሴቶች ስለሆነ ዓመቱን ሙሉ ከሚያገኟት መቆጠብ ቅቤ ማጠራቀም ይጠበቅባቸዋል ::
‹‹እኔም እናትና አባቴ ቤት በዓልን ለማክበር ስሄድ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ እሰራለሁ:: ከሴቶች መስቀል ጀምሮ ቤተሰቡ የሚመገበውን በማዘጋጀት የተበላበትን በማጽዳት ልጆች በመንከባከብ ለእንግዳ ቡና በማፍላት ብቻ አንድም እረፍት አይኖርም ነገር ግን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚመጣ ስለሆነ ሁኔታው በጣም አስደሳች ነው›› ትላለች::
የ15 ዓመት ሴት ልጇ ለመስቀል በዓል ከፍ ያለ ፍቅር እንዳላት በመግለጽ እሷ ሙያውን አያስተማረቻት ልጇም እየወደደችው ሀገር ቤትም ስትሄድ እየሰራች አያቶቿን እንድምታስደሰት ነው የነገረችኝ::
አዎ መስቀል በጉራጌ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነው እንደተባለውም በዓላት በሙሉ ለሴት ልጆች አድካሚና ፈታኝ ቢሆኑም ጥለውት የሚያልፉት ትዝታና ደስታ ግን ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ ሴቶቹም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከትውልድ ትውልድን እየተካ እዚህ ተደርሷል::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016