ባለራዕዩ – በሻካራማው መንገድ

የተክለኃይማኖት ትዝታዎች

መሀል አዲስ አበባ ሰፈረ – ተክለኃይማኖት። የበርካቶች መገኛ የብዙኃን መኖሪያ። ይህ አካባቢ ሁሉም በአቅሙ ሰርቶ፣ ለፍቶ ያድርበታል። ዕድሜ ጠገቡ ሰፈር ተሳስበው ፣ ተዋደው የሚ ኖሩበት ዋርካ ነው ። በዚህ ስፍራ ብዘዎች በላባቸው ወዝ ፣ በጉልበታቸው ድካም ይኖራሉ።

እዮብ ተወልደመድህን በዚህ ሰፈር አፈር ፈጭተው ፣ ውሃ ተራጭተው ካደጉ የአካባቢው ፍሬዎች አንዱ ነው። ተክለኃይማኖት ለእዮብ የልጅነት ታሪኩ ብቻ አይደለም ። ከወጣትነት ዕድ ሜው ተሻግሮ ጎልማሳነቱን በፍቅር ኖሮበታል። ሥራ ይዞ ገንዘብ ቆጥሮበታል። ልጅ ወልዶ ስሞበታል።

እዮብ በሰፈሩ ኑሮን ለማሸነፍ፣ አልሆነው የለም። ራሱን ለመቻል ፣ ከማማው ከፍታ ወጥ ቷል ። መልሶ ደግሞ ከዝቅታው ታይቷል ። ሁሌም ወድቆ ለመነሳት ሲሞክር ተንገዳግዶ አይቀርም። ሕይወትን ከሀሁ ፣ መጀመር ከዳዴ መቀጠል ያውቅበታል። ለእሱ ደስታ ከመከራ ብርቁ አይደለም። በለስላሳና ሻካራ የሕይወት ጎዳናዎች ደጋግሞ ተመላልሷል።

ተክለኃይማኖት ለእዮብ የዝምታው መደበቂያ ነበር። ልጅነቱን በብቸኝነት ገፍቶበታል። ብሶቱን ከራሱ አውግቶበታል። ሰፈሩ ለእሱ፣ እሱም ለሰፈሩ ልዩ መገለጫዎች ናቸው። በዚህ ሥፍራ ተወዶ ተከብሯል፣ አግኝቶ አጥቷል ፣ ወድቆ ተነስቷል። እዮብ ስለሰፈሩ ለማውራት ቃላት የለውም። ተክለኃይማኖት ለእሱ ታሪኩ ነው። ሕይወትን ያነበበበት፣ ኑሮን ያየበት፣ የልብ መስታወት።

በዚህ ሰፈር ቀኝ እጅ የሆነላቸው በርካቶች ስሙን በበጎ ሲያነሱት ውለዋል።ዕንባ የታበሰላቸው፣ ጎዶሎ የሞላላቸው ፣ መርቀው፣ አመስግነው አይጠ ግቡትም። ዓላማው ከዓላማቸው ያልገጠመ ጥቂቶች ደግሞ ስሜቱን ሊነጥቁ ፣ ተስፋውን ሊያ መክኑ ሞክረዋል ። እሱ ግን ከዕቅዱ ሸሽቶ፣ ከሃሳቡ ተናጥቦ አያውቅም ። ሁሌም ዓላማው የሰፋ፣ መንገዱ የራቀ ነው። ህልሙን ያሳካል ፣ ጅምሩን ይጨርሳል።

ልጅነትን ወደኋላ …

ለጥንዶቹ የመጀመሪያ ወንድ ልጅ የሆነው እዮብ የልጅነቱ የመጀመሪያ ዓመታት በፍቅር የተሞሉ ነበሩ። በእነዚህ ጊዜያት ከወላጆቹ ፍቅር እንክብካቤን አላጣም። እሱም እንደ እኩዮቹ በቤተሰብ እቅፍ ውሎ አደረ። ይህ እውነታ ግን ብዙ አልዘለቀም። የአባቱ በሥራ ምክንያት ከቤት መራቅ ታሪኩን ሊቀይረው ግድ አለ።

እዮብ አባቱን ተከትሎ ወደ ምዕራብ ሐረርጌ አሰበ ተፈሪ አመራ። የዛኔ አስራ አንደኛ ዓመት ዕድሜውን መጀመሩ ነበር። አጋጣሚው ከእናቱና ከታናናሽ ወንድሞቹ የለየው ብላቴና ውሎ አድሮ የሰው ሀገር እንግድነትን ተላመደ። የአባቱ የሥራ ባህሪ ከቤት የሚያውል አልሆነም ። ማለዳ ወጥተው ምሽት የሚገቡበት ጊዜ ይበረክታል።

የአባቱ እንደ ልብ ከቤት አለመገኘት እያደር የእዮብን ብቸኝነት አባሰው። ትኩረት በሚያሻው ዕድሜ ፍቅር ማጣቱ ትንሹን ልጅ ምርጫ አሳጣው። እያደር አካባቢውን ይመስል ያዘ። ቤት እየጠበቀ ከሱቅ ሥራ መዋል ግዴታው ሆነ።ትምህርት ቢጀምርም በቂ ዕውቀት አልጨበጠም።የት ነህ? የት ዋልክ ? የሚል ፈቃጅ ከጎኑ አጣ። ናፍቆት በአንጀቱ እየተላወሰ፣ የወላጅ ፍቅር በዓይኑ እየዞረ ግዴታውን ተቀበለ።

ያለ ታዛቢና ተቆጪ የሚያድርባቸው ጊዜያት በረከቱ።በትልቁ ቤት ብቻውን ውሎ ማደር ፣ ሰንብቶ መክረም ልምዱ ሆነ። የራሱ አዛዥ አለቃ ለመሆን በሩ ሰፋለት። ‹‹ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ›› የሆነው ታዳጊ ያለአንዳች ከልካይ ሰፊውን ሜዳ ናኘበት፣ ቦረቀበት።

ቀናት አልፈው ቀናት ተተኩ።የእዮብ ባህሪ መለወጥ፣ መቀየር ጀመረ። ከሱቅ መዋሉ ከገንዘብ አስተዋወቀው ። ጣፋጭ መብላት መጣጣት አዘወተረ።ልጅነቱ እሳትን ከውሃ አላስለየውም። የሚጠቅም የሚጎዳውን ሳይመርጥ ባሻው መንገድ ተራመደ። ‹‹ተው ፣ እረፍ ፣ አደብ ግዛ›› የሚል ተቆጪ አጣ። የእሱ ጊዜ ‹‹ልጅነቴ ማርና ወተቴ›› የሚባልለት አልሆነም። ይህ ዕድሜ ለእዮብ ማንነት የማይፈዝ ማህተም አሳርፎ እንደዋዛ አለፈ።

አፍላነት

ወቅቱ በመላው ሀገሪቱ አዲስ የለውጥ እሳት የተቀጣጠለበት ነበር ።ወርሀ ግንቦት 1983 ዓ.ም። ይህ እውነታ እዮብን ከአሰበ ተፈሪ ወደ አዲስአበባ እንዲመለስ አስገደደው። ባደገበት በኖረበት አካባቢ ሁኔታዎች ተቀየሩ። ለውጡን ተከትሎ የመጣው እንቅስቃሴ እዮብን ከክፉ ዓይኖች ጣለው። ሰበብ ፈልገው የሚያሳድዱት፣ የሚከተሉት በረከቱ። ይህ እውነታ በነፃነት ላደገው ልጅ ፈተና ሆነ።

ያን ጊዜ ሰዎች ሲሮጡ ‹‹ሌባ፣ቀማኛ፣›› ተብለው የሚገደ ሉበት፣ አንዳንዶች በየሰበቡ ኃይላቸውን የሚያሳዩበት ነበር። እንዲህ አይነቱ ሀቅ ለፈጣኑ እዮብ ፈተና ሆነ። ‹‹እናውቀዋለን›› ባሉ የቅርብ ዘመዶቹ ተሳደደ።ጉልበታሙ ኃይለኛው ወጣት በቀላሉ እጅ አልሰጠም።ቀን እስኪያልፍ ቀን ጠበቀ። ክፉ ጊዜውን ሽሸግ ፣ ድበቅ ብሎ አሳለፈ ።ያም ሆኖ ነገሮችን አልረሳም። የበደሉትን አልዘነጋም።

ውሎ አድሮ ነገሮች ተረጋጉ። እዮብ ከቤተሰቡ ውሎ እንዳደረ ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል ገጠመው። እንደ እኩዮቹ ደብተር ይዞ፣ ሰአት ጠብቆ ትምህርት ቤት ተመላለሰ። ይህ ጊዜ ብዙ ላየው ትንሹ እዮብ የተመቸ አልሆነም። ቀድሞ የጨበጠው ዕውቀት የለም ። በትምህርት ከእኩዮቹ እኩል መራመድ አልቻለም። እንደተማሪ ክፍል አለመግባቱ ደግሞ ስንፍናውን አጋለጠ።

እዮብ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ደጋግሞ ወደቀ። እንዲያም ሆኖ በሚማርበት የፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት ባህሪውን ለመለወጥ ትንሽ ጭላንጭል አላጣም። ቆም ብሎ የሚያስብበት አፍታ ቢያገኝ ስለማንነቱ ይጨነቅ ፣ ያስብ ያዘ ።

ከዚህ በኋላ የነበሩት ጊዜያት ለእዮብ ማስተዋልን ጨመሩለት።ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት ሰጠ።ትናንት እንደዋዛ የባከኑትን ጊዜያት በጥናት ተካቸው። ጎበዝ ተማሪ ሆነ። ጊዜው ደርሶ ዳግም ስምንተኛ ክፍልን ተፈተነ። ነባር ታሪኩ መልኩን ለወጠ ፣ በጥሩ ውጤት ማለፉን አወቀ ። በአዲሱ ዓመት የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱ መልካም ሆነለት።

አሁን እዮብ ዕድሜ እየጨመረ ፣ ወጣትነቱ እያበበ ነው።ይህ ጊዜ ለእሱ የጎረምሳነት ኃይል ብቻ አልሆነም። በእናቱ ቤት ላቅ ያለ የኑሮ ችግር ስለመኖሩ እያስተዋለ ነው። ቀድሞ የነበረው የቤተሰብ መለያየት በልጆች ሕይወት ጫና አሳድሯል።ይህን አሳምሮ የሚያውቀው እዮብ ስለ ሁሉም አስትንፋስ አጥብቆ እያሰበ ነው።

እዮብ ጎበዝ ከሚባሉት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች አንዱ ሆኗል።ለትምህርቱ የሰጠው ትኩረት ውጤት ደርቦለት ዕውቅናን ችሮታል። ውሎ አድሮ ግን ይህ ጥንካሬው ዕንቅፋት አላጣውም። እሱ በኑሮ ደረጃ ከእኩዮቹ አቻ አልሆነም። ችግር አብዝቶ የሚጎበኘው የእናቱ ጓዳ ፍላጎቱን በወግ አልሞላም።

ትምህርት – በባዶ ሆድ

አሁን እዮብ ምግብ ከሚበላበት የማይቀ ምስበት ጊዜ በርክቷል። በባዶ ሆድ ትምህርት ይሉትን መቀበል እየከበደው ነው።ይህ ችግር የእሱ ብቻ አይደለም። ከቤት ያሉት እናቱና ወንድሞቹም ይጋሩታል። እህል ባልሻረ አፉ ውሎ ሲገባ ኩርማን እንጀራ አይቆየውም። ከባዱ የሕይወት ምዕራፍ እየፈተነው ፣ መንገዳገድ ይዟል። አሁን በውጉ ለመኖር አንዱን ጥሎ ፣ አንዱን ሊመርጥ ግድ ነው።

እዮብ ፀንቶ ከቆየበት ዓላማ ሊፋታ ጊዜው ደረሰ። ውስጡ ቢያዝንም ምርጫ የለውም።የዘጠኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ የቀን ሥራ ፈላለገ ።1988 ዓ.ም። ይህ ወቅት እንደ እዮብ ላሉ አፍላ ወጣቶች ቀላል አልነበረም።ሁሉም ጉዳይ በሰው፣ በዘመድ ነው።ማንም ባሻው ዘው ብሎ ሥራ አይገባም። ለእሱ ሥራው ካልተሳካለት የቤቱ ችግር ይበረ ታል፣ ርሀቡ ይጠናል።

ለሥራ ፈላጊው ወጣት ቀን አልጎደለም።በአንዲት ሴት መልካምነት ከአንድ የእንጨት መሰንጠቂያ ድርጅት እንጀራው ተገኘለት። ቦታው ለቤቱ የቀረበ ነው።ተጨማሪ ወጪ የለውም። ማልዶ ከቤት ሲወጣ ብዙ አይሻም። አንዲት ጉርሻ ከእናቱ ምርቃት ጋር በቂው ነው ። የእዮብ ልብ በደስታ ሞላ።ችግር የፈታውን ቤተሰብ ሊታደግ ነውና ለፈጣሪ ምስጋና ተንበረከከ ።

ሥራና ሥራ …

እነሆ እዮብና ሥራ በፊት ለፊት ተገናኙ።አሁን ከዚህ ውሎ የተሻገረ ሌላ ዓላማ የለውም። በዕለተ ሀሙስ የመጀመሪያውን ቀን በሥራ አሳለፈ። ከአንድ ቀን በኋላ አስር ብር ተከፈለው።የእዮብ ደስታ ልዩ ነበር።አስር ብሩን ለእሱ ትርጉሙ ይለያል። የተሰጠውን ሳያጎድል ለእናቱ አስረከበ። የዛን ቀን መላው ቤተሰብ ምሳና ራቱን በልቶ ማደሩን አይዘነጋም፡።

ከዚህ በኋላ የእዮብ ታታሪነት በሥራው ይገለጥ ያዘ። ጉልበቱን ሳይሰሰት ይሰራል። ከተሰጠው ድርሻ አልፎ ይገኛል። ለሻይ ቡና የሚያጠፋው ምንም ሳንቲም የለም። አራት ሰአት ላይ ሠራተኛው ብስኩት በሻይ ሲበላ እሱ አይሞክረውም። ልጅነቱን በሚያስታውሰው እጅግ በሚወደው ብስኩት ይጨ ክናል።

አንዳንዴ ውስጡ አብዝቶ ይጠይቀዋል።እሱ ግን እንዳይለምድበት ሲሰጋ እንዳልሰማ ይተወዋል። አብረውት የሚሰሩ ባልደረቦች በየቀኑ ዳቦ ገዝተው ሻይ አስቀድተው እንዲበላ ይጋብዙታል። የእዮብ ምላሽ ግን ሁሌም አንድ ነው ።ለጠየቁት ሁሉ ‹‹ፆመኛ›› ነኝ ሲል ይመልሳል። ከሚሰጠው ገንዘብ አንዳች ሳንቲም አያጣፋም።እንደወጣት ብዙ ቢያምረውም የቤቱን ችግር ያስቀድማል።

እዮብ የሳምንት ክፍያው አርባ ብር ሲገባ የእናቱን ጎዶሎ ያለአንዳች መሳቀቅ ይሞላ ያዘ። ይህኔ ቤተሰቡ በልቶ ማደሩ ሰላም ሰጠው። ለቤት ሰጥቶ የምትተርፈውን አስር ብር በኪሱ ይዞ ከሌሎች ላለማነስ ጣረ። ባልንጀሮቹ ሲጋብዙት እሱም የአቅሙን ያደርግ ጀመር።

በሻይ ለስላሳ የተጀመረ ግብዣ ውሎ አድሮ ደረጃው አደገ። ቀስ እያለ ከድራፍት ፣ ከቢራው መንደር ዘለቀ። አንዳንዴ አረፍ ባለ ጊዜ ያለፈበትን ውጣውረድ ያስበዋል። በልጅነቱ የከፈለው ዋጋ ፣ የደረሰበት እንክርትና በደል ውል ይልበታል። ትናንትናው ለእሱ የክፉ አሻራ ትዝታ ነው።ዛሬን ባይወድቅም ባሳለፈው ታሪክ ውስጡ ደምቷል፣ ዓይኑ አንብቷል።

በደል የወለደው ቂም

እዮብ ሁሌም በልጅነት ዕድሜው ክፉ የሠሩትን ያስባል። አዲስ አበባ ለመመለስ ምክንያት የሆነው አጋጣሚ ወለል ብሎ ይታየዋል።እሱ የሆነበትን በደል አይረሳም።ይህን ሲያስታውስ የሰዎቹ ምስል በአካል ይቀርበዋል።ድርጊታቸው ፣ ማሳደዳቸው፣ ስም ማጥፋታቸው ትውስ ይለዋል።

ይህ ትዝታ ያለፈውን እየመዘዘ ፣ የክፉ ታሪኮቹን ስዕል የሚያጎላ ነው። እንዲህ በተሰማው ጊዜ ውስጡ የሚሞላው ቁጭት ብቻ ይሆናል።እነሱን በተራው ሊያገኛቸው ፣ ሊበቀላቸው ይሻል።የልጅነት ደስታውን ነጥቀው ፣ ፈገግታውን ያፈዘዙበት፣ ሩጫውን የገቱበት ክፉዎች ድርጊት እንደጥላ ተከትሎታል።

እዮብ አሁንም ኃይለኝነቱ ከእሱ ነው።የአፍላነት ወኔው ይበልጥ ግሏል።ራሱን ቢችልም ይህ ብቻ አልበቃውም። ከወቅቱ ሰዎች መቅረብ መጠጋትን ፈልጓል። ይህን የማድረግ ፍላጎቱ ደግሞ የእሱ ሚስጥር ብቻ ነው። አጋጣሚው ይጠቅመዋል። አሁን የዛኔ የጎዱትን፣ መልሶ መጉዳት፣ ያስለቀሱትን ዳግም ማስለቀስ ዕቅዱ ሆኗል። የሆዱን በሆዱ ይዞ፣ ወዳሰበው ተራመደ።ለዓላማው የፈለጋቸውን አላጣቸውም። መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖ ተቃናለት።

የቀረባቸው የተክለኃይማኖት አውራጃ አመራሮች አልራቁትም። ቅልጥፍናውን ወደዱት።በፊታቸው ግርማ ሞገስ ሆነለት።በወቅቱ ካድሬዎች ወጣቶችን መያዝ ማደራጀት ይሻሉ።እዮብ ለዓላማቸው የተመቸ፣ የተቃኘ ሆነላቸው። እንደታሰበው የአካባቢውን ወጣቶች አሰባስቦ አደራጀ።የፈጣኑና ቀልጣፋው ልጅ ታዛዥነት የብዘዎቹን ልብ ገዛ። የትንሹ ልጅ ውሰጠት በሀሴት ተሞላ።

የዘመኑ ሥርዓት በራሱ ዕቅድ የሚመራ ነው። ጊዜውን ተጠቅሞ ወደቀጣዩ ያልፋል። ለራሱ ዓላማ ከእነሱ መዝለቅ የፈለገው እዮብ ይህ የገባው ቆይቶ ነበር። ወደ የቀበሌው ያመራው አዲሱ ድልድል ዕውን በሆነ ጊዜ ከልብ ደነገጠ ፣ አምርሮም አለቀሰ። ያሰበውን ሳያሳካ ከቦታው መነጠሉን ቢያውቅ ተስፋ ቆረጠ ።

የሥራ ድልድሉ በወጣቶቹ ፍላጎት ተመስርቶ ተለየ።የእዮብ ሃሳብ ከሌሎች የራቀ ሆኖ ምርጫው ውትድርና ሆነ።ይህን የሰሙ ሁሉ ሳቅ ቀደማቸው።እዮብ ቁመትና እድሜው ለውትድርና የሚመጥን አይደለም ።ለስሜቱ የተጠነቀቁ ‹‹ይቅርብህ›› ሲሉ መከሩት።

ይቅር ለእግዜር …

አሁን ያዘጋጀው የበቀል ልምጭ ላይዘረጋ ታጥፏል።እንዳሰበው ከከፍታው ተቀምጦ ጠላቶቹን አልተበቀለም።በእሱ ሳይሆን በአጋጣሚዎች መንገድ መጓዙ አቅጣጫውን አስለውጧል።ከጎኑ የነበሩ መልካሞ ሰዎች በጎነት አልራቀውም።ሲመክሩት ‹‹እህ…›› ብሎ ሰማቸው። በማታው ክፍለጊዜ ያቋረጠውን ትምህርት እንዲቀጥል ሲያበረቱት ሃሳቡን ተቀብሎ ጠንክሮ ተማረ።

አሁን እዮብ በዕድሜ በስሎ በአእምሮው ዳብሯል።ይህ ለውጥ ያለፈውን እያስጣለ በመልካም መንገድ እያራመደው ነው ።ትናንት አብሮት የቆየው የበቀል መንፈስ አሁን ከእሱ የለም።በውስጡ በጎነት ነግሷል።በመሥራት መለወጥ፣ በመተው መርሳት እንዳለ ገብቶታል። ያለፈበት መንገድ ብዙ እንዳሳየው አላጣውም።ለራሱ ዓላማ ከቀረባቸው ሁሉ ክፉ ደጉን ተምሯል።ትናንት ዛሬ ሆኖ እንደማይቀጥል እየገባው ነው።በጊዜ የማይለወጥ፣ የማይቀየር እንደማይኖር አውቋል።

እዮብ ከለውጡ ሰዎች ጋር በነበረው ጊዜ ግምገማ ይሉትን ተምሯል።ይህ አጋጣሚ ደግሞ ሀቀኝነቱን ያስመሰከረ ነበር ። እሱ ጥፋት ያየባቸውን ፈጽሞ አያልፍም፣ ለጥቅም የተገዙትን፣ በሥልጣን የተመኩትን በማስረጃ እየለየ ለክስ ያቀርባል። ይህ ማንነቱ በብዙዎች ዘንድ አላሰወደደውም። ጥርስ አስገብቶ አስነክሶታል። የእድሜው አፍላነት ከሀቅ ተዳምሮ ከበርካቶች ተላትሟል። የወቅቱ ፖለቲካ ባይገባውም ለያዘው ዓላማ የጸና ፣ በእጅጉ የበረታ ነበር።

እዮብ የወጣቶች ሊቀመንበር በሆነ ጊዜ ከብዙዎች ሞግቷል። እውነትን በእውነት ማውጣት ልምዱ ነውና ካልመሰሉት ጋር አይራመድም፡። ውሎ አድሮ የፖለቲካ ጉዳይ ቢሰለቸው ሁሉን ትቶ ወደራሱ ተመለሰ ።ይህ ጊዜ ከሜጋ ማተሚያ ጋር አገናኘው። በእጅ ሙያው ብዙዎች ይፈልጉታል።ይህን ህንፃ ጨምሮ የቀድሞውን ባህር ትራንስፖርት ድርጅት ሙሉ አልሙኒየም ያለበሰው እሱ ነበር።

እዮብ ራሱን ለሥራ ሰጥቶ በበረታ ጊዜ ጤንነት አልሰማ ይለው ጀመር። ዓይኑን ያመዋል፣ ውስጡን ይጨንቀዋል።ደጋግሞ መድኃኒት እየወሰደ ከራሱ ታገለ።በጊዜው የኢትዮ- አርትራ ጦርነት ነበር።ሥራውን የሰጡት ሰው ኤርትራዊ ናቸው።እሳቸው ችግሩን አልተረዱም፡፤ የሚታይበትን ለውጥ ከራሳቸው አያይዘው ስጋት ገብቷቸዋል።ንብረታቸው እንዳይ ወረስ፣ እንዳይባክን እየፈሩ ነው።

ይህ እውነት የገባው እዮብ ከህመሙ እየታገለ ለታማኝነቱ ይጥራል።የተፈራው አልቀረም። ግለሰቡ ወደ ሀገራቸው ተሸኝተው ሥራውን ልጆቹ ተረከቡ።ከዚህ በኋላም እዮብ ትጋቱ አልቀረም።በህመም እየተሰቃየ አብሯቸው ዘለቀ።ቆይቶ ነገሮች ከአቅም በላይ ሆኑ።ህመሙ በረታ፣ስቃዩ ጨመረ።አጋጣሚው ምክንያት ሆኖ ከሥራው ተፋታ።

ራስን መቻል …

የእረፍት ቆይታው ወደቀበሌ አመላልሶ ከሊቀመንበርነት አገናኘው። ይህ አጋጣሚ ከብዙዎች አውሎ ወደሙያው መለሰው። ለመጀመሪያ ጊዜ ድንቅ የእጅ ሥራውን አስመስክሮ አንድ ሺ ሁለት መቶ ብር ተከፈለው። ይህ ገንዘብ ለእሱ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነበር።እዮብ አሁንም እናቱን አልረሳም። የሚያገኘውን ይዞ ለቤት ያስረክባል። እንዲሀ አይነት ክፍያዎች ሲደጋገሙ እናቱ እንጀራ ጋግረው መሸጥ ጀመሩ።የእሱ ጥረት ተቃንቶም በግቢው ውስጥ የራሱን የእንጨት ሥራ ለመክፈት ተዘጋጀ።

ጎን ለጎን የቀበሌ ሊቀመንበርነቱን አልተወም።ችግር ላለባቸው ምላሸ እየሰጠ፣ በጎደለው ሁሉ እየሞላ ጥቂት ተጓዘ። ይህ አይነቱ ይሁንታ ለብዘዎቹ አላመቸም። ግምገማው ወቀሳው ተደጋገመ።‹‹ሂስህን ዋጥ፣ አልውጥም›› ከሌላው ጎራ አላስማማውም።ለብዙዎቹ የጎን ውጋት፣ የቅርብ ስጋት ሆነ።

የሱስ ፈተና

ራስን መቻል ሂደት በእንጨት ሥራ ተጀመረ።እጀ መልካሙ ባለሙያ የሚፈልጉት ደንበኞች በረከቱ። እዮብ አንዳንዴ ቁጭ ሲል ጫት ይቅማል። ይህ እውነታ ከልጅነቱ የተከተለው ነው። የገንዘብ አቅሙ ሲጨምር ፣ አጠናከረው። ጫቱ በቀላሉ የማይተወው ሱስ ሆነበት።

እዮብ አሁንም ቤተሰቦቹን አልተወም።ታናናሾቹን በራሱ ገቢ ያሳድራል። ሁሉም ተምረው ራሳቸውን እስኪችሉ መጠበቅን ግዴታው አድርጓል።ያሰበው ተሳክቶ ከግቡ ሲደርስ ወደራሱ ተመለሰ።ከዚህ በኋላ ቤተሰብ ውስጥ ሆኖ መቀጠል አያሻውም። እናቱን በቅርብ እየደጎመ ከቤተሰቡ ተነጠለ።የራሱን ቤት ተከራይቶም የሸቀጥ ሱቅ ከፈተ።

ይህ አጋጣሚ ለጫት፣ ለሀሺሽ ሱስ አመቸው። ምርኮኛ ሆኖ እጁን ሰጠ። እዛው ውሎ አደረ።ብቻነቱ ነጻነትን ሰጠው። እሱን ያሉ ከእሱ ቢመስሉ ተከታዮቹ በረከቱ። አርአያነቱ በጎ እንዳልሆነ ቢገባውም ‹‹ይቅርባችሁ›› አላለም። በሥራው ቢገንም ተግባሩ ላይ ሰነፈ።

የእጆቹን ሥራ የሚሹ ባለበት ይፈልጉታል።ባገኙት ጊዜም እንዳያመልጣቸው ቤታቸው እስከ ማሳደር ይደርሳሉ። እዮብ አይጀምረው እንጂ ሥራውን ከያዘው እጅን በአፍ የሚያስጭን ድንቅ ውጤት አጠናቆ ያስረክባል። እሱ ስለነገ አይጨነቅም። የዕለቱን ካገኘ በቂው ነው።አሁን የሱስ ደረጃው ከፍ ብሏል።ይህ እውነታ ክብሩን አስጥሎ ችሎታውን ፈትኖታል።

1995 ዓ.ም ።እዮብ የሕይወት መንገዱን የሳተበት፣ ጤናው የተቃወሰበት ፈታኝ ዓመት። በዚህ ወቅት ብዙ ሰርቶ ብዙ በትኗል፣ ብዙ ደክሞ ብዙ ባክኗል።አንድ ቀን ግን ይህ ታሪክ ‹‹ነበር›› ሊባል ጊዜው ሆነ።እሱን ፈልጎ ካለበት የመጣ አንድ ወዳጁ ከነበረበት አውጥቶ ከአንድ ሥራ አገናኘው።ቦታውን ለቆ ሲርቅ እሱን ብለው የከበቡት የጫት ጓዶቹ ተለዩት።

ግራ ጎን ፍለጋ…

እነሆ እዮብ ከተሻለው መንገድ እየቆመ ነው። ከቆየበት ሥራ ከፍ ብሎ የኢንዱስትሪውን መንደር ተቀላቅሏል።ይህ አጋጣሚ ለብቻው አልመጣም።የእዮብ ዓይኖች ከአንዲት ቆንጆ አርፈው ልቡ በፍቅር ተረቷል።ከዛሬ ነገ ልጅቷን፣ ውበቷን አሳልፋ ለሰጠችው ጉብል ፍጹም ታማኝ ሆኗል።እዮብ ራሱን ሊገዛ ሞከረ።አላቃተውም።ማንነቱን ከሱስ አቅቦ ለክብሯ ተጠነቀቀ።ከእሷ ሲሆን ጥንካሬው ተከተለው።ውሎው ተቀየረ።ልምዱን ተጠቅሞ የኢንዱስትሪ መንደሩን አደራጀ። በጥረቱ ስኬታማ ሆነ።

በነበረው የቀበሌ ቤት ከቆንጆይቱ ጋር አብሮነትን ቀጠለ።ወላጆቿ አላሳፈሩትም።ሽምግልናውን ተቀብለው ሚስቱ እንድትሆን መርቀው ሰጡት።ጎጆው ተቀለሰ፣ አዲስ ሕይወት ተጀመረ።አሁን እዮብ የራሱ ብቻ አይደለም።ለሚስቱ ይጨነቃል፣ ላደራጀው ማህበር ያስባል።

ለፈጠረው አዲስ ሥራ የጠየቀው ብድር ሲሳካ በራሱ ወጪ ዕቃ ገዝቶ ሙያውን አጋራ። ውጤቱ መልካም ሆነለት። ማህበሩ አትራፊ መሆን ሲይዝ አፈንጋጮቹ በዙ፣ ሽኩቻ፣ ንትርክ ተጀመረ። ልፋት ድካሙ መና ቀረ፣ ዓይኑ እያየ ማህበሩ እንደዋዛ ፈረሰ።እዮብ ይህ በሆነ አፍታ ጤናው ተቃወሰ፣ ጨጓራው ደም አነባ፣ የረጋ ደም ከአፉ ተፋ። እርር፣ ድብን አለ። ኀዘን ብስጭት ቢጎዳው ከሆስፒታል አልጋ ተገኘ።

እዮብ ስለሚስቱ አብዝቶ ተጨነቀ።በእሱ ምክንያት ከንቱ መቅረቷ ያስቆጨው ጀመር።ድንገት የሰማው የምስራች ግን ለውስጡ ፈውስ ሆነ።ባለቤቱ ነፍሰጡር ነበረች። ወዲያው ሱስ ይሉትን እርግፍ አድርጎ ሊተወው ወሰነ።ተሳካለት።የመጀመሪያ ልጁን አቅፎ እንደሳመ መካከለኛ ባለሀብት ሆኖ ተመዘገበ።

የእዮብ ኩላሊቶች…

ሩጫው ቀጥሏል።አሁን እዮብ የትናንቱ አይደለም። ታሪኩ ተቀይሮ መልካም አባወራ ሆኗል።ሰፈሩ በልማት ሲፈርሰ ኮንዶሚኒየም አግኝቷል።እሱ ግን ጤና ይሉት የለውም።የደም ግፊት ይዞታል።የራስ ምታት ፣ የልብ ህመም፣ ያሰቃየዋል። በህክምና ክትትል መድኃኒቶችን እየወሰደ ነው። 2006 ዓ.ም ደግሞ ካለፉት ዓመታት የከበደ ሆነበት።

አንድ ቀን ምርመራ ላይ ያገኘው ሀኪም በአስቸኳይ ወደ ሌላ ሆስፒታል ጻፈለት። ሳይውል ሳያድር መሄድ ነበረበት።ዕለቱን ያገኘው ሌላ ሀኪምም ውስጡ እያዘነ ሁለቱም ኩላሊቶቹ መድከማቸውን ነገረው። ስለ ንቅለ ተከላ፣ ዲያሌሲስና ህክምናው ዘረዘረለት። በወቅቱ ያስፈልገው የነበረው ገንዘብ 400 ሺ ብር ነበር። እዮብ ይህን ገንዘብ በእጁ አለ። ግን ለሚስቱ ሊተው ወሰነ ። የተባለውን ትቶ በማስተገሻ መድኃኒት ቢቆይም ህመሙ ብሶ አሰቃየው። ያገኛቸው ሀኪሞች ሁሉ ስለ ዲያሌሲስ ይነግሩታል። የእሱ ልብ ግን ይህን ሊያደርግ አልፈቀደም።ከከፋ ህመሙ ጋር ሲታገል ጊዜያት ተቆጠሩ። እዮብ መሞቱ ላይቀር ቤተሰቡን መበተን አይፈልግም።ሚስጥሩንና ገንዘቡን ለሚስቱ ሸሽጎ ማስቀመጥን ይሻል።

ህመሙ ያሰቃየው ይዟል።አልቻለም።እንደምንም ተመክሮ ህክምናውን ጀመረ።በድንገት ባለቤቱ አወቀችበት። ለወራት ውስጡ ቢቃወስም በጥንካሬ አገገመ። አሁንም ብዙ ያስባል።እንደሱ ዲያሌሲስ የሚያ ደርጉ ምስኪኖች ያሳዝኑታል። አብዛኞቹ ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ ነው። በህመሙ ብዙ ነገራቸውን አጥተዋል።

አምርሮ እያዘነ ርምጃውን አፋጠነ።ፊርማ አሰባስቦ ድምጽ ሆናቸው።ውጣውረዱ ፍሬ ያዘለት።ፈቃድ አወጣ፣ ከሚመለከታቸው ቀርቦ የአደባባይ ሰልፍን አስፈቀደ።ተሳካለት።መስከረም 2008 ዓ.ም በፖሊስ ማርሽ ታጅቦ ፣ በበርካቶች ተደግፎ ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› ማህበርን አወጀ።

እዮብ አቅም የሌላቸውን ለማገዝ በሚቀመጡ ሳጥኖች፣ በየባዛሩ በሚደረጉ ዝግጅቶች፣ ገንዘብ እየለቀመ ለህልውናቸው ታገለ።መጽሄቶች ታተሙ፣ በሚዲያዎች ሰፊ ትኩረት ተቸረው። በዚህ ብቻ አልበቃውም። ብዘዎች እንደሚሉለት ከለውጡ በፊት በከተማዋ ማዕድ ማጋራትን የጀመረው እሱ ነበር። በአረንጓዴ ዐሻራ መረሀ ግብሩም አባላቱ ‹‹እየሞትንም ቢሆን እንደግፍሃለን›› በሚል መርህ ችግኞችን በመትክል ተሳትፈዋል። ከደጋፊዎቻቸው ለመከላከያ ሠራዊቱም ደም እንዲለገስ አድርገዋል።

እዮብ እስኪሞት ቃል ለገባለት ዓላማው ጽኑ ሆኖ እንደቆመ ነው።ማህበሩ አቅም ሲያንሰው ስለ ሌሎች መኖር ሲል ኮንዶሚኒየሙን ሸጧል። ይህን ማድረጉ ፈጽሞ አያስቆጨውም። ከህመም እየታገለ፣ መሮጥ መባከን ልማዱ ነው። ይህ እውነታ ግን ውሎ አድሮ ዋጋ ያስከፍለው ያዘ።

የጉዳት መጠኑ አጥንቱን አሳሳው።አካሉ ክፉኛ ተጎዳ።የእሱን መድኃኒቶች ለሌሎች በማሳለፉ ጠንካራ አግሮቹ ዛሉ ፣ አንድ ዱላ ይዞ መውተርተር ጀመረ።አልተሻለውም።እንደምንም በሁለት ክራንች መጓዙን ቀጠለ።በጀርባ መተኛት ብርቅ ሆነበት።በእጅጉ ታመመ፣ ተሰቃየ።እንዲያም ሆኖ መኪና መንዳቱን አላቆመም።

የአንድ ቀኑ ክስተት ግን ነገሮችን እንዳልነበር ለወጣቸው።እዮብ ክራንቹን ተመርኩዞ ወደ መጸዳጃ እየወጣ ነበር ። በድንገት ሸርተት ብሎ ከመሬቱ አረፈ።አፋፍሰው ከሆስፒታል ቢያደርሱት ብረት እንዲገባለት ሆነ። ይህ ብቻውን አልጠቀመም።ከወገቡ በታች መላወስ ተስኖት ‹‹ፓራላይዝድ›› ሆነ።እዮብ እንዲህ መከሰቱ አሳዝኖታል።አሁንም ግን ለሌላ ዓላማ አልሰነፈም።ማህበሩ ላይ ‹‹ሰላም፣ ጤና›› የሚል ቃል አክሎ ትውልድ በሚቀይር ስያሜ አሳደገው።

እዮብ አካሉ በዊልቸር ላይ ከዋለ በኋላም አልቦዘነም። ድጋፍ ለሚያሻቸው ሁሉ አበክሮ ታግሏል።ኃላፊነቱን በብቃት ተወጥቷል።እዮብ ስለወደፊቱ ታላቅ ዓላማን ሰንቋል። ወደፊት የማህበሩን ምክርቤት መስርቶ ለሌሎች ማስረከብ ፍላጎቱ ነው።

የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የሆነው እዮብ ዛሬም ጠንካራ ሚስቱ ከጎኑ ናት።ኑሮን ለማሸነፍ በሾፌርነት ሙያ ቤተሰቧን እያሳደረች ነው።ቤተሰቡ ዛሬ የግል ቤት የለውም።በቤት ኪራይ ችግር መፈተኑን ይዟል።እሱ በልጅነቱ ያሳለፈው ውጣውረድና የተራመደበት የስህተት መንገዶች በልጆቹ እንዲደገም አይፈልግም። አሁንም ቢሆን ስለሰው በጎ የመሆን ሰብዕናው አይለወጥም።ዲያሌሲሱን እየወሰደ በመልካምነቱ መስመር መጓዙን ይቀጥላል።

‹‹ባለራዕይ አይቆምም››

‹‹ባለራዕይ አይቆምም›› የእዮብን የሕይወት ጉዞ የሚዳሰስ ግለ ታሪክ ነው።ይህ መጽሀፍ የተጻፈው በጠንካራው፣ በልበ ሙሉው የኩላሊት ህመምተኛ እዮብ ተክለመድህን ነው።ገጾቹ ሲገለጡ እዮብ ከልጅነት እስከ ጉልምስና ዕድሜው የተራመደባቸውን ሻካራማ መንገዶች ያሳያሉ። እዮብ ዛሬ አካሉ ቢጎዳም ጥንካሬ አልራቀውም። መልካምነቱ ከእሱ ነው። ስለሰዎች ይኖራል።ስለመኖር ይታገላል። ሕይወትም ትቀጥላለች።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You