የያዝነው መስከረም ወር ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ብዙ ነው። አዲስ ዓመትን በመቀበል የተጀመረው የመስከረም ወር በአዲስ ዓመትነቱ ብዙ ተዘክሯል። ወሩ የተስፋ፣ ከጨለማው ክረምት ወደ ነፋሻማውና በጸደይ ወደ ተንቆጠቆጠው ወቅት የመሻገር ምልክትም ነው። አዲስ ዓመቱን የተስፋ ምልክቱን ችቦ በማብራት፣ ከጎመን ምንቸት ወደ ገንፎ ምንቸት አሸጋግረን እያሉ ኢትዮጵያውያን ተቀብለውታል። በደማቅ ባህላዊ አልባሳቶቻቸው ተውበው፣ በደስታ አስተናግደውታል።
ወሩ ከዚህም ባሻገር በርካታ የቱሪዝም ፋይዳዎች ያሉት የበዓላት ወር ሊሰኝ የሚችልም ነው። በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በዚህ በመስቀል ደመራ ወቅት አዲስ ዓመታቸውን በዚህ ወር ያከብራሉ፤ የቀድሞው የደቡብ ክልል ቤተሰብ ለነበሩት የወላይታ፣ የጎፋ፣ የጋሞ፣ የሀዲያ፣ የከንባታ ፣ የከፊቾ ፣ወዘተ ብሔረሰቦች ይህ ወር ትልቅ ቦታ አለው። ብሔረሰቦቹ ሰሞኑን በደማቅ የበዓል አከባበር ላይ ናቸው።
በዓሉን የሚያከብሩት ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩት የየብሔረሰቡ አባላት ወደ ትውልድ ስፍራቸው ሀገር ቤት በመግባት ነው። በእዚህ ወቅት በእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ ይታያል፡፡
ወሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድም የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበርበት እንደመሆኑ ትልቅ ስፍራ አለው። በዓሉ በአዲስ አበባና በሌሎችም ከትንሽ እስከ ትልቅ ከተሞች፣ በየመንደሩም ጭምር በአደባባይ በድምቀት ይከበራል፡፡
በኦሮሞ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓልም ሌላው የወሩ ታላቅ በዓል ነው። ይህ በዓል በዋናነት በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበር ሲሆን፤ በየአካባቢውም በተመሳሳይ በድምቀት ለቀናት ይከበራል። ዘንድሮ ደግሞ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሥነሥርዓት የሚከበረው የመውሊድ በዓልም የዚሁ የመስከረም ወር ድምቀት ሆኗል።
ሁሉም በዓላት መሰባሰብን የሚጠይቁ ናቸው፤ በግልም፣ በቤተሰብም አምሮ ተውቦ ለመገኘት ብዙ ጥረት ይደረጋል። ለዓመታት የተለያዩ የቤተሰብ አባላት ይገናኙባቸዋል፤ መደጋገፍ ጎልቶ ይታይባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ሰፊ ዝግጅት ይደረጋል።
እነዚህ በዓላት በድምቀት ያለምንም የጸጥታና ደህንነት ችግር እንዲከበሩ፣ የትራንስፖርት ስምሪቱ የተሳለጠ እንዲሆን፣ ሕዝቡ እንደልቡ እንዲንቀሳቀስ መንግሥትና የተለያዩ አደረጃጀቶች አጥብቀው ይሠራሉ። የበዓላቱ ባለቤቶችም ከግለሰብ አንስቶ እስከ ተቋማት ድረስ በዓላቱ በሰላምና በድምቀት እንዲከበሩ አጥበቀው ይሠራሉ። ዘንድሮም ይሄው እየተደረገ ነው።
በሌሎች በዓላት ላይም ተመሳሳይ ዝግጅት እንደሚደረግ ይታሰባል። ሁሉም የየራሱ በዓል በድምቀት እንዲከበር ከሚያደርገው ርብርብ በተጓዳኝ የሌላውም በዓል በተመሳሳይ መልኩ እንዲከበር ማድረግ ላይም መሥራት ያስፈልጋል።
ይህ ሲሆን በዓላቱ በሰላም ይከበራሉ፤ ከበዓላቱ የሚጠበቁ የቱሪዝም ጥቅሞችም ይገኛሉ። የእነዚህ በዓላት የቱሪዝም ፋይዳ ከፍተኛ ነውና ከበዓልነታቸው ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ምንጮችም ናቸው። የበዓላቱ ብዛትና በድምቀት መከበር ሲታሰብ፣ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጎልቶ ከሚወጣባቸው ወቅቶች አንዱ ነው ሊያሰኝ ይችላል። ከፍተኛ የሆነ የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰት የሚታይበትም ነው። በዓላቱ የውጭ ዜጎችም በብዛት የሚታደሙባቸው እንደመሆናቸው ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ቱሪስት ወደ ሀገሪቱ በመግባት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ ይጠበቃል።
መላው ሕዝብ ሊባል በሚችል ደረጃ እንዲሁም የውጭ ቱሪስቶች በሚነቃነቁባቸው በእነዚህ በዓላት ወቅት ከፍተኛ ሀብትም አብሮ ይንቀሳቀሳል። ግብይቱ፣ ልገሳው፣ መገባበዙ ፣ ወዘተ ይጦፋል። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉን በማስተዋወቅና ማስጎብኘት ብቻ ሳይሆን በገቢም የበለጠ ሀብት መሰብሰብ እንዲችል ትልቅ አቅም ይሆናል።
ከበዓላቱ ሀገርንም በቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፤ በተለይ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ የግሉ ዘርፍ ተቋማት እነዚህ የቱሪዝም ዘርፉን በአያሌው የሚያንቀሳቅሱ በዓላት በሚገባ እንዲከበሩ፤ እንዲሁም ተገቢው ሀብት እንዲገኝ ለማድረግ መሥራት ካለባቸው የዓመቱ ወቅቶች ይህ ወቅት አንዱ መሆኑን ተረድተው መሥራት ይኖርባቸዋል። ለሀገር ተጠቃሚነት ሌት ተቀን በመሥራት ከእዚህ የቱሪዝም አዝመራ ሀገር ተገቢውን ምርት መሰብሰብ እንድትችል መትጋት ይኖርባቸዋል።
እንደሚታወቀው መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እየሠራ ነው፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት ዕቅድ ዋና ምሰሶ አድርጎ ከያዛቸው ዘርፎች አንዱ የቱሪዝሙ ዘርፍ ነው። ይህን ሲያደርግ ደግሞ ዘርፉ የሚያድግበትን መደላድል በመፍጠር ነው። ዘርፉ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዲዋቀር አድርጓል፤ ሀገሪቱ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ቢኖሯትም፣ አዳዲስ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን በግዙፍ ፕሮጀክቶቹ ቀርጾ ወደ ሥራ አስገብቷል፤ ሌሎችም ወደ ሥራ ሊገቡ በመንገድ ላይ ይገኛሉ። በቀጣይም ሌሎች ይገነባሉ። እነዚህ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ፣ የውጭ ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ሊያራዝሙ የሚችሉ መሰረተ ልማቶች በእነዚህ በዓላት ወቅት እንዲጎበኙ ለማድረግ መሥራት ከቱሪዝም ዘርፉ የሚጠበቀውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይጠቅማል።
የዓለም ቱሪዝም ቀን የሚከበረው በዚሁ በመስከረም ወር ነው፤ እነዚህ በርካታ በዓላት ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አቅም መሆናቸውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ ለኢትዮጵያውያን ማስተዋወቅ፣ ማስጎብኘትና ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተጠናክሮ መሥራት ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም