ከዓለም የቆዳ ስፋት 27 በመቶ በሚሸፍኑት፣ ከዓለም ሕዝብ የ42 በመቶው ባለቤት በሆኑት፣ ለጠቅላላው የዓለም ምርት 27 በመቶ ያህሉን በሚያበረክቱት እንዲሁም በፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከሚገኙ የዓለም ሀገራት መካከል ግንባር ቀደሞች በሆኑት ብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት የተመሠረተው ‹ብሪክስ› (BRICS) አባል ሀገሮች የገቢ ንግድ ከፍተኛ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
መረጃዎቹ እንዳሉት፤ የአባል ሀገሮቹ በዓለም ላይ ያሉ ሸቀጦችን ወደ ሀገራቸው በማስገባት ረገድ 14 በመቶ ጥቅል ድርሻ አላቸው፤ የቻይናን የገቢ ንግድ ብቻ ብንመለከት እስከ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ሲደርስ፣ በጥቅሉ አምስቱ ሀገሮች ብቻ 3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር የገቢ ንግድ ልውውጥ አላቸው።
ቡድን 7 በመባል የተሰባሰቡት ሀብታምና ሃያላን ሀገሮች የጋራ ሀብት እዚህ ሀብት ላይ አይደርስም፤ የብሪክስ ስብስብ ሀገሮች ከቡድን 7 ሀገሮች በላይ በፍጥነት እያደጉ ያሉ፣ በቀጣይም ለማደግ ሰፊ ተስፋ ያላቸው ሀገሮች ናቸው፤ ቻይናና ህንድን የመሳሰሉት ሀገሮች ደግሞ የበለጠ ለማደግ ምቹ ሁኔታና ተስፋ እንዳላቸውም መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
ጥምረቱ አጀማመሩ ምጣኔ ሀብታዊ ዓላማዎች ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ ጥምረት ቀስ በቀስ የተደራጀ ዓለም አቀፋዊ የጂኦፖለቲካ ቅርፅና መዋቅር ይዞ፣ ዛሬ የ‹‹ቡድን ሰባት›› (G7) አቻ ተፎካካሪ ሆኖ እየተጠቀሰ ነው። የጥምረቱ አባላት ያቋቋሙት ‹‹ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ›› (New Development Bank) የምዕራባውያን፣ በተለይም የአሜሪካ፣ ተፅዕኖ ጎልቶ የሚታይባቸውን ነባሮቹን የፋይናንስ ተቋማት (የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት) ያላቸውን አይነት ኃላፊነት እንደተሰጠውም ይገለፃል።
በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም የኃያላን መንግሥታት ኅብረት ተገዳዳሪ ለመሆን እየጣረ እንደሚገኝ የሚነገርለት ይህ ጥምረት፣ የበርካታ ሀገራትን ቀልብ መሳብ ችሎ ከ40 በላይ ሀገራት የጥምረቱ አባል ለመሆን ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። ጥምረቱ ባለፈው ነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም፣ በጆሃንስበርግ (ደቡብ አፍሪካ) ባካሄደው 15ኛው ዓመታዊ ጉባዔው፣ የአባልነት ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት መካከል የስድስቱን (ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኢራን፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና አርጀንቲና) የአባልነት ጥያቄ ተቀብሏል።
ከአዳዲሶቹ የ‹ብሪክስ› አባላት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ አባልነቷ በምጣኔ ሀብታዊና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ውጤት እንደሆነና ይህ አባልነትም በቀጣይ ጊዜያት በምጣኔ ሀብትና በፖለቲካ መስኮች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝላት ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የጥምረቱ አባል መሆኗን ተከትሎ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ብሪክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ካሉ ስብስብ ኃይሎች መካከል በህዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚና በመደመጥ አቅሙ እያደገ የመጣ ቡድን ነው። ይህ ቡድን እያደገ ከመጣ በኋላ፣ ከ40 የማያንሱ ሀገራት ‹ብሪክስ›ን ለመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል፤ ከእነዚህ ሀገራት መካከል አሁን ስድስት ሀገራት መመዘኛውን አሟልተው የብሪክስ አባል መሆን ችለዋል። ይህ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ኩራትና ዲፕሎማሲዊ ድል ነው።›› ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአባልነት ስትመረጥ ታሪኳ፣ የሕዝብ ብዛቷ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ ስለታመነበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ፣ በግብርና ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት እና የመደመጥ አቅሟ እያደገ መምጣትም ‹ኢትዮጵያን አባል ማድረግ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን (South-South Cooperation) እውን ለማድረግ እንደሚያስችል፣ ኢትዮጵያ በሌለችበት ትብብሩ ሊሳካ አይችልም በሚል ታምኖበት መሆኑንም ገልጸዋል።
‹‹ከሁሉም ጋር ባካሄድነው ንግግር የኢትዮጵያ የ‹ብሪክስ› አባል መሆን ለአፍሪካም ሆነ ለየደቡብ-ደቡብ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አምነዋል›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አሁን እየተመዘገበ ያለውን ለውጥና ድል ዓለም በደንብ ተገንዝቦት እውቅና እየሰጠው እንደሚገኝም ጠቅሰው፣ ይህ ለኢትዮጵያም ትልቅ ድል መሆኑን አስታውቀዋል።
‹‹ዝም ብሎ መግባት ሳይሆን በእያንዳንዱ መስፈርት በኢኮኖሚ እድገት፣ በሕዝብ ቁጥር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመደመጥ አቅማችንና ወደፊት ባለን ተስፋ ምክንያት ‹በአፍሪካ ትልቅ ተደማጭነት ያላት ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያን ጥለን አፍሪካን አካተትን ማለት አንችልም› የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነው ጥምረቱን የተቀላቀልነው። ጥምረቱን መቀላቀላችን ብቻም ሳይሆን በጥምረቱ ውስጥ ያለን ተደማጭነትና ግንኙነት ጠንካራ እንዲሆን አድርጓል። ይህ በጣም ትልቅ ድል ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።
ሀገሪቱ ባልገባችባቸውና መግባት ባለባት መድረኮች ላይ ሁሉ እየተሳተፈች ድምጿን ከሀገሯ በላይ በአህጉርና በዓለም ደረጃ የምታስደምጥ ሀገር እንደምትሆንም አመልክተዋል። በስንዴ ምርት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በከተሜነት፣ በአጠቃላይ በሀገራዊ ምርት ያስመዘገበቻቸውን ድሎች በዲፕሎማሲውም እየደገመች መሆኗን አስታውቀው፣ ‹‹ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ የ‹ብሪክስ‹ አባልነት ጥያቄዋ ተቀባይነት ማግኘቱ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ በተለይም የኢንቨስትመንት፣ ዘርፍ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የምጣኔ ሀብት ጥናት ምሁራን ይገልፃሉ። በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና በኢባዳን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ፣ ኢትዮጵያ የ ‹ብሪክስ› አባል እንድትሆን መወሰኑ፣ ተጨማሪ የፋይናንስ አቅርቦት እና የገበያ እድል በመፍጠር የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማጠናከር ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ የ‹ብሪክስ› የኢንቨስትመንት ዘርፍ የትኩረት መስኮች ከኢትዮጵያ የዘርፉ የትኩረት መስኮች ጋር የሚጣጣሙ በመሆናቸው አባልነቱ ለሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። የ‹ብሪክስ› አባል መሆን የኢንቨስትመንት ፋይናንስ የዚህ አደረጃጀት አባል መሆን የፋይናንስ ተጠቃሚ ያደርጋል። አባል ሀገራቱ ያቋቋሙት ባንክ (New Development Bank) ሀገራቱ የሚገጥማቸውን የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ እጥረት የማቃለል ዓላማ ያለው በመሆኑ፣ ለኢንቨስተሮች ተጨማሪ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። የኢንቨስትመንት ፈንድ ለማግኘት ይረዳል። ለአስቸኳይ የፋይናንስ ችግሮች መፍትሄ ይሆናል። ይሁን እንጂ ባንኩ ትልቅ የኢንቨስትመንት ባንክ ሆኖ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ለመሆን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ይጠቁማሉ።
‹ብሪክስ› ከኢንቨስትመንት ሚናው በተጨማሪ በአንዳንድ የውጭ ሃይሎች የሚደርሱ አሻጥሮችን ለማስታገስና ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖኦ እንደሚኖረውም ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ይናገራሉ። ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ትልቅ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አሻጥሮች ሲፈፀሙባት እንደነበር ይታወሳል። የምዕራቡ ዓለም ጣልቃ ገብነት አንዱ መገለጫ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ማዳከም ነው። ጥምረቱ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለውን አሻጥር (የውጭ ምንዛሬና የገበያ ክልከላዎችን…) ለመቀነስ ይረዳል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ጫና ባጋጠማት ጊዜ የ‹ብሪክስ› አባል ብትሆን ኖሮ ብዙ ጫናዎች ይቃለሉላት ነበር›› ይላሉ።
የ‹ብሪክስ› አባልነት የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ለማግኘት ከሚያደርገው እገዛ ባሻገር፣ የገበያ አማራጭን በማስፋት ረገድም አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ያስረዳሉ። የጥምረቱ አባላት ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ቁጥርም ሆነ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መሆናቸው ትልቅ የገበያ ባለቤት ያደርጋቸዋል። ይህ የትልቅ ገበያ ባለቤትነት አማራጭ የገበያ እድሎችን በማስፋት ለምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ግምት ውስጥ ከሚያስገቧቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ የገበያ እድል (Market Availability) ነው። አምራቾች ሰፊ ገበያና ከፖለቲካ ጫና ነፃ የሆነ የቢዝነስ ከባቢ ይፈልጋሉ፤ ‹ብሪክስ› እነዚህን እድሎች ስለሚያመቻች የጥምረቱ አባል መሆን ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ያበረታታቸዋል።
‹‹የ ‹ብሪክስ› ባንክ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። የኢንቨስትመንት ማደግ የምርት መጠንን ያሳድጋል፤ የምርት ማደግ ደግሞ የገበያ እድልን ያሰፋል። ባንኩ የሚፈጥረው የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አቅርቦት እድል እና የጥምረቱ አባል ሀገራት የገበያ አቅም ተመጋጋቢ ናቸው›› ይላሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፣ የ ‹ብሪክስ› አባል መሆን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ቢሆንም ሊያስከትለው ስለሚችለው ጉዳትም በጥልቀትና በጥንቃቄ ማሰብ እንደሚገባ ይመክራሉ። እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ የ ‹ብሪክስ› አባልነት አዳዲስ የኢንቨስትመንትና የገበያ አማራጮችን እንዲሁም በመስፈርቶች ያልተገደበ ብድር ለማግኘት ሰፊ እድል የሚፈጥር ቢሆንም፣ የጥምረቱ አባል መሆን ስለሚያስገኘው ጥቅም በጥልቀት ማሰብ ያስፈልጋል። የ ‹ብሪክስ› ልምድና የገንዘብ አቅም ከነባሮቹ ተቋማት ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ነው። ይህም በማበደር አቅሙ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል።
የልማት አጋሮች የሆኑት ነባሮቹ ተቋማት (የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት…) ለኢትዮጵያ የ‹ብሪክስ› አባልነት ምን ዓይነት ምልከታ ሊኖራቸው እንደሚችል ጥልቅ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል። የእነዚህ ተቋማት ምላሽና ምልከታ አሉታዊ ከሆነ፣ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጠር ይችላል። ስለሆነም የብሪክስ አባል መሆን ስለሚያስገኘው ጥቅምና ሊያስከትለው ስለሚችለው ጉዳት በጥልቀትና በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልጋል። ‹አባል መሆናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? አባል ባለመሆናችንስ ምን ይቀርብናል?› ለሚሉት ጥያቄዎች ምክንያታዊ የሆነ ትንታኔ ማዘጋጀትና በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ጥቅሙን ብቻ በማየትና ከጀርባ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ባለማጤን ለአባልነቱ አዎንታዊ ግምት ብቻ መስጠት አዋጭ አይሆንም›› በማለት ስለ ‹ብሪክስ› አባልነት ጥቅሞችና ጉዳቶች ሚዛናዊ ዕይታና ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
‹ብሪክስ› ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን ከጂኦ-ፖለቲካዊና የደህንነት ፍላጎት ጋር አጣምሮ የተደራጀ እንደሆነ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ ጥምረቱ በዓለም ባንክና በሌሎች የፋይናንስ ተቋማትና ሥርዓቶች በኩል በምዕራቡ ዓለም የተያዘውን የፋይናንስ ቁጥጥር የበላይነት ለመገዳደርና ለማስቀረት ጥረት የሚያደርግ በመሆኑ አባልነቱ ሊያስከትለው የሚችለው ጫና ችላ ሊባል እንደማይገባም ይመክራሉ።
‹‹አባልነቱ ሀገሪቱን ለሌላ ጫና እንደሚዳርጋት የሚገልፁ አንዳንድ ተቃውሞዎች አሉ። ጥምረቱ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ለምጣኔ ሀብታዊ ዓላማ ነው። ‹ጫና ይኖራል› ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥም አይቻልም።› ሲሉም ያስገነዝባሉ። ‹‹የጥምረቱ አባል ለመሆን ጥረት እንደተደረገው ሁሉ፣ ከአባልነቱ በሚገባ ለመጠቀምም ስትራቴጂካዊ የሆነ አሠራር መከተልና መተግባር ይገባል። አገሪቱ ከ‹ብሪክስ› አባልነቷ በሚገባ ተጠቃሚ እንዳትሆን መሰናክል የሚፈጥሩ አሠራሮችን ማስተካከልና መዘጋጀት ያስፈልጋል›› ይላሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም