ከዲጅታላይዜሽን በስተጀርባ ላሉተግዳሮቶች ትኩረት እንስጥ

 አዲሱ ዓመት ለሀገራችን የሰላም ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የብልጽግና እንዲሆንልን ተመኝተን ዓመቱን በመልካም ምኞት አሃዱ ብለን መጀመራችን እሰየው የሚያሰኝ ነው። ምኞታችን ምኞት ብቻ ሳይሆን እውን ሆኖ ወደ ተግባር እንዲቀየር ማድረግ ደግሞ የሁሉም ኃላፊነት ነው ። ከዚህ የተነሳም እያንዳንዱ ዜጋ ለራሱም ሆነ ለሀገሩ ብሩህ ነገዎች ከእኔ ምን ይጠበቃል የሚለውን ጠይቆ በሚገባ ማወቅ ይጠበቅበታል ።

በተለይም እንደሀገር ባሳለፍነው ዓመት አላሰራ ብለው ወደኋላ ሲጎትቱን የነበሩ አሠራሮች ምንድናቸው ብሎ ፤ እነሱን አሻሽሎና አዘምኖ በማስቀጠል ጥሩ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻል የአዲሱ ዓመት ትልቁ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል ፤ በተለይም እንደ ሀገር የተጀመረው የዲጅታላይዜሽን ሥርዓቶችን ክፍተቶች አርሞ አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ ነው ።

አንድ የአሠራር ሥርዓት (ሲስተም) ሲዘረጋ ሥራን በፈጠነ ሁኔታና በአጭር ጊዜ በማከናወን አገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ እንዲረዳ ታስቦ ነው። ይህ ደግሞ ጊዜ፣ ጉልበትና አላስፈላጊ ወጪን በማስቀረት ተገልጋይን ከእንግልት የሚታደግ አሠራር ነው። ይህን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ችግሮች መቅረፍ ችሏል። እንዴትስ ነው ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሚሉትን ጉዳዮች ማየት ያስፈልጋል።

አሁን ላይ በአብዛኛው በመንግሥት የሚሰጡ አገልግሎቶች ወደ ዲጅታላይዜሽን አሠራር ሥርዓት (በሲስተም) እየተቀየሩ ነው ፤ እነዚህን የአሠራር ሥርዓቶች ቆም ብለን መፈተሽ ተገቢ ነው በትራንስፖርት ፣ በጤና ፣ በትምህርት እና በሌሎችም ዘርፎች አገልግሎቶች ዲጅታላይዝድ እየሆኑ ነው ።

በርግጥ አገልግሎቶችን ዲጅታላይዜሽን ማድረግ በራሱ ግብ አይደለም ። ግቡ በአጭር ጊዜ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት ነው ። ለዚህ ደግሞ ዲጅታላይዝድ የተደረገ አገልግሎትን በየጊዜው መገምገም እና በሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ የማስተካከያ ርምጃዎችን መውሰድ ወሳኝ ነው። ይህንን በተመለከተ አገልግሎት ፍለጋ ሄጄ ያጋጠመኝን ዝብርቅርቅ ላካፍላችሁ።

አሁን ላይ በመዲናችን የሚገኙ አብዛኛው ጤና ተቋማት አገልግሎታቸውን ዲጅታላይዝድ እያደረጉ ነው። በተለይ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በየቀኑ የሚያስተናግዱ ጤና ጣቢያዎች ላይ አሠራሩ ተግባራዊ መደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳ ይታመናል።

እግር ጥሎኝ የሄድኩበት የጤና ጣቢያ ያጋጠመኝ ግን ከዚህ የተለየ ነው ፤የቀደመውን የማንዋል አሠራር የሚያስናፍቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይህ ሃሳብ ደግሞ በወቅቱ አገልግሎቱን ፈልገው የመጡ ሰዎችም ሃሳብ እንደሆነ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።

ቀደም ሲል በማንዋል በሚሠራበት ወቅት አንድ ሰው ጤና ጣቢያ ገብቶ አገልግሎቱን አግኝቶ የሚሄድበት ሰዓትና አሁን አገልግሎቱ ዲጅታላይዝድ ከተደረገ በኋላ ያለው ሁኔታ ፈጽሞ አይገኛኝም።‹‹ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ›› አይነት ሆኖ እርፍ ብሏል።

በእለቱ የነበረው የሰው ብዛት ወረፋም ለጉድ ነበር።አንድ ሰው ቅድሚያ ካርድ ክፍል ደርሶ ካርድ ለማውጣት በትንሹ 20 ደቂቃ ይፈጅበታል። ቀጥሎ ደግሞ ህክምና ወደ የሚያገኝበት ክፍል ወረፋ ደርሶት ለመመርመር ብቻ ቢያንስ 40 ደቂቃ ይወስዳል። ተያያዥ ምርመራዎች ከታዘዙለትማ አገልግሎቱን ለማግኘት ምን ያህል ጊዜ ሊፈጅበት እንደሚችል በቀላሉ ማሰብ ይቻላል።

ታዲያ በትንሹ ስናሰላው ለአንድ ሰው ከካርድ ክፍል ተነስቶ ምርመራ ክፍል ያለውን ሂደት ጨርሶ ለመውጣት ብቻ አንድ ሰዓት ያህል ጊዜ ያስፈልገዋል ማለት ነው። ይህንን ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር ስናሰላው ደግሞ ነገሩን “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉት አይነት ያደርገዋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ እግዜር ረድቷችሁ ሲስተሙ እስካልተቋረጠ ድረስ ነው። ሲስተሙ ከተቋረጠ ደግሞ እስከሚመጣ ድረስ የሚፈጀውን ጊዜ ማሰብ አይከብድም።

አጋጣሚ ሆኖ በሄድኩበት ቀን መብራት መጥፋቱን ተከትሎ ሲስተሙ ተቋረጠ። ይህ የሆነው አምስት ሰዓት ከሩብ ላይ ሲሆን ከትንሽ ቆይታ በኋላ መብራት ቢመጣም ሲስተሙ ሊመጣ አልቻለም። ከዚያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ባደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ለስድስት ሰዓት አምስት ጉዳይ ላይ ሲስተሙ ቢስተካከልም አገልግሎት የሚሰጡት ሠራተኞች ደግሞ በቦታቸው የሉም፤ ለምሳ ወጥተዋል።

ለህመሙ ፈውስን ፈልጎ ደጃቸውን የረገጠው ህብረተሰብ ከህመሙ ጋር እየታገለ ከምሳ እስኪመለሱ መጠበቁ የግድ ሆኖበት ቢጠብቅም ከሰዓት እነሱ እንደገቡ ሲስተሙ በድጋሚ እልም አለ። ምሬታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉ አንዳንድ ሰዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም ሲስተሙ አልመጣም እኛ ምን እናድርግ የሚል ምላሽን ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት።

ሲስተሙ መጣሁ! ጠፋሁ! የሚል ከሆነ ህሙማኑን ለማስተናገድ የሚያስችል ሌላ አማራጭ መኖር ነበረበት። በሌላ በኩል ደግሞ ሲስተሙም እያለ ቢሆንም አንድ ሰው ለማስተናገድ የሚወስደው ጊዜ ይህንን ያህል መርዘሙ ለምን አስፈለገ የሚሉት ጥያቄዎች ናላዬን ቢያዞሩት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሠራተኞች እና ኃላፊዎች ማነጋገር መርጥኩ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ እንደገና በማንዋል እየተመዘገበ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደረገ።

ከዚያ ቀን በፊት ባሉት ቀናት ግን እንደዚህ አይነት ችግር አጋጥሞ አገልግሎቱን ሳያገኙ ወደቤታቸው የተመለሱ ሰዎች እንዳሉ ማረጋገጥ ችያለሁ። በድጋሚ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወደ ተቋም የምመለሰበት አጋጣሚ ቢፈጠርም በዕለቱ ሲስተም ባይጠፋም አሠራሩ ግን ፍጥነት የሌለው እንደነበር መመልከት ችያለሁ።

በሌላ አጋጣሚ በትራንስፖርት ዘርፉም ላይ እንዲሁ አጋጥሞኛል ፤ እንደሚታወቀው ከአዳማ አዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት አሰጣጥ ዲጅታላይዝድ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ለሌብነትና ለብልሹ አሠራር በር ከፋች መሆኑን መመልከት ችያለሁ። አዲሱ አሠራር ህዝቡን ለረጃጅም ሰልፍ፣ ለእንግልትና ለአላስፈላጊ ወጪ እየዳረገው ይገኛል።

የትራንስፖርት ትኬት ለመቁረጥ ያ ሁሉ ህዝብ ወረፋ እየጠበቀ ሳለ እዚያው መናኸሪያ ውስጥ ያሉ ሃይ ባይ ያጡ መኪኖች ለአንድ ሰው 200 መቶ ብር በማስከፈል ከዚያ ጭነው ሲወጡ ይታያል። ታዲያ ሲስተም መዘርጋቱ ለምን አስፈለገ አያሰኝም?።

ይህ ከሲስተም ጋር ተያይዞ የሚታይ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ያሳየናልና ሊታሰብበት ይገባል። እንደተረዳሁት ከሆነ ጎልቶ የታየው የሲስተሙ ችግር ሳይሆን ሲስተሙን ላይ የሚሠራው የሰው ኃይል የኮምፒውተር አጠቃቀም ችግርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው።

በሁሉቱም ዘርፎች ብዙ ተገልጋይ ያላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በሚገባ ተጠንቶ ስር ሳይሰድ እልባት ሊሰጠው ይገባል ። ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ኃላፊነታቸው መወጣት አለባቸው ፤አበቃሁ።

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን  መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You