ሩሲያ ‘የጥቁር ባህር ስምምነትን’ ለማደስ የሚደረገው ጥረት የማይሳካ ነው አለች

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተመድ ‘የጥቁር ባህር የእህል ስምምነትን’ ለማደስ የሚያደርገው ጥረት የማይሳካ መሆኑን ተናገሩ።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ድጋፍ የሚሹት አሜሪካ እና አውሮፓ በተቀረው ዓለም ላይ ንቀት እያሳዩ ነው ያሉት ላቭሮቭ ሩሲያ ተመድ ስምምነቱን ለማደስ የሚያደርገውን ጥረት ባትቃወምም በቅርቡ ያቀረበው ምክረሃሳብ ግን ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።

ላቭሮቭ ይህን ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት በአካል በተገኙበት እና ምዕራባውያን አጋሮቻቸው ለኪቭ ድጋፍ በሻቱበት የኒው ዮርኩ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው። ላቭሮቭ ከጉባዔው ጎንለጎን ከ30 ሀገራት በላይ ከመጡ ዲፕሎማቶች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ተመድ ሩሲያ በፈረንጆቹ 2022 በዩክሬን ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች በኋላ አንዳቸው ሌላቸውን ለማሸነፍ በሚያደርጉት ጥረት የምግብ እጥረት ቀውስ እና አዲስ የዲፕሎማቲክ ፍጥጫ ተፈጥሯል የሚል ወቀሳ አቅርቧል።

ላቭሮቭ 193 አባል ሀገራት ባሉት የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በአብዛኛው የዓለም ማኅበረሰብ እና ለማሸነፍ የቅኝ ግዛት ዘዴን በሚጠቀሙ ጥቂቶች መካከል ትግል እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በፈረንጆቹ ሐምሌ 2022፣ በቱርክ እና በተመድ አማካኝነት የተደረሰው እና ዩክሬን እህሏን በጥቁር ባህር በኩል ወደ ውጭ እንድትልክ ያስቻላት «የጥቁር ባህር የእህል ስምምነት» ሩሲያ ከስምምነቱ በመውጣቷ ምክንያት ፈርሷል።

ሩሲያ ከስምምነቱ የወጣችው በስምምነቱ መሠረት የምትፈልገው ተፈጻሚ አለመሆኑን በመግለጽ ነበር። ላቭሮቭ ለተመድ ዋና ጸሐፊ በጻፉት ደብዳቤ ተመድ ያቀረበው ምክረሃሳብ ሊተገበር የማይችል እና የማይሳካ መሆኑን መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You