በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለውን የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ ሥራዎች
ተሠርተዋል። ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። ከእነዚህም ውስጥ በትምህርት ሚኒስቴር ተቋማዊ ለውጥ
ማምጣት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎችን ከማስጀመር አንስቶ፤ የትምህርት ፖሊሲዎችን የመከለስ ሥራዎች
ተካሂደዋል።
ለሀገራዊ የትምህርት ጥራት ተጠቃሽ የሆነውን ኩረጃ ባህል ለማስቀረት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና
በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ፣ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችም የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ ተደርጓል። የመንግሥት
ዩኒቨርሲቲዎችም ራስ ገዝ የሚሆኑበት የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ ሆኗል።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ሆኗል። በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር
ደረጃቸውን ለማስተካከል ትልቅ ሥራ ተሠርቷል። የወላጅ ተማሪ መምህር ኅብረትም (ወተመህ) በአዲስ የኃላፊነት
መንፈስ ወደ ሥራ የተገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በሥነምግባር የታነፀ ፣ ለሀገርና ለሕዝብ ብሩህ ነገዎች ተስፋ
የሚጣልበት ትውልድ ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኘው ዘርፈ ብዙ ሥራ፣ ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑም
በተጨባጭ እየተስተዋለ ነው።
በርግጥ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የደረሰበት ውድቀት ከሀገር ህልውና ጥያቄ የሚተናነስ አይደለም፡፡
ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ስብራት ለመጠገን ትምህርት ሚኒስቴር እንደ ተቋም የጀመረው ሁለንተናዊ ጥረት የመላው
ሕዝባችን ይሁንታ የተቸረው ነው ።ይህንን የሕዝብ አጋርነት አሟጦ መጠቀም ከቻለ በዘርፉ ትልቅ ታሪክ መሥራት
እንደሚ ያስችለው ይታመናል።
በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ ለሚታየው ስብራት አንዱ በተማሪዎች ላይ የሚታየው ከራስ ጥረትና
ልፋት ይልቅ በሌሎች ትከሻ ወረቀትን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ ይህን መጥፎ ልምድ ሥር እየሰደደ እንዳይሄድ
መንግሥት ከጀመረው አበረታች ርምጃዎች በተጨማሪ የተማሪዎችና የወላጆች እንዲሁም የመምህራን ሚና የላቀ
ነው፡፡
ትምህርት ሚኒስቴርም ችግሩን ለመቅረፍ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች አቋራጭ የኩረጃ
መንገዶችን ለመዝጋት የጀመራቸውን ሥራዎች በአዲሱ የትምህርት ዘመን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል።
በዚህም በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት የገነገነውን የኩረጃ ባህል ታሪክ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ሕዝቡ አሁን ላይ ለትምህርቱ ዘርፍ የፈጠረውን የባለቤትነት መንፈስ የበለጠ በማጠናከር የጀመረውን
የፋይናንስና የማቴሪያል ድጋፍ በማሳደግ ትምህርት ቤቶችን ፣ ተጨማሪ ክፍሎችን እንዲገነባ ፣ ነባሮቹንም እንዲያድስ
፣ የትምህርት ግብአቶችን በማሟላት ረገድ ተገቢውን ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን
በቀጣይም መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለው ሀገራዊ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ፤የትምህርት መዋቅሩ
አስተማማኝ ይሆን ዘንድ በተጠናከረ ሁኔታ ተደራጅቶ ወደ ሥራ የገባው የወላጅ ተማሪ መምህር ኅብረት (ወተመህ)
ሊበረታታ ይገባል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ የሚያሳዩትን ፍላጎት እውን ለማድረግ
በትምህርት ሥራው ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
በየጊዜው ትምህርት ቤቶች ተፈላጊውን የብቃት ደረጃ ማሟላታቸውን በመገምገም ብቃታቸው ለተረጋገጠላቸው
ብቻ በኃላፊነት ዕውቅና እንዲያገኙ፤ ችግር ያለባቸው ዕድሳት እያገኙ አቅማቸውን የሚገነቡበት ሕጋዊነት ያለው
ሥርዓት መዘርጋት ፤ በትምህርት ተቋማት መካከል መልካም የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር የሚያስችል አሠራርም
መፍጠር ተገቢ ነው፡፡
በዚህም የትምህርት ተቋማት ደረጃ ምደባና ሞዴል ትምህርት ቤቶችን በጥራት የመምረጥና ዕውቅና የመስጠት፣
ከተፈላጊው ደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ክፍተታቸውን በማሳየት በቀጣይ ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ
እንዲችሉ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ተፈላጊ ግብ የሆነውን የተማሪዎችን ውጤትና ሥነምግባር ማሻሻል ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት እየተፈተነ ካለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመታደግ በቀደሙት ዓመታት
የተጀመሩ በተለይም ከጥራት ጋር የተያያዙና ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን በዚህም ዓመት በጠንካራ ተቋማዊ እና ሕዝባዊ
አቅም ማስቀጠል ያስፈልጋል፤ለዚህም ከወዲሁ በቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት መፍጠር ወሳኝ ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም