ተደራሽነቱን በማስፋት የሀገር ኩራት የሆነው ባንክ

በሀገሪቱ የባንክ አገልግሎትን በማስተዋወቅ እና በማዳረስ ግንባር ቀደም ነው። በኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ ላይም አሻራውን በማኖር 80 ዓመታትን ተሻግሯል። አዛውንቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሪፎርም ሥራዎቹ እየታደሰ አዳዲስ አገልግሎቶችንና አሰራሮችን በማምጣት አድማሱን እያሰፋ በአገልግሎትና ተደራሽነቱ የሀገር ኩራት ሆኗል።

ከዘመኑ ጋር ዘምኖ በዕድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰ ያለው ባንኩ፣ እንደ ሀገር የገጠሙትን በርካታ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻለ ቀዳሚ የፋይናንስ ተቋም መሆኑን ባንኩ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።

እ.ኤ.አ በ2025 ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ባንክ ለመሆን እየተጋ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከከፍታው ከፍ ብሎ የፋይናንስ ተቋማት ዋርካ መሆኑን ቀጥሏል። ባንኩ ሁለገብ የባንክ አገልግሎት በመስጠት እያስመዘገበ ካለው ስኬት ባለፈ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣም ይገኛል። በተለይም የሀገሪቷን ችግሮች በከፍተኛ መጠን ማቃለል ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ ግዙፉ ፕሮጀክቶች ውስጥ የጎላ አበርክቶ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሙ አሮጌ የተባለውን 2015 ዓ.ም በስኬት ማጠናቀቅ እንደቻለ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ይገልጻሉ። ፕሬዚዳንቱ የ2016 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት ባንኩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች እየተፈተነ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደቻለ ተናግረዋል።

ባንኩ፤ በአገሪቷ የኢኮኖሚ አውድ ውስጥ ሆኖ የሚሠራ እንደመሆኑ ኢኮኖሚው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ በሆኑ ችግሮች ሲፈተን ቆይቷል። በአገር ውስጥና በውጭ የተፈጠረው ጦርነት የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስና በሀገሪቱ ያለው ችግር እጥፍ ድርብ እንዲሆን አድርጓል። ዓለም አቀፍ ጫናው 300 ዶላር ይገዛ የነበረውን ማዳበሪያ 1100 ዶላር እንዲገዛ ማድረጉ፣ የእህል ዋጋ እንዲጨምርና የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ አይነተኛ ድርሻ ነበረው። ይሁንና ባንኩ እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመቋቋም የማዳበሪያ ግዢን ጨምሮ ግዙፍ በሆኑና የሀገሪቷን ችግሮች ማቃለል ይችላሉ ተብሎ በታመነባቸው ፕሮጀክቶች እንደ ገበታ ለሀገር፣ ህዳሴ ግድብና በሌሎች ዘርፎችም የጎላ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል ሲሉ ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል፤ ባንኩ በዓባይ ግድብ ሰፊ ሥራ የሠራበትና ብዙ የለፋበት እንደሆነ ጠቅሰው፤ 90 በመቶ የኢንቨስትመንት ድርሻ እንዳለውና በዕቅዱ መሰረት እየሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።

‹‹ባንኩ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ትላልቅ የስትራቴጂ ኮሞዲቲ የሆኑ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ሌሎችም የምግብ ዘይትና ስኳር የመሳሰሉትን ሸቀጦች ማቅረብ መቻሉ ተአምር ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ምናልባትም ሙሉ ሰላም ኖሮ በሙሉ አቅም በሁሉም ጥጋ ጥግ ገብቶ መሥራት ቢቻል ከዚህም በላይ ስኬታማ መሆን ይቻል እንደነበር አስታውቀዋል፤ የዓለም ሰላም ማጣት ለኢትዮጵያም ሰላም ማጣት አንድ ምክንያት እንደመሆኑ ሁሉም ሰው ለሰላም ሊተጋ ይገባልም ብለዋል።

ባንኩ ያስመዘገባቸው ዋና ዋና ስኬቶች

‹‹የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከቀደሙትና ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ አገራት ተርታ መሰለፍ መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ‹‹ለዚህም ባንኩ ከአንድ ዓመት በፊት የጀመረውን የሪፎርም ትግበራ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ችሏል። በፓይለት ደረጃ ከተጀመሩ አስር ቅርንጫፎች ጀምሮ ወደ 200 የባንኩ ዋና ዋና ቅርንጫፎች በአዲሱ የባንክ ኦፕሬቲንግ ሞዴል ሥራ ተጀምሯል። የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ስትራክቸርና ቅርንጫፍም እንዲሁ ደንበኛን ማዕከል ባደረገ አወቃቀር ሥራ መጀመር ችሏል። 20 ከሚደርሱ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ሦስት ሺ500 የሚደርሱ ሠራተኞች ወደ ዋናው መስሪያ ቤት አዲሱ ቢሮ እንዲገቡ ተደርጓል›› ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ግዙፉ ባለ 53 ፎቅ አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንጻም ልዩና የከተማዋ ፈርጥ መሆን የቻለ ህንጻ ነው። ህንጻው በዋናነት ለባንኩ ዋና መስሪያ ቤትነት የሚያገለግል ሲሆን፤ በተጨማሪም ለማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ሱቆች፣ ሬስቶራንቶች፣ የሲኒማና የመዝናኛ እንዲሁም ትላልቅ የስብሰባ አዳራሾች ይገኙበታል። ከቢሮ ውበት በተጨማሪ የባንኩ ሠራተኞች አለባበስም እንዲሁ ያማረና የተዋበ ሆኗል። ሁሉም የባንኩ ሠራተኞች በሙሉ ጥቁር ሱፍና በነጭ ሸሚዝ እንዲሁም ወርቃማ በሆነ ከረቫት ሆነው ደንበኞቻቸውን የሚያገለግሉ ይሆናል። ይህም የባንኩ ደንበኞች የባንኩን ሠራተኛ በቀላሉ ለይቶ መስተናገድ እንዲችል የሚያግዝ ነው።

ዓመቱ ግዙፉን ህንጻ ከማጠናቀቅ በተጨማሪ ልዩ ቅርንጫፍ የተከፈተበት የስኬት ዓመት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ ከ200 እስከ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የሚከፈቱ መሆናቸውን አስታውሰዋል። አሁን ላይ ግን ከዋናው ቢሮ አቅራቢያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹ዐቢይ ቅርንጫፍ›› በ2ሺ560 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ መከፈቱን ተናግረዋል።

ዐቢይ ቅርንጫፉ ዲጅታል ቴክኖሎጂን በሙሉ አቅሙ የታጠቀና ዓለም የደረሰበትን ቴክኖለጂ በሙሉ የያዘ ቅርንጫፍ ነው። ከቅርንጫፍ በዋናነት ከሚሰጠው የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ የኮርፖሬት ባንኪንግ ትላልቅ ደንበኞች የሚስተናገዱበት ከመሆኑም በላፈ ደንበኞቹ እንደ ቢሮ መገልገል የሚችሉበትና የባንኩ ታላቅ ቅርንጫፍ በመሆኑ ዐቢይ ቅርንጫፍ በማለት መሰየሙን አመላክተዋል።

የባንክ ተደራሽነትና ዲጅታላይዜሽን

‹‹የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል አካባቢ የባንኩ አጠቃላይ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ግብይት ከ23 በመቶ የሚበልጥ አልነበረም። ይሁንና በተጠናቀቀው 2015 ዓ.ም በዲጅታል ቴክኖሎጂ የተደረገው ገንዘብ ልውውጥ 66 በመቶ መድረስ ችሏል›› ብለዋል፤ ይህም በገንዘብ ሲለካ ሦስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ደንበኞች ወደ ባንኩ ሳይመጡ በቤታቸውና ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲያንቀሳቅሱ ማድረግ አስችሏል። ባንኩ የነዳጅ ግብይትን ለመደገፍ በሲቢኢ ፊውል አፕና በነዳጅ አፕሊኬሽን በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የባንክ ተደራሽነት ሊኖረው ይገባል በሚል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በበጀት ዓመቱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም ሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ 127 ሺ ለሚደርሱ ተበዳሪዎች ከስምንት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ማበደር ተችሏል፤ አመላለሱም ውጤታማ ነበር። የገንዘብ ዝውውሩ ሲጨምር መሰረተ ልማቱ ላይ ጫና የሚፈጠር በመሆኑ እሱንም በማጎልበት ብዙ ሥራ ተሰርቷል። ከክልል መንግሥታት፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከመንግሥት ተቋማት ጋር የዲጅታል ክፍያ አገልግሎትን ማስፋት ሥራ በሰፊው ተሠርቷል። በካሽ የሚገዙ የመንግሥት ግዢዎችን በማስቀረት በካርድ የሚፈልጉትን ግዢ መፈጸምና መቆጣጠር እንዲችሉ ተደርጓል። ይህም በበጀት ዓመቱ ከተሰሩ ሥራዎች መካካል በስኬት የሚጠቀስ ነው።

በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ሀዋላን ማስገባት የሚያስችል ‹‹ኢትዮ ዳይሬክት›› የሚባል አፕሊኬሽን ሥራ ላይ የዋለበት ዓመት እንደነበር የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህም በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ለቤተሰቦቻቸው ሃዋላ ካሉበት ሆነው በነጻ መላክ የሚያስችላቸው አሰራር ስራ ላይ የዋለና አሁን ሊጠቀሙበት የሚያስችላቸው ነው።

የባንኩ ተቀማጭ፣ ብድርና የብድር አመላለስ

ከአንድ ዓመት በፊት አጠቃላይ የባንኩ ሀብት አንድ ትሪሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ብቻ ከአንድ ትሪሊዮን ብር ያለፈ በመሆኑ የበጀት ዓመቱ አንዱ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል። ከዚሁ ገንዘብ ውስጥም 151 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ብድር መስጠት ስለመቻሉ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ባንኩ ከዚህ ቀደም ከ80 እስከ 85 በመቶ የሚያህለውን ገንዘብ ለመንግሥት ተቋማት ያበድር የነበረ መሆን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን 77 በመቶ ያህሉን ብድር ለግል ተበዳሪዎች መስጠት እንደተቻለ አስረድተዋል። ይህም ባንኩ እንደ ልማት ተቋም ተቀማጭ ገንዘቡን ከግል ወስዶ ለመንግሥት ይሰጣል የሚለውን አመለካከት መቀየር አስችሏል ነው ያሉት።

‹‹በቀጣይም ባንኩ የልማት ሥራው እንዳለ ሆኖ አብላጫውን ብድር በግል ንግድ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ያበድራል›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ልማቱ የሚመጣው የግሉ ዘርፍ በሚያንቀሳቅሰው ቢዝነስ በመሆኑና የባንኩ አዲስ ስትራቴጂ መሆኑንም አመላክተዋል። ባንኩ ያበደረውን በመሰብሰብ ረገድም ዓመቱ ስኬታማ እንደነበር ነው የተናገሩት።

እሳቸው እንዳሉት፤ በብድር ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ 141 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ ገቢም 119 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፤ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገብ ችሏል። የባንኩ ደንበኞች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት 41 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች አሉት። ይህም በአገሪቱ የባንክ ሂሳብ ሊኖረው ከሚችለው ከ60 በመቶ ሰው በላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ አለው ማለት ነው። በውጭ ምንዛሪም እንዲሁ ከሶስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋውን ለማዳበሪያ ወጪ ማድረግ ተችሏል። በብድርም እንዲሁ ባንኩ ለማዳበሪያ ግዢ የሚውል 50 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቷል።

ማኅበራዊ ኃላፊነት

ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ለተለያዩ ተቋማት እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል። በጦርነት ማግስት ብዙ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሰረት በተለይም በአማራና በአፋር ክልል ለሚገኙ ዜጎች 367 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። ‹‹ገበታ ለትውልድ›› በሚል ፕሮግራም መንግሥት ያደረገውን ጥሪ ለመቀላቀል አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በአንድ ቀን በመክፈል የአገር ኩራት መሆኑን አስመስክሯል። በችግኝ ተከላም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ችግኞችን ከዋናው መስሪያ ቤት እስከ ቅርንጫፍ የሚገኙ የባንኩ ሠራተኞችን በማስተባበር ተተክሏል።

በቀጣይም ባንኩ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ የበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል የተመዘገበው ስኬት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚሠራ ይሆናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሪፎርሙን መሰረት በማድረግም እየተገዙና እየተተገበሩ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን የበለጠ ወደ መሬት በማውረድ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት የቴክኖሎጂ መሪነቱን ያረጋግጣል ብለዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ሀብት ማምጣት የባንኩ ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ ተቀማጭ ገንዘብ በማምጣት የውጭ ምንዛሪ ማሰባሰብና በብድር የሚሰጠውን ገንዘብ በወቅቱ በመሰብሰብ ጠንክሮ ይሠራል። በተያያዘም አራቱን የሪፎርም ምሰሶዎች ማለትም ደንበኛን ማዕከል ማድረግ፤ በዲጅታል መሪ የመሆን ቁልፍ ተግባራትና ገቢ መጨመር ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራባቸው ሲሆኑ፤ ከሌሎች እንደ ኢትዮ ቴሎኮም ሳፋሪ ኮም ጋር በጋራ በመተባበር በሰፊውና በሁሉም አማራጮች ህዝቡ ጋር ለመድረስ ትልቅ ጥረት ይደረጋል።

ነጻ አገልግሎት በመስጠት ለባንክ ኢንዱስትሪው መንገድ ያሳየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ካሉት 1937 ቅርንጫፎች መካከል አትራፊ የሆኑት ከአስር በመቶ የሚበልጡ አይደሉም። ቀሪዎቹ በሙሉ ለህዝብ አገልግሎት ለመስጠት የተከፈቱ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፤ በቀጣይ ይህ አሠራር የሚዘልቅ አለመሆኑን ተናግረዋል። በተለይም መንግሥት የባንክ ዘርፍን ለውጭ ባንኮች ጭምር በሚፈቅድበት ጊዜ አሰራሩን ዓለም አቀፋዊ ያደርጋል። በዚህም የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ከውጭ ባንኮች ጋር ተወዳድሮ ሌሎች ባንኮች የደረሱበት ደረጃ መድረስ የአዲሱ ዓመት ዕቅዱ እንደሆነም አብራርተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You