ቀናት ሳምንታትን፤ ሳምንታት ወርን ፤ ወራት አመትን እየወለዱ በተንሰላሰለ የጊዜ ሂደት ውስጥ ትውልድ ተፈጥሮ በትውልድ ይተካል። ትውልዶችም ዘመናቸውን በሚዋጅ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሮቻቸው የየራሳቸውን ጥሩም መጥፎም የታሪክ ትርክቶችን ፈጥረው ያልፋሉ። በዚህም በቀጣይ ትውልዶች የሚወቀሱበት ወይም የሚወደሱበት እውነታ ይፈጠራል።
ይህንን ሰብአዊ መስተጋብር ታሳቢ በማድረግም በየትኛውም ዘመን የኖሩ ትውልዶች የመጪ ትውልዶችን ብሩህ ነገዎች ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን ሲፈጽሙ፤ በዚህም የትውልዶችን ቀጣይነት ብቻ ሳይሆን ከትናንት ዛሬ፤ ከዛሬ ደግሞ ነገ የተሻለ ኑሮ የሚኖሩበትን በጎ ኅሊና ፈጥረው፣ ለዚህም በቁርጠኝነት ሲንቀሳቀሱ ማየት የተለመደ ነው።
ይህ ከቤተሰብ የሚጀመረው ትውልዶችን በበጎ ኅሊና ለራሳቸው፤ ለቤተሰባቸው እና ለሀገራችው እንዲጠቅሙ አድርጎ የማብቃት፤ ሰውነታቸውን በተሟሉ ሰብዓዊ እሴቶች ሙሉ የማድረግ ኃላፊነት በእኛም ሀገር ዘመናት ያስቆጠረ ትልቁ ማኅበራዊ እሴታችን ነው፤ የትውልዶችን የመንፈስ ፣ አዕምሮ እና ሥነ ልቦና ስብዕና በመቅረጽ ሂደትም አልፋና ኦሜጋ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ከዚህ የተነሳም እንደ ሀገር በመጣንባቸው የረጅም ዘመናት ታሪክ ውስጥ፤ እንደ ሕዝብ ተቻችሎና ተከባብሮ መኖር ችለናል፤ ይህ ታሪካዊ እውነታ እንደ ሀገር የምንኮራበት ትልቁ የታሪካችን ትርክት ከመሆን አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ደምቀን የምንታይበትና የምንሰማበት መልካችን እና ቋንቋችን መሆን ችሏል። በዘመናት መካከል መጥተው ያለፉ እና ያሉ ትውልዶችም የማንነት ግንባታ ጡብ ሆኗል።
የአሁኑም ትውልድ ቢሆን በብዙ ተግዳሮቶች /ፈተናዎች ውስጥ፤ ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ከፍሎ ለማለፍ የተገደደ ቢሆንም፤ አብዛኛው ማንነቱ የተገነባው የራሱንና የጎረቤቱን፤ የማኅበረሰቡንና የሀገሩን፤ ከዚያም አልፎ የመጪዎቹን ትውልዶች ነገዎች ብሩህ ማድረግ በሚያስችሉ መንፈሳዊ፣ አዕምሯዊ እና ሥነ ልቦና እሴ ቶች ነው።
«ጠላትህን እንደራስህ ውደድ» ከሚለው የክርስትና መንፈሳዊ አስተምሮ የሚገራው ማንነቱ ፤ «ለጎረቤቱ መልካም ሥራ ያልሠራ እንደ አመነ አይቆጠርም» በሚለው የእስልምና ትልቅ እሴት የሚቀዳው መንፈሳዊ ልምምዱ ፤ በበጎ ኅሊና ላይ የተገነባው ማኅበራዊ መስተጋብሩ፤ በየዘመኑ ፈተና ሆነው ከፊቱ የቆሙ የራስ ወዳድነት ዘመን አመጣሽ አስተምህሮዎች እና የፖለቲካ እሳቤዎች ሊፈጥሩ ይችሉ የነበረውን ሀገራዊ ጥፋት መሻገር እንዲችል አቅም ሆነውታል።
ስለ ሀገሩ እና ነፃነቱ ፍጹም ቀናኢ፤ ሁሌም ይህንን ታሳቢ ያደረገ የማንነት ዝግጅት እንዲኖረው ረድተውታል። እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ/ ሕዝብ ከራሱ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ነፃነት የማንቂያ ደውልና የመንፈስ ጽናት እንዲሆን አስችለውታል። በዓለም አቀፍ አደባባዮች ቀና ብሎ የሚራመድበትን የሥነ ልቦና ከፍታ አላብሰውታል ።
በትውልዶች ቅብብል ውስጥ ባለ የማንነት ግንባታ እያለፈ ያለው ይህ ትውልድም ፤ እንደ ትውልድ ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት፤ ከሁሉም በላይ የቀደሙት አባቶቹና አያቶቹ እሱን አምጠው የወለዱበትን በጎ ኅሊና እና ኅሊናው የተገነባበትን እሴቶች በአግባቡ ሊያጤናቸው፤ ሊረዳቸው፤ የራሱ ሊያደርጋቸው፤ ለመጪዎቹ ትውልዶች ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ ሊያጎለብት፤ ሊያሳድጋቸው ይገባል።
አሁን እያጋጠመው ያለውን ተግዳሮት አሸንፎ ፤ ዓይኑን ከፍቶ ያያቸውን ብሩህ ነገዎች የራሱ ማድረግ የሚችለው፤እንደ ማኅበረሰብ ብዙ ፈተናዎችን በጽናት ተሻግረን ዛሬ ላይ እንድንደርስ ያስቻሉንን ፤ ከራስ ወዳድነት ይልቅ ስለሌላው መኖርን መርሕ አድርገው ጸንተው ለቆሙ እሴቶቻችን ተገቢውን ከበሬታ መስጠት ሲችል ፤ በነሱ የመታመን የማንነት ስሪቱን የአደባባይ መገለጫው ሲያደርገው ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም