ተረት ሀሳብ ነው፣ ፍልስፍና ነው፣ ጥበብ ነው፣ ምርምር ነው ፡፡ ዳሩ ግን ተረት ይህን ያህል ጥልቅ ሀሳብ አይመስለንም፤ እንዲያው ዝም ብሎ እንቶፈንቶ ነገር ይመስለናል ፡፡ እርግጥ ነው ተረት ፈጠራ ነው፤ በፈጠራው ውስጥ ግን ጥበብና ምርምርን እናያለን ።
ተረት ሀሳብ ነው ስንል ሰዎች ለመግባባትና ሀሳባቸውን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ነው ፡፡ በተረት አማካኝነት ስነ ምግባርን፣ አስተዋይነትን፣ ያስተምሩበታል፤ የክፋትን፣ የተንኮልንና የምቀኝነትን መጥፎነት ያሳዩበታል ።
ተረት ጥበብ ነው፤ እንዲያውም የኪነ ጥበብ መጀመሪያው ተረት ነው ብንል ትክክል መሆናችንን ማሳያዎች አሉን ። ለምሳሌ ፊልም፣ ቴአትር ወይም ድራማን እንውሰድ፡፡ ተዋናዮቹ የሚተውኑት በምናብ የተፈጠረውን ገጸ ባህሪ ወክለው ነው ፡፡ገጸ ባህሪ የእነርሱ ባህሪ አይደለም ።ለምሳሌ እልም ያለ ሰካራም ሰው መጠጥ የማይወድ ገጸ ባህሪ ሆኖ እየተወነ ያስተምራል ፡፡ ወይም በተቃራኒው ምንም መጠጥ የማይወድ ሰው እልም ያለ ሰካራም ሆኖ ሊተውን ይችላል ። በዚያ ውስጥ ተመልካቹ የሚማረው የፊልሙን፣ የቴአትሩን ወይም የድራማውን ጭብጥ ነው፡፡
እነዚህ የኪነ ጥበብ ሥራዎች መነሻቸው ተረት መሆኑን የሚያሳዩን ገጸ ባህሪ አላብሰው ማስተማራቸው ነው ፡፡ በተረት ውስጥ ሊነገር የሚፈለገው መልዕክት በጦጣ፣ በዝንጀሮ፣ በጅብ ወይም በሌሎች እንስሳት እየተወከለ ይነገራል ።የተነገረውን ነገር እንስሳቱ ብለውት ወይም አድርገውት አይደለም፤ ዳሩ ግን በዚያ ውስጥ ሀሳብና መልዕክት ነው ማስተላለፍ የተፈለገው ፡፡ በተለይም ለልጆች ተረት ይነገራቸዋል ፡፡ የጦጣ ብልጥነት፣ የዝንጀሮ የዋህነት፣ የጅብ ሆዳምነት ብዙ ጊዜ በተረቶች ውስጥ የተለመደ ነው ፡፡ ይሄ እያደገ ሲሄድ ገጸ ባህሪያቱ ከእንስሳት ወደ ሰውነት መጡ ማለት ነው ፡፡
እንዲያውም በተረት ውስጥ እንኳን እንስሳት ዛፎች ራሱ ገጸ ባህሪ ይደረጋሉ ፡፡ አንድ የማውቀውን ተረት ልናገርና ወደ ጽሑፋችን ዋና ሀሳብ እገባለሁ ። ዛፎች እየተጨፈጨፉ በደል ሲደርስባቸው አንድ መላ አሰቡ ፡፡ በቃ እኛ ዛፎች ከዚህ በኋላ ማንም እንዳይቆርጠን በህብረት ሆነን ራሳችንን መከላከል አለብን፤ እምቢ ማለት አለብን ብለው ተስማሙ ፡፡ በዚህ ስምምነት ውስጥ ሆነው አንድ ሰው ዛፍ ሊቆርጥ መጣ ። ሰውየው የያዘው መጥረቢያ እጀታው እንጨት ነው፤ ያ ማለት ከዛፍ የተቆረጠ ማለት ነው ።ይህንን ሲያዩ ዛፎች ‹‹ለካ ጠላታችን ከእኛው የወጣ ጠማማ ነው›› አሉ ይባላል ፡፡ ይሄ ተረት ምን ያህል መልዕክት እንደያዘ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም ፡፡
የተረት ነገር ጣፈጠኝና መግቢያዬን አስረዘምኩት ። በአገራችን ብዙ ተረት አዋቂዎች አሉ፣ ብዙ የስነ ቃል ሀብቶች አሉ፣ ብዙ የዕደ ጥበብና የኪነ ጥበብ ሥራዎች አሉ።ዳሩ ግን ተረትና አባባል እንኳን ሳይቀር የምንዋሰው ከፈረንጅ ነው ።ከአገራችን የተረት አባቶች በላይ እነ ኤዞፕን እናውቃለን ፡፡ ከኤዞፕ ተረቶች የማያንሱ ግን የአገራችን ተረቶች ነበሩ፡፡ አገራችን ከሰማንያ በላይ ብሄር ብሄረሰቦች እያሏት ግን እንዲህ አይነት ፍልስፍናዎቻቸውን አላጠናንም፤ አልተጠቀምነውም ፡፡ አንድ ጋዜጣ ላመስግን ፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ሁሌም ርዕሰ አንቀጹን የሚጀምረው በአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ተረት ነው ፡፡ ያ ተረት ሀሳቡን ግልጽ ያደርግለታል፤ ከአሰልቺ አገላለጽም ወጣ ብሎ ጥበባዊ አገላለጽ ይኖረዋል ፡፡
እስኪ ለዛሬ በክስታኔ ጉራጌ እና ፀማይ ቋንቋዎች የሚነገሩ ተረቶችን እንቃኝ ፡፡ ተረቶችን የምንቃኘው ጥናትን መሰረት አድርገን ነው። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይህን ጥናት ሰርቶ በ2010 ዓ.ም በመጽሐፍ አዘጋጅቶ አስቀምጦልናል ፡፡ መጻሃፉ ሲመረቅ በመድረኩ ስለነበርኩ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት እንደሚገኙ ሰምቻለሁ፤ ሄዶ ማንበብ ይቻላል ለማለት ነው ።
መጽሐፉ እንደሚነግረን ተረቶቹ በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ ናቸው ። ማህበረሰቡ እውቀቱን የሚያስተላልፈው በእነዚህ ተረቶች አማካኝነት ነበር። አጥኚው ተረቶችን በየቋንቋዎቻቸውና በአማርኛ ያስቀመጠ ሲሆን ለዚህ መጣጥፍ የአማርኛውን ትርጉም ተጠቅመናል ፡፡
ታዲያ ስለክስታኔ ጉራጌም አጥኚው ከሰጠን መረጃ ትንሽ እናካፍላችሁ ፡፡ የክስታኔ ጉራጌ ህዝብ የሚኖረው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ ሲሆን በመስቃንና በማረቆ ወረዳዎችም ይኖራሉ ፡፡ ከአዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ ስንወጣ ከ85 ኪሎ ሜትር ጉዞ በኋላ እናገኛቸዋለን። የጉራጌ ሕዝብ አመጣጡ ከሰሜን ኢትዮጵያ እንደሆነም ጥናቱ ያሳየናል ፡፡ በነገራችን ላይ ጥናቱ ሰፊ ስለሆነ ለዚህ ጽሑፍ ተረቶች ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው ፡ ፡ ጥናቱ ቋንቋውን በጥልቀት ይተነትናል፤ በተለይም ሰዋሰዋዊና ስነ ልሳናዊ ባህሪያቱን ከአማርኛ ትርጉማቸው ጋር ያሳየናል ፡፡ እሱን ከመጽሐፉ አንብቡትና (ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን) ለዛሬው ተረቶቻቸውን ነው የምናየው ፡፡
ጅብ እና አንበሳ
ጅብና አንበሳ ጎረቤታሞች ነበሩ ፡፡ ጅብ ላም ሲኖረው አንበሳ ደግሞ በሬ ነበረው ፡፡ ከብቶቻቸውን ተራ በተራ ይጠብቁ ነበር ፡፡ በአንበሳ ተራ ጊዜ ላሟ ትወልዳለች ፡፡ አንበሳው ጥጃዋን እና የላሚቱን እንግዴ ልጅ ከበሬው እግር ላይ ቋጥሮ ወደ ቤቱ ይዞ ይገባል ፡፡ ይህ ሲሆን ጅብ ያያል፡፡
‹‹ዋው! ላሜ ወለደችልኝ፤ ጥጃዬን ስጠኝ›› ብሎ ጅብ ይጠይቃል ።አንበሳም ‹‹ዞር በል ባክህ!›› ያንተ ላም መቼ ነው የወለደችው? የኔ በሬ ነው የወለደው›› ይላል ፡፡
ጅብ ‹‹እሺ በቃ መተማመን ካልቻልን በሽምግልና እንዳኝ ብሎ ጥያቄ አቀረበ ፡፡ ‹‹እሺ ማን ፍርዱን ይስጠን!›› አለ አንበሳ በትዕቢት ። ጅብም ‹‹የእርስዎ ሽማግሌዎች ጦጣ እና ዝንጀሮ ሊፈርዱልን ይችላሉ›› ብሎ መለሰ ፡፡ አንበሳም በሀሳቡ ተስማማ ፡፡ ሽማግሌዎችም ቀጠሮ ያዙ፡፡
በቀጠሮው ዕለት ዝንጀሮ ፈርቶ ቶሎ ሲመጣ ጦጢት ዘግይታ መጣች ።ጦጢት የዘገየችበት ምክንያት ዝንጀሮው ትክክለኛ ፍርድ ለመፍረድ ይፈራል ብላ ስላሰበች ነበር ፡፡ በመጨረሻም ጦጢት ስትመጣ አንበሳ አይቷት ‹‹እስካሁን የት ቆይተሽ ነው በቀጠሮው ሰዓት ያልተገኘሽው?›› ብሎ በቁጣ ሲጠይቃት ‹‹ኧረ ችግር አጋጥሞኝ ነው›› ብላ በትህትና ትመልሳለች ፡፡ ‹‹ምን ቸግሮሽ ነው? ለማንኛውም ዛፉ ሥር ተቀምጠን እንነጋገራለን›› አላት ።
ጦጢትም የደረሰባትን ችግር ስታስረዳ ‹‹አይ አባ! እኔ ባህር ተቃጥሎብኝ እያጠፋሁ፣ ሰማይ ተንዶብኝ እየገፋሁ ሆኖ ነው እስካሁን የዘገየሁ›› ብላ መለሰች ፡፡ አንበሳውም ‹‹ከመቼ ወዲህ ነው ባህር የሚቃጠለው ሰማይ የሚናደው?›› ብሎ ሊበላት ሲል ጦጢት ዛፍ ላይ ወጥታ
‹‹አንተስ ከመቼ ወዲህ ነው በሬ የወለደ?›› ብላ እውነቱን ተናገረች ይባላል፡፡
በዚህ ተረት ውስጥ ጥልቅ ፍልስፍና እናገኛለን ፡፡ በገሃዱ ዓለም ያሉ በእንዲህ አይነት ነገር አዋቂነታቸው የሚመሰገኑ ሰዎች አሉ ፡፡ እንግዲህ ይህን ተረት የፈጠረው ሰው ነው ፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ከምናደንቃቸው ሰዎች በፊት እንዲህ አይነት ፍልስፍና ያላቸው ማህበረሰቦች ነበሩ ማለት ነው ።ይሄ የጦጣዋ ዘዴ ፊት አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) የሚታወቁበት ዘዴ ነው። አባ መላ የተባሉትም በዚህ ዘዴኛነታቸው ነው ። አንበሳው ኃይለኝነቱንና አስፈሪነቱን ተጠቅሞ የማይሆን ነገር ሲል እሷም የማይሆን ነገር መለሰችለት ፡፡ በቀጥታ ‹‹በሬ አይወልድም›› ብላ ከመሟገት ሌላ ዘዴ ፈጠረች ማለት ነው ፡፡ በእንስሳት በሚነገሩ ተረቶች ውስጥ ጦጣ የብልጥነት ገጸ ባህሪ ነው የሚሰጣት ፡፡
ይህ በክስታኔ ጉራጌ እና ፀማይ ቋንቋዎች ተረቶች ላይ የተሰራ ጥናት ከ40 በላይ ተረቶችን የያዘ ነው ።ተረቶቹ በሚነገሩባቸው ማህበረሰብ ቋንቋና በአማርኛ ተቀምጧል ።አሁን ደግሞ በፀማይ ማህበረሰብ ከሚነገሩ ተረቶች አንዱን እና ስለፀማይ በጥቂቱ ጠቅሰን ቀሪውን አንብቡት።
የፀማይ ህዝብ የሚኖረው በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በበና ፀማይ ወረዳ ውስጥ ሲሆን በቡራ፣ በግስማ፣ በቦላ፣ በጎኔ በአየመሌ ይገኛሉ። የፀማይ ህዝብ ፀማኮ ወይም ፀማይ ሲባል ቋንቋው ፀማይኛ ይባላል ፡፡
ውሻ እና ቀበሮ
አንድ ጌታውን በታማኝነት የሚያገለግል ውሻ ነበር ።እነርሱ በሚኖሩበት አካባቢ ደግሞ አንድ ቀበሮ ነበረች ።ቀበሮዋም ማታ ማታ የግቢውን አጥር ትዞራለች ፡፡ ቀበሮዋ አጥሩን ስትዞር ውሻው ይጮሃል ።ከዕለታት አንድ ቀን ውሻው ከግቢ ሲወጣ ጠብቃ ‹‹ለምንድነው ግን ማታ ማታ የምትጮኸው?›› ብላ ታናግረዋለች።‹‹የጌታዬን ቤት ስለምጠብቅ ነው›› ብሎ ይመልስላታል ። ቀበሮዋም አግባባችውና ከቤቷ ሄደው ምግብ ጋበዘችው ፡፡ ውሻውም በተራው ሌላ ቀን ቀበሮዋን ይጋብዛታል ፡፡ ቀበሮዋ ስትመጣ ግን የቤቱ ባለቤቶች ቀበሮዋን በድንጋይ ያባርሯታል ።ቀበሮም በዚህ ቂም ይዛ ውሻውን ማደን ጀመረች። ከዚያ በኋላ ውሻና ቀበሮ ጠላት ሆኑ ይባላል፡፡
በተረቶቻችን ውስጥ እንዲህ አይነት ሐተታ ተፈጥሮዎች አሉ።እነዚህ አጋጣሚዎች አፈ ታሪክ ናቸው ።ለምሳሌ በቅሎ የማትወልድበት ምክንያት፣ ሚዳቋ ከአንድ በላይ የማትወልድበት ምክንያት በሐተታ ተፈጥሮ የሚነገር አፈ ታሪክ አላቸው። ምናልባት መነሻ ምክንያት ሊኖራቸው ስለሚችል ፈጠራ ብቻ ናቸው ብሎ ማለፍም ይከብዳል፡፡
በተረቶቻችን ውስጥ የፍልስፍና እና የምርምር ጅማሮዎችን እንረዳለን። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ራሱ መነሻቸው ምናባዊ ፈጠራ ነው ። እነዚህ ተረቶቻችን ለብዙ ነገር ጅማሮ የሆኑ ናቸው ።ለምሳሌ ከ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ በፊት የነበሩ የልቦለድ መጽሐፎች አጀማመራቸው በተረት መልክ ነው። ‹‹እንዲህ እንዲህ ነበር›› ብለው ይጀምራሉ። ይህም ተረቶች የጥበብ መነሻ እንደሆኑ ያሳየናል።እነዚህን ተረቶቻችንን ልናጠና እና ልንመረምራቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2011
ዋለልኝ አየለ