የምርጫ ዓመት የወረት «ፍካት»

መራር የትዝብት ወግ፤

በሀገሬ ጉዳይ ካልገቡኝ፣ እንዲገቡኝ ብሞክርም እውነቱ ሊበራልኝ ካልቻለባቸውና፣ ለወደፊቱም ቢሆን ግልጽ ይሆኑልኛል ብዬ እጅግም ተስፋ ከማላደርግባቸው በርካታ ብሔራዊ ጉዳዮቻችን መካከል አንዱ የሀገሬ የፖለቲካ ሥሪትና ባህርይ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ሀገሬም ሆነች ፖለቲካዋ “ውል አልባ” ሆነው እንደተወሳሰቡብኝ እነሆ የወጣትነት ዕድሜዬን ፈጅቼ፣ ጉልምስናዬን እየተከዝኩ በመሻገር ወደማይቀረው የአዛውንትነት ቅጥር ውስጥ ለመግባት ወደ ደጃፉ እየተቃረብኩ እገኛለሁ። ነገስ የፖለቲካችን ቅብጥብጥና ቅርጽ አልባ ገጽታ ምን ሊመስል ይችላል? አዋቂዎቹ ፈጣሪና ነገ ሀገሪቱን የሚረከበው ትውልድ ብቻ ናቸው።

ለጊዜው የጃጀውንና የሺህዎች ዓመታት ዕድሜ የሚቆጠርለትን አዛውንቱን የአቴናዊያን የዲሞክራሲ ፍልስፍናና የዓለም አቀፍ ወረራ ታሪክ ለጊዜው ወደ ጎን ገፍተን የዚህቺው የእኛይቱ “ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ ኢትዮጵያችን” ነውጠኛና አብዮተኛ ቀዳሚው ትውልድ “ስለ አማላዩ የዲሞክራሲ ትሩፋት” ድምጹን ከፍ አድርጎ መጮኽ የጀመረበትን ዘመን እንቁጠር ብንል ወደ ስድስት ዐሠርት ዓመታት ዕድሜ መቃረቡን ታሪክን ዋቢ አድርገን መተማመን እንችላለን።

በተለይም ከወቅቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ግቢ ውስጥ ተቀምሞና ተቀነባብሮ፣ በአብዛኛው ውጭ ሀገራት በትምህርት ላይ ይገኙ በነበሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ደምቆና ፈክቶ በሀገራችን ውስጥ የአንደበት ልማድ እንጂ የግብር ባላንጣ በመሆን የባህል ያህል ሥር የሰደደውና ሲያፋጀን የባጀው “ዲሞክራሲ” የሚሰኘው የአፍ ማሟሻ ስለምን ከመንግሥታዊ ሥርዓተ መንበራችን ጋር መላመድ እንዳተሳነው ለመረዳት ግራ ያጋባል። ቆም ብለን ምክንያቱን እንመርምር ብንልም የብሶት ስሜት ውስጥ ስለሚከተን “ተከድኖ መብሰሉ” ሳይሻል አይቀርም።

“ዲሞክራሲዊ የወታደር አስተዳደር ነኝ!” እያለ በኡኡታ ሲያስተጋባ የኖረው የደርግ ሥርዓት በአሥራ ሰባት ዓመት ዘመነ ህልውናው ቆሜለታለሁ ይል የነበረውን ፍልስፍና አፈር አስልሶ እርሱ ራሱም ግባ መሬቱ እንዴት እንደተፈጸመ የትናንት ታሪክ ስለሆነ ብዙም ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም። ከሞቱ አሟሟቱ የከፋው ይህ ወታደራዊ ሥርዓተ መንግሥት ለእልፈት የተዳረገው በ1980 ዓ.ም ያጸደቀው “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ” የሚሰኘውን ሕገ መንግሥት ሳይኖርበት አብሮ በመገነዙ ጭምር ነው። በሕገ መንግሥቱ ውሥት ደመቅ ብሎ የሚታያው ቃል “ዲሞክራሲ” የሚለው መሆኑን ልብ ይሏል።

የደርግ ሥርዓተ መንግሥትን ቀብር አስፈጽሞ መንበረ ሥልጣኑን በአጽሙ ላይ ያደላደለው የወያኔ ኢህአዴግ ሥርዓትም “ዲሞክራሲን” ከየትኞቹም የዓለም ሀገራት ይልቅ ድምጹን ከፍ አድርጎ እያንቆለጳጰሰ በሀገር ውስጥ ለሃያ ሰባት ዓመታት በቆየባቸው ዓመታት ሲፈጸመውና ሲያመረተው የነበረው የግፍ አዝመራ መልክና ዓይነት፤ እንኳን በሕያዋን ምድር ቀርቶ በሲዖል ውስጥም ቢሆን ሳጥናኤል ይፈጽመዋል ተብሎ እስከሚያጠራጥር ድረስ ሀገሪቷንና ሕዝቧን ከምን ዓይነት መከራ ውስጥ ከትቶ እንደነበር ምድርም ሰማይም ምስክሮች ናቸው።

ይሄው ኢህአዲጋዊ ሥርዓትም ከህዳር 1987 ዓ.ም ጀምሮ እንደ መርግ አሸክሞን ያለፈው “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” የሚል ሕገ መንግሥት መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ዲሞክራሲ በሚል “ማዕረግ” የተለበጠውን ሕገ መንግሥት ዛሬም ድረስ በጫንቃችን ላይ እንኮኮ ብለን እየተንገዳገድንም ቢሆን እንደተሸከምነው አለን። የትኛዋ ድምጻዊት ነበረች፡-

“ሃሳብ እሹሩሩ ውረድ ከጀርባዬ፣

መሸከምም አልችል አፈር ነው ሥጋዬ” በማለት ያንጎራጎረችው? እኛ ግፉዓን ዜጎች “ሃሳብ እሹሩሩ” እያልን የምናንጎራጉረው ወቅታዊ የስሜት ሕመማችንን ለማስታመም ብቻ ሳይሆን ህልሙም ፍቺውም በጠፋብን በርካታ ብሔራዊ ጉዳዮች ግራ በመጋባት ውስጥ ተዘፍቀን ጭምር ነው። “ኦ ዲሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!” በማለት ቀደም ላለው አንደኛው ጽሑፌ የተጠቀምኩበት ርዕስ ዛሬ ከርዕስነት ከፍ ብሎ የዘወትር ብሶት መገለጫ እስከመሆን ደርሷል።

ብሩህ ዘመን ተመኝተን የሰላም ጥማችንን ለማርካት “ዋንጫ ነዎር!” እያልን መነቃቃት ስንጀምር እንደ ፍርጃ የተፈጸሙትና እየተፈጸሙብን ያሉ ብሔራዊ መከራዎቻችን ብዛት በአንድ ሺህ አንድ ሌሊት ተተርከው የሚጠናቀቁ ስላይደሉ እንዲሁ ብቻ በእህህ እንደቆዘመን ውስጣችን ነፍሮ እንደታመመን አለን። እኮ ምን ቢነካን? ምን ብንሆን ነው ችግሮቻችንን እንደ ትቢያ ከላያችን ላይ ከማራገፍ ይልቅ እርስ በራሳችን እየተፋለምን ጥሎ በመውደቅ ላይ ሙጭጭ ያልነው? ኢትዮጵያ ሆይ ጽናቱን ይስጥሽ።

“ምነው ሁሌ እንግዳ በመጣ!”

የባልና ሚስት ወግ፡- በጋብቻ የተጣመሩ የአንድ ቤተሰብ ባለትዳሮች ያለመታደል ሆኖ ሦስት ጉልቻ ከጎለቱበት ዕለት ጀምሮ ለፍሬ እስከበቁበት ዕድሜ ድረስ በሰላም ኖረው አያውቁም ይባላል። ጥሎባቸው አባወራውም ሆነ እማወራዋ በፍጹም ተግባብተው የሚያደርጉት አንዳችም ነገር የለም – ይለናል ሀገራዊ የአዛውንቶች ወግ።

እነዚሁ ባልና ሚስቶች ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ፣ በውሎ አምሽቷቸው ንትርክ የቤታቸው ባህል ሆኖ ስር ቢሰድም እንግዳ በመጣ ቁጥር ግን ደስተኛ ለመምሰል “በወዳጆቻቸው ፊት የሚጠራሩት እከልዬ፣ ውዴ፣ ማሬ፣ ወለላዬ” እየተባባሉ ነበር። ድንገት ባልን በእንግዶች ፊት ካስነጠሰው “ትንታህን ለእኔ ያድርገው” በማለት ሚስት ፈጥና አቅፍ አድርጋ ታባብለዋለች።

ሚስቱ እንግዶችን ለማስተናገድ ወዲያ ወዲህ ስትል ድንገት ካነቀፋትም ባል ሆዬ ፈጠን ብሎ “ለእኔ ያድርገው” በማለት ዘሎ ይጠመጠምባታል። ይህንን ያስተዋሉ እንግዶቻቸው የባልና ሚስቱ “ተውኔታዊ ድርጊት” እውነት እየመሰላቸውና እያደናነቁ “ትዳር ማለት የእነርሱ ብቻ ነው” በማለት ሲያመሰግኗቸው ኖረዋል።

ይህ “ድራማዊ ክስተት” ትርጉም አልሰጠው ያለ ባል አንድ ቀን የጥሞና ጊዜ ወስዶ “ፈጣሪ ሆይ በሰላም እንድኖር ከፈለግህ እንግዶችን በላይ በላይ አዥጎድጉድለኝ” ብሎ ጸለየ ይባላል። ሚስትም እንዲሁ በለሆሳስ ተማጽኖ “አምላኬ ሆይ! ምን ቢቸግረን መስተንግዶውን እንደምንም ብለን ስለምንወጣው እንግዶችን ከቤታችን አታሳጣን” ብላ ተሳለች ይባላል።

“ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ” ብዬ የሞራል ትምህርቱን እንዲያሰላስሉ ለአንባቢያን ዕድል ለመስጠት ጽሑፌን እዚሁ ላይ ብገታ በወደድኩ ነበር። ገና በዋናው ሃሳቤ ላይ ጫን ስላላልኩ የሞራል ትምህርቱን ለማብራራት እጅግም አስፈላጊ አልመሰለኝም። ለማንኛውም ግን እንግዶች እግራቸውን ገና ወጣ ሲያደርጉ “ወደ ቆምንበት ባህርያችን እንመለስ” እንደሚባባሉት ባልና ሚስት የእኛም ሀገራዊ ጉዳይ ዝርዝር ባያስፈልገውም እንዲዚያ ይመስለኛል።

“ምን ነበረበት ዓመቱ በሙሉ ሀገራዊ ምርጫ ቢከወንበት!i?”

ሁሉንም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የምመስለው በአደይ አበባ ነው። ወቅቱም ወራቱም ሃሳቤን ስለሚያጎለብትልኝ በመስከረም ወር ላይ ሆነን አማላዩዋን የአደይ አበባና የፖለቲካችንን ባህርይ እያነፃፀርን ብናወራ ግር ሊለን አይገባም። በመሆኑም በመጀመሪያ ስለ አዲስ ዓመቷ ማብሰሪያ ሀገራዊ የአደይ አበባችን ባህርይ ጥቂት ልበል። ይህቺ የመስከረምና የጥቅምት አበባ አብባና ፈክታ የምታማልለን ለጥቂት ሣምንታት ያህል ብቻ ነው። በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢማ ከጥቅምት በኋላ ለመድኃኒት እንኳን ብትፈለግ ላትገኝ ትችላለች።

ዕንቁጣጣሽን በተሰናበትን ማግስት እርሷም መልኳና መዓዛዋ ረግፎና ነጥፎ በመክሰም አብራ እብስ ትላለች። የአደይ አበባ ፍካትና ውበት መስክ ላይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ቤት ውስጥ ቀጥፈው አምጥተው ልክ እንደ ጓደኛዋ እንደ ጽጌሬዳ አበባ በተዋበ የአበባ ማስቀመጫ (Vase) ውስጥ አሽሞንሙነው ቢያስቀምጧት ወይንም በቤት ወለል ላይ ጎዝጉዘው እንድመቅባት ቢሉ በውበቷ እያማለለች ልትቆይ የምትችለው ለአንድ ቀን ወይንም ለሰዓታት ያህል ብቻ ነው። ወዲያው ጥውልግልግ ብላ ትደርቃለች፤ ከስማም ትጠፋለች።

የሀገሬን ፖለቲከኞች በአደይ አበባ የመስልኳቸው ያለብልሃት አይደለም። ምርጫ በመጣ ቁጥር የዲሞክራሲን፣ የፍትሕን፣ የሰብዓዊ መብቶችን ክብርና ዋጋ እየለፈፉ ሲያማልሉን መመልከት የተለመደ ነው። እነርሱ የሚመረጡ ከሆነ ለመረጣቸው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለሚቃወሟቸውም ጭምር ዲሞክራሲን “ያለ ገደብ በማፍሰስ” ሀገሪቱንና ሕዝቧን ወደ ላቀ ከፍታ በማሸጋገር የታዳጊነት ሚናቸውን እንደሚወጡ የሚሰብኩን ልኩን እያለፉ ጭምር ነው።

በየሚዲያው ሲወጡም አረፋ እየደፈቃቸው ጭምር በፖለቲካ ማኒፌስቷቸው እየማሉና እየተገዘቱ ለሕዝብ እንደሚቆሙና “ከራሳቸው በፊት ወገናቸውን” እንደሚያስቀድሙ “ድንጋይ ነክሰው” ሲምሉና ሲገዘቱ ዕድሜ ደጉ ብዙ አሳይቶናል።

የምርጫ ወራት አልፎ ሥልጣንና ወንበራቸውን ባደላደሉ ማግሥት ግን ትከሻቸው እያበጠና ድምጻቸው እየጎረነነ አየር ላይ ተንሳፈው ሕዝቡን ቁልቁል ማየት ይጀምራሉ። ነገሩ ቁልቁል በማየት ብቻ ቢወሰን በተሻለ ነበር፤ ከዚህ የሚከፋው ከፍ ብለው ከወጡበት ተራራ አናት ላይ ቆመው ቁልቁል በሕዝብ ላይ የመከራ ናዳ በማዝነብ “በጊንጥ ልንገርፋችሁም እንችላለን” እያሉ ጮክ በማለት ማስፈራራታቸው ጭምር ይፋ ቢገለጽ ሀሰት አያሰኝም።

ለመመረጥ የተሸቆጠቆጠ ሁሉ፤ መንበሩን ካደላደለ በኋላ ፈጥኖ የሚታየው ራሱንና ኪሱን እንዴት እንደሚያሳብጥ ብቻ ነው። ስለዚህም ነው ልክ እንደ አደይ አበባዋ ምርጫ በመጣ ቁጥር አማልለውን ፈጥነው የሚከስሙት። “ምነው ሁሌም የምርጫ ሰሞን በሆነ” ብለን የምንመኘውም ቢያንስ የለሰለሰ ቋንቋቸው ዛሬ ከምናደምጠው የጭንቀት ዜና በእጅጉ ስለሚሻል ነው።

እኒያ በምርጫ ሰሞን በየቄያችን እየተገኙ “በመላእክት ቋንቋና ትህትና” እንድንመርጣቸው ሲቅለሰለሱ የነበሩ “እንደራሴዎቻችን” በችግር ማራኪነት የውጥር ተይዘን መላው ሲጠፋብን ወዴት ተሰወሩ? ከፍ ባለ የሸንጎ ወንበራቸው ላይ ተሰይመው የምናያቸው ሁሉ ዛሬ ድምጻቸው ስለምን ራቀን? የመረጥናቸው ለእኛ “እንደራሴ” እንዲሆኑ ነው ወይንስ “እንደራሳቸው” እንዲሆኑ? ቢያንስ ክርስቶስ ራሱ “‹ጠይቁ ይመለስላችኋል›፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል” የሚል ድፍረት ለደቀመዛሙርቱና ለእኛ ለሃይማኖቱ ምዕመናን እንድንተገብረው ስለፈቀደልን ምድራዊ መንግሥታችንም ይህንን መሰሉን ጥያቄ ስለምን ትጠይቃላችሁ ብሎ ፊቱን እንደማያጠቁርብን ተስፋ እናደርጋለን። ስለምን ቢሉ “መንግሥታችን ዲሞክራሲያዊ” ስለሆነ ሥጋት አይገባንም።

የገዢው ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ ሲያሻን ተፎካካሪ፣ ስንፈልግ ተቃዋሚ እያልን በተለዋጭ ስሞች ስናነሳና ስንጥላቸው የምንውለው ፖለቲከኞች ዝምታም በእጅጉ ግራ የሚያጋባ ነው። በምርጫ ሰሞን ምድሩም ሰማዩም አልበቃ ብሏቸው እንደማይቦርቁ ሁሉ በሀገር ላይ መከራ ሲዘንብ ዝም በማለት እንደ እኛ እንደ ተራ ዜጎች በአደባባይ ከመሟገት ይልቅ ስለምን ሱባዔ እንደሚመርጡ ግልጽ አልሆነልንም።

ሀገራዊ ችግሮች ሲከሰቱ “በመነጋገር እንተማመናለን እንጂ የፍልሚያ ሸማ አንጣጣልም” ያሉትን ቃላቸውን ዘንግተው “ውሻን ምን አገባት ከእርሻ” እንዲሉ ድምጻቸውን አጥፍተው ይሸሸጋሉ። የኢኮኖሚው ምህዳር የናስ ወስከንባይ ሆኖ አናታችን ላይ ሲደፋ ለሕዝቡ ችግር መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ አብረውን ያላዝናሉ። ስለ ትምህርት ጥራት፣ ስለ ፍትሕና ርትዕ በአደባባይ እንቆምላችኋለን ብለው እንዳልፎከሩት ሁሉ የቁርጥ ቀን ሲመጣ “የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ” እንዳለችው ኮረዳ የእርስ በእርስ ገመናቸውን እየዘከዘኩ “ጆሯችንን ጭው” ያደርጋሉ።

ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሕመም ጨክኖ የመፍትሔ መድኃኒት ከመፈለግ ይልቅ ፖለቲከኞቻችን በሙሉ ሩቅ ለሩቅ ቆመው በሀገሬ ሕመም ሲሳለቁ መመልከት ተስፋ ማስቆረጥ ብቻ ሳይሆን እነርሱን በመምረጣችን በፀፀት እንድንቀጣ ምክንያት እየሆኑ ነው። ምንም እንኳን ፖለቲካ የጥሎ ማለፍ “ድሪያ” መሆኑ ቢገባንም እንደአሁኑ ዘመን መልከ ጥፉው ገጽታው እንዲህ አግጥጦ ያስፈራራናል ብለን ስለማሰባችን ግን በግሌ እርግጠኛ አይደለሁም።

ችግሮቻችንን በመነጋገርና በመቀባበል ስለምን ለመፍታት ተሳነን? በእልህ የወዛ የፖለቲካ ባህል ኢትዮጵያን የት ሊያደርሳት ይችላል? እልሃችን ምላጭ ቢያስውጠንም ዞሮ ዞሮ ግን የዋጥነው ስለት ምን ውጤት እንደሚያስከትል ለማንም ይጠፋዋል ተብሎ አይገመትም። ውሉ የጠፋው ይህን መሰሉ ሀገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳያችን ነው ያልገባን፣ ይገባናል ብንልም የሚወሳሰብብን፣ ለወደፊቱም ይገባናል ብለን ተስፋ ለማድረግ የተቸገርነው። ኢትዮጵያዬ ሆይ ጽናቱን ይስጥሽ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You