የአደባባይ በዓላትና ወጣቶች

በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበር ነው። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ወጣቶች ፣ ቁጥራቸው የበዛ የእምነቱ ተከታዮች ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዲፕሎማቶች፣ የተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች (ቱሪስቶች) እና ሌሎች እንግዶች ይታደሙበታል ።

የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እና ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው የዓለም ሀገራት ውስጥም በድምቀት የሚከበር የጌታችን የመድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ከጠፋበት መገኘት የሚያበስር ትልቅ በዓልም ነው።

በተመሳሳይ መስቀል በዓል በዋለ በቀጣዩ ቅዳሜና እሁድ ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓልም ሰፊ የአከባበር ሥርዓት ወግና ትውፊት ያለው ከመሆኑም በላይ የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት ተሠብስቦ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የእምነቱና የባህሉ ተከታዮች በደማቅ ሁኔታ እየተከበረም ይገኛል፡፡

እነዚህ ሁለት በዓላት የሚውሉበት መስከረም ወር ደግሞ የሚወደድ ሁሌም በየዓመቱ እንዲመጣ የሚናፈቅ ጊዜም ነው፡፡ ወደበዓላቱ ስንመጣ ሁለቱም በዓላት የፍቅር የአንድነትና የምስጋና ናቸው፡፡ ሰዎች አምላካቸው የከፈለላቸውን ዋጋ የሚያስታውሱበት በሌላ በኩል ደግሞ ከዘመን ዘመን ተሸጋግረው ስለመገኘታቸው የሚደሰቱበትም ነው፡፡

በሌላ ጎን እነዚህ በአንድ ወር ላይ የሚውሉ የአደባባይ በዓላት በህዝብ ውስጥ የሚፈጥሩት ማህበራዊ ትስስር አንድነት ከፍ ያለ ከመሆኑም በላይ የተፈጠረውን የማህበረሰብ አንድነትና አብሮነት በማጠናከሩም በኩል ያላቸው ሚና እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በህዝቦች አንድነት ውስጥ መተዋወቅ አለ። በመተዋወቅ ውስጥ መከባበር አለ። በመከባባበር ውስጥ ደግሞ ሰላም አለ። የአደባባይ በዓላት ለአንድ ማህበረሰብ የኪነጥበብ እድገትና ለከያኒዎች መፈጠር አስተዋጽኦ አላቸው። በሀገራችን የአደባባይ በዓላት ላይ የሚታዩት ጭፈራዎችና ዘፈኖች ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ብዙዎቹ የሀገራችን የባህል ዘፈን ተጫዋቾችና ተወዛዋዦች አፋቸውን የፈቱት፣ ሰውነታቸውን የፈተሹትና ወገባቸው ያፍታቱት ጥምቀትን አሸንዳን/ሻደይንና ፊቼ ጨንበላላንና ኢሬቻን በመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።

በኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላትን ወቅቱን ጠብቆ ከማከበር ያለፈ፣ ለማጎለበት፣ በቅርስነት ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ እስካሁንም ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶቻችንን ማለትም የመስቀል በዓል፣ ፊቼ ጫምበላላና የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በቀጣይነትም የጥምቀትና ኢሬቻ በዓላትን ለማስመዝገብ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ነገር ግን እንደ አሸንዳ/ሻደይን የመሳሰሉ በዓለም አደባባይ እኛነታችንን ሊገልጹ የሚችሉና በአደባባይ በልጃገረዶች የሚከበሩ በዓላትንም ተገቢውን እውቅና የማሰጠት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ።

እነዚህ እንደ ጥምቀት፣ ዳመራ፣ አሸንዳ/ሻደይ፣ ፊቼ ጨንበላላ፣ ኢሬቻና ሌሎች በዓላት እኛነታችንን ከማሳወቅ ባለፈ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን የመሳብም አቅም ያላቸው ናቸው። በዓላቱ ቱሪስቶችን መሳብ በተለይ ለየአካቢው ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማስገኘት በሚችሉ መልክ የማልማትና የማስተዋወቁ ሥራው ከእኛ የሚጠበቅ ቢሆንም አሁንም ባሉበት ሁኔታ ግን በተለይም ሰላማችን ከተጠበቀ ቱሪስትን የመሳብ አቅማቸው ላቅ ያለ ነው። የአደባባይ በዓላቱ በሚከበርባቸው አካባቢዎች የበዓሉ ተሳታፊዎች የሚደምቁባቸውን አልባሳት፣ ጌጣጌጥ፣ የአካባቢውን ባህላዊ ምግቦችና ሌሎቹም እንኳን ከውጭ መጥቶ ለሚያያቸው ለእኛም በውስጣቸው ላለን ሰዎች ሁሌም አዲስ ምንጊዜም አስደናቂ የመሆን አቅማቸው ትልቅ ነው።

በተለይም በያዝነው የመስከረም ወር እንደ መስቀል ደመራና ኢሬቻ የመሳሰሉ ትልልቅ በዓላት ይከበራሉ፡፡ እነዚህን በዓላት ለማክበር የሚወጣው የህዝብ ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም ፡፡ ሁለቱም በዓላት ትልቅ ከመሆናቸውም በላይ ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚገናኙበት ባህላቸውን ወጋቸውን ለማያውቃቸው የሚያስተዋውቁበት ከምንም በላይ ደግሞ የፈጠራቸውን አምላክ አብዝተው የሚያመሰግኑበትና ክረምት አልፎ በጋ መድረሳቸው የሚያስደስታቸው በዓላት ናቸው፡፡

በእነዚህ በዓላት ላይ ታሞ አልጋ የያዘ አልያም ከሀገር የወጣ ካልሆነ በቀር አደባባይ ሳይወጣ በቤቱ የሚቀር አንድም ሰው የለም፡፡ ሕጻን አዋቂው የክት ባህላዊ ልብሱን ለብሶ በባህል ማጌጫዎቹ የሚችለውን ያህል ተውቦ ብቻ ምን አለፋችሁ ታይቶ የማይጠገብ ትዕይነት የሚታይባቸው ናቸው፡፡

እነዚህ ውብና ድንቅ በዓላቶቻችንን ከምን ጊዜውም በላይ በሰላምና በደስታ እንዲከበሩ ደግሞ ሁላችንም ሃላፊነት ያለብን ስለመሆኑ መግለጽ ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴርም በመስከረም ወር በሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ላይ የሚታደሙ ጎብኒዎችን ቆይታ አስደሳችና የተሳካ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንና በተለይም ወጣቶች ሰላምን በማስጠበቅ በኩል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሚኒስቴሩ በዚህ ወር ደመራ መስቀል እሬቻና የዓለም የቱሪዝም ቀን ስለሚከበሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት ስለመደረጉ እየገለጸ ቢሆንም በተለይም ወጣቶች ይህንን ጥረት ማገዝ እንዳለባቸው ደግሞ አሳስቧል፡፡

የመስቀል ደመራ እንዲሁም የኢሬቻ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ከኃይማኖት ተቋማት በዘርፉ ከሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በድረ ገጹ ያሰራጨው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቱሪስቶችን ቆይታ አስደሳችና የተሳካ ለማድረግ ከሆቴል ባለቤቶች ከጸጥታ ተቋማት አስጎብኚዎች ( ከቱር ኦፕሬተሮች) ና ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በመወያየት የቅድመ ዝግጅቱ ሥራ እየተከናወነም ነው፡፡

ከፊታችን በርካታ የአደባባይ በዓላት የሚካሄዱ በመሆኑ ኢትየጵያውያን በነቂስ ወጥተው በበዓሉ ላይ እንዲሳተፉ ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ሰላምን እንዲሰብኩና እንዲዝናኑ ያስፈልጋል፡፡

በተለይም ወጣቶች ለሁሉም ነገር ግንባር ቀደም እንደመሆናቸው መጠን ራሳቸውን ከጥፋት ኃይሎች ሴራ በማራቅና ሀገራቸውን በማስቀደም በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ የበኩላቸውን ሊወጡም ይገባል፡፡

ኢትዮጵያውያን በርከታ አኩሪ ባህሎች ያሉን እርስ በእርሳችን ለመከባበርና ለመዋደድ ምክንያት የማንፈልግ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምድ ያለን ነን፡፡ ለዚህ ማሳያው የገዳ ሥርዓታችን ነው፡፡ ታዲያ ሁሉም ወጣት ራሱን በዚህ መልኩ ቀርጾና እኔ ለሀገሬና ለህዝቤ ሰላም እቆማለሁ እተባበራለሁ ብሎ ሊነሳ ይገባል፡፡ ይህ በሆነ መጠን ደግሞ ጠላቶቻችን እያፈሩ ሰላማችን እየተረጋገጠ እንደ ደመራና ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በዓላቶቻችንን ተገቢውን ክብር አግኝተው ታዳሚውም የሚገባውን በረከትና ደስታ ሸምቶ ቤቱ እንዲገባ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

የአደባባይ በዓላት የተለያዩ አካላትን የሚያሳትፉ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ያሳያሉ፡፡ የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያዊ አንድነትን ከማጉላት ባለፈ ቱሪስቶችን በመሳብ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ፡፡

በዓላቶቹ በተከታዮቻቸውና አማኞቻቸው ይለያዩ እንጂ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓላት በመሆናቸው የተለያ እምነትና ባህል ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በዝግጅቶቹ ላይ የሚሳተፉባው ናቸው፡፡

ከፊታችን የሚከበሩት የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ሥርዓታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ የወጣቱ ሚና የጎላ ነው፡፡

“የአብሮነት፣ የወንድማማችነትና የፍቅር መገለጫ የሆኑ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን በጋራ እናክብር” በሚል መሪ ሃሳብም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በዓላቱ በሰላም ይከበሩ ዘንድ ወጣቶች የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

ከ5 ሺ በላይ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች የተሳተፉበት ውይይት መድረክ በማካሄድም በተለይም በቀጣይ ሳምንት የምናከብራቸው የደመራና መስቀል በዓላት ከአዋኪ ነገሮች በጸዳ ከተማችንን ሀገራችንን ይበልጥ በሚያሳውቅ ሁኔታ እንዲከበር ብሎም በዓሉን ለመታደም አደባባይ የወጣው ህዝብ በሰላም ወደየቤቱ እንዲገባ ሰፊ ሥራ በወጣቶች እንደሚጠበቅ ነው የተገለጸው፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች በዓላቱ ያለምንም ፀጥታ እክል ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ለማስቻል ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋገጡ ከመሆኑም በላይ ህዝቡም እንዲያግዛቸው ጥሪ ስለማቅረባቸው ተገልጿል።

በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዲችል ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው በዝርዝር ውይይት ካደረጉ በኋላ የበኩላቸውን ለመወጣት በዓመት አንዴ በጉጉት ተጠብቀው የሚመጡ በዓላቱም ያለምንም ጸጥታ ስጋት በተረጋጋና በአስደሳች ሁኔታ እንዲከበሩ ለማድረግ ዝግጅታቸውን ስለማጠናቀቃቸው እንደገለጹም የከተማዋ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘገባ ያመለክታል፡፡

የአደባባይ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት ልዩ ልዩ የጥፋት አጀንዳዎችን ይዘው በታዳሚው መካከል ሰርገውና ተመሳስለው የሚገቡ ኃይሎች እንደሚኖሩ መገመት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የጥፋት ኃይሎች እቅዳቸው ይከሽፍ ዘንድ መሥራት ያለብን ሁላችንም ብንሆንም በተለይ ወጣቶች የከተማው ብሎም የበዓላቱ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቅ ባለቤት መሆናቸውን በማመን ሰፊ ሥራንም ሊሰሩ እራሳቸውንም ከአጀንዳቸው ሊያርቁ ይገባል፡፡

ለበዓላቱ በሰላም መጠናቀቅ በወጣቱ የሚሰሩ ሥራዎች ደግሞ በአደባባዮች ላይ ብቻ ሳይሆን ሰዎች በየመንደራቸው ሰብሰብ ብለው በዓላቱን በሚያከብሩባቸው የመዝናኛ ቦታዎች ሁሉ ሊሆን እንደሚገባ ደግሞ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩልም ህብረተሰቡ የደመራንም ሆነ የኢሬቻን በዓል ለማክበር በአደባባዮች ላይ ሲገኝ ራሱን ከጥፋት ኃይሎች በመጠበቅ ንቁ በመሆን አካባቢው ላይ ምን እየተፈጠረ እንዳለ በማወቅና በማሳወቅ ሊተባበር ይገባዋል፡፡

በዚህ መልኩ እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ከተቻለ ወጣቶች የድርሻቸውን ከተወጡ ራሳቸውንም የጥፋት ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ካላደረጉ በዓላቱን በሰላም ከማክበር አልፈን ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መረጋገጥ ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ይሆናል፡፡

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You