የትውልዱ አዲስ የታሪክ ትርክት

 መገኛውን በጉባ ወረዳ ያደረገው ታላቁ የዓባይ ግድብ አንድ ሺ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ስፋት የሚሸፍን ነው፡፡ የሀገር ኩራት የሆነው ይህ ታላቅ ግድብ መገኛውን ኢትዮጵያ በስተምዕራብ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ጉባ ያድርግ እንጂ በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የተቀመጠ ስለመሆኑ ብዙም ጥርጣሬው የለኝም፡፡

ቤተ ሰሪ ደም የለውም ይባላል፤ እርግጥ ነው ደም የለውም፡፡ ምክንያት ቢባል ቤቱ የሳር ክዳን ያለው ጎጆ ይሁን አሊያም ዛኒጋባ፤ አሞራ ክንፍ ይሁን ወይም ደግሞ ባለአንድ እና ከዚያም በላይ ወለል ያለው ሕንፃ፤ ቪላ ይሁን ወይም ሌላ እንደየኪሱ መጠን የሚሠራ ነው።

ባለቤቱ ቤቱን በቀጣይ ዘመን የሚኖርበት እንደመሆኑ ያለውን አንጡራ ሀብት አሟጥጦ ይቀልሳል፤ አጠናቅቆም ወደቤቱ ሲገባ የ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› መልካም ምኞት ይከተለዋል፡፡ ኢትዮጵያም የዓባይ ግድብን በመንግሥቷ አስተባባሪነትና በልጆቿ ተባባሪነት ወደሥራ ከገባች እነሆ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ምንጣሮውን፣ ቆፋሮውን፣ ወዘተ… አጠናቅቃ ቅድመ ውሃ ሙሊት የነበረውንም ጉድጉዷን አከናውኗ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ዋና የተባለውንና የተናፈቀውን የመጀመሪያውን ዙር ውሃ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዟ ይታወሳል፡፡ የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቁንም በጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካይነት ማብሰሯ አይዘነጋም፡፡

በእርግጥ ይህም የሆነው ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ በፈጣሪ ቸርነት በተገኘው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ነው፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሰንደቃችን ያህል ምልክታችን ወደ ሆነውና በግንባታ ላይ ወዳለው ታላቁ የዓባይ ግድብ መንቆርቆር ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የተፈለገው ውሃ መያዙን አጋርም አደናቃፊም ማየቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውሃ ሙሊቱንና ዓመታዊ የሥራ ክንውንን በተመለከተ ኢትዮጵያ የውሃ አጠቃቀሟ ፍትሐዊና ሚዛናዊ እንደሆነ ይቀጥላል ማለታቸው የሚረሳ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ ሥራዋን በአንክሮ ትሠራለች፤ በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ቀና ትልና የሰማዩን መጥቆር ትመለከታለች፤ ፈጣሪም የእርሷ ተባባሪ እንደሆነው ሁሉ የኢትዮጵያን ሰማይ በደመና ይሞላል፤ በደመና መሙላት ብቻ ሳይሆን በሀገሬ ሰማይ ላይ የሚያዣብበው ደመና ወደውሃ ይቀየራል። ያለስስት ታላቁን ግድብ ይሞላዋል፤ በቃ ይኸው ነው – በትይዪዋ ያለውን ጩኸት ሳትሰማ የመጀመሪያውን ሙሌት በድል ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ‹‹የውሃ አጠቃቀማችን ፍትሐዊ እንዲሆን እሻለሁ›› በሚል ጽኑ እምነት ዝግጅቷን ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ላይ አጠናቃ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ቀጥታ ስርጭት ለኢትዮጵያውያንና ለወዳጆቿ በኩራት፤ እንዲያዩት መደረጉ የአደባባይ ምስጢር ሆኖ አልፏል፡፡

ኢትዮጵያ፣ የገነባችው ግድብ የሚዳሰስ ቅርስ ወይም ሐውልት አይደለምና ግንባታውም ሆነ ውሃ ሙሌቱ አንዳች ሳይናጠብ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማከናወኗ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ያንን ስታደርግ በማን አለብኝነት መንፈስ አልነበረም፤ አይደለምም፡፡ ከውሃ ሙሌቱ ጎን ለጎን ድርድሩንም እንደምታስኬድ ደጋግማ ስትናገር ቆይታለች፤ አሁንም እየፈጸመች ያለው ያንኑ ቃሏን ነው፡፡

በ2014 ዓ.ም ነሐሴ 5 ቀን ይፋ የተደረገው የሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም ኢትዮጵያ ቃሏን ጠብቃ ያከናወነች ተግባር እንደሆነ አይረሳም፡፡ በወቅቱ ‹‹ኢትዮጵያ ከእኛ ጋር ሳትስማማ ለሦስተኛው ዙር ለመሙላት እየተዘጋጀች ነው›› በሚል ጉዳዩ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት

 ቢቀርብም፤ በወቅቱ ግድባችን በውሃ መሞላት ብቻ ሳይሆን ካሉት ሁለቱ ተርባይኖችም ዓይኖቻችን የናፈቁትን ብርሃን ማፍለቅ መጀመራቸውን መስማት ችለናል።

በዚህ ሂደት ሁሉ ኢትዮጵያ በወንዙ ፍትሀዊ አጠቃቀም ዙሪያ በያዘችው አቋም እንደጸናች ነው። በቅርቡ ‹‹የአፍሪካ ሀብት ለአፍሪካውያን ብልጽግና›› በሚል መሪ ሐሳብ የአፍሪካ የወሰን ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ባተኮረው 2ኛው ‹‹አፍሪ ራን›› ፎረም ላይ እንኳን፤ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበው እንደነበር የሚታወስ ነው ፡፡

ሁለቱ የታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት (ግብጽና ሱዳን) ከአፍሪካ ኅብረት ይልቅ የድርድር ሒደቱ በአሜሪካ ወይም በአውሮፓ ኅብረት አሊያም ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አደራዳሪነት እንዲካሄድ ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ፤ የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ እንዲሉ ጉዳዩ የአፍሪካውያን በመሆኑ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ትሻለች ፡፡

ይህን ማለቷ የሌላውን ሀገር ወይም ተቋም አሳንሶ ማየት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ነገር ግን የእነርሱ ድርሻ ከታዛቢነት እንዲዘል አትሻም፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ ምክረ ሐሳብ ቢሰጡ አትከፋም። ከዚህ ከዘለለ ግን እውነታን ለመጨፍለቅ የተነሳ ክንድ አድርጋ የምታይ ትሆናለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን መሻቷ ለእኔ ብቻ የሚል ሳይሆን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ነው።

አሁን በግድቡ ዙሪያ የሚነገሩ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ቦታ አይኖራቸውም፤ ከ ‹‹ግድቡ መገንባት የለበትም›› ጀምሮ ‹‹የተገነባው ግድብ ከእኛ ፈቃድ ውጪ ውሃ መሞላት የለበትም›› እስከሚለው ድረስ ኢትዮጵያ ብዙ ተግዳሮቶችን በብቃትና በብልሃት አልፋለች፡፡

እርግጥ ነው እስከ ሦስተኛው ዙር የነበረው የውሃ ሙሌት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በተለይ በግብጽ በኩል ያልተፈነቀለ ድንጋይ ባይኖርም ከቃሏ ዝንፍ ያላለች ኢትዮጵያ ግን ሦስቱንም ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት አጠናቃለች፡፡

የተለመደው ተጽዕኖ ዛሬም ድረስ ያልተረቋረጠ ቢሆንም ኢትዮጵያን ዓለምአቀፍ መርህን መሠረት ባደረገ መንገድ እያካሄደች አራተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ባለፈው ጳጉሜን 6 2015 ዓ.ም በተሳካ ሁኔታ ማከናወኗን በአደባባይ ይፋ አድርጋለች። ይህም የትውልዱ አዲስ የታሪክ ትርክት ሆኖ ተዘግቧል።

አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ መጠን እና 145 ሜትር ከፍታ ያለው ታላቁ የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍ ብሎ የተቀመጠና እንደ ዓይናችን ብሌናችን የምንሳሳለት ነው ! አበቃሁ ፡፡

ወጋሶ

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You