ለትምህርት ጥራት፤ መምህራንንም ማጥራት

መምህርነት የሙያዎች ሁሉ አባት ነው። መምህርነት ትውልድን የመቅረፅ ክቡር ሙያ ነው፡፡ መምህርነት የሰው ልጅን ያህል ክቡር ሕንፃ የሚታነፅበት በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄና ብስለትን ይጠይቃል፡፡ በሌሎች ሙያ ዘፎች ለአብነት በምህንድስና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥራቸው ቢጣመም መልሰው ሊያቃኑት ይችላሉ። ቢበላሽ ያፈርሱታል፡፡ የተጣመመ የሰው ሕንፃ ግን በቀላሉ አይቃናም፡፡

መምህርነት የሰው ልጆችን ወደ ሠለጠነ የማኅበራዊ ዕድገትና ብልፅግና ከፍታ የሚያወጣ መሰላል ነው። የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ በአንድ ወቅት ‹‹እኔ ጠፈር ላይ የወጡትንም አላደንቅም። የማደንቀው እነዚህን ሰዎች ለትልቅ ደረጃ ያደረሷቸው መምህራንን ነው›› ማለታቸውን ይታወሳል፡፡

የአንድ ሀገር የትምህርት ጥራትም ካላት የመምህራን ጥራትና ብቃት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፡፡ ዓለማችን በየዘመነ መንግሥታቱ ያጋጠማትን ውድቀቶችና መንስኤያቸውን ብንመረምር፤ ጉዳዩን ከመምህራን ሚና ጋር በአንድ ወይም ደግሞ በሌላ በልኩ የሚያቆራኘው ምክንያት ስለመኖሩ መገንዘብ እጅጉን ቀላል ነው፡፡

ይህን እሳቤ ዳምጠው ወልዴ ‹‹ለስኬታማ የመምህርነት ሙያ ቁልፍ መሣሪያዎች ምንድ ናቸው›› በሚል በ2009 ዓ.ም ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ውስጥ ‹‹አንድ ሀገር የትምህርት ጥራት ካላት የመምህራን ጥራትና ብቃት አይበልጥም፡፡ አያንስምም›› ሲሉ ያጠናክሩታል፡፡

ዜጎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ብቁና በምክንያታዊነት የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረ ገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ የትምህርት ጥራት እጅጉን ወሳኝ ነው፡፡

መምህራን ደግሞ ለትምህርት ጥራት ሁነኛ ተዋናይ ናቸው፡፡ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ መምህር ከሚጫወተው ሚና ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዝ አይገኝም። ትምህርት ቤቶች በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ካሉ ሌሎች አቻ ተቋማት ጋር ራሳቸውን ቢያነፃፅሩ ጥራትና ብቃት ያላቸው መምህራን ከሌሏቸው የትምህርት ጥራት ሊጠበቅም ሊዳብርም አይችልም። ምክንያቱ ደግሞ ለድርጅትም ሆነ ለተቋም ሕይወት የሚሰጡትና ሊሰጡትም የሚችሉት መምህራን ስለሆኑ ነው።

አንድ ሀገር ስኬትና ኪሳራን የምታወራርደው ባለመችው፣ እልምታም ባበቃችው ትውልድ ነው። ትምህርት ደግሞ ይህን ትውልድ እውን ለማድረግና ለአንድ ሀገር እድገት መሠረት፣ ዋልታና ማገር መሆኑ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያም፣ ‹‹የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም››፣ ተማር ልጄ… ተማር ልጄ….. ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው›› የሚለው የእናት አባት ምክር ከቃል አልፎ በሙዚቃ ተከሽኖ ትውልድ የተሻገረባት፣ ‹‹መማር ያስከብራል ሀገርን ያኮራል!›› የሚለው ቃልም በዜማ ታጅቦ በዝማሬ ሲሰማ የቆየባት ሀገር ናት።

በሀገሪቱ መምህርነት እጅግ ከተከበሩ ሙያዎች ቀዳሚው ነው፡፡ ሙያው ምን ያህል ይከበር እንደነበር ጠንቅቆ ለመረዳትም ሌላው ቀርቶ ከመምህር ጋር በጋብቻ መተሳሰር ከዕድለኝነት ጋር ጭምር የሚቆራኝ መሆኑን ማስታወስ በቂ ነው። ‹‹የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ፣ ወሰዳት አስተማሪ›› ተብሎ መገጠሙም ለዚህ ማስረጃ መሆን የሚችል ነው፡፡

በእርግጥም ከትናንት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ጉዞ ውስጥ መምህራን በአስቸጋሪ ሁኔታ ጭምር ተረማምደው ራሳቸውን አቅልጠው ለሌሎች ብርሃን ሆነዋል፡፡ ይብዛም ይነስም ለተገኘው ውጤት የነበራቸው አስተዋፅእ ማንም ሊክደው የማይችል ሃቅ ነው፡፡

ይሁንና በሀገሪቱ ሲተገበር የነበረው የትምህርት ሥርዓት የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋት ላይ እንጂ ጠንካራ ዜጋን ማፍራት በሚችሉ ምሁራን ልማት አንፃር ኪሎው ሲፈተሽ አልተሠራው ወደሚለው አቅጣጫ የሚያመዝን ነው፡፡

በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የመምህራን የብቃት ችግር ለትምህርቱ ጥራት ውድቀት አስተዋጽኦ ሲያደርግ እንደሚስተዋልም በተደጋጋሚ ተነግሯል። ለትምህርት ጥራት መልፈስፈስ ብሎም ሞት በተለይ አንዳንድ መምህራን ለሚያስተምሩበት ክፍል የሚመጥን አቅም የሌላቸው መሆን በምክንያትነት ይነሳል። ችግሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም ሳይቀር የሚስተዋል መሆኑ ደግሞ ቀውሱን ሌላ ምስል ይሠጠዋል።

ይህ ማለት ግን ብቃቱ ያላቸውና በሙያዊ ሥነምግባርም ሆነ እውቀት በርካቶችን የሚያስማሙ በተገኙበት ሁሉ የአክብሮት ብሎም የአድናቆት ጭብጨባ የሚያስቸራቸው ጉምቱ መምህራን የሉም ማለትም አይደለም፡፡

ሆኖም የአቅም ውስንነት ያለባቸው፣ አቅም እያላቸውም የማስተማር ተነሳሽነት የጎደላቸው ቁጥር ጥቂቶች ናቸው በሚል ብቻ የሚታለፍ አይደለም። አንዳንዶቹም ከነጭራሹ ማስተማር ከሚጠይቀው ጥበብ ብሎም ሳይንስ ጋር እንደማይተዋወቁ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡

በብዙ የትምህርት ሊቃውንት ተደጋግሞ እንደተፃፈውና እንደተነገረው ‹‹ማስተማር ሳይንስም ጥበብም ነው። ማስተማር በጥበብነቱ እንደተማሪው፣ እንደወቅቱ፣ እንደኅብረተሰቡ የእድገት ደረጃ እያደገ እየተሻሻለ እየተለወጠ የሚሄድ ነው።

ከታች አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለው እርከን የመምህራን ሙያዊ ቁመና ከጊዜ ጋር አብሮ ማራመድ፣ ለመምህራን አቅም ግንባታ ትኩረት መስጠት የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ሂደት ሲታሰብ አብሮ ልብ ሊባል የሚገባው መሠረታዊ ነጥብ መሆን እንዳለበት እርግጥ ነው፡፡

ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ መምህራን የሙያቸው ባህሪይ የሚያስገድዷቸው ዝግጅት አንዱ የሚያስተምሩትን ትምህርት ጠንቅቆ ማወቅናም ማሳወቅ ነው። ትምህርት የነገ የሀገር ተስፋ የሆኑ ተማሪዎችን በእውቀት፣ አመለካከትና ሥነምግባር ቀርጾ የማውጣት ቁልፍ ሲሆን ፈተና ደግሞ የዕውቀት መለኪያ ነው። ፈተና ተማሪዎች በትምህርት ወቅት በገበዩአቸው እውቀቶች ልክ የሚፈተሹበትና የሚለኩበት ሚዛን ነው።

የመምህራን የማስተማር ብቃት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ ተማሪዎች በሥርዓተ-ትምህርቱ ሊጨብጡት የሚገባን ንድፈ-ሀሳቦችን theo­retical knowledge ወይንም ዕውቀት በአግባቡ መጨበጣቸው እንዲሁም የተማሩትን ተፈትነው ማለፍ መቻላቸው ነው።

በዚህ የአቅም ልኬት ሚዛን ስንመለከተው በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የመምህራን አቅም ጥያቄ ውስጥ ስለመሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃዎችን ማቅረብ እጅጉን ቀላል ነው። መጥቀስ ካስፈለገም በተለይ ባለፉት ሁለት ብሔራዊ ፈተናዎች የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት ማስታወስ ብቻውን በቂ ነው፡፡

አስደንጋጩ የውድቀት ምጣኔ ለእኔ የተማሪዎቹ አቅም እንዳለ ሆኖ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ አስተማሪዎች ከተመለመሉበት፣ ከሠለጠኑበት መንገድ እና የተንሻፈፈ ጉዞ እንዲሁም ሁለንተናዊ አቅም ጋር የሚተሳሰር ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም ይህ የመምህራን አቅም ጉዳይ አሳሳቢ ስለመሆኑ ከሚስማሙት ወገን ናቸው፡፡ ‹‹በሚያስተምሩበት ትምህርት ፈተና ተሰጥቷቸው ምዘናውን ያለፉ ከ50 በላይ ያገኙ መምህሮቻችን ከ30 በመቶ በታች ናቸው›› ሲሉ መደምጣቸው የሚታወስ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከታች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ያለው የትምህርት አሰጣጥ ጥራት የጎደለው መሆኑ ታምኖበት የተሻሻለ የትምህርት ፍኖተ ካርታና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ይሁንና ለትምህርት ጥራት ሥርዓተ ትምህርት መቅረፅ ወይም የትምህርት ፖሊሲን ማሻሻል ብቻ ውጤት በቂ አይደለም።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ እርምጃ የሚጠበቀውን ያህል አመርቂ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በተለይም እያንዳንዱ መምህር የተሻለ አዲስ ትውልድ በመቅረፅ ረገድ ያለውን ሁለንተናዊ አቅም በመፈተሽ ሊሆን የግድ ይላል፡፡

ብቁና ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት ዩኒቨርሲቲን የሚቀላቀሉና ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ተማሪዎችን ለማጣራት የተኬደበትን ውጤታማ መንገድ መምህራንን በማጣራትም ሊደገም ይገባል፡፡ ጥራት የሚጀምረው ያላጠራውን በማጥራት ነው፡፡ በተለይ ለትምህርት ጥራት፣ መምህራንንም ማጥራት የግድ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ይረዳኛል፣ ትውልድ እና ሀገርን ከውድቀት ይታደጋል ብሎ በማመን አዲስ የትግበራ አቅጣጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ አጋርነቱን እየተወጣ ነው፡፡ በተለይ ከመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራት ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል፡፡

በዚህ ሂደትም ለትምህርት ጥራት፣ አስተማሪውን ማጥራት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች እጅግ ወሳኝ መሆናቸውንም ሁሉም ልብ ሊል ይገባል፡፡ ምክንያቱም ብቃት በሌላቸው መምህራን የተማሩ ተማሪዎች በሥነ ምግባር፣ በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የታነፀ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መሆን አይቻላቸውም። የኪሳራ አቅምና ጥፋት መጠናቸውንም በቀላሉ መገንዘብ የሚቻል ነው፡፡

ብቃት በሌላቸው መምህራን የተማረ ዶክተር የሆነ ሰው አክሞ ማዳን አይሆንለትም፡፡ ብቃት በሌላቸው መምህራን የተማረ ዳኛ በሙያው መነፅር ሰዎችን እኩል አይመለከትም፡፡ በመርህና በሕግ ተመስርቶ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ ጥቅማ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ውሳኔን ቀዳሚ ምርጫው ያደርጋል፡፡

ይህ እንደመሆኑም ለትምህርት ጥራት ሥርዓተ ትምህርት መቅረፅ ወይም የትምህርት ፖሊሲን ማሻሻል ብቻው ለውጥ አያመጣም። ኢትዮጵያ ተስፋን ከሰነቀችባቸው የሥርዓት ለውጦች መሀል አንዱ በትምህርቱ ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ የሚፈለገውን ግብ እንዲመታ በተለይም በየደረጃው በቂና ብቁ መምህራንን ማፍራት ያስፈልጋል።

የመምህራንን የቅጥር ሥርዓት ማስተካከልና የተለያዩ የምዘና ሥርዓቶችን መዘርጋት እጅጉን ወሳኝ ነው። ለትምህርቱ ጥራትና ዕድገት ቁልፍ እና ዋነኛ የማዕዘን ድንጋይ ለሆኑት ሙያዊ ምልመላና ሥልጠና፣ ምደባና ደመወዝ፣ ግምገማና እድገት እንዲሁም የአካዳሚ ነፃነት ልዩ ትኩረት መስጠት ይጠይቃል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራን የኑሮ ሁኔታ፣ ክህሎትና የሥራ ዲሲፕሊን እንዲሁም የሥራ አካባቢን ማሻሻል ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የመምህራንን ኑሮ በመቀየር መምህራን ስለ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከማሰብ ወጥተው አንብበውና ተዘጋጅተው እንዲያስተምሩ ማድረግም መረሳት የለበትም፡፡ ፍላጎትና ተሰጥኦ ላይ መሠረት ያደረገ የመምህርነት ሙያ ሥልጠና መስጠት የትምህርት ጥራቱን ለማጎልበት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ እውነታ አኳያ በተለይም ትውልድን የመቅረፅ ሙያዊ ኃላፊነት የተጣለባቸው ዜጎች ተደርገው የሚወስዱት መምህራን፤ ታሪካዊ ሚናቸውን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዜጎች እውቀትን የሚሹ፣ ለእውነት የቆሙ፣ በዕውቀት ላይ ወደተመሠረተ ውሳኔ ላይ የሚደርሱ፤ በሰላምና በመቻቻል የሚያምኑ ሆነው እንዲቀረፁ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው።

የትምህርት ጥራት ችግሩ በአንድ ሌሊት እንዳልተፈጠረ ሁሉ መፍትሔውም በአንድ አዳር ሊመጣ አይችልም። ለማስተካከል ረጅም ጊዜና ከባድ ዋጋን ይጠይቃል። ይሁንና የትናንት ስህተት የፈጠረውን የዛሬ ስብራት ተረድቶ ዘላቂ መፍትሔ ከሚፈጥሩት ወገን ለመሆን እራስን ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡

ታዋቂው የሳይንስ ሊቅ አልበርት አንስታይን እንዳለውም «አንድን ነገር በተመሳሳይ ዘዴ ደግሞ ደጋግሞ በመሥራት የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው» በመሆኑም አዲሱን የለውጥ መንገድ የግድ ልንቀበልና በተለየ መንገድ በመራመድ ለችግሩ መፍትሔ ልንሰጠው ይገባል፡፡

መንግሥትም ለትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት የሆኑ ስንክሳሮችን ለማስተካከል የጀመራቸውን ውጤታማ የማጥራት ተግባራት እንደ ተማሪው ሁሉ መምህራንም እየቃኘ ይበልጡን ሊቀጥል ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ገና አልረፈደም !።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You