ያልጎበጡ ትከሻዎች…

ልጅነት…

ልጅነቷን ተወልዳ ባደገችበት የእናት አባቷ ቤት አሳልፋለች። የዛኔ ሕይወት ለእሷ መልካም የሚባል ነበር። ይህ ዕድሜ ከእኩዮቿ የቦረቀችበት በደስታ ተጫውታ ያለፈችበት ነው። ዛሬ ላይ ቆማ ትናንትን ስታስብ ያለፈው ታሪክ በነበር ይታያታል። ልጅነት የእሷነቷ ልዩ ትዝታ ነው።

ከፍ ማለት ስትጀምር ውበቷ መጨመር ያዘ። ‹የአካሏ ለውጥ በገሀድ ታየ። እንዲህ በሆነ ጊዜ እሷን የሚያዩ ዓይኖች በረከቱ ። ጋብቻን የሚሹ ዝምድናዋን ፈለጉ። ወላጆቿ ለትዳር ከጠየቋቸው ብዙዎች ለአንደኛው ውስጣቸው ፈቅዶ ይሁንታን ቸሩት። ወደው፣ መርቀው ልጃቸውን ሰጡት።

መኪያ መሐመድ እንደገጠሩ ባህልና ወግ ተዳረች። ውላ አድራ ግን ከአካባቢዋ የምርቅበት ምክንያት ተፈጠረ። መኪያን ከጉራጌዋ ምድር ‹‹አውድ›› ቀበሌ መሀል አዲስ አበባ ያመጣት የትዳሯ ጉዳይ ነበር። የዛኔ ከገጠር ወደ ከተማ ስትገባ ብቻዋን አልነበረም። የትዳር አጋሯ ባለቤቷ አብሯት ነበር።

ይህ የሆነው ከዓመታት በፊት ነው። መኪያና ባለቤቷ የትውልድ ቀያቸውን ለቀው አዲስ አበባ ሲመጡ መተማመኛቸው ሠርቶ ማደር ብቻ ሆነ። እንዲያም ሆኖ ሁለቱን በአንድ ጎጆ የሚያሳድር አቅም አላገኙም። መኪያ ከባሏ ተነጥላ አክስቷ ቤት ልትኖር ግድ አላት። የግላቸው እየሮጡ ኑሯቸውን ሊደጉሙ ሞከሩ።

ችግር የፈታው ጎጆ…

ሁለት ዓመታት በዚህ ልፋት ድካም ታለፈ። ጥንዶቹ እንደ ባልና ሚስት ከአንድ ቤት ሳይድሩ ጊዜያትን ቆጠሩ። ውሎ አድሮ ግን እንደአቅማቸው ለመኖር ወስነው ጎጆ ወጡ። በመጀመሪያዎቹ ወራት ሕይወት እንደታሰበው አልቀለለም። ካልሲዎች እያዞረ የሚሸጠው አባወራ ሚስቱን ይዞ ራሱን ለመቻል ጥቂት ተንገዳገደ።

ውሎ አድሮ ግን ሁኔታዎች ተለወጡ። የባልና ሚስቱ ተሳስቦ ማደር ቤታቸውን አቀናው። በድካም ውሎ የሚገባው ባል የሚስቱ ፍቅር፣ አገዘው። የእሱ መልካምነት ጎጆውን ሞላው። መኪያ ባለኔቷን ታከብራለች፤ ይህን ማድረጓ በምክንያት ነው። እሱ ደግና የዋህ ነው። ሚስቱን አያበሳጭም፣ ቤት ጎጆውን አይበድልም።

የጥንዶቹ ሕይወት በብቸኝነት አልቀጠለም። ጎጆ ትዳራቸው በልጅ ስጦታ ተባርኳል። አሁን ሁለቱም ከቀድሞ ይበልጥ መሮጥ አለባቸው፤ ሦስት ነፍስ በወጉ ይኖር ዘንድ የሕይወት ትግሉ ግድ ሆኗል። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ሕፃኑን ማሳደግ እየከበዳቸው ነው። ሁሉን ያልቻሉት ጥንዶች አሁንም ከዘመድ ቤት ተመልሰዋል።

አባወራው ሚስቱንና ልጁን አጥግቦ ፣ የዕለት ወጪውን ለመሸፈን እረፍት ይሉትን አያውቅም። ማልዶ እንደወጣ የሚሸጠውን ይዞ ሲዞር ይውላል። ተመልሶ ቤት ሲገባ ግን ድካም ልፋቱን መርሳት ልማዱ ነው። የሚስቱ ፈገግታ ‹‹አይዞህ ባይነት›› ርቆት አያውቅም።

ባልና ሚስቱ ልጃቸው በወግ ያድግ ዘንድ ሀገር ቤት ልከዋል። አሁን በሁለቱም ትከሻ የሚወድቅ ከባድ ኃላፊነት እያሮጣቸው ነው። ባል በንግድ፣ ሚስት በልብስ አጠባው ሲለፉ ይወላሉ። አንዳንዴ የመኪያ ባለቤት ውሎ ሲገባ የተለየ ድካም ፊቱ ይታያል። ልቡን ደግፎ ይጨነቃል፣ ራሱን ይዞ ይተክዛል። ሚስት የባሏ ህመም ቢያሳስባት ስትተክዝ ታድራለች። ማግስቱን ሁሉም ሰላም ይሆናል። ሁለቱም ቸር ተሳስበው ይለያያሉ።

ልጆችን በችግር

አሁን መኪያ ሌላ ልጅ ጨምራለች። ኑሮ ቢወደድ፣ ቢከፋም ሕይወት በእነሱ ቤት እንደቀድሞው ነው ። አሁንም ሁለተኛው ልጅ ገጠር ተልኮ ሩጫው ቀጥሏል። የባል ባህርይ አንዳች አልተለወጠም። ዛሬም ከነድካሙ ስለቤተሰኑ አብዝቶ ይጨነቃል። አሁንም ስለራሱ ስለሚስቱ መኖር ከልብ ያስባል።

አልፎ አልፎ ብቅ የሚለው የአባወራው ህመም የመኪያ ጭምር ሆኗል። እንዲህ በሆነ ቁጥር በደግ ባሏ ጭንቅ አብራ ትታመማለች። መለስ ሲልለት ፊቷ ይፈካል። አንደበቷ ይፈታል። ባልና ሚስቱ አዲስ አበባ ያመጣቸው ሕይወት ሌት ተቀን እያለፋቸው ነው። አሁን የአራት ቤተሰብ ሕይወት ያሳስባቸዋል። አንዱን ሲሞሉት ሌላው እንዳይጎድል፣ እንዳያፈስ ይጥራሉ፣ ይለፋሉ።

አባወራው ከበሽታው እየታገለ ነው። የሚመላለስበት ችግር የልብ ህመም መሆኑን አውቆታል። በየቀኑ ስለቤተሰብ ማሰቡ ህመሙን እያባሰው ነው። ሁሌም የሚስቱ ነገር ያስጨንቀዋል። እንደ አባት የልጆቹን ዓይን እያየ፣ ጉንጫቸውን እየነካ፣ አለመሳሙ ያስቆጨዋል። በፍቅር እያቀፈ፣ እያጫወተ አለመቅረቡ ያበግነዋል።

ይህ ሁሉ የመጣው በኑሮ አለመመቸት፣ በድህነት ምክንያት ነው። እሱ ከራሱ አልፎ ለጎጆው ቢተርፍ፣ በቂ ገቢ ቢኖረው ልጆቹን ገጠር አይልክም። በናፍቆት አይንገበገብም። አባወራው ይህ ስሜት ከህመሙ እየተደመረ ለጤናው ፈተና ሆኗል።

አሁንም ተመሳሳይ ሕይወት እንደቀጠለ ነው። ጥንዶቹ በሁለቱ ልጆች ሌሎች ሁለት አክለው አራት ልጆች ቆጥረዋል። ይህ እውነታ የህመምተኛውን አባወራ ኃላፊነት ይበልጥ አክብዷል። ያለፈው ችግር ሳይፈታ ሌላ መጨመሩ ያለመፍትሔ እያራመደው ነው።

ያልጎበጡ ትካሻዎች

መኪያ አራት ልጇቿን ሀገር ቤት አስቀምጣ ለኑሮ መታገሏ እያደከማት ነው። ከምንም በላይ የባሏ ጭንቅ። አባወራው በህመም በተፈተነ ቁጥር ልጆቹን በትኖ እንዳያልፍ አብዝቶ ይጨነቃል። ይህ ጭንቀቱ የሚያስከትለው ስሜት የልብ ህመሙን እየቀሰቀሰ ባሻው ይጥለዋል።

የአራት ልጆችን ሕይወት የተሸከመው የጥንዶቹ ትከሻ በድካም እየጎበጠ ነው። መኪያ ሁሌም በዚህ አቅም ብቻ መኖር እንደማይቻል ታስባለች። የቤተሰቧን ሕይወት ለመለወጥ እሷ መቁረጥ መወሰን እንዳለባት እየገባት ነው። ይህ ውሳኔ ከዐረብ ሀገር ጉዞ አድርሷታል። ይህን ብታደርግ ባሏን ታሳርፋለች፣ ቤተሰቦቿን ልጆቿን ከችግር ታወጣለች።

አባወራው ውሳኔዋ ቢያስደነግጠውም አልተቃወማትም። እሱ ሚስቱ ከዓይኑ ባትርቅ ይወዳል። እንደአጋር ግራ ጎኑ ሆኗ ቤት ጎጆው ቢሞላ ፈቃዱ ነው። የታሰበው ይሆን ዘንድ ፓስፖርት ያወጣችው መኪያ ቀኑ ደርሶ ጉዟው ዕውን እንዲሆን ተመኘች። አንድ ቀን በላቧ ወዝ፣ በጉልበቷ ድካም ታሪክ እንደሚቀየር፣ ችግራቸው እንደሚያልፍ ታውቃለች። እናም ጓዟን ሸክፋ ይህን ዕለት በጉጉት ትጠብቃለች።

ከቀናት በአንዱ ግን ህልሟን ያመከነ፣ ጉዟዋን ያከሸፈ ምላሽ ደረሳት። ለጉዞ የተዘጋጀችበት ዕቅድ መሰረዙ፣ መዘጋቱን ሰማች። በወቅቱ መኪያ ከልቧ አዝና አንገቷን ደፋች። ‹‹አደርገዋለሁ›› ያለችው ሃሳብ አለመሳካቱን ስታውቅ ተስፋ ቆረጠች።

መኪያ ይህን ባወቀች ማግስት ገጠር ተመልሳ ከልጆቿ ቆየች። አሁን ከራሷ አልፎ እናቷን ማስቸገሯ ከልብ ያሳስባት ይዟል። እናቷ በቂ ገቢ የሌላቸው ምስኪን ለፍቶ አዳሪ ናቸው። የእሷን ልጆች ለማሳደግ በየቤቱ አዛባ ይዝቃሉ። የልጃቸው ችግር ችግራቸው ቢሆን ሸክሟን ሊያቀሉ እየደከሙ ነው።

አሁን መኪያ ኑሮን የምትለውጥበት፣ ባሏን ከድካም የምታሳርፍበት መንገድ ጠፍቷታል። ተመልሳ አዲስ አበባ ስትገባ ባለቤቷ እንደእሷው ሲጨነቅ አገኘችው። አሁንም ከዘመድ ቤት ያልወጣው ኑሯቸው አብዝቶ እያሳሰበው ነው። ይህ የከፋ ሀሳብ ከህመሙ አውሎ ያሳድረዋል።

ሕይወትን በስጋት

ከቀናት በአንዱ የመኪያ ባለቤት መንገድ ወድቆ ተገኘ። ችግሩን የተረዱ ልበ መልካሞች ከሆስፒታል አስተኝተው ለቤተሰብ አሳወቁ። የመውደቁ ምክንያት አብሮት የቆየው የልብ ህመሙ ነበር።

መኪያ የባሏን ሆስፒታል መግባት ባወቀች ጊዜ ትይዘው ትጨብጠው ጠፋት። በህመሙ አብራው ታመመች። ከጭንቀቱ ተጋርታ፣ ከጉኑ እየተኛች በእኩል ተንገላታች። ኑሮ ፈትኖ የበተናቸው ልጆቹ ሳይሰበሰቡ የእሱ በድንገት መውደቅ አምርሮ አስለቀሳት፡፤

አባት ልጆቹን ለማየት በእጅጉ ናፍቋል። ሁሌም የሚሳሳላቸው ፍሬዎቹ ዛሬ እንደ እንጀራ ርበውታል። ደጋግሞ ‹‹ልጆቼን አሳዩኝ›› እያለ ነው። አባት ያሰበው ሁሉ ሆነ። ገጠር የቆዩት አራት ልጆች ካሉበት መጥተው ትንፋሻቸውን አጋሩት፣ ዓይናቸውን አሳዩት።

ለሦስት ወራት በሆስፒታል ተኝቶ የታከመው አባወራ ከህመሙ አገግሞ ለቤቱ በቃ። መኪያ የምትወደው ፣ የልጆቿ አባት በሕይወት መትረፉ አሰደሰታት። በውስጧ የሚመላለሰው ክፉ ሀሳብ ስጋት ሆኖ አብሯት ከርሟል።

አባወራው ከሆስፒታሉ ሲወጣ ሀኪሞች ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጡት። አሁን ያለ ሥራ በእረፍት ሊቆይ ግድ ይለዋል። ህመምተኛው እንደተነገረው ራሱን አልጠበቀም ። ቤቱ ገብቶ አንድ ወር እንደቆየ ዳግም ህመሙ አገረሸ።

ሆስፒታል ለአንድ ወር የተኛው አባወራ ታክሞ፣ ድኖ ተመለሰ። ይህ አጋጣሚ ግን መኪያን ለጉዳት ዳረጋት። በማስታመም የተንገላታችው ወይዘሮ እጅ እግሯ ተያዘ። ‹‹ልቤን፣ ራሴን ማለት ያዘች›› ውሎ አድሮ ሲሻላት ወደ ትናንቱ ሩጫዋ ተመለሰች። በዚህ መሀል ግን የመኪያ አዕምሮ ብዙ ማሰብ ጀመረ። አሁን ቤተሰቡ ለሦስት ተከፍሏል። እሷ ከዘመድ ቤት፣ ልጆቿ በገጠር ባሏ በጥገኝነት።

በሃሳብ ሁሉም ቦታ የምትባዝነው ወይዘሮ ይበልጥ የባሏ ጉዳይ ያስጨንቃታል። የእሷ ከዘመድ ቤት መኖር እሱን ብቸኛ አድርጓል። የእነሱ መለያየት ልጆቹን አርቋል። ይህን ዕውነት ደጋግማ ስታስብ ‹‹ራስሽን አጥፊ›› የሚል ስሜት ይፈትናታል። ባሏ ልጆቹን በትኖ ሲሞት እየታያት ልትቀድመው ትወስናለች።

አባወራው እንዳይሠራ ቢታዘዝም ይህን ማድረግ አልቻለም። ኑሮን ለማሸነፍ፣ ችግርን ለማምለጥ ከአድካሚ ሥራው ተመለሰ። ልብስ እያጠበች የምታግዘው ሚስቱ ከጎኑ አልራቀችም። አዳራቸው ቢለያይም ‹‹አይዞህ፣ አለሁህ›› ትለዋለች።

ምኞት በአንድ ታዛ…

ጊዜያቶች ተቆጠሩ። አባወራው ያዝ ለቀቅ ከሚያደርገው ህመሙ እየታገለ ዓመታትን ገፋ። አንድ ቀን ደግሞ ሁለቱን በአንድ የሚያደርግ አጋጣሚ ተከሰተ። ችግራቸውን የተረዳች አንዲት ሴት ለአንገት ማስገቢያ ብቻ በምትሆን ማረፊያ አሰጠጋቻቸው።

አሁን የጥንዶቹ ሃሳብ ሞልቷል። የተጠጉበት ትንሽዬ ቤት አልጠበባቸውም። ከገጠር አራቱንም ልጆች አምጥተው ጎዶሎውን ሞልተዋል። ሕይወት ከነችግሩ በደስታ ቀጥሏል። መነፋፈቅ ፣ ‹‹ነበር›› ሆኖ ተረስቷል፤ ዕንባን ያበሰ ብሶት ያራቀ ታሪክ ዕውን ሆኗል።

ኑሮ በዚህ ጎጆ ጉራይማይሌ እየሆነ ነው። ሲገኝ ቀምሶ ሲጠፋ ተደፍቶ ማደር ብርቅ አይደለም። ለሆድ እንጂ ለሥራ ያልደረሱት ልጆች ዛሬም የወላጆቻቸው ዕዳ ሆነዋል። ከመኖር ውጪ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። መኪያ ከልብስ ማጠብ ጎን በጉልት ሥራ ትውላለች። ከትናንቱ በባሰ የሥራ ጫና አላት። አሁንም ስለጎጆዋ ትተጋለች። ከድካም ልፋቷ አላረፈችም ።

እነሆ ! በዚህ ውጣውረድ አስር የችግር ዓመታት ተቆጠሩ። እንዲያም ሆኖ የቤቱ አምስተኛ ልጅ ‹‹መጣሁ›› እያለ ነው። መኪያ እርጉዝ ብትሆንም ለቤተሰቡ ጉሮሮ መሮጧን ቀጥላለች። ችግር አልቀለለም። አባወራው ጤና የለውም። ከዓመታት በኋላ የተነሳው የልብ ህመም ይሰማው፣ ያስጨንቀው ይዟል።

ትንሹ ልጅ ተወልዶ ጥቂት ወራት ባለፉ በአንድ ማለዳ ባልና ሚስቱ ከቤት ሊወጡ ተነሱ። ዕለቱን አባወራው የሀኪም ቀጠሮ ነበረው። ይህን የምታውቀው ወይዘሮ አብራው ልትሄድ ተዘጋጀች። እሱ ግን አልፈቀደም። እንደልማዳቸው ወደ የእንጀራቸው ሊሰማሩ ተለያዩ።

መኪያ ጉልት እንዳለች አንድ የስልክ መልዕክት ደረሳት። ባለቤቷ በጠና ታሞ ሆስፒታል ገብቷል። ስትሮጥ የደረሰችው ወይዘሮ ባሏን ስታይ ደነገጠች። ኦክሲጂን ተሰክቶለት ከላይ አብዝቶ ይተነፍሳል፤ ቀርባ ዳሰሰችው፣ተጠግታ አዳመጠችው። እንደምንም ታግሎ ‹‹ደህናነኝ›› ሲል መለሰላት።

ውሎውን በህክምና አሳልፎ ም ሽቱን ከ ቤቱ ገ ባ። መኪያ በደስታ ‹‹እፎይ !›› ስትል ተነፈሰች። አራቱ ልጆቹ አባታቸውን ከበው አመሹ። አባወራው አምስተኛውን ልጅ ታቅፎ ፤ ራሱን እየዳሰሰ ቆየ። ምሽት አራት ሰዓት ሲሆን ታሪክ ተለወጠ። ደጉ አባወራ፣ ለፍቶ አዳሪው ጎልማሳ ትንፋሹ በድንገት ‹‹ህቅ..›› አለች።

የፈተና ዓመታት…

ከዚህ በኋላ የቀጠለው ሕይወት ለመኪያ በእጅጉ የከፋ ሆነ። አምስት የሙት ልጆችን ያለ አጋዥ፣ ያለ ረዳት ማሳደጉ ከበዳት። ጉልቱን እየሠራች፣ ልብስ አጠባውን ቀጠለች። ተጠምታ እየተራበች ልጆቿን ትምህርትቤት ላከች። እሷ ብትጎዳም ልጆቹ ቀለም ለዩ፣ ፊደል ቆጠሩ ።

መኪያ ጥልቅ ኀዘኑ ተደምሮ ችግሩ ፈተናት። አንዳንዴ የምታደርገው ሲጠፋት ልጆቿን ሰብስባ መንግሥትን ‹‹ተረከበኝ›› ልትል ታስባለች። መልካም ሰዎች ሲመክሯት ደግሞ እነሱን ላለመበተን ወስና ትጠነክራለች። ደግነቱ ችግሯን የሚረዱ ከእጃቸው ያካፍሏታል። አዋጥተው፣ ተሰባስበው ያጎርሷታል።

የመኪያ ልጆች ለብሰው፣ ተከናንበው የሚያድሩበት በቂ ልብስ የላቸውም። ሰዎች የሚቸሯቸውን ተጋፈው፣ ተቃቅፈው ያድራሉ። የአምስት ልጆች ባዶ ሆድም እንደነገሩ ውሎ ያድራል።

ዘንድሮ …

አሁን አዲስ ዓመት ብቷል። የመኪያና ልጆቿ ችግርም በእኩል አልፎ ዘመኑን ተሻግሯል። ዘንድሮ ግን ወይዘሮዋን መልካም ዓይኖች አይተዋታል። ከወደቀችበት አሳዛኝ ሕይወት የሚያላቅቅ ዕድል ገጥሟታል። ከአቅመ ደካሞቹ ዜጎች አንዷ መሆኑ ቢታወቅ የቤት ባለቤት ሆና ቁልፉን ተረክባለች።

ትናንት በብርድ በውርጭ፣ በስቃይ፣ ያለፉ ክረምቶች ዘንድሮ የሞቀ ቤት አሸንፏቸዋል። የተራቡት ባዶ ሆዶች ግን አሁንም እየጮሁ ነው። ልክ እንደቤቱ ስጦታ ለእነሱም በረከት የሚቸራቸውን ይሻሉ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You