የዳዊት ነገር
ዳዊት መንግስቱ ይባላል። እድሜው 55 ዓመት ነው። ጎፈሬውና ተክለቁመናው ሲታይ ግን ወጣት ያስንቃል። ውሃ፣ አነስተኛ ፍራሽ፣ ቴፕ፣ የፕላስቲክ ሸራ ከአጠገቡ አለ። ሁሉም በየፈርጃቸውም ተሰድረዋል። እርሱ የተቀመጠበት ሥፍራ መስቀለኛ መንገድ ሲሆን፤ ቦታው ከፍ ያለና ጥላውም ምቹ ነው። በአራቱም አቅጣጫ ሁኔታዎች አማትሮ ለማየት ያመቻል።
ዳዊት ላለፉት ሦስት ዓመታት በዚህች ስፍራ አንድ ቦታ ከአንድ ግለሰብ አጥር ጥግ ቁጭ ብሎ ሙዚቃ ያደምጣል። ከራሱ ጋር በፅሞና ይነጋገራል፤ ከሰዎች ጋር ብዙም አይገጥምም። ሰዎች ወደአልተፈለገ መንገድ እንዳይወስዱት ጥንቃቄ ያደርጋል። ሙዚቃ የሠላም በር መክፈቻ፣ የተከዘ የሚፅናናባት፣ የተደሰተ የበለጠ ደስታውን የሚያጣጥምባት ስጦታ ናት ይላል።
በአሁኑ ወቅት የሚቀመጥባትን ቦታ በምቾቷና ስትራቴጂክ መስሎ ስለታየው እንደመረጠው ይናገራል። እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ በዚያው አካባቢ ይቆያል። ብቻ በአካባቢው ለቅሶ ከሌለ ሙዚቃን ከማዳመጥ አይቆጠብም። ሙዚቃን ለማወደስ አንደበቱ ትጨነቃለች፤ ስለ ሙዚቃ ሲናገርም ለቃላት ምርጫ ይጠበባል። ሙዚቃ ለእርሱ የነፍስ ጥሪ ናት። ቀደም ሲል የመጠጥ ሱሰኛ ነበር ። ከሦስት ዓመታት በፊት ከዕለታት በአንዷ ቀን ግን ከባድ ውሳኔ ወሰነ። መጠጥ የሚባል ነገር ከንፈሬን አይነካውም አለ። አደረገውም። ሱሱ ሙዚቃ ማዳመጥ ሆነ።
ውትድርና
ዳዊት እስከ ስምንተኛ ክፍል ሰሜን ሆቴል አካባቢ በሚገኘው ወይዘሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ተምሯል። ከዚህ በላይ በትምህርቱ አልገፋም። በ1974 ዓ.ም የውትድርና ዓለምን ተቀላቀለ። የእናት አገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ኢትዮጵያ በጠላት እንዳትደፈር የጠመንጃ ቃታ እየሳበ ጠላትን አብረክርኳል። በዱር በገደሉ ‹‹እምቢኝ ለአገሬ፤ እምብኝ ለእናቴ አትደፈርም ትጥፋ ሕይወቴ›› ብሎ እንደ ነብር እያጓራ በታሪክ ገድል የራሱን ድርሻ አኑሯል። በዚህም የ፲ አለቃ ማዕረግ አግኝቷል። በእናቱ አገሩን ዳር ድንበር እያስከበረ፤ እየተዋደቀ ዓመታትን አሳልፏል። ዳዊት እግረኛ ቃኝ ነበር። በጦር ግንባር ሆኖ በኤርትራ ውስጥ ከረን፣ መለብሶ በሚባሉ ግንባሮች ለረጅም ዓመታት አገልግሏል። በመጨረሻዎቹ የውትድርና ሕይወቱ ወቅት የተለያዩ ፅሁፎችን ሲሠራ ስለነበር ኮር 06/07 በሚባል ስፍራ ፖለቲካ መምሪያ ውስጥ ፀሀፊ ሆኖ ገባ። ከዚያም ወደ አስመራ ሄዶ የታይፕ ትምህርት ተምሯል። ይህ የሆነው በ1979 ዓ.ም ነበር። ከአጭር ጊዜ አገልግሎት በኋላ ሁኔታዎች ሲበላሹ ተመልሶ ወደ እግረኛ ወታደርነቱ ተመልሶ ገባ። ጦርነት ተጀመረ። እርሱና ጓደኞቹ በመጨረሻ ወደ ሱዳን ሸሹ ። ምስቅልቅሉ የወጣው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአንድ ወቅት ለእናት አገሩ ባለአደራ፤
ለአገሩ ሟች የነበረውን ፲ አለቃ ዳዊት ከሰባት ወራት የሱዳን ቆይታ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
በውትድርና ሕይወት በርካታ ጓደኞቹን በተለያዩ ቦታዎች ተለይተውታል። ያንን ሁኔታ ሲያስታውስ ዛሬም የጦርነት አስከፊነት ከፊቱ ድቅን ይላል። አልፎ አልፎ ደግሞ ከጦር ሜዳ ነፍሳቸው የተረፈ ጓደኞቹን እያገኘ ኤርትራ ውስጥ ስላሳለፉት ህይወት እያወጉ በትካዜ እየተናጡ፤ በደስታ ማዕበል ውስጥ እየዋኙ ከአዲስ አበባ አስመራ በሃሳብ ይመላለሳሉ፤ ይተክዛሉ።
ምን ይሠራል?
ለዳዊት ማንኛውም ሥራ ክቡር ነው። ከስርቆት ውጭ የሰው ልጅን የሚያሳፍር አንዳች ነገር የለም ይላል። ከውትድርና ዓለም በኋላ ሕይወቱን ለማሸነፍ ሲል በርካታ ሥራዎችን ከውኗል። ለአዳዲስ ቤት ሰሪዎች ቀለም ቀብቶ አሳምሮ አስረክቧል። ውበቱ የፈዘዘ ቤት በቀለም አፍክቶ እንደ አዲስ ቤት በሰዎች ላይ አዲስ ስሜት ፈጥሯል።
ዳዊት የኑሮ አቀበቷን ለመንካት ሲንጠራራ፤ ቁልቁለት ከሸለቆ ውስጥ ላለመውደቅ ያልሞከረው ሥራ የለም። ወዛደር ሆኖ ከአንዱ ሰፈር ወደ ሌላ ሰፈር እቃ አመላልሷል። እንደ ህፃን ልጅ ከአንዱ መንደር ወደ ሌላ ሰፈር መልዕክት አድርሷል። ዛሬም ቢሆን ለሰዎች ይላላካል። ዳዊት የሚፀየፈው ስርቆት ብቻ ነው። እርሱ ሙዚቃውን ካጣጣመ ብዙም ግድ የለውም። ከመጠን በላይ ቢቸገር እንኳን በለሆሳስ ከሰዎች ገንዘብ ይጠይቃል እንጂ የሰውን አይመኝም ።
አሜሪካ አልፈልግሽም!
ለአንገት ማስገቢያ የቀበሌ ቤት አለው። ውጣ ውረዶችን እያለፈ ዛሬ ላይ ቢደርስም በሕይወት በመቆየቱ ብቻ ደስተኛ ነው። ዳዊት ከውትድርና ሕይወቱ ብዙ ተምሯል። ከምንም በላይ ግን የአገር ፍቅር ምትክ የለሽ እንደሆነ በአውደ ውጊያ ውሎ ተገንዝቧል። ከኢትዮጵያ ወደ ሌላ አገር ሂዶ የመኖር ዕድል ቢያጋጥመውም በተግባር ግን አላደረገውም። ወላጅ አባቱ እርሱ ከውትድርና እንደመጣ ሞቱ። እናቱ በአሁኑ ወቅት አምቦ ይኖራሉ። ሦስት ወንድሞችና አንድ እህት አለው። እርሱ ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ነው። ሁሉም እህት ወንድሞቹ የሚኖሩት አሜሪካ ነው። እናም የስልጣኔ ማማ ወደሆነችው አገር ና! ብለው ሁኔታዎችን ቢያመቻቹለትም ቆፍጣናው ወታደር ግን አሜሪካን አልፈልግሽም፤ አገሬ ትፈልገኛለች ሲል በሃሳባቸው ሳይስማማ ቀረ። ‹‹እኔ በአሜሪካ የሚታየኝ ምቾቱ ሳይሆን የስደት ሕይወቱ ነው›› ይላል። የአገሬ ፍቅር በምንም አይተካም የሚለው ዳዊት፤ ግን ለአንድ ልጄ የተሻለ ትምህርት ስለሚያስፈልገው አጎቶቹ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹለት መጠየቁን ይናገራል ።
ሰዎች ምን ይላሉ?
ዳዊት በአካባቢው ሰዎች እይታ ውስጥ ገብቷል። በሙዚቃ መንፈስ አካባቢውን እያነቃቃ ሰውንም እያስደመመ ይኖራል። ከሙዚቃ ምርጫው ባሻገር የዳዊት መመሰጥና የማይለዋወጥ ባህሪ ደግሞ በእጅጉ አጃዒብ ያስብላቸዋል። በተለይም ይህ የማይለዋወጥ ባህሪው በርካቶችን ያስገርማል፣ ያስቃል፣ ብሎም እንዲህም አለ እንዴ? ብለው ወደራሳቸው ተመልሰው እንዲያስቡ ይገፋፋቸዋል። ሙዚቃው አገራዊ ፍቅር የተላበሱ፣ ስለ ሠላም የሚሰብኩ፣ ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ፣ አገራዊ ወኔ የሚቀሰቅሱና በራሳቸው ለዛ እና ውበት የተሞሉ ናቸው። ዳዊት ብቻ ሳይሆን አላፊ አግዳሚው እየተመሰጠ ቆም ብሎ ከሙዚቃው በረከት ይቋደሳል።
ግልጽነቱና ታማኝነቱ ብሎም ስለሰው ያለው ክብር በራሱ ውበት አለው ሲሉ ይመሰክሩለታል፤ የአካባቢው ነዋሪዎች። የዳዊት አኗኗር ብዙዎችን መነጋገሪያ አድርጓል። ከአንዲት ስፍራ ለዓመታት ቁጭ ብሎ አንድም የሚያስቀይም ቃል ተናግሮ አያውቅም ። በአንድ ስፍራ ቁጭ ብሎ ብዙዎችን እየታዘበ ብዙዎችንም እያስደመመ የሚኖር ወጣ ያለ ሰው ነው። ያች ስፍራ ያለ ዳዊት፣ ዳዊትም ያለዚያች ስፍራ ውበት፤ ድምቀት እና ስሜት የላቸውም። አንዳቸው ለአንዳቸው የመኖር ሚስጥር እስኪመስሉ ድረስ በአካባቢው ሰው እይታ ውስጥ ናቸው፤ ምንም እንኳን አንደኛው ግዑዝ ሌላኛው አካል በነፍስ ያለ ቢሆንም። የአካባቢው ሰው በሙዚቃ ማዕበል ሰፈሩን ሠላም የሚያደርገውን ወታደር ወደውታል ‹‹ሰላም ዋልክ?›› ብለው ከማለፍ ይልቅ ከአጠገቡ አረፍ ብለው ቆየት ባሉ ዜማዎች የሙዚቃ ጥማቸውን ይቆርጣሉ። ልባቸውን በትዝታ እየዋለለ፤ የሲቃ እንባ ከፊታቸው ላይ ቁርርር… ይላል። በሙዚቃ ፍቅር እያከነፋቸው፤ ሠላማቸውን ይሰጣል፤ ሠላሙንም ያገኛል።
አንዳንድ ሰዎች የሚያዳምጣቸውን ሙዚቃ ኮፒ አድረገህ ስጠን ይሉታል። እርሱ ግን በገንዘባችሁ ግዙ ይላቸዋል እንጂ አይሰጣቸውም። ሙዚቃ ዝም ብሎ አይበተንም ክቡር ነው ይላል ። ሰዎችን አብዝቶ ማውራት ወደ ሀሜት ስለሚወስድ ብዙ መነጋገር አይፈልግም ። ከዚህ ሁሉ ፍቱን የሆነውን ሙዚቃ ማዳመጥ ጥቅሙ የጎላ ነው ይላል። ባለቤቱም ይህን በሚገባ ስለምትረዳ አትጋፈውም፤ ስሜቱን ታዳምጣለች።
መልካሙ ተበጀ ትፈለጋለህ!
፲ አለቃ ዳዊት መጥፎ መልዕክት ያላቸውን ሙዚቃዎች አያዳምጥም። በርካታ ሰዎች የዘመኑን ሙዚቃ እንዲያዳምጥ ይጋብዙታል። እርሱ ግን ዘመንኛውም አይመቸውም፤ ግብዣቸውንም አይቀበልም። ግን ማህሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ንዋይ ደበበ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ አስቴር አወቀ፣ ሂሩት በቀለ እና የመልካሙ ተበጀ ሙዚቃዎችን አብዝቶ ይወዳል። ግን በአካል አግኝቶ ስሜቱን ሊገልጽለት የሚፈለግው መልካሙን ተበጀን ነው። የእርሱን ሙዚቃ እንደ ዳዊት ደጋግሞ ያዳምጠዋል። የእርሱን ሙዚቃ ሲያዳምጥ ማንንም አያናግርም።
መልካሙ ተበጀ ከወዴት አለህ? ተብለሃል። የዚህ አምድ እንግዳችን በሕይወት ዘመኑ አድናቂህ ነው። ዳትሰን ሰፈር ከመንገድ ዳር ሆኖ ለሦስት ዓመታት ያለማቋረጥ ሙዚቃህን እያዳመጠ፤ ለሌሎችም እያስደመጠ በስሜትም እየተመሰጠ ዛሬም ከዚያ ስፍራ አለ። እናማ ከምንም በላይ ይህ ቆፍጣናው ወታደር፤ የሙዚቃህ አድማጭ የአንተ ወደር የለሽ አድናቂ ካለህበት ሊመጣ ይፈልጋልና እባክህ እንፈላለግ ይልሃል። አንተ ከሙዚቃ ሕይወትህ እርሱም ከውትድርና ልምዱና ከእናት አገር ጥሪ ውስጥ ያገኘውን ልምድ ብቃት ሊያወጋህ ይሻል። በተለይም ደግሞ
ኧረ መላ በሉ ዘመድ ወዳጆቼ
ዓይናፋር ሆኛለሁ ዓይናፋር ወድጄ፤
የሚለውን ሙዚቃህን እንደ ነፍስያው ይወዳታል። በአካል አግኝቶህ አንዷን የስንኝ ቋጠሮ በድምፅህ እንድትወጣለት ይጓጓል። እናስ ጋሽ መልካሙ ምን ትላለህ?
ምን ያስባል?
ዳዊት አሁን ካለው አኗኗሩ ብዙም የተለየ ነገር አይጠብቅም። ብቻ ግን የአገር ሠላም፣ የአገር ፍቅር ካለ ሁሉ ሸጋ ሁሉ መልካም እንደሚሆን ያምናል። የሙዚቃን መግኒጢሳዊ ኃይል አይክድም። እጁን እስከሚንተራስ ከሙዚቃ ለመለየት ከቶውንም ለአዕምሮው ሹክ ማለት አይፈልግም። አሁን አንድ ልጁ ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲያቀና ይተጋል። ሁለተኛ ልጅ ወደዚህች ምድር ለማምጣት አልፈቀድም፤ ገና መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ያምናል። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ሌላ ፍጥረት ማሰቃየት አልፈልግም ባይ ነው። አንዱ ልጄ ከተባረከ ለኢትዮጵያ ባለውለታ እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ ይላል። ብዙ ህልሞቹን በልጁ ውስጥ የማየት ፅኑ ፍላጎት አለው። በተቻለው ሁሉ ለልጁ ይኳትናል። እስካሁን በተመሳሳይ ሕይወት ውስጥ መኖሩ ያስተክዘዋል። የነገን ፈጣሪ ያውቅልኛል ይላል። በአሁኑ ወቅት ድለላ መተዳደሪያው ነው። ሥራውም አልፎ ገጭ በመሆኑ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ነው። ሰዎችም ያላቸውን ከሰጡት አይጫናቸውም። ዋናው ሠላምና ፍቅር ስለሆነ ሰውን አያስጨንቅም። ብቻ እርሱ ሙዚቃ አይጉደልበት፤ እርሱም ከሙዚቃ አይጉደል እንጂ ኑሮ እንዳይገፋ የለምና ይኸው እኛም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር