ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ መስፈርቱ ሰብዓዊነት ብቻ ነው!

 ዓለማችን በተለያዩ ምክንያቶች ሕዝቦቿ ችግር ላይ ሲወድቁ እና የሌሎችን ድጋፍ ሲሹ ለእነዚህ ሕዝቦች መድረስ የምትችልበትን የራሷን ሥርዓት አበጅታለች፡፡ በዚሁ አግባብ ለዘመናት ሲገጥማት በነበረ ሰው ሰራሽ (እንደ ጦርነት) እና የተፈጥሮ (ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥን የመሳሰሉ) በአደጋዎች ምክንያት ከፍ ያለ ሰብዓዊ ቀውስ ለገጠማቸው ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ስታደርስ ቆይታለች፤ እያደረሰችም ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ከድህነቷ ባሻገር የእነዚህ የሰው ሰራሽም ሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች በተደጋጋሚ ተጠቂ ሆናለች፡፡ ዜጎቿም በእነዚሁ ምክንያቶች ለሞት፣ ለስደት፣ መፈናቀልና ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ጦርነትና ሌሎችም መሰል ክስተቶች ደግሞ በኢትዮጵያ ጎልተው ከሚጠቀሱ ዜጎችን ለችግር እያጋለጡ ካሉ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በእነዚህ ክስተቶች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ታዲያ አንድም በራስ አቅም፤ እጅ ሲያጥርም የውጪ መንግሥታትና ድርጅቶችን ጠይቆ ሰብዓዊ ድጋፍን ማድረስ የተለመደ ነው፡፡ ይሄው ሲደረግም ቆይቷል፡፡ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት እንደ ሀገር ከፍ ያለ ተጽዕኖ በነበረው ጦርነት፤ እንዲሁም ድርቅና መሰል ጉዳዮች ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ የተጋለጡ ዜጎችን ደርሶ መደገፍ የተቻለውም በዚህ መልኩ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ እና ለማደግ እየተፍጨረጨሩ ባሉ ሀገራት ለዜጎች እንዲደርስ የሚፈለገው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በራስ አቅም ማድረግ ያልቻለ ሀገር የድጋፍ አድራጊ ሀገራትና ተቋማትን የሰጥቶ መቀበል መንገድ ይሁነኝ ብሎ መቀበል ይጠበቅበታል፡፡ ይሄው መንገድ ለዘመናት በኢትዮጵያም ተንሰራፍቶ ቆይቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ በራሷ ለመቆም ቀና ቀና ማለቷ እምብዛም ያልተዋጠላቸው አልጠፉም፡፡ ቀና ማለቷ ስጋት የሆነባቸው ኃይሎችም አልጠፉም፡፡ እናም ሰብዓዊ ድጋፍ እንደ አንድ አንገት ማስደፊያ መሳሪያ ተደርጎ የተያዘ እንደመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ላለው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት መልስ ማግኘትም እንደ ሀገር የእጅ ተጠምዛዥነትን ሰብዕና እንድትላበስ ወደማስገደድ አመራ፡፡

ይሄ ግን ፈጽሞ የሚሆን አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ጉዳይ የፖለቲካ እና የዜጎች ልዕልና ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ፈጽሞ ከሰብዓዊ ድጋፍ ጋር የሚያያዝ አይሆንም፡፡ እናም ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ ስም የሀገርና ሕዝብን ሉዓላዊነትና ክብር ለመጨፍለቅ የሚደረግ ጥረት ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡

ለሰብዓዊነት በሚል ከተቋቋመ ተቋም እና ይሄንኑ ተቋም ካቋቋመ ሀገርም ይሄን መሰል አካሄድ ፈጽሞ የሚጠበቅ አይሆንም፡፡ ለእኔ ካልተገዛህ፣ የእኔን ሃሳብና መንገድ ካልተከተልክ ለዜጎችህ የሰብዓዊ ድጋፍ አላደርስም ማለትም ከፖለቲካ እሳቤ እንጂ ፈጽሞ ከሰብዓዊነት የሚመነጭ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያም በተደጋጋሚ እየታየ ያለው ይሄን መሰል አካሄድ፤ ባልተገባ ክስና ውንጀላ ምክንያት የፖለቲካ ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲባል በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች የሚደርስን የሰብዓዊ ድጋፍ እስከማቋረጥ የደረሰ ርምጃ መወሰዱ ይታወቃል፡፡ ይሄ ተግባር ደግሞ ዜጎች ለከፋ ችግር እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡

ለአብነትም፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ሌሎችም አጋር የሰብዓዊ ተቋማትና አካላት በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ሰብዓዊ ድጋፍ ለተወሰኑ ወራት ማቋረጥ ያሳደረውን ተጽዕኖ መመልከት ይቻላል፡፡ ሆኖም ይሄን ከሰብዓዊነት ዓላማ ባፈነገጠ ምክንያት የተፈጠረውን የዜጎች ሰቆቃ ለመግታት የፌዴራል መንግሥቱ በራሱ አቅም ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል፡፡

በዚህም በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ሰቆቃ ለመቀነስና ክፍተቱን ለመሙላት መንግሥት ከራሱ የመጠባበቂያ የምግብ ክምችት ወጪ አድርጎ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ለአራት ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

አሁንም የአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ከአራት ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች የሁለተኛ ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ይሄንኑ የመጠባበቂያ መጋዘኑን በድጋሚ ለመክፈት ተገድዷል፡፡ ከችግሩ ክብደት አኳያም የሁለተኛውን ዙር ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማድረስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል፡፡

በዚህ መልኩ በየ45 ቀኑ በዙር እንዲደርስ የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፉ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ መንግሥትም ይሄን ኃላፊነቱን ለመወጣት ባለው አቅም እየሠራ ሲሆን፤ ሥራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም ከክልል መንግሥታት ጋር በጥምረት እያከናወነ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ የሰብዓዊ ድጋፍን ለሰው ልጆች የማድረስ ኃላፊነት የአንድ ሀገር መንግሥት ብቻ የቤት ሥራ ሊሆን አይገባውም፡፡ ምክንያቱም የሰብዓዊ ድጋፍ ለሰው ልጆች ከሰው ልጆች የሚደርስ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሰው መሆንን እንጂ የፖለቲካ አመለካከትና አቋምን የሚሻ ተግባር አይደለም፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች (ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶች…) የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን መደገፍ ከሁሉም የሰብዓዊ አካላት የሚጠበቅ እንጂ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የብቻው ኃላፊነት አለመሆኑን መገንዘብ፤ ሀገራትና ተቋማትም ሰብዓዊነትን ማዕከል አድርገው በዚህ ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል!

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You