ውሃ ለሰው ልጅ መሠረታዊ የሕይወቱ አካል መሆኑን ተከትሎ፤ መንግሥት በቻለው አቅም ተደራሽ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት በህግ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ውሃ በተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ እንዲቀርብ እየተደረገ ቢሆንም፤ የአገልግሎት መቋራረጥን ምክንያት በማድረግ ከነዋሪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡
በተለይ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ውሃ በቧንቧ መጠቀም ብርቅ በመሆኑ፤ በመንግሥት ድጎማ በተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ እየቀረበ ያለው ውሃ በተለያየ መንገድ በመኪና እና በጋሪ ተጉዞ ነዋሪው ጋር ከተመን በላይ እየተሸጠ ገበያው ደርቷል የሚል ጥቆማ ደርሶናል፡፡
ጥቆማውን መሠረት በማድረግ በከተማዋ ውሃ የማስተዳደር፣ ተደራሽ የማድረግ፣ ለሚሰጠው አገልግሎትም ክፍያ የመሰብሰብ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጉዳዩን እንዴት ያየዋል? ስንል ከተገልጋይ የሰማነውንና የታዘብነውን በባለሥልጣኑ የውሃ አቅርቦትና ሥርጭት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአቶ ፍቃዱ ዘለቀ ጥያቄ አቅርበን፤ እርሳቸውም ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ የአዲስ አበባ ከተማ የውሃ አቅርቦት ታሪክ ምን ይመስላል ከሚለው እንነሳ?
አቶ ፍቃዱ፡- ከታሪክ እንደምንረዳው፤ የውሃ ስርጭቱ በቧንቧ ቤት ለቤት ውሃ ማቅረብ መነሻ ያደረገ አልነበረም። መጀመሪያ ውሃ መቅረብ የጀመረው ከምንጭ ነው። ምንጩም ከእንጦጦ የተገኘ ነበር። የውሃ አቅርቦት ተደራሽነቱም ውስን ነበር። የምንጭ ውሃ ተጠቃሚዎችም መሳፍንት ተብለው የሚጠሩ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ነበሩ።
በመቀጠል በነፃ ቦኖ በሚባለው የውሃ አገልግሎት መስጫ ቤተ መንግሥት፣ ስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አካባቢዎች ብቻ ተደራሽ ሲደረግ ነበር። አብዛኛው ማህበረሰብ የሚጠቀመው ከምንጭና ከወንዝ ነው። ከተማዋም አሁን በምትገኝበት ደረጃ የሰፋች አልነበረች። በመሆኑም የተጠቃሚውን ቁጥርና የሚቀርበውን የውሃ መጠን በመረጃ አስደግፎ ለማቅረብ ያስቸግራል። በወቅቱ የውሃ አቅርቦት ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ የሚነሳም አልነበረም። በጊዜው ወንዞችም ሆኑ ምንጮች ጥሩ ነበሩ። ይህ ከአንድ መቶ አመት በፊት የነበረ ታሪክ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አዲስ አበባ ከተማ የምንጭ ውሃ ከመጠቀም ከወጣች በኋላ እንዴት ወደ ዘመናዊ የውሃ ስርጭት ቻለች?
አቶ ፍቃዱ፦ አዲስ አበባ ወደ ዘመናዊ የውሃ ስርጭት የገባችው በሁለት አይነት መልኩ ነው። ከመሬት አካል በላይ ከሚሰበሰብ ወይንም ገፀምድር፣ እንዲሁም ከመሬት ውስጥ በቁፋሮ ከሚገኝ ወይንም ከከርሰምድር ነው። ባለስልጣኑ ከእነዚህ ሁለት ምንጮች ውሃ አምርቶ ለተጠቃሚው እያሰራጨ የሚገኘው።
በግድብ ደረጃም በአዲስ አበባ ከተማ በስተምእራብ በኩል በ1948 ዓ.ም አካባቢ የተገነባው የገፈርሳ ግድብ ሲሆን፤ የዚህ ግድብ ውሃ ስርጭት የተጀመረው በቦኖ አገልግሎት ነው።አገልግሎቱንም ሲሰጥ የነበረው በማዘጋጃ ቤት ውስጥ በተቋቋመ ውሃ ቢሮ ወይንም ውሃ ክፍል አማካኝነት ነበር። በመቀጠል በ1963 አካባቢ መጀመሪያ ደግሞ የለገዳዲ ግድብ ሥራ ጀመረ።
በዚሁ መሠረት ከለገዳዲ ግድብ በቀን 50ሺ ሜትሪክ ኪዩብ፣ ከገፈርሳ ግድብ ደግሞ በቀን 23ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ እየተመረተ ለከተማዋ ነዋሪ ሲቀርብ የነበር። ባለሥልጣን መሥሪያቤቱም በአዋጅ ተቋቁሞ የውሃ ታሪፍ እየሰበሰበ ሥልጣን ያለው ተቋም ሆኖ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደግሞ ሶስተኛው የገርቢ ግድብ ለአገልግሎት በቃ። ከምንጭ ወደ ግድብ ተሸጋግሮ የውሃ አቅርቦት አገልግሎት እየሰፋ የመጣው በዚህ መልኩ ነው። አሁን ላይ ለአዲስ አበባ ከተማ የውሃ አገልግሎት እየተዳረሰ ያለው ከሶስቱ ግድቦች ነው።
የውሃ ልማቱን ሥራ በተመለከተም፤ የገፀምድር ውሃ የሚገኘው በክረምት ወቅት የሚዘንብ ዝናብ በግድብ ውስጥ በማጠራቀም ወይም በመሰብሰብ ነው፡ ፡የገፀምድር ውሃ ጭቃ የያዘ ስለሚሆን በግድቡ ማጣሪያ ጣቢያ ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል። በዚሁ መሠረትም የተሰበሰበውን ወይም የተጠራቀመውን የዝናብ ውሃ ከአዲስ አበባ ከተማ በስተምእራብ በኩል በሚገኘው ገፈርሳና በለገዳዲ ግድቦች በሚገኙ የማጣሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የማጣራት ሂደት ይከናወናል።
ድሬ ግድብ የራሱ የማጣሪያ ጣቢያ ስለሌለው ልክ እንደለገዳዲ ግድብ ጥሬ ውሃ ይይዝና በገፈርሳና በለገዳዲ ግድቦች በሚገኝ የውሃ ማጣሪያዎች ውስጥ እንዲጣራ ይደረጋል፡ ፡ከገፀምድር የተገኘው ውሃ በዚህ መልኩ ከተጣራ በኃላ ለህብረተሰቡ ይሰራጫል።
ሌላው የከርሰምደር ውሃ ልማት ሥራ ደግሞ ጉድጓድ በመቆፈር ውሃ ወደ ሥርጭት የሚገባበት አሰራር ነው። ከ2000 ዓ.ም በፊት በየአካባቢው አልፎ አልፎ ጉድጓድ በመቆፈር ውሃ የሚቀርብበት ሁኔታ ነበር። የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦት እየተጠናከረ የመጣው ከ2001 ዓ.ም በኋላ ነው። በዚሁ መሰረትም ለውሃ መገኛ ይሆናሉ የተባሉ መሬቶችን በጥናት በመለየት የሚከናወን ሲሆን፤ አሁን በደረስንበት ደረጃም እስከ አምስት መቶ ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር ውሃ ማግኘት ተችሏል። በዚህ ወቅት 238 ጉድጓዶች በሥራ ላይ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ የሚወጣው ውሃ ተሰብስቦ ወደ ስርጭት ማእከል (ኔትወርክ) ውስጥ እየገባ ለህብረተሰቡ እንዲቀርብ ይደረጋል።
በአጠቃላይ ከርሰ ምድር ማለት ለዘመናት በመሬት ውስጥ የተከማቸ ውሃን ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማድረግ ነው። ከከረሰ ምድር ውስጥ የሚወጣ ውሃ ብዙ ማጣራት አይፈልግም። ንጹህ ውሃ ነው። ውሃው ወደ ስርጭት ከመወሰዱ በፊትም አይረን፣ ፍሎራይድ፣ ማንጋኒዝ የተባሉ ንጥረነገሮች በውስጡ መኖሩን እንዲሁም የሙቀቱና የቅዝቃዜው መጠን ይለካል። የዓለም ምግብና ጤና ድርጅት (ደብሊው ኤች ኦ) ካስቀመጠው መስፈርት በታች መሆንና አለመሆኑ ተረጋግጦ በክሎሪን ታክሞ ወደ ህብረተሰቡ እንዲሰራጭ ይደረጋል።
የገፀምድርና ከርሰምድር ውሃ አስፈላጊነታቸው ጥያቄ ውስጥ አይገባም። እንደውሃ መገኛ አይነቱ ሁለቱም ተቀናጅተው ጥቅም ላይ ይውላል። ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንደየሀገሩ ሀብት ተጨባጭ ሁኔታ አንዱን አይነት ወይም ሁለቱንም በማጣጣም ነው።የዓለምአቀፍ ተሞክሮም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው።
በሀገራችንም በአሁኑ ጊዜ አቃቂ ክፍል አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ ቱሉጉዶ እና ኮዬፈጬ በሚል በየደረጃው በሥፋት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ነን። የከተማዋን የውሃ ፍላጎት ለማሟላትና በአቅርቦት መካከል ያለውንም ክፍተት ለመሙላት ጥረት ማድረግ የተቻለውም እነዚህን ሥራዎች በመሥራት ነው።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአሁኑ ጊዜ በድምሩ ከገፀምድርና ከከርሰምድር በቀን ወደ 792ሺ ሜትሪክ ኪዩቢክ ውሃ አምርቶ የማቅረብ አቅም ተፈጥሯል። ተቋሙ ይህን አቅም ቢፈጥርም፣ ከከተማዋ ነዋሪ የውሃ አቅርቦት ፍላጎት ጋር በንጽጽር ሲቀርብ ልዩነቱ የሰፋ ነው። በአሁኑ ጊዜም ለከተማው ነዋሪ ወደ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩቢክ የውሃ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ይገመታል።
አዲስዘመን፡- አዲስ አበባ ከተማ ለነዋሪዎችዋ ልታቀርብ የምትችለውን የውሃ መጠን ለማወቅ በጥናት የመለየት ሥራ ተሰርቷል?
አቶ ፍቃዱ፡- እንደሀገር ወይም አዲስ አበባ ከተማ ከከረሰምድርና ከገፀምድር ይሄን ያህል ሜትሪክ ኪዩብ የውሃ መጠን ይገኛል፤ ይህን ያህል ውሃ የመሰብሰብ አቅም አለ በሚል በዝርዝር የተከናወነ የጥናት ሥራ የለም። ነገር ግን በየጊዜው እየተጠና ፕሮጀክት ተቀርፆ እየለማ ነው። ወደ ምርት ተቀይሮ ውሃ ለተጠቃሚው እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑ አያጠያይቅም። እኛ ጥናት እየሰራን ያለነውም ለምንፈልገው ወይም ለምናስበው ፕሮጀክት ብቻ ነው። ባጠናነው አካባቢም የምናገኘውን የውሃ መጠን እየወሰንን እንሔዳለን።
ለምሳሌ ለገዳዲ ግድብ ከመሰራቱ በፊት፣ ከግድቡ ሊገኝ የሚችለው የውሃ መጠን ይታወቃል። ውሃም የሚመረተው ግድቡ በተሰራበት ዲዛይን መጠን ልክ ነው።የከርሰምድር ውሃ መገኛዎችን በተመለከተም ወደ ትግበራ የሚገባው እንዲሁ ጥናት ተካሂዶ ነው። ለምሳሌ የአቃቂ ከርሰምድር የመጀመሪያ የጥናት ሥራ በቀን እስከ 223 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማምረት የሚያስችል የከርሰ ምድር ውሃ መጠን መኖሩን ነበር።ለህብረተሰቡ ውሃ የምናሰራጨው በዚህ መልኩ በየፕሮጀክቱ እያረጋገጥን በማልማት ነው ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በሥራ ላይ ካሉ የውሃ ማሰራጫ ግድቦች ተጨማሪ አዳዲስ ሥራዎች የሉም ማለት ነው? አያይዘው የሚገልጹልን ግድቦች በደለል የመሞላት ችግር ያጋጥማቸዋል። በዚህ ረገድ ያለበት ደረጃ እና ተጽእኖ ምን ይመስላል?
አቶ ፍቃዱ፡- በደለል ከመሞላት ጋር የተያያዘው፤ በገፀምድር ውሃ መገኛ ላይ ከሚያጋጥም ችግር ወይም ተግዳሮት መካከል አንዱ ይህ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ካልተሰራ ገድቦች በደልል የመሞላት ሁኔታ ከፍተኛ ነው። ወደ ግድቡ የሚገቡ ወንዞች ወይንም ወደ ግድቡ የሚገባው ጎርፍ የሚሰበሰብበት ምድረ አካል ይታወቃል። እነዚህን አካባቢዎች በአረንጓዴ ልማት መንከባከብ ካልተቻለ በጎርፍ መልክ ወደየግድቦቹ የሚገባው ውሃ አፈር ብቻ ሳይሆን ደረቅ ቆሻሻን ጨምሮ የተለያዩ ባእድ የሆኑ ነገሮችን ሰብስቦ ወደ ግድቡ ይገባል። እነዚህ ለግድቦቹ ውሃ የመያዝ መጠን መቀነስ አንዱና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
አሁን ካለው የከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።የገፈርሳ ግድብ ከዚህ ቀደም የአርሶአደሮች መኖሪያ፣ ከግብርና ሥራ ውጭ የከተማ አገልግሎት ያልነበረበት አካባቢ ነበር። አካባቢው ለግድብ ሥራም ሲመረጥ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ነበር። ለገዳዲና ድሬ ግድቦችም አካባቢዎቹ ተመርጠው ግንባታው እንዲከናወን የተደረገው እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ነው። አሁን ላይ ግን አካባቢዎቹ ወደ ከተማ መኖሪያነት በመለወጣቸውና አረንጓዴ ስፍራ መሆኑ በመቅረቱ ለግድቦቹ በደለል መሞላት ስጋት ሆነዋል።
በተለይም ወደ ገፈርሳ ግድብ ከሁለት አቅጣጫዎች የሚገቡ ወንዞች ወይም ተፋሰሶች አሉ። ከሁለቱ በአንደኛው ቡራዩ በሚባለው አካባቢ ተፋሰስ ላይ ሰፊ ቁጥር ያለው ህብረተሰብ በመስፈሩ ወደ ግድቡ የማያስፈልጉ ነገሮች የመግባታቸው እድል በመስፋቱ ስጋቱን ከፍ አድርጎታል።
ተቋሙ በተቻለ መጠን በግድቡ ዙሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በመሥራት ስጋቱን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። የአካባቢው ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲያከናውኑ፣ ህብረተሰቡንም በማሳተፍ እንዲሁም ከአካባቢ አስተዳደሮች ጋር በመናበብ ሥራ እየተሰራ ነው። ድሬ ግድብ ላይም በተመሳሳይ ባለሥልጣኑ ፕሮጀክት ቀርፆ ከኔዘርላንድ መንግሥት ጋር በመተባበር የተፋሰስ ጥበቃ ሥራ እየሰራ ይገኛል። እንዲህ ያለውን የጥበቃ ሥራ በማስፈት የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት እቅዱ ቢኖርም፤ የከተማ መስፋፋቱ እስካለ ድረስ ግን ፈተናውን መቋቋም አዳጋች ይሆናል።
ለግድቦቹ ተፋሰስ በሆኑ ስፍራዎች በስፋት የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በመሥራት ወደ ግድቡ ደለል እንዳይገባ መከላከል፤ በተለይም ግድቡ ጠርዝ ድረስ የእርሻ ሥራ እንዳይከናወን፣ መኖሪያ ቤቶችና ኢንዱስትሪዎች እንዳይስፋፉ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ነው።
አዳዲስ ግንባታዎችን በተመለከተ፤ ባለስልጣኑ በቀን 792ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም ፈጥሯል። ይህን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው በየአመቱ ሥራዎች እየተሰሩ በመምጣታቸው ነው ። ከከርሰ ምድሩም ሆነ ከገፀምድሩ ውሃ የማልማት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም ሱሉልታ አካባቢ ገርቢ ግድብን ለመሥራትም የጥናት፣ ወሰን የማስከበር፣ ቴክኒካል ሥራዎች፣ ኮንትራክተር የመምረጥና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቋል። የግድቡ ግንባታ የሚከናወነው ከቻይና መንግሥት በሚገኝ የገንዘብ ብድር ነው። ብድሩ እንደተለቀቀም ወደ ሥራ ይገባል።
ይህ ፕሮጀክት የቆየ ነው። በወቅቱ የተያዘው የሶስት አመት ፕሮጀክት ተብሎ ነበር።የግድብና የማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ ሥራዎች እንዲሁም ከማጣሪያ ጣቢያው ወደ ሰሜን አዲስ አበባ ክፍል ኔት ውርክ (መስመር) ዝርጋታንም ያካተተ ነው። ሌሎችም ተጨማሪ ሥራዎች አሉት። በወቅቱም ለሥራው የተቀመጠው የገንዘብ መጠን ወደ 95 ሚሊየን ዶላር አካባቢ ነው። ከግድቡ ስፍራ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚመጣው ውሃ በበላይ ዘለቀ አድርጎ ድል በር አካባቢ ላይ የመጀመሪያውን ማጠራቀሚያ በማለፍ ሽሮ ሜዳን ቀጨኔ፣ጉለሌ አካባቢን በከፊል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በዋናነት በስተሰሜን ያለውን በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ ያለውን የውሃ አገልግሎት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው።
ነገር ግን ገንዘቡ ባለመለቀቁ ወደ ሥራ አልተገባም። ገንዘቡ ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ድርድር የሚፈታ ጉዳይ ነው። ገንዘቡ ቢለቀቅም ለውጦች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። ገንዘቡ ከተገኘ ግን ከሁለት አመት ባልበለጠ ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል። የፕሮጀክት ሥራውን ከዳር ለማድረስ ከሚደረጉ ጥረቶች ጎን ለጎን ባለሥልጣኑ መሥራት የሚጠበቅበትን ሥራዎች አጠናክሮ በመቀጠል የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል።
እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን ያህል ነው? ከተባለ ውሃ አቅርቦት ላይ የተሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ ነው። ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ለ15 አመታት ሲሰራ የነበረው የከርሰምድር ውሃ አገልግሎት አቅርቦት ላይ ነበር።
ከዚህ አንጻር እንዴት እየተሰራ እንደሆነ ለማስረዳት ከ2011ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ አመታት ተጨማሪ ውሃ ወደ ከተማው እንዲገባ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል።2011 ዓ.ም ኮዬፈጬ ከሚባል የከርሰምድር ውሃ መገኛ፣ 44ሺ ሜትሪክ ኪዩቢክ፣ በ2012 ዓ.ም ደግሞ በከተማዋ ከተለዩ ከፍተኛ የውሃ አገልግሎት አቅርቦት ችግር ባለባቸው ጉድጓድ በመቆፈር 10ሺ ሜትሪክ ኪዩቢክ ውሃ ወደከተማዋ እንዲገባ ተደርጓል። እንዲሁም በ2013ዓም ከቱሉ ጉዶ የከርሰምድር ውሃ መገኛ ፕሮጀክት 68ሺ ሜትሪክ ኪዩብ፣ በተጨማሪም በ2014ዓም ከለገዳዲ ክፍል ሁለት ፕሮጀክት እንዲሁ 86ሺ ሜትር ኪዩብ ከከርሰምድር ውሃ በማውጣት አቅም ተፈጥሯል።
በ2015 ዓ.ም ከፍተኛ የውሃ አገልግሎት አቅርቦት ችግር ያለባቸው በተለይም የጋራ መኖሪያቤቶች ባሉባቸው ፉሪ፣ ሃና፣ በረከት፣ ጀሞ ተብለው በሚጠሩና በሌሎችም ቦታዎች አካባቢውን ያማከለ ጉድጓድ በመቆፈር ወደ 68ሺ ሜትሪክ ኪዩቢክ ውሃ በማውጣት አቅም የመፍጠር ጥረት ተደርጓል። በድምሩ ከ2011 እስከ 2015ዓም ባሉት አመታት ከ275 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ ተጨማሪ ውሃ ወደ ከተማዋ እንዲገባ ተደርጓል።
በዚህ መልኩ በየአመቱ ሥራ እየተሰራ ተጨማሪ ውሃ ወደ ከተማዋ እንዲገባ ቢደረግም የከተማው የውሃ ፍላጎት ሊጣጣም አልቻለም። ለመኖሪያም ሆነ ለተለያየ አገልግሎት እየተከናወነ ያለው ግንባታ ወደ ላይ ወይም ፎቅ መሆኑ በውሃ አቅርቦትና በፍላጎት መካከል ክፍተት እንዲፈጠር የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል። የመሬት አቀማመጡም በራሱ ተግዳሮት ፈጥሯል። ለውሃ መገኛ ቅርብ የሆኑና በአቀማመጣቸውም ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ብቻ ውሃ የሚያገኙበት፣ ምቹ ባለመሆናቸው፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆስፒታሎችና ትላልቅ የሚባሉ ፕሮጀክቶች በስፋት በአካባቢው በመኖራቸው ውሃ የማያገኙበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።
እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት እንደውሃ መገኛ ሁኔታ የፈረቃ ሥርዓት በመዘርጋት ሁሉም በተራ አገልግሎቱን እንዲያገኝ እየተደረገ ነው። ህብረተሰቡም በሥርዓቱ ውስጥ ገብቶ በአገልግለቱ ተጠቃሚ የመሆን ዝግጁነቱን አሳይቷል። አሁን ላይ ከህበረተሰቡ እየተነሳ ያለው ከአካባቢ አካባቢ ልዩነት ለምን ተፈጠረ የሚል በፈረቃ አገልግሎት ፍትሐዊነት ላይ ያተኮረ ቅሬታ ነው።
እዚህ ላይ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ለከተማው የሚሰራጨው ውሃ ሁሉም ከአንድ ቋት ውስጥ አይደለም። ውሃ ወደ ተለያየ አካባቢ ለማሰራጨት ጥረት ሲደረግ በተለያየ የአሰራር ዘዴ ወይም ሥርዓት ነው። ሌላው ፕሮጀክቶች ሲነደፉ ተልእኮ ወይም ዓላማ አላቸው። ለምሳሌ ‹‹የአቃቂ ክፍል ሶስት ለ›› የሚባለው በቀን 70ሺ ሜትር ኪዩብ እንዲሰጥ ዲዛይን ተደርጎ የተሰራ ፕሮጀክት ዓላማውም ፕሮጀክቱ የተነደፈውም አቃቂ ገላን አካባቢ ከተቆፈሩ ጉጓዶች፣ በምእራብ በኩል ሄዶ፣ ዓለምባንክ ቤተል አካባቢ ላለ ህብረተሰብ፣ ሰበታ በከፊል ይዞ እስከ ጦር ኃይሎች ድረስ ውሃ ለማቅረብ ነው።
የለገዳዲ ግድብ ደግሞ ማዕከል የተደረገው ምሥራቅ አዲስ አበባ ከተማን፣ሰሜን ደግሞ በከፊል ውሃ እንዲያሰራጭ ነው። ሁሉም የየራሳቸውን ተልኦኮ ይዘው ስርጭቱን እንዲያከናውኑ በመደረጉ አይገናኙም። የውሃ ስርጭት ፈረቃው ውሃ የሚገኝበትን መሠረት ያደረገ ነው። በህብረተሰቡ ዘንድ ፍትሐዊ ያልሆነ ስርጭት ያለ እንዲመስል ያደረገው አሰራሩ ላይ ያለውን ሁኔታ ካለመረዳት ነው። አሁን ባለው አሰራር ፈረቃቸው ተጠብቆላቸው ውሃ እያገኙ ያሉ አካባቢዎች ለምሳሌ ከለገዳዲ ግድብ ውሃ የሚያገኙ ክፍለ ከተሞች የካ በከፊል፣ ቦሌ፣ አራዳ፣ ጉለሌ በከፊል፣ ቂርቆስ በከፊል ናቸው። ለገዳዲ ግድብ የኃይል አቅርቦት አጠቃቀሙ አነስተኛ በመሆኑ፤ በዚህ በኩል እንደክፍተት የሚነሳ ነገር አይኖርም። በቀን እስከ 180ሺ ኪዩቢክ የሚያመርተውን ውሃ 24 ሰዓት ያሰራጫል። በእነዚህ አካባቢ የመስመር መሰበርና የተለያየ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር ፈረቃቸው እንደተጠበቀ ነው።
ሌላው ለገዳዲ ክፍል ሶስት ለ የሚባለው ሲሆን፤ ይሄም በዓለም ባንክ በኩል አድርጎ፣ጦርኃይሎች፣ ሳርቤት፣ ንፋስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ በከፊል ኮልፌቀራኒዮ፣ ቂርቆስና ልደታ አካባቢዎችን ይሸፍናል። በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የውሃ ስርጭት ስምንመለከት ደግሞ አቃቂ ክፍል ሶስት ለ አካባቢ 24 ጉድጓዶች ተቆፍሮ፤ 24 የተለያየ ቦታ ማሰራጫ (ትራንስፎርመር) ተገጥሟል። ጤናማ የሆነ የውሃ ስርጭት እንዲኖር 24ቱም የከርሰምድር ውሃ መገኛዎች ላይ ኤሌክትሪክ መቋረጥ አይኖርበትም። ኤሌክትሪክ ከተቋረጠ አካባቢዎቹ ውሃ የማግኘት እድላቸው የጠበበ ይሆናል።
የከርሰ ምድር ውሃ ከተለያየ ቦታ ተሰብስቦ የሚሰራጭ በመሆኑ፤ በኢኮኖሚውም ቢሆን አዋጭ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ 24ቱም ጉድጓዶች ጀነሬተር እንዲኖራቸው አልተደረገም። የጀነሬተር አገልግሎት የሚያገኙ አራት የውሃ መግፊያዎች ቢኖሩም የጀነሬተሩ የመስራት አቅም ስምንት ሰዓት ብቻ ነው። የመግፋት አቅሙም ከ30 በመቶ በላይ አይደለም። የውሃ አቅርቦቱ በእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑ ፈረቃውን ማስጠበቅ አልተቻለም።
አዲስዘመን፡- የውሃ መሰረተ ልማት ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ እንደሆነ ይታወቃል።ባለሥልጣኑ ያለው አቅም እንዴት ይገለጻል?
አቶ ፍቃዱ፡– ባለሥልጣኑ ለሰጠው አገልግሎት ከተጠቃሚው የሚሰበስበውን ገንዘብ የሚያውለው ለአነስተኛ ፕሮጀክቶች ሥራ ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው የሚያውለው ለጥገና እና ለሌሎች ወጭዎች ነው። የልማት ሥራ የሚሰራው ከተማ አስተዳደሩ ከሚሰበስበው ገቢ ውስጥ በሚመድበው ነው። ውሃና ሳንቴሽን መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ክፍል ተቋቁሟል። ይሄ ክፍል ተልእኮውን የሚወጣው በየአመቱ ከከተማ አስተዳደሩ በሚመደብለት ገንዘብ ነው።
በተጨማሪም እንደ ዓለም ባንክ ያሉ በዘርፉ ላይ ድጋፍ ከሚያደርጉ ዓለምአቀፍ ተቋማት በሚገኝ ብድር በተመሳሳይ የልማት ሥራ ይከናወናል። የውሃ አቅርቦትን ለመጨመርና ክፍተትን ለመሙላት በጀት የሚገኘው በእነዚህ መንገዶች ነው።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከቧንቧ ውሃ ቀጥታ ከማግኘት ይልቅ በጀሪካን በግዥ የሚጠቀመው ነዋሪ እየበዛ ነው። ባለሥልጠኑ ይሄን እንዴት ያየዋል?
አቶ ፍቃዱ፡- በከተማዋ አሁንም በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ክፍተት መኖሩ ግልጽ ነው። በዚህ ወቅት ከውሃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። ከአየር መዛባት እና ከኢኮኖሚ አቅም ጋር ይያያዛል። ከተማው እያደገ ሲሄድ፤ ያንን የሚመጥን ሥራ እየሰሩ መሄድ ያስፈልጋል። እኛም እየሰራን ያለነው በዚህ መንገድ ነው።
ውሃ በጀሪካን መግዛት የሚፈጠረው በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ነው። አንዱ በሚያጋጠሙ በተለያዩ ምክንያቶች በየቀኑ ቀርቶ ውሃ በፈረቃ ለማድረስ እንኳን የተቀመጠውን አሰራር መተግበር ባለመቻሉ ነው። ሌላው ለልማቱ ሥራ የሚያስፈልጉ ግብአቶች በውጭ ምንዛሪ በግዥ የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ችግር ነው። ያም ሆኖ ግን አሁን ያጋጠሙትን ችግሮች እንደተቋም የሚፈታና የምንሻገረው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ሰውም፣ ህንጻም፣ አትክልትም የሚጠጡት በተመሳሳይ የታከመ ውሃን ነው። ይሄ የውሃ ብክነትን አያስከትልም?
አቶ ፍቃዱ፡- ትክክል ነው፤ ችግሩ አለ። ሆኖም ግን አሁን ላይ ለይቶ ለመጠቀም የሚያበረታታ ቁርጠኝነት እየታየ ነው። ከመጠጥ ውጭ ለሆኑ አገልግሎቶች የሚውል ውሃ አጣርቶ በማቅረብ ረገድ፤ አሁን ላይ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች የተሻለ አቅም ፈጥረዋል። ተጣርቶ የሚወጣው ውሃም በቦኖ እንዲሰራጭ በማድረግ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እየሆነ ነው። በተለይ በከተማዋ ውስጥ እየተከናወኑ ላሉ የአረንጓዴ ልማቶች በስፋት እየዋለ ይገኛል። ውሃ መልሶ የማልማት ክፍል በማቋቋም ባለሙያዎች ተሟልተው በእቅድ እየተሰራ ነው።
የሚጠጣ ውሃ ሽፋን ወይም አቅርቦት የሚፈለገው ደረጃ ማድረስ ሳይቻል፤ የማይጠጣ ውሃን በኔትወርክ ደረጃ ለመሥራት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። አሁን ላይ በሁለተኛ የውሃ አማራጭ ላይ እየተሰራ ያለው በሚፈለገው የውሃ ደረጃ ላይ ያሉትን በመለየት ለእጥበት፣ ለአትክልትና ለተለያየ አገልግሎት እንዲውሉ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመዲናዋ የመኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ግዙፍ ግንባታ የሚያከናውኑ የውሃ አማራጮችን በራሳቸው እንዲያመቻቹ እየተደረገ ስለመሆኑ ይነገራል።ጉዳዩ ስለሚመራበት ሁኔታ ቢያብራሩልን?
አቶ ፍቃዱ፡- የከተማዋን የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ለመሙላት ሁለተኛ የውሃ አማራጭ ከመጠቀም ጎን ለጎን ባለሥልጣኑ ላለፉት አምስት አመታት ሲሰራባቸው የቆየው ሌላው መንገድ ከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚዎች፣ የመጠጥ ውሃን ለመጠጥ ብቻ ሳይሆን ለሌም የሚያውሉ አካላት ጉድጓድ በመቆፈር በራሳቸው ውሃ አመንጭተው እንዲጠቀሙ የማበረታት ሥራ ሲሠራ ነበር። ከነዚህ አካላት ጋርም ቀድሞ በመመካከር እንዴት መደጋገፍ ይቻላል? በሚለው ላይ ወደ ትግበራ የገባው መክሮ ነው።
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ከርሰ ምድር ለመቆፈር ፍቃድ የሚሰጠው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ፍቃድ የሚሰጠው ባለሥልጣኑ ነው። ሶስተኛ ወገንም ሆነ ባለሥልጣኑ ለሚያለማው ውሃ ፍቃድ ከባለሥልጣኑ ማግኘት ይኖርበታል።የማስተዳደር ስልጣንም በአዋጅ ተሰጥቶታል። በዚሁ መሠረት ከ2011 ዓ.ም በኋላ በስፋት ሥራዎች ተከናውነዋል። የህብረተሰቡም ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል። ባለስልጣኑ ፍቃድ መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ባሉት አመታት ለ388 ለተለያዩ ድርጅቶች ጉድጓድ የመቆፈር ፍቃድ ሰጥቷል። ፍቃድ ከወሰዱት መካከል ደግሞ 163 ደንበኞች የአጠቃቀም ፍቃድ ወስደዋል።
በፍቃድ አሰጣጥ ሂደትም፤ በአካባቢው ላይ በአምስት መቶ ሜትር ክልል ውስጥ ቀድሞ የተቆፈረ ጉድጓድ አለመኖሩና የሚቆፈረው ጉድጓድ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጥቅም የማይጎዳና ችግር የማያስከትል መሆኑ ይታያል። እንዲሁም የህብረተሰብ ጥቅም የሚቀድም በመሆኑ እንደሆስፒታል ያሉ ለማህበረሰቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅድሚያ እንዲያገኙ የእነርሱን ፍላጎት ማረጋገጥ፤ ባለሥልጣኑም በአካባቢው ላይ ጉድጓድ ለመቆፈር የያዘው እቅድ አለመኖሩ ቀድሞ ይረጋገጣል።
አዲስ ዘመን፡-የሰው የአኗኗር ዘይቤ መቀየሩ በውሃ አቅርቦቱ ላይ ጫና አላሳደረም ?
አቶ ፍቃዱ፡-የሰው የአኗኗር ዘይቤው በመቀየሩ የውሃ ፍላጎትም ጨምሯል። የውሃ ልማት ሥራ ፈታኝ ነው የሚባለው ለዚህም ነው። ባለፈው አመት
በስድስት ወር ውስጥ በተሰበሰበ መረጃ በቀን እስከ 200 ሊትር ውሃ የሚጠቀም የህብረተሰብ ክፍል መኖሩ ተረጋግጧል።በተለይም ወደ ላይ ከፍታ ያላቸው ፎቆች መብዛታቸው ስርጭቱን አዳጋች አድርጎታል።ለባለስልጣኑ ፈተና የሆነው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን ሊያቀርብ የሚገደደው ከፍታ የመውጣት የግፊት መጠኑ ከአስር ሜትር ያልበለጠ መሆን እንዳለበት ነው። ባለ አንድ ወለል (ግራውንድ ፕላስ ዋን) ቤት የሚደርስ ማለት ነው። ከዚህ በላይ ላለው ፍላጎት የተጠቃሚው ኃላፊነት ነው። መሬት ላይ ወይንም ከጣሪያ በላይ የውሃ ማጠራቀሚያ በመስቀል ችግሩን ማቃለል ይኖርበታል።
አማራጭ በመውሰድ በኩል ችግሩ ጎልቶ የሚታየው በጋራ መኖሪያ ቤቶች ነው።ለባለስልጣኑ ከሚቀርቡ ቅሬታዎችም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።እኛ ግን አሁንም መልእክት እንዲተላለፍልን የምንፈልገው ባለሥልጣኑ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ መንቀሳቀስ አይችልም። አማራጩን ይጠቀሙ። አስፈላጊውን ምክር አገኝተው ወደ ተግባር በመግባት ችግራቸውን ያቃልሉ። አስፈላጊ ከሆነም በምክር እናግዛለን። ውሃ ለጋራ መኖሪያ ቤት የንጽህናም ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
አዲስዘመን፡- ታሽጎ ለገበያ የሚቀርብ ውሃ መበራከት ባለሥልጣኑ በሚሰጠው የውሃ አገልግሎት ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ይኖር ይሆን?
አቶ ፍቃዱ፡- ባለሥልጣኑ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የሚኖረው ተጽእኖ የለም። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከምናመነጨው ውሃ ጋር አይገናኝም። መገኛቸው ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ነው። አቅርቦቱ ክፍተት ሊሸፍን ይችላል። ነገር ግን የዋጋ ጉዳይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ስለማያደርግ ሊያማርር ይችላል። ቀደም ሲል በነበረው ታሪፍ ባለሥልጣኑ አንድ ሜትር ኩብ ውሃ በአንድ ብር ከ75 ሳንቲም እና በሁለት በር ከ40 ሳንቲም እያቀረበ አንድ ሊትር የታሸገ ውሃ እስከ 20 ብር የሚሸጥ ከሆነ የህብረተሰብን የውሃ አቅርቦት ጥያቄ መልሷል ለማለት አያስደፍርም።
መንግሥት የመጠጥ ውሃ አግልግሎትን የሚያቀርበው በድጎማ ነው። ውሃ መሰረታዊ ነገር ስለሆነ መቅረብም ያለበት በዚህ ደረጃ ነው። መዘንጋት የሌለበት ለህዝብ ጥቅም ሲባል በግለሰቦች የለማ ውሃ እንኳን ቢኖር ባለሥልጣኑ ወርሶ ለተጠቃሚው ማቅረብ እንደሚችል በአዋጅ ስልጣን ተሰጥቶናል። በመሆኑም ከውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በባለሥልጣኑ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የገጠመ ፈተና የለም።
አዲስዘመን፡- በሥራ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ ጠንካራ ጎኖች እንዲሁም ለክፍተቶቹ የተሰጠ መፍትሄ ላይ ሃሳብ ቢሰጡን?
አቶ ፍቃዱ፡- የባለስልጣኑ ትልቁ ተግዳሮት በውሃ አቅርቦትና በፍላጎት መካከል ባለመጣጣሙ እርካታ ማምጣት አለመቻሉ ነው። ይህ መሰረታዊ ችግር ተደርጎ ይወሰዳል። ሌላው የውሃ መሰረተ ልማት ላይ የጥንቃቄ መጓደል ነው። ውሃ መሥመር ላይ ግንባታዎች ይከናወናሉ። ወደ መሰረተ ልማቱ መግቢያ ላይ አጥር በማጠር መግቢያ ማሳጣትና በዚህም ልማቱን የማስተጓጎል ሁኔታ ያጋጥማል። ውሃ ለማልማት የወሰን ማስከበር ችግርም አለ። የውሃ መስመሮች በተዘረጉባቸው ጋራዦችና ሌሎችም አገልግሎቶች ማከናወን አንገብጋቢ ላልሆኑ ነገሮች ውሃ በመጠቀም ማባከን፣ በቁጠባ አለመጠቀም አለ።
ለችግሮች ባለሥልጣኑ ያስቀመጠው መፍትሄ የከተማዋን ውሃ ፍላጎትና አቅርቦት ለማቅራረብ የአስር አመት ስትራተጅ እቅድ ነድፎ እየሠራ ይገኛል። ቀደም ሲል የጠቀስኩት ገንዘብ አስኪለቀቅ ከሚጠበቀው የገርቢ ግድብ ግንባታ በተጨማሪ 500ሺ ሜትር ኪዩብ በቀን የማምረት አቅም ያለው ሲቢሎ የተባለ ግድብ ፕሮጀክት የጥናት ሥራ ተጠናቅቆ የቀረው ገንዘብ የማፈላለግ ሥራ ነው። እንዲሁም በቀን 600 ሺ ኪዩቢክ ውሃ በቀን ማምረት የሚችል ዓለም ቱጂዶ ፕሮጀክትም የጥናት ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። እነዚህ ሁሉ በአስር አመት እቅድ ውስጥ የተካተቱ ናቸው። ከከርሰ ምድርም በተመሳሳይ ውሃ የማውጣቱ ሥራ ይጠናከራል። በእቅዱ መሰረት ሥራዎች ከተከናወኑ ከተማዋ የተሻለ የውሃ አቅርቦት ይኖራታል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ፍቃዱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም