በጋና ለሩሲያው ቫግነር የድጋፍ ሰልፍ አስተባብረዋል የተባሉ ክስ ተመሰረተባቸው

በጋና ለሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር የድጋፍ ሰልፍ አስተባብረዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ፖሊስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተዘጋጀውን የድጋፍ ሰልፍ የመሩ ናቸው ባላቸው አምስት ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን አረጋግጧል።

በጋና ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው ታኳሪዲ ግዛት ጥቂት ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ የተካሄደው የቫግነሩ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በአውሮፕላን መከስከስ ሕይወቱ ከማለፉ 10 ቀናት ቀደም ብሎ ነበር።

በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች የቫግነር ቅጥረኛ ቡድንን መለያ ከነቴራ አጥልቀው እና የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ እንደነበር የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቫግነር እንደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሊቢያና ማሊ ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ ስምሪት አለው። በጋና ሰልፉን እንዳዘጋጁ የተጠረጠሩ ሰዎች በሚቀጥለው ሳምንታት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን የቀረበባቸው ክስ ይዘት በተመለከተ ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ አጋር የነበረው ፕሪጎዢን የሚመራው የዋግነር ኩባንያ በዩክሬን ጦርነት ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ይሁንና ባለፈው ነሀሴ ወር የዋግነር ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት የነበረው አውሮፕላን መከስከሱ ይታወሳል።

ኢምብራየር ሌጋሲ የተሰኘው አውሮፕላን ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሲበር እንደነበር የሩሲያ አቪዬሽን ባለሥልጣናት አስታውቀው ነበር። አውሮፕላኑም በሰሜናዊ ሞስኮ በሚገኘው ቴቨር ክልል የመከስከስ አደጋ እንዳጋጠመውም ባለሥልጣናቱ አረጋግጠዋል።

ገር ግን ከቫግነር ጋር ግንኙነት ያለው ግሬይ ዞን የተሰኘው የቴሌግራም ገጽ ጄቱ በሩሲያ ጦር ተመትቶ መውደቁን ዘግቧል። በጋና ይህ ከመሆኑ 10 ቀናት አስድሞ ነበር ጥቂት ሰልፈኞች ድጋፍ ለማድረግ አደባባይ የወጡት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You