ጠንካራ የውሃ አጠቃቀም ሕግ ያስፈልገናል

በየትኛውም ሚዛን እንመዘን፣ በየትኛውም መስፈርት እንለካ የውሃ አጠቃቀማችን ሕግ ቢኖር በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሚሆን ለመናገር የሚከብድ አይደለም። ይህንን ድፍረት የተሞላበት የሚመስል ድምዳሜ በማስረጃ ለማየት እንሞክር።

በሀገራችን ውሃን በተመለከተ ያለው እውነታ እርስ በርሱ የሚጋጭና ግራ የሚያጋባ (ፓራዶክስ) ነው። ሀገራችን እንደ ሀገር “የውሃ ማማ” ነች። የብዙ የውሃ አካላት /ወንዞች ሀይቆች /ባለቤት ነች። ይህም ሆኖ ግን ሕዝቦቿ በንጹህ ውሃ እጥረት የከፋ ችግር ውስጥ ካሉ የዓለም ሕዝቦች አንዷ ናት ።

እውነታው ግራ የሚያጋባ / አያዎ “ፓራዶክስ” ነው። ግራ አጋቢው የሀገራችንን የውሃ ማማነት ሳይሆን ማማነታችንን ወደ ተጠቃሚነት መለወጥ አለመቻላችን ነው። የውሃ ሀብታችንን በተለይም ለመጠጥ ተብሎ ብዙ ዋጋ ተከፍሎ የሚመረተውን ውሃ ለተገቢው ዓላማ በኃላፊነት ማዋል ስላለመቻላችን ነው።

“ንፁህ ውሃን ንፁህ ውሃ ለማይፈልጉ ተግባራት” በማዋል በኩል በዓለም የሚስተካከለን በጭራሽ ያለ አይመስልም። ይህም በሀገራችን ላይ ያለው የውሃ ሀብት ምን ያህል ለአደጋ እንደተጋለጠና በግዴለሽነት እየባከነ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ።

እዚህ ላይ “ንፁህ ውሃ የማይፈልጉ” ስንል ሰውን ብቻ ንፁህ ውሃ ፈላጊ አድርገን እንዳንወስድ መጠንቀቅ አለብን፤ ሕይወት ያለው ሁሉ ንፁህ ውሃን ይፈልጋል እና ፤ የማግኘትም ሙሉ መብት አለው። እኛ ሀገር ግን በአብዛኛው የንፁህ ውሃ የሚውለው ሕይወት ላለው ፍጡር ሳይሆን ግኡዝ ለሆነ አካል የተለያየ አገልግሎት ነው።

ለምሳሌ ለመኪና እጥበት የሚውለውን ፣ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት ለመጠጥ የተዘጋጀውን ውሃ እንመልከት። እኛ ሀገር እኮ ይህ መኪኖች እየታጠቡ ያለው ነዋሪዎች ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረድ በሚከፍሉበት ንፁህ የቧንቧ ውሃ ነው። በዚህ ጉዳይ ያለኝን አንድ ገጠመኝ ላካፍላችሁ።

፣ ጠዋት ከቤቴ ወደ ሥራ ስመጣ አልፌው የምመጣው አንድ ግቢ አለ። ባለቤቱ ባለ መኪና ናቸው። የ10 ዓመት አካባቢ ልጃቸው ሁሌ መኪናዋን ያጥባል። የሚያጥበው ጊቢ ውስጥ ያለው ቧንቧ ላይ ረጅም ላስቲክ አስገብቶ በላስቲኩ መኪናዋ ላይ በመርጨት ነው።

ልጁ ከአለባበሱ ጀምሮ ሥራውን እንደ መዝናኛም፣ እንደ ስፖርትም እየተጠቀመበት ስለመሆኑ ከፈገግታው ጀምሮ ሁኔታዎቹ ይናገራሉ። አሁን ችግሩ የልጁ፣ ወይም ልጁ ጋ አይደለም። ችግሩ በዚህ አይነት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ሲንቀሳቀስ ሀይ በል የሚለው ከልካይ ሕግ /መመሪያ አለመኖሩ ነው ። ውሃው ሁሌ ጠዋት ጠዋት ዝም ብሎ እንደ ጉድ ይፈሳል።

ከብዛቱ የተነሳ ቀጭንና ረጅም፣ በሳር የለመለመች ቦይ ሰርቷል። ሁሌም አጠገቡ ማንም ሰው የለም። አንድ ቀን (ሥራውን ካደነቅሁለት በኋላ) ውሃውን እየቆጠበ ቢጠቀም ጥሩ እንደሆነ ነገርኩት። መልስ አልሰጠኝም። እነሆ፣ ዛሬም ድረስ በገፍ እንዳፈሰሰ አለ።

የዚህን ልጅ የውሃ አባካኝነት (ውሃ የማያልቅ ሀብት ይመስል) ከሌሎች እሱን መሰሎች ጋር ተዳምሮ (በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት በቀን ከ700‚ 000 በላይ ሰው የሚሞትባት፤ 2.2 ቢሊዮኖች ንፁህ ውሃ የማያገኙባት ዓለማችንን ይዘን) በየቀኑ ሊባክን የሚችለውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ መገመት ይቻላል። ያኔ፣ በመግቢያ ላይ “ሕግ ቢኖር” የተባለውን ካልደገፋችሁ ከምላሴ ፀጉር ይነቀል።

ሌላ ልጨምር ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ከ45 በላይ ወንዞች አሉ። በአብዛኛዎቹ ወንዞች አካባቢ መኪና አጣቢዎች አሉ። ቧንቧ ላይ ደቅነው በመርጫዋ (የውሃ ወንፊቷ) እየረጩ ከማጠብ ውጪ፣ አንዳቸው እንኳን ከወንዙ እየቀዱ መኪናዎቹን ሲያጥቡ አይታችኋል? ታዲያ ይሄንን ምን ይሉታል?? ቢያንስ ቢያንስ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ግፍ የለውም? እንዲህ እንዲህ እያላችሁ ከተሞቻችንን ብትፈትሹ (የአዲስ አበባን ዝም ነው) ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚው ሰው ሳይሆን ምን እንደ ሆነ ትደርሱበታላችሁ።

በተመሳሳይ ወደ ኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ደግሞ እንሂድ፤ በሀገራችን፣ በተለይም በከተሞች፣ የግንባታ (ኮንስትራክሽን) ሥራዎች በገፍ መሰራት ከጀመሩ ቢያንስ ሁለት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። አንዳንዶቹ ከተሞች (ሰፈሮች) ጭራሽም ፈርሰው እየተሰሩ ነው። ሌሎቹን ሁሉ ትተን የፎቆቹንና ግዙፍ ተቋማትን ብቻ እንኳን ብናስብ፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ የምድር አሸዋ … በሚል ልናሰላቸው ምንም አይቀረንም። ልብ በሉ፤ ከጥቂቶች በስተቀር፣ እነዚህ ሁሉ የሚጠቀሙት ንፁህ የመጠጥ ውሃን ከቧንቧ እየቀዱ ነው። አይዘገንንም??

እንደ ሕግና ደንብ (እኛ ያለን አይመስለኝም) ቢሆን ኖሮ አንድ ባለ ሀብት ሕንፃ ሲገነባ እዛው የሚገነባበት አካባቢ የጉድጓድ ውሃ በማውጣት ነው ለግንባታ ተግባሩ ማዋል ያለበት። ወይም፣ ከአካባቢው ካለ ወንዝ ጠልፎ፤ ወይም፣ አካባቢው ላይ የተበከለ ውሃ እንኳን ካለ እሱን በመርዝ አጥርቶ ወደ ጥቅም በመቀየር ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅበታል እንጂ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ከቧንቧ እየቀዳ ለግንብ አያጠጣም። በኢትዮጵያ ግን ይህ የለም፤ አይታሰብምም።

ከዚህ ሁሉ ብልሹ አጠቃቀማችን ላይ በየቤቱ፣ በየአስፋልቱ (እየፈነዳ) … ሲፈስ የሚከርመውን ጨምሩበትና አስሉት። ያኔ በዓለም ተወዳዳሪ የሌለን የውሃ አባካኞች መሆናችንን እየዘገነናችሁም ቢሆን ትረዳላችሁ።

እዚች ጋ ዶቸ ቬለ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የኮሌራ በሽታ ከጎርጎሮሳዊው 2005 ዓ.ም ጀምሮ በድሃ ሀገሮች እየጨመረ መጥቷል። በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ባልተሟሉባቸው ሀገራት ከንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ጋር ተያይዞ የአካባቢና የግል ንፅህናን ለመጠበቅ አስቸጋሪ በሆነባቸው ቦታዎች በሽታው የከፋ ጉዳት ያደርሳል” ይህ እንግዲህ ሌላው ተያያዥ ችግር ነው።

የንፁህ ውሃ መጠጥ ፍላጎትና አቅርቦት

በ2018 “ወተር ኤይድ” የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት የንፁህ ውሃ አቀርቦት ሳይኖር፤ ከጤና፣ ከትምህርትና ከፆታ እኩልነት ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ግቦችን ማሳካት እንደማይቻል በመግለጽ፤ ፖለቲከኞች ለውሃ አቅርቦት ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

በንፁህ ውሃ አቅርቦት ችግር በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ከአጠቃላይ ሕዝቧ 42% የሚሆነው ብቻ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያገኝ ነው። ከዚህ ውስጥ ንፅህናውን የመጠበቅ እድል ያለው 11% ያህሉ ብቻ ነው።

አዲስ አበባን እንደማሳያ ብንወስድ፤ በቀን ወደ 1ሚሊዮን 300ሺህ ሜትር ኪዩብ ያስፈልጋታል። አቅርቦቷን ስንመለከት ደግሞ 722ሺህ ሜትር ኪዩብ ሆኖ እናገኘዋለን። መስተዳድሩ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር ባሳተመው መጽሔት ላይ በ2015 ዓ.ም 186 ነጥብ 52 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ መመረቱን አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ ምን ያህሉ በትክክል ሕይወት ላላቸው (ሰው፣ እንስሳትና እፅዋት) ፍጡራን ይውላል፤ ምን ያህሉስ ለግኡዛን (መኪና፣ ግንብ) እየዋለ ነው? ብለን ብንጠይቅ መልስ የሚሰጠን ያለ አይመስለኝም።

ከተግባራቱ አንዱ “የውሃ ብክነትን መቀነስ” የሆነው መሥሪያ ቤትም ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፤ ደረቱን ነፍቶ በአደባባይ ሊቆም የሚችል ምላሽ አለው ለማለት ያስቸግራል።

እዚህ ላይ ዛሬ በአግባቡ ልናስተውለው የሚገባው፤ውሃ አላቂ ሀብት ከመሆኑ አንጻር፤ሀብቱን ባልተገባ መልኩ በብክነት ጨርሰነው የነገው ትውልድ ለከፋ አደጋ እንዳይጋለጥ ነው። ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ጠንካራ የውሃ አጠቃቀም ሕግ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል ፤እኛም ኃላፊነት እንደሚሰማው ሕዝብ ውሃ መቆጠብን ባህላችን ማድረግ ይጠበቅብናል።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን  መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You